Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አሚን አጠቃላይ ሆስፒታል በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው ሆስፒታል ሥራ ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ስለሕክምና አገልግሎት ሲታሰብ፣ ተገልጋዩን ሐሳብ ላይ ከሚጥሉ ሰቀቀኖች አንዱ ለሕክምና የሚወጣው ወጪ ነው፡፡ በተለይ የግል ሆስፒታሎች ከካርድ ጀምሮ የሚጠይቁት የገንዘብ መጠን የተገልጋዩን የመክፈል አቅም ያላገናዘበ በመሆኑ፣ በርካቶች ተገቢ ሕክምና ማግኘት ሲሳናቸው ይስተዋላል፡፡

‹‹ታማሚዎች እኛ ጋር ሲመጡ ቅድሚያ ገንዘብ መያዝ አለመያዛቸውን አንጠይቅም፤›› የሚሉት ዶ/ር ተክለአብ ዛይድ ሀብተሚካኤል፣ የአሚን አጠቃላይ ሆስፒታል ባልደረባ ናቸው፡፡ ‹‹መጥቶ ሳይታከም የሚሄድ ሰው አይኖርም፡፡ በአቅም ደረጃ ሁሉንም ማኅበረሰብ ያማከሉ ክፍሎች አሉን፤›› በማለት አክለዋል፡፡

ላለፉት ሰባት ዓመታት በሕክምና ዘርፍ ሲያገለግል የቆየው አሚን አጠቃላይ ሆስፒታል ለሕክምና አገልግሎት ተስማሚና የራሱን ሆስፒታል በማስገንባት ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. አስመርቋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገባው አዲሱ ሆስፒታል፣ 60 የመኝታ ክፍሎችን ያሉት ከመሆኑም በተጨማሪ ለ200 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር አስችሏል፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት እንደጀመረም ታውቋል፡፡

‹‹ይህን ሆስፒታል ለመገንባት ስንነሳ ከዚህ ቀደም ስንሰጥ የነበረውን አገልግሎት ይበልጥ ለማስፋት በማሰብ ነው፡፡ ሆስፒታሉ ከተደራጀበት ቴክኖሎጂና የባለሙያዎች አቅም አንፃር ኅብረተሰባችንን በስፋት ለማገልገልና ለሕክምና ወደ ውጭ የሚጓዙ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን መንገላታትና ከፍተኛ ወጪ የሚያስቀር ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ውስጥ ለማከም ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም በላይ ከጎረቤት አገሮች የሚመጡ ታካሚዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል አቅም ይፈጥርልናል፤›› በማለት ዶ/ር መሀመድ ሽኩር የአሚን አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በምርቃቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሉ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በአራት የሥራ ክፍሎች ያዋቀረ ሲሆን፣ የውስጥ ደዌ ሕክምና፣ የቀዶ ጥገና ሕክምና፣ የማህፀንና ጽንስ ሕክምና እንዲሁም የሕፃናት ሕክምና ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ሆስፒታሉ አጠቃላይ የሕክምና አገልግሎት የሚያቀርብ ሲሆን በተለይም የጉበት፣ የጨጓራና የአንጀት ሕክምናዎችን በልዩ መልኩ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ዲፕሎማቶች በተገኙበት የሆስፒታሉ የምረቃ ፕሮግራም ላይ በእንግድነት የተገኙት የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን በበኩላቸው የመንግሥት ትኩረት የመጀመርያ ደረጃ ጤና አገልግሎት በመላ ኢትዮጵያ ማዳረስ ስለመሆኑ አውስተዋል፡፡ ሚኒስትሩ የግሉ ባለሀብት በአሁኑ ወቅት ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ያለበት ሁኔታን በማውሳት፣ ከመንግሥት እኩል ወይም በተሻለ ደረጃ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

 የጤና ሚኒስቴር፣ አገርና ሕዝብ ለማገልገል፣ ሕመምተኞችን ለመርዳት በዚህም ሌሎችም ጠቅሞ ለመጠቀም ፈቃደኛ በሆኑና በኢትዮጵያ መሥራት ለሚፈልጉ የግል ባለሀብቶች ሙሉ ድጋፉን እንደሚሰጥና እንደሚያበረታታ በሚኒስትሩ ተገልጿል፡፡

የመንግሥትን ቁርጠኝነት በሦስት ነጥቦች አማካይነት የተገለጸ ሲሆን፣ አንደኛው ሙሉ በሙሉ ጤና ተቋማት የራሳቸውን አገልግሎት መስጫ ገንብተው በመክፈት የሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ አገልግሎት ለመስጠት የሚፈልጉ ካሉ ቢሮክራሲውን በማሳጠርና ከመሬት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ማገዝ አንደኛው ነው፡፡ በተጨማሪም ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በጋራ ለመሥራት ለሚፈልጉ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም በሽርክና የሚሠሩበትን መንገድ ማመቻቸትም የሚኒስቴሩ ሚና እንደሆነ ተነግሯል፡፡ መሣሪያ እንዲሁም የጤና ባለሙያ ይዞ በመምጣት ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ውጭ ሄዶ በመታከም የሚገኙ አገልግሎቶችን እዚሁ ለመስጠት ፈቃደኛ ለሆኑም ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተብራርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች