Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአሜሪካ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሪፎርም እንደምትደግፍ አስታወቀች

አሜሪካ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሪፎርም እንደምትደግፍ አስታወቀች

ቀን:

በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሪፎርም አሜሪካ እንደምትደግፍና ይህም ሪፎርም ዘላቂና አስተማማኝ መረጋጋትን፣ ብልጽግናንና የፖለቲካ አካታችነትን እንደሚያመጣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር አስታወቁ፡፡

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮ-አሜሪካን ዶክተርስ ፈንድ ከአሜሪካን የሰርጅን ኮሌጅ አጋርነት ጋር በመተባበር፣ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ሕክምና ተቋማት ውስጥ ለሚያገለግሉ ሐኪሞች ያዘጋጁትን የሁለት ቀናት ሥልጠና አምባሳደሩ ሲከፍቱ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ኅብረተሰቡ ለብልጽግና፣ ለኅብረት፣ ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ዕውን መሆን ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ አሜሪካ ከጎን እንደምትቆም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ከ1940ዎቹ በፊት ጀምሮ እየተጠናከረ የመጣው አጋርነት ትኩረት ያደረገው በኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ሥርዓትና በሕዝቡ ጤናና ደኅንነት ላይ መሆኑን አምባሳደሩ አመልክተው፣ መንግሥታቸው በጤና ሥርዓቱ ላይ ካበረከተው ድጋፍ መካከል በአሁኑ ጊዜ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቀደም ባሉት ዓመታት ደግሞ የጎንደር ሜዲካል ሳይንስ ኮሌጅን ማቋቋሙ እንደሚገኝበት አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ኤችአይቪ፣ ቲቢ እና ወባ የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎችን ለመዋጋት እንዲሁም የኢቦላ ወረርሽኝንና ሌሎች ዓለም አቀፍ የጤና ጉዳቶችን ለመከላከል በምታካሂደው እንቅስቃሴ አሜሪካ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የበኩሏን አስተዋጽኦ ማበርከቷንም አክለዋል፡፡

በአሜሪካና በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የምሁራንና ተመራማሪዎች ልውውጥና የዕውቀት ሽግግር እንዲካሄድ ለማድረግ በአሜሪካ የሚገኙ ልዩ ልዩ ተቋማት የየበኩላቸውን ጥረቶች በማበርከት ላይ መሆናቸውን፣ ከጥረቶቹም መካከል በኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች በምርምርና በምዘና ዙሪያ ለሚያካሂዱት ሥልጠናዎች የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠቃሽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት መንግሥታቸው ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንደኛው፣ ከግሉ ዘርፍና ከብዙኃን ድርጅቶች (ሲቪል ሶሳይቲ) ጋር ያለውን አጋርነት ማጠናከር ላይ ያተኮረ መሆኑን አመልክተው፣ በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ ከሚገኙ ከ200 በላይ ከሚሆኑ የግል ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ጋር በመተባበር በኤችአይቪ፣ በቲቢ፣ በወባና በሌሎችም ጤና ነክ ጉዳዮች ዙሪያ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንደ አምባሳደሩ፣ ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በኤችአይቪ፣ በቲቢና በወባ ላይ ትኩረት ያደረገ የክሊኒካልና የፕሮግራም ምርመራ እንዲሁም የጤና ሥርዓቱን የማጠናከር ተግባር ተከናውኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የምርምር ግኝቶችን ለመካፈልና የጤና አገልግሎቶችን ለማሻሻል እንዲቻል በየዓመቱ ጉባዔ ይካሄዳል፡፡ ለእነኚህ ሥራዎች ውጤታማነት አሜሪካ በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ታደርጋለች፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ዓምና ላወጣው አዲስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች (ሪፎርም) እንዲሁም ስትራቴጂክ ፕላን አዘጋጅቶ ተግባራዊ ለማድረግ በተካሄደው እንቅስቃሴ ላይ መንግሥታቸው ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት እገዛና ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር አሚር አማን (ዶ/ር) ለዓውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ እንዲህ ዓይነቱ ዓውደ ጥናት በኢትዮጵያውያንና በትውልደ ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎች መካከል የዕውቀት ሽግግር ለማካሄድ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሕክምናና ቀዶ ሕክምና ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረገውና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አዳራሽ ከሐምሌ 1 እና 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በተካሄደው በዚሁ ሥልጠና ላይ የኩላሊት በሽታና ንቅለ ተከላ፣ የካንሰር በሽተኞች እንክብካቤ፣ የስኳር በሽታ፣ ተላላፊ በሽታዎች፣ ጥራት ያለው የሕክምና አሰጣጥና የሕክምና ትምህርት ተቋማት አመራር ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡

የኢትዮ አሜሪካ ሐኪሞች ቡድን ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ፈንታ (ዶ/ር) ‹‹በሥልጠናው ላይ የሚሰጠው ትምህርት በአገራችን ያሉ ባለሙያዎች ዘመኑ የደረሰበት ዕውቀትና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከማስተዋወቅ ባለፈ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የሕክምና ተቋማት ከተውጣጡት ባለሙያዎች ልምድን እንዲቀስሙ ያስችላል፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ዓይነቱን ሥልጠና የተከታተሉት በሕክምና ሥራ ላይ እያገለገሉ የሚገኙና ከ200 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ትምህርቱን የሰጡት ደግሞ በውጭ አገሮች ዕውቀትና ከፍተኛ ልምድ ያዳበሩ 37 ዶክተሮች ናቸው፡፡

ሥልጠናውም ባለሙያዎቹ ከዳያስፖራ አቻዎቻቸው ዓለም አቀፍ ብሎም በወቅታዊ የሕክምና ሒደት ላይ ዕውቀትንና ልምድን እንዲቀስሙ በማድረግ በኢትዮጵያ የሕክምና አሰጣጥን ለማሻሻል ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...