Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የክረምት በጎ ፈቃድ ፕሮግራማችን ትውልድ የምንቀርፅበት ካለን የምናካፍልበት ነው›› አቶ ባልቻ ጥበቡ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚና የቦሌ ክፍለ ከተማ ሰብሳቢ

ከተቋቋመ 21 ዓመታትን ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ የተቋቋመ ነው፡፡ በኢኮኖሚው ዘርፍ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችና የማነቃቃት ሥራዎችን ይሠራል፡፡ በማኅበራዊ ዘርፍም እንዲሁ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን የማስተባበር, የቅስቀሳና የማደራጀት ሥራም እንዲሁ ይሠራል፡፡ የተቋቋመለትን ዓላማ በምን ያህል መጠን ማሳካት እንደቻለና ተልዕኮውን ለመወጣት ያሉበትን ተግዳሮቶች በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን ተሰናባቹን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባልቻ ጥበቡን አነጋግራቸዋለች፡፡ 

ሪፖርተርማኅበሩ የተቋቋመለትን ዓላማ በአግባቡ እያስፈጸመ ነው ብለህ ታምናለህ?    

አቶ ባልቻማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ፈተናዎች እየገጠሙት እያለፈ ነው የመጣው፡፡ ያሉበት ችግሮች ግን ተፈትተው በሚጠበቅበት መጠን እየሠራ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ በተለያዩ ወቅቶች ትግል ሲደረግ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ መንፈስ ከወረዳ ጀምሮ ጉባዔ ማድረግ ተጀምሯል፡፡ አዳዲስ አቅም ያላቸውን ወጣቶች ወደ ማኅበሩ ስቦ ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ነው በየወረዳው ጉባዔ ማድረግ ያስፈለገው፡፡ ማኅበሩ የሠራቸው መልካም ሥራዎች ቢኖሩም ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነቱን ተወጥቷል ብሎ ለመናገር ግን አያስደፍርም፡፡ ኃላፊነቱን ተወጥቷል ከተባለ የአዲስ አበባ ወጣቶች ጥያቄ ተመልሷል ማለት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ጥያቄ ደግሞ የብዙኃኑን ትብብር የሚጠይቅ ነው፡፡ እንደ ማኅበርም የወጣቱ ችግሮች ተቃለው አላየንም፡፡ ስለዚህ የማኅበሩ ይህ ቀጣይ የቤት ሥራው ነው፡፡ ትኩረት አድርጎ በሚሠራበቸው የበጎ ፈቃድ ሥራዎቹን ግን እንደ መልካም ተሞክሮ መነሳት ይችላል፡፡

ሪፖርተርየወጣቱ ዋና ዋና ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?

አቶ ባልቻባደረግነው ጥናት መሠረት የመጀመርያው የአዲስ አበባ ወጣቶች ጥያቄ ኢኮኖሚያዊ ነው፡፡ በከተማው ነዋሪ የሆነም ሆነ ከየክልሉ የሚመጣው ሠርቶ ማደር አልቻለም፡፡ በከተማዋ ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር አለ፡፡ ለወጣቱ የኅብረተሰቡ ክፍል ሠርቶ በልቶ ማደር እንዲችል የተመቻቸለት ነገር የለም፡፡ ማኅበሩ የሥራ ዕድል መፍጠር ባይችልም መንግሥት እንዲፈጥር ግን ጫና ያደርጋል፡፡ መንግሥት በሚፈልገው መጠን የወጣቱን ችግር መፍታት የሚችል የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ከማድረግ አኳያም ግን ክፍተቶች ነበሩብን፡፡ ከዚህ ባሻገርምተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ወጣቱን ይፈትናሉ፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግሮች አሉ፡፡ እርስ በርስ ተረዳድቶ፣ ተደጋግፎ መኖር ላይም ችግር አለ፡፡ 

ሪፖርተርማኅበሩ የተቋቋመበትንላማ ለማሳካት የገንዘብ ችግር አለበት? የገንዘብ ምንጩስ ምንድነው?  

አቶ ባልቻአገር በቀል የብዙኃን ማኅበር ሆኖ ነው የተቋቋመው፡፡ የሚተዳደረው በአባላት ወርኃዊ መዋጮ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ማኅበሩ ከመንግሥት ጋር በተደረጉ መግባባቶች የተሰጡት ቦታዎች አሉ፡፡ምሳሌ በፊት በአኢወማ ሥር የነበሩ የንግድ ቦታዎቸን በማኅበሩ ሥር እንዲገቡ ተደርጎ እነሱን በማከራየት ማኅበሩ ገቢ ያገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ምንም ዓይነት ገቢ የለውም፡፡ ማኅበሩ ገንዘብ የሚያስፈልገው ለሥራ ማስኬጃ ብቻ ነው፡፡ በቀጥታ ለወጣቱ ብድር ሰጥቶ የማደራጀት ሚና የለውም፡፡ እኛ ሥራ አጥ ወጣቶችን እንመለምልና መንግሥት ሥራ እንዲፈጥርላቸው ተፅዕኖ የማድረግ ሚና ነው ምንጫወተው፡፡ 100 ሺሕ በላይ አባላቶች ሲኖሩት፣ በዓመት የአባልነት መዋጮ 12 ብር ይከፍላሉ፡፡

ሪፖርተርበጎ ፈቃደኞችን አስተባብሮ ለማኅራባዊ ችግሮች ምላሽ በመስጠት ረገድ ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ ነው፡፡ የዛሬ ዓመት የተጀመረ እስኪመስል ብዙ አዳዲስ ነገሮች ታይተዋል፡፡ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ማስተባበር የጀመራችሁት መቼ ነው?

አቶ ባልቻየበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተጀመረው ባለፈው ዓመት አይደለም፡፡ ባለፈው ዓመት ግን ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ የበጎ ፈቃድ ሥራ የጀመርነው 1995 .. ጥቂት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመያዝ ክረምት ላይ ከፍሎ መማር የማይችሉ የደሃ ልጆችን በማስተማር ነበር፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት ብቻችንን ይህን ሥራ ስንሠራ ቆይተናል፡፡ ከዚያ በኋላ መንግሥትም አምኖበት አስተዳደሩም ተቀብሎት ፅዳት፣ የሰብዓዊ አገልግሎቶችን አስፍቶ መሥራት ቀጥሏል፡፡ ዘንድሮ 17 ዓመታችንንም አስቆጥረናል፡፡ ክረምት ላይ ተጀምሮ በጋ ላይ የሚቋረጠውን ነገር ነበር እንደ ችግር የምናየው፡፡ የክረምት በጎ ፈቃድ ፕሮግራማችን ትውልድ የምንቀርፅበት፣ ካለን የምናካፍልበት ነው፡፡ በእነዚህ 17 ዓመታት ውስጥ የዓምናውና የዘንድሮ የተለየ ነው፡፡ 

ሪፖርተርዓምና 100 የሚበልጡ የአቅመ ደካማ ቤቶች በበጎ ፈቃድ እንዲታደስ ተደርጓል፡፡ በከተማዋ ግን ችግር የባሰባቸው ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ አሉ፡፡ በወቅቱ እንዲያውም የአንዱ ቤት ታድሶ የእኔ አልታደሰም በሚል ጭቅጭቅ የተፈጠረባቸው ቦታዎችም ነበሩ፡፡ በፕሮግራሙ የሚታደሱ ቤቶችን ቁጥር ከማብዛት አኳያ ገንዘብ ምን ያህል ችግር ሆኖባችኋል? 

አቶ ባልቻጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) አንድ ቤት እናድስ በሚል የጀመሩት ፕሮጀክት ነበር፡፡ በከተማ ደረጃ 100 ምናምን ቤቶችን ለመገንባት ነበር ዕቅድ የተያዘው፡፡ ከታቀደው በላይ በርካታ ቤቶች ተጨምረው ታድሰዋል፡፡ ከተማችን ላይ ያለው የኑሮ ሁኔታ እጅግ በጣም የተለያየ ነው፡፡ ጥሩ ኑሮ የሚኖር አለ፡፡ በዚያው መጠን ደግሞ እንዲህም መኖር ይቻላል ወይ በሚያስብል የኑሮ ደረጃ ላይ የሚኖሩም አሉ፡፡ የእነዚህን ዜጎች ቤት እናድስ ብለን ስንነሳ በጣም ተቀባይነት አገኘን፡፡ ወጣቱ፣ ባለሀብቱ፣ ታዋቂ ሰዎች ያላቸውን እዚያው ማዋጣት ጀመሩ፡፡ አንዳንድ አትሌቶችና አርቲስቶችም አንዳንድ ቤቶች ወስደው ጥሩ አድርገው አድሰዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር አብዛኛዎቹ ቤቶች ወጣቱ ከኪሱ ገንዘብ እያዋጣ የሚቀየር ቆርቆሮ ካለ ቆርቆሮ ገዝቶ፣ የፈረሰ ግድግዳንም ጭቃ አቡክቶ በጉልበቱ ነው የሠራው፡፡ ካስተባበርነው ማኅበረሰቡ እርስ በርስ ይረዳዳል፡፡ ደስ የሚለው ያለፈው ዓመት ተግባራችን ከአባላት ውጪ ሁሉም የኅብረተሰቡ ክፍል የተሳተፈበት ነው፡፡

ሪፖርተርበዚህ ዓመት አንድ ሚሊዮን በጎ ፈቃደኞች ይሰማራሉ ተብሏል፡፡ ምን ያህል ቤቶችን ለማደስ አቅዳችኋል?

