Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የአዴፓን አጀንዳዎች ማሳካትና ለውጡን በማስቀጠል ላይ በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነውና በክልሉ አመራሮች መካከል...

‹‹የአዴፓን አጀንዳዎች ማሳካትና ለውጡን በማስቀጠል ላይ በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነውና በክልሉ አመራሮች መካከል ልዩነት አልነበረም›› አቶ ደመቀ መኮንን፣ የአዴፓ ሊቀመንበር

ቀን:

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (አዴፓ) ክልላዊ አጀንዳዎችን ማሳካትና ለውጡን ወደፊት ማስቀጠል ላይ በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌና ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ባልተጠበቀ ሁኔታ በተገደሉት በአማራ ክልል አመራሮች መካከል ልዩነት እንዳልነበር፣ የአዴፓ ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታወቁ፡፡

ወቅታዊ ጉዳዮችንና በዋናነት በአማራ ክልል በተፈጠረው ግድያና አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የአዴፓ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ እንደገለጹት፣ የክልሉ አመራሮችም ሆኑ ሌሎች ለውጡን ለማስቀጠል የሚታገሉት አካላት ለዴሞክራሲ፣ ለፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ለሰብዓዊ መብት መከበር ነው፡፡

በአጠቃላይ አዴፓ እንደ ድርጅት፣ ክልሉም ሆነ አገሪቱ እንዲሁም ሁሉም ዜጎች የዴሞክራሲ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈሉን አስረድተዋል፡፡ ይሁንና ለክልሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብለው እምነት የተጣለባቸው አመራሮች መገደላቸው የሚያስቆጭ መሆኑንም አክለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ያም ቢሆን የአመራሮችን ግድያ አቀናባሪ ናቸው ከተባሉት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጀርባ ሆኖ፣ ሴራውን ያቀናበረ አካል አለ ብለው እንደሚያምኑም አቶ ደመቀ አስረድተዋል፡፡

በአመራሮቹ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት አዴፓንና ክልሉን ለማፍረስ በተደራጀ ሁኔታ የተፈጸመ ሴራ መሆኑን ተናግረው፣ አዴፓና የለውጥ ኃይሎች ከአገራዊ ለውጥ በፊትም ሆነ በኋላ የታገሉት ለዴሞክራሲ፣ ለፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ለሰብዓዊ መብት መከበር በመሆኑ፣ አሁንም ያንን ለመጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩና እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች፣ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች መብትና ጥቅምን ማስጠበቅ፣ የተዛቡ የአማራ ትርክቶችን ማረቅና የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ጥያቄዎች እንዳይታፈኑ አዴፓ ሲታገል መቆየቱን አቶ ደመቀ አብራርተዋል፡፡

የተነሱት ጥያቄዎችና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ ምላሽ ለመስጠት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ያለ ዕረፍት በመሥራት ላይ እያሉ፣ አሳፋሪና ኢሰብዓዊ ድርጊት በእነሱ ላይ መፈጸሙ አሳዛኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምንም ቢሆን ግን የክልሉ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም ከፍተኛ መስዋዕትነት ሲከፍል የኖረ፣ በቀላሉ የማይፈርስና የማይናጋ መሆኑን የሚያሳይበት ጊዜም መሆኑንም አክለዋል፡፡

በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሆነው የኢትዮጵያን አብሮነት የማይፈልጉና አማራ ጠል ትርክቶችን በማራመድ ሕዝቡን የሚከፋፍሉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የጠየቁት አቶ ደመቀ፣ የክልሉ ሕዝብ የሞቱትን አመራሮች ራዕይ ለማስቀጠል፣ ክልሉንና አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከምንጊዜውም በተሻለ ሁኔታ ቁርጠኛ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...