በአዲስ አበባ እየተከበረ የሚገኘው የኦሊምፒክ ሳምንት ባለፈው እሑድ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. የኦሊምፒክ ስፖርቶች በሆኑት በእግር ኳስና በአትሌቲክስ ተጀምሯል፡፡ በዕለቱ በተለያየ የሥልጣን እርከን ላይ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር ያደረጓቸው እግር ኳሳዊ ክንውኖች ይጠቀሳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን በጥምረት ያዘጋጁት የኦሊምፒክ ሳምንት ‹‹ኦሊምፒዝም ለሰው ልጆች ክብር፣ ሰላምና አንድነት›› በሚል መሪ ቃል የሚከናወን ሲሆን፣ ዝግጅቱን በክብር እንግድነት ተገኝተው ያስጀመሩት ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ናቸው፡፡
የኦሊምፒክ ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጁን 23 (ሰኔ 16) ጀምሮ የሚከበር ቢሆንም፣ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ተፈጥሮ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት የተነሳ ወደ ሰኔ 30 ቀን እንዲሸጋገር መደረጉ አይዘነጋም፡፡
ላለፉት ዓመታት በዓይነ ቁራኛ ሲተያዩ የቆዩት የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች መካከል የተደረገው እግር ኳሳዊ ክንውን ስፖርቱ ለሰው ልጆች አንድነትና ሰላም እንዲሁም መቀራረብ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑ ታይቷል፡፡ ዝግጅቱን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢሕአዴግም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ ፕሮግራሙ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