አቶ ባልቻበርካታ ቤቶችን ለማደስ ዕቅድ መያዙን አውቃለሁ፡፡ ምን ያህል ቤቶችን ለማደስ እንደታቀደ ግን አላስታውስም፡፡

ሪፖርተርአዲሱ የኢትዮጵያ የሲቪል ሶሳይቲ ሕጉ ማኅበራት በአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ገቢ ማሰባሰብ እንዲችሉ ይፈቅዳል፡፡ ገቢ አሰባስባችሁ አቅማችሁን በማጠናከር ልትሠሩ አስባችኋል?

አቶ ባልቻፈንዶች ቢገኙ የተሻሉ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ መሥራት ይቻላል፡፡ በዋናነት ግን ማኅበራችን የሰው ሀብት ሲኖረው ነው የተሻለ መሥራት የሚችለው፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ገንዘብ ሳይሆን አመለካከት ነው የሚጠይቀው፡፡ ሰው ባለው መደገፍ ከቻለ ትልቅ ነገር ነው፡፡ መልካም ሐሳብ በራሱ እንደ ውጤት ነው፡፡ በጎ ፈቃድ የእነዚህ ሁሉ ድምር ነው፡፡ ገንዘብ ብዙ ላያስፈልገን ይችላል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ወጣቶችን ሊስብ የሚችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለማሟላት ፈንድ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተርወጣቱ የኅብረተሰቡ ክፍል በከፍተኛ መጠን ለተለያዩ ሱሶች የተጋለጠ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ለወጣት ነው የምሠራው የሚለው የእናንተ ማኅበር በዚህ ረገድ ምን እያደረገ ነው?  

አቶ ባልቻከዓመታት በፊት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወጣቱ ለሱስ ተጋላጭ ነው፡፡ ማኅበሩም ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ የእግር ጉዞ ፕሮግራሞች አዘጋጅቷል፡፡  የሱስ ተጠቂዎች ቁጥር ግን እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህንን ወጣት ለመታደግ ሰፊ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል፡፡ ከዚህ ባሻገርም እነዚህ ወጣቱን ለሱስ እየዳረጉ ያሉ መድኃኒቶችና ዕፆች የሚገቡበትን በር መዝጋት ያስፈልጋል፡፡ ሱስ ሥራ ከመፍታት ጋርም ይያያዛል፡፡ ሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን ስናናግር ሥራ በማጣት ሱስን እንደመደበሪያ በማየት የገቡ እንደሆነ ይነግሩናል፡፡ እንዲህ ያሉትን ከከተማው አስተዳደር ጋር በመነጋገር ወጣቶቹ ሥራ የሚያገኙበትን ዕድል ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡  

ሪፖርተርወጣቱ ጊዜ ሊያሳልፍባቸው የሚችሉ ምን ያህል የወጣት ማዕከላት በአዲስ አበባ ይገኛሉ?

አቶ ባልቻ– በአዲስ አበባ ከመቶ የሚበልጡ የወጣት ማዕከላት አሉ፡፡ ማዕከላቱ ግን ለወጣቱ ሳቢና ማራኪ ሆነው ጊዜ የሚያሳልፉበት ቦታ ከመሆን አኳያ ሰፊ ክፍተት እንዳለ ገምግመናል፡፡ ለወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርም ሪፖርት አድርገንና አምኖበት ማዕከላቱን ሳቢ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል፡፡ በወጣት ማዕከላቱ ኢንተርኔት ካፌ እንዲከፈት፣ አዳራሾች ከመሰብሰቢያነት ባለፈ ወጣቶች ችሎታቸውንና ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት እንዲሆኑ ጠይቀናል፡፡ አብዛኛዎቹ ማዕከላት ያሉበት ቦታ ሳቢ አይደለም፡፡ ጣራው ተሠርቶ አለ ብቻ ከሚሆን ወይም የስብሰባ አዳራሽ ብቻ ከሚሆን ወጣቶች የሚሰባሰቡበት የሚለወጡበት አዳዲስ ነገሮች የሚፈጥሩበት እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡   

ሪፖርተርከማዕከላቱ ባሻገር ወጣቶች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችስ አሉ ማለት ይቻላል? ምክንያቱም ኳስ የሚጫወቱበት ቦታ የቸገራቸው በየመንገዱ ከመኪና ጋር ድብቅብቆሽ ሲጫወቱ ይታያል?

አቶ ባልቻወጣቱ ሊውልባቸው የሚችሉ ቦታዎች በተለይ በመልሶ ማልማት አካባቢዎች ላይ የሉም፡፡ የጤና ቡድን አቋቁሞ ዱብዱብ ማለት በቦታ ምክንያት ከባድ  ሆኗል፡፡ ነባር ሜዳዎች በራሱ ለተለያዩ ልማቶች እየዋሉ ነው፡፡ በየአካባቢው የነበሩ ኳስ ሜዳዎች በአንድ ወቅት በብዛት ለድርጅቶች ይሰጡ ነበር፡፡ በዚህ ላይ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ በዚህ መነሻ ባለፈው ዓመት ላይ በአሥሩም ክፍለ ከተሞች በእያንዳንዱ ሁለት ዞናል ስታዲዮሞች እንዲገነቡ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የተጀመሩ ስታዲዮሞች፣ የታጠሩ ቦታዎችም አሉ፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲገነቡ ዞናል ስታዲዮም ባይሆን የፋትሳል ሜዳዎችን ያካተቱ እንዲሆኑ ጥያቄ እያቀረብን ነው፡፡ በቀጣይ ይካተታል ብለን እናስባለን፡፡ አሁንም ግን በቂ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡

ሪፖርተርየወጣት ማኅበሩ የመንግሥት ተለጣፊ ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡ ነፃ አይደላችሁም ይባላል፡፡ በዚህ ላይ ምን ትላለህ? 

አቶ ባልቻማኅበሩ ከመንግሥት ጋር መገናኘት የለበትም፡፡ የሚያገኛኙን የጋራ ሥራዎቻችን ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ በዘለለ የፖለቲካ ጫና የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያለበት ማኅበር እንዲሆን አይፈለግም፡፡ ማኅበራችን የተቋቋመበት ዓላማም ሕገ ደንባችንም ይህንን አይደግፍም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት የሚቀያየሩ የመንግሥት ኃላፊዎች ማኅበሩ በሥራቸው እንዲሆን ጫና የማድረግ ነገር አለ፡፡ ማኅበሩም ደግሞ በነበሩ አመራሮች ፍላጎት የፓርቲ አባል የመሆንና ተልዕኮ የመቀበል፣ በመንግሥት ላይ ተለጥፎ የመንቀሳቀስ ነገር እንዳለበት ገምግመናል፡፡ ማኅበሩ ከተቋቋመ 21 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ገና የተመሠረተ አካባቢ ለበርካታ ዓመታት በጣም ጠንካራ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ብዙ ወጣቶች የሚከተሉት ማኅበር ነበር፡፡ መሀል ላይ ደግሞ የተዳከመበት፣ አመራሮቹም የግል ጥቅማቸውን በማሳደድ ተጠመዱበት ወቅት ነበር፡፡ ከዚያ መልሶ የማንሠራራት ነገር አሳይቶ ነበር፡፡ የመጨረሻ ግምገማችን የሚያሳየው ማኅበሩ ለድርጀትና ለመንግሥት ተላላኪና ተለጣፊ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ ያበቃነው ደግሞ ማኅበሩ ውስጥ ስንሠራ የነበርን መሪዎች ነን፡፡ ያለው ጣላቃ ገብነት በሁለት መንገድ የሚታይ ነው፡፡ አንደኛ ማኅበሩ ራሱ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባበት ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የግል ፍላጎታቸውን ማራመድ የሚፈልጉ አመራሮች ማኅበሩ በዚያ እንዲቃኝ ጫና ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ ተፅዕኖ ነፃ የሆኑ ወጣቶችን መፍጠር አለብን የሚል ሐሳብ ይዘን ወደ እንቅስቃሴ ገብተናል፡፡ እኔ በማስተባብርበት ቦሌ ክፍለ ከተማ ላይ 12 ወረዳዎች ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የወጡ አዲስ ኃይል ያላቸውን ወጣቶች አምጥተናል፡፡ ለጥቅምም ሆነ ለፖለቲካ ብለው ማኅበሩን ተለጣፊ የሚያደርጉ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያላቸው ወጣቶች በየወረዳው እያመጣን ነው፡፡ እነዚህ ማኅበሩን ተለጣፊ ከመሆን ያድናሉ፡፡

ሪፖርተርየመንግሥት ተለጣፊ በመሆናችሁ ምን ምን ችግሮች ገጥሟችኋል?

አቶ ባልቻበአብዛኛው ወጣት ዘንድ ማኅበሩ የመንግሥት ድርጅት እንደሆነ ተደርጎ መታመኑ ራሱ ዋናው ችግር ነው፡፡ በምንሠራቸው ሥራዎች የማኅበሩን ሳይሆን የመንግሥትን አጀንዳ እንደምናስፈጽም ነው የሚታሰበው፡፡ እዚህ መፍታት ያለብን የወጣቶችን ጥያቄ እያለ፣ በሌላ ጉዳይ መጠመድ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ አንቺ ላይ እምነት የለውም፡፡ ማኅበሩ የልጄን ችግር ያስወግድልኛል የሚል ወላጅ፣ ማኅበሩ የሚታገለው ለእኔ ነው የሚል ወጣት የለም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...