Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየእስልምና ምክር ቤት የሐጅ ጉዞ የተቃና እንዲሆን ከአየር መንገድ ጋር ተባብሮ በመሥራት...

የእስልምና ምክር ቤት የሐጅ ጉዞ የተቃና እንዲሆን ከአየር መንገድ ጋር ተባብሮ በመሥራት ላይ እንደሆነ አስታወቀ

ቀን:

የውጭ ምንዛሪ እጥረት ራስ ምታት ሆኖበታል

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዘንድሮ ምዕመናን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ መካና መዲና የሚያደርጉት የሐጅ ጉዞ የተቃና እንዲሆን፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ሰፊ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ ማኔጅመንት ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ኃላፊዎች ጋር ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል በሰጡት የጋራ መግለጫ፣ በዘንድሮ የሐጅ ጉዞ ምዕመናን መንገላታት እንዳይደርስባቸው ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም እንደተናገሩት፣ አየር መንገዱ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር የረዥም ጊዜ ግንኙነት አለው፡፡ በሐጅ ጉዞ ወቅት የሚፈጠሩ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል፣ አየር መንገዱ ከእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች ጋር ተከታታይ ስብሰባዎች በማካሄድ ጠንካራ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡

በአብዛኛው በሳዑዲ ዓረቢያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ከምክር ቤቱ ጋር በመመካከር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የገለጹት አቶ ተወልደ፣ የምዕመናኑ ጉዞ የተሳካ እንዲሆን የሚያግዙ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እንደሚላኩ ተናግረዋል፡፡

ከመላው ዓለም ለሐጅ ወደ መካና መዲና ሦስት ሚሊዮን ያህል ምዕመናን የሚጓዙ በመሆናቸው አውሮፕላኖች በጅዳ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ተደራርበው በማረፍ ከፍተኛ መጨናነቅ እንደሚፈጠር ተገልጿል፡፡ በኤርፖርት መሠረተ ልማቶችና በመካና መዲና ከተሞች ከፍተኛ መጨናነቅ እንደሚፈጠር የተገለጸ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን መንገላታት እንዳያጋጥማቸው የሚረዱዋቸው 30 የሠለጠኑ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ የአየር መንገዱ ሠራተኞች እንደተመደቡ ተነግሯል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ 5,000 ምዕመናን ለሐጅ ጉዞ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ሲያጓጉዝ፣ የሳዑዲ አየር መንገድ 5,000 ያህል ያጓጉዛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባዘጋጃቸው 268 መቀመጫዎች ባሏቸው ዘመናዊ ዲሪምላይነር አውሮፕላች እ.ኤ.አ. ከጁላይ 12 እስከ ጁላይ 30 ቀን 2019 ባሉት ቀናት 19 በረራዎች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እንደሚያደርግ፣ በመልስ ጉዞ ከኦውገስት 20 እስከ ሴፕቴምበር 7 ቀን 2019 ደግሞ 19 በረራዎች እንደሚያከናወን ታውቋል፡፡ አየር መንገዱ በአጠቃላይ ከአፍሪካ 40,000 ምዕመናንን በ228 በረራዎች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እንደሚያጓጉዝ ተጠቁሟል፡፡  

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ኮሜርሺያል ኦፊሰር አቶ ኢሳያስ ወልደ ማርያም በሁሉም በረራዎች ላይ ሀላል ምግቦች መዘጋጀታቸውን፣ በአውሮፕላኖቹ ውስጥ መንፈሳዊ መዝሙሮች (ተክዚራ) እና የፀሎት ማስተላለፊያዎች መዘጋጀታቸው፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የፀሎት ሥፍራዎችና የማስተናገጃ ድንኳኖች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ተቀዳሚ  ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ በኢትዮጵያ ለተጀመሩ በጎ ለውጦች መንግሥትንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) አመስግነዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች፣  የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች ለተጓዦች መልካም አቀባበል በማድረግ፣ በማስተናገድና በማማከር ላይ እንደሆኑ ተቀዳሚ ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡ አየር መንገዱ ለሐጅ ተጓዦች ልዩ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ በማስተናገድ ላይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የሐጅ ተጓዦች በተለይ ከገጠሪቷ ኢትዮጵያ የሚመጡ በመሆናቸው መዘግየትና እየተንጠባጠቡ በመምጣት ለአየር መንገዱ እክል እንደሚፈጥሩ ገልጸው፣ ይህ እንዳይሆን ሕዝቡን የማንቃት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አባል አንዋር ሙስጠፋ (ዶ/ር)፣ የምክር ቤቱ የቴክኒክ ኮሚቴ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች ገምግሞ እንዳይደገሙ ከአየር መንገዱ ጋር በቅርበት በመሥራት ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ለሙስሊም ተጓዦች ተስማሚ የሆነ መስተንግዶ እንዲኖር እየተሠራ በመሆኑ፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ የሐጅ ጉዞ እንደሚኖር አንዋር (ዶ/ር) እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኤርፖርት ውጪ በመካ ለሚሰጠው የሎጂስቲክስ አገልግሎት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ ‹‹የአየር መንገዱ ሠራተኞች ሆቴል ድረስ መጥተው የሐጅ ተጓዦችን ሻንጣ በመመዘን ለሚሰጡት አገልግሎት ማመስገን እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ ሐጅ ሚኒስቴር 10,000 ምዕመናን እንዲጓዙ ፈቃድ መስጠቱን የገለጹት  አንዋር (ዶ/ር) ወደ፣ 15,000 ለማስፈቀድ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከኮታው በላይ ከ13,500 እስከ 14,000 የሚሆኑ ምዕመናን ገንዘብ ከፍለው በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

አንድ የሐጅ ተጓዥ 78,150 ብር ክፍያ በባንክ የሚያስገባ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 48,000 ብር በዶላር ተመንዝሮ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ቀደም ብሎ ገቢ እንዲደረግ የሐጅ ሚኒስቴር እንደሚያዝ ያስረዱት አንዋር (ዶ/ር)፣ ይህን ለማድረግ ምክር ቤቱ ከፍተኛ የዶላር እጥረት እንደገጠመው ተናግረዋል፡፡ ምክር ቤቱ የዶላር እጥረቱን ለመቅረፍ ከባንኮች ጋር በመነጋገር ላይ ቢሆንም፣ በተፈለገው ፍጥነት በቂ ዶላር ሊቀርብ እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡ አየር መንገዱንም የመፍትሔው አካል ለማድረግ እንደታሰበ ተገልጿል፡፡

የመጀመርያው የሐጅ ጉዞ ዓርብ ሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሚጀመር ይጠበቃል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ የሐጅ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ የሐጅ ጉዞ የሰጠው ኮታ 43,337 ቢሆንም፣ በታሪክ ከ10,000 በላይ ምዕመናን ተጉዞው እንደማያውቁ ተገልጿል፡፡ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኮታውን መጠቀም ያልተቻለው ከሳዑዲ በኩል ክልከላ ኖሮ ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ በኩል የአቅምና የዝግጅት ማነስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር በመተባበር፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ታሪካዊ የእስልምና ሥፍራዎች በመካከለኛው ምሥራቅ ለማስተዋወቅ ንግግር መጀመሩ ተገለጸ፡፡ በትግራይ ክልላዊ መንግሥት የሚገኘውን የአልነጃሽ መስጂድና የሐረር ከተማን በመካከለኛው ምሥራቅ በማስተዋወቅ ቱሪስቶችን ለመሳብ በጋራ ጥረት እንደሚደረግ አቶ ተወልደ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...