Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ለመቅረፍ አዳዲስ የኃይል ማመንጫዎች ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኃይል ኤክስፖርት በከፊል እንዲቆም ተደርጓል

ከመጋቢት ወር ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የኤሌክትሪክ ኃይል ፈረቃ ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲቆም መደረጉን ያስታወቀው የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ በቀጣይ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችሉ አዲስ የኃይል ማመንጫዎች ወደ ሥራ እንደሚገቡ አስታወቀ፡፡

የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎች ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በ2010 ዓ.ም. የዝናብ ወቅት አነስተኛ የውኃ መጠን ወደ ጊቤ ሦስት፣ መልካ ዋከና፣ ፊንጫ አመርቲ ነሼና ቆቃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች መግባቱ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ሳይገለጽ፣ ከሚያዝያ ወር መጨረሻ ደግሞ በይፋ ተገልጾ ወደ ኃይል ፈረቃ መገባቱን አስታውሰዋል፡፡ በተለይ በአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የአንበሳውን ድርሻ የሚወጣው የግልገል ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ግድብ የውኃ ከፍታ በከፍተኛ መጠን በመቀነሱ፣ ከፍተኛ ጫና እንደተፈጠረ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ 1,870 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨው ጊቤ ሦስት በሙሉ ኃይሉ ለማመንጨት 892 ሜትር የውኃ ከፍታ ሊኖረው ሲገባ፣ በግንቦትና በሰኔ ወር ጥሩ የዝናብ ሥርጭት በመኖሩ የውኃው ከፍታ እየተሻሻለ መጥቶ 830 ሜትር ደርሷል፡፡ በሌሎቹም ግድቦች የውኃ ከፍታ መጠን እስከ ሰኔ 30 ቀን እየጨመረ በመምጣቱ ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ የመኖርያ ቤቶች ከኤሌክትሪክ ኃይል ፈረቃ እንዲወጡ መወሰኑን ስለሺ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ የድንጋይ ወፍጮዎች ለአንድ ወር ከብሔራዊ የኃይል ቋት ኃይል እንዳያገኙ መወሰኑንም እንዲሁ፡፡

ኢንዱስትሪዎች ቀን ከማምረት አቅማቸው 50 በመቶ እንዲጠቀሙ፣ ከምሽቱ 5 እስከ 11 ሰዓት በሙሉ ኃይላቸው እንዲያመርቱ መወሰኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ኅብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይልን በቁጠባ እንዲጠቀም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሱዳንና ጂቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጄኔሬሽንና ኦፕሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዳርጌ እሸቴ እንደተናገሩት፣ ለሱዳን 250 ሜጋ ዋት ያህል ሲቀርብ ነበር፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው የኃይል እጥረት ወደ ሱዳን የሚላከው ኃይል ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ መደረጉን የገለጹት አቶ አንዳርጌ፣ ወደ ጂቡቲ የሚላከው የኤሌክትሪክ ኃይል በ50 በመቶ እንዲቀንስ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ ማድረግ እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀስ በመሆኑ፣ ባቡሩ ጂቡቲ ከገባ በኋላ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ እየገጠመው ኦፕሬሽን ላይ ከፍተኛ ችግር በመፈጠሩ 50 በመቶ የሚለውን ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡

ከፈረቃ ሰዓት ውጪ ተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ በመኖሩ ፈረቃው ቢነሳም የኃይል መቆራረጡ እንደማይኖር ማረጋገጫው ምንድነው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፣ በፈረቃ ወቅት ኃይል ሲለቀቅ ተመልሶ የሚጠፋው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ኃይል በሚለቀቅበት ወቅት በተመሳሳይ ሰዓት የመገልገያ መሣሪያዎቹን የሚለኩስ በመሆኑ፣ በሚፈጠረው ከፍተኛ የኃይል ጫና ትራንስፎርመሮችና ፊውዞች ስለሚቃጠሉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ ያለውን የኃይል ማሰራጫ መረብ ለማሻሻል በ54 ከተሞች የማሻሻያ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ሽፈራው፣ ፕሮጀክቱ ከሦስት እስከ አራት ዓመት እንደሚፈጅ ጠቁመዋል፡፡ የኤሌክትሪክ መስመር ማሻሻያ ሥራ በሚከናወንበት ወቅትም ሠራተኞች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲቋረጥ ተደርጎ ስለሚሠራ፣ አልፎ አልፎ የኤሌክትሪክ መቋረጥ እንደሚከሰት አስረድተዋል፡፡

ስለሺ (ዶ/ር) በበኩላቸው በቀጣይ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችሉ፣ የገናሌ ዳዋ ሦስት የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያና የአይሻ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡ 254 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ገናሌ ዳዋ ሦስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያ በሙከራ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ነሐሴ 2011 ዓ.ም. ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ 125 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የአይሻ የፀሐይ ኃይል ጣቢያ በታኅሳስ ወይም በጥር 2012 ዓ.ም. ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ የጂኦተርማል፣ የንፋስና የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች ገንብቶ ኃይል እያመነጨ እንዲያቀርብ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በፀሐይ ኃይል ልማት 800 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም የሚኖራቸው ስድስት ፕሮጀክቶች በጨረታ ሒደት ላይ እንደሆኑ፣ ሦስት የንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶችን በቶሎ አስመርቆ ወደ ብሔራዊ ቋት ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ2013 ዓ.ም. ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በአጠቃላይ 8,774 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ጣቢያዎች በግንባታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ከፍተኛ ካፒታል ፈሶበት ዝቅተኛ ታሪፍ የሚሰበሰብበት በመሆኑ ዘርፉ ተጎድቶ እንደቆየ ተገልጿል፡፡ በጥገናው ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ማነቆ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊዎቹ፣ በአሁኑ ወቅት በ90 ሚሊዮን ዶላር የመለዋወጫ ግዥ እንደተፈጸመ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ በግድቦች የውኃ ፍሰት (Spillage) እንዳይኖር፣ የኃይል ብክነት በመቀነስ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ማቀዳቸውን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች