ሰላም! ሰላም! ‹‹ቢያልፍልን ነው ወይስ ቢያልፍብን የሚገርመው?›› ብላቸው አዛውንቱን ባሻዬን፣ ‹‹ደግሞ ምን ሰማህ?›› አሉኝ ተሰላችተው። ጉድ በማያልቅበት አገር ዕድሜያቸው ረዝሞ መከራ ያያሉ። አንዳንዴ እሳቸውን እያየሁ ‘እግዜርም አውቆ ሰማይን አርቆ’ እላለሁ። አስባችሁታል አማካይ የዕድሜያችን ጣሪያ እንደወጉ ሰባና ሰማንያ ቢሆን? ኑሮና በጀታችን ኦዲት ሲደረጉ ለካ አርባ አካባቢ ስንደርስ ሰከን የሚያደርገን ወዶ አይደለም ያስብላል። ግን ‘ጣሪያችንና ኪሳችን እኩል እያፈሰሱ የጎርፍ ኑሮ እየኖርን፣ ሰነባበትን አልሰነባበትን ምን ልዩነት አለው?’ ብላችሁ ለማን ትተነፍሱታላችሁ? እውነቴን እኮ ነው። የሚያየውን ዓይቶ ጊዜን አሰናስሎ የሕይወትን ትርጉም ለማብላላት አቅም ያጣው ቁጥሩ በላቀበት በዚህ ዘመን፣ እንዲህ ያለውን አስተያየታችሁን በጨለምተኝነት ብቻ ሳይሆን በሽብርተኝነት ሊያሳማችሁ ይችላል። ያውም ነገራችን ሁሉ ወዲህና ወዲያ በሆነበት ሰሞን፡፡ ገና ከአዲሱ በጀት ላይ በሚደርሰን ቁራሽ አፋችንን ሳናረጥብ? ለነገሩ የዘመኑ ትውልድ በጠዋት ቁርሱን በድራፍት በሚያወራርድበት በዚህ ጊዜ ምንስ ቢፈጠር፣ ማን ማንን ቢያማ ምን ይገርማል! መተማማት እንደሆነ የዘመናችን ወረርሽኝ ሆኖ ሁላችንንም ለክፎናል!
ታዲያ ባሻዬ ሲጠይቁኝ የመለስኩት፣ ‹‹እንደ እኛ ዓይነት ችግር በችግር በተደራረበበት አገር ከበጀት ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ተዘረፈ፣ መወራረድ አልቻለም ተብሎ ፓርላማ ሪፖርት ሲቀርብ መስማት ነውር አይደል?›› የሚል ነበር። ‹‹ያልተሠራበትና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የወጣው ሲደመር ናላ ያዞራል እኮ፤›› ብላቸው፣ ‹‹እህ በጀት መድበን ስናበቃ መቆጣጠር አቅቶን ወሬውን ማን ያውራልን?›› ብለው ዝም አሉ። ዝምታቸው ሲቀጥል አንዳንዴ ባሻዬ እንዲህ ላለው ጨዋታ አይመቹም እያልኩ ተለየኋቸው። ሐሜት አይወራረድ! እስኪ አሁን ምን አለበት ስለአደባባይ ጉዳችን ብንነጋገር? አጉል ያልሆነውን ነን፣ የማንፈጽመውን እናስባለን ማለት ተለምዶ ይኼው ጨዋታም በገደብ ሆነ። ሆድ ይፍጀው ማለት ብቻ። እኔ አንዳንዴ የመናገር ነፃነት የተተነበየለትን ያህል አልፀደቀም ሲባል ስሰማ፣ ጨቋኙ መንግሥት ወይስ እኛው ራሳችን የሚለው ጥያቄ በአዕምሮዬ እየተመላለሰ ያወላግደኛል። ከሐሳብ እስከ መንገድ እያወላገደን ሦስተኛውን ሚሊኒየም ከጀመርን አሥራ አንድ ዓመታት መንጎዳቸው እንደ ተዓምር ካልታየ ምን እንደሚታይ ራሳችሁ ፍረዱ! መፍረድ ካቃታችሁ ወደ ለላይኛው ጌታ አመልክቱ!
መቼም የጨዋታ ቀስቃሹ ጨዋታ ነው። ሰሞኑን አይገኝም ብዬ በገፍ የማስገባው ያልተጣራ ወሬና አሉባልታ ጭንቀት እየፈጠረብኝ ሥራ አላሠራኝ ቢለኝ፣ ለምሁሩ ለባሻዬ ልጅ ደወልኩና ‹‹እባክህ ቡና እንጠጣ›› እያልኩ ሥራ ሳስፈታው ሰነበትኩ። ቡናን ወደ ውጭ በመሸጥ ከተጠቀምነውና ወሬን በቡና ይዘን ካቃጠልነው ዕድሜ ይበልጥ በማንኛቸው እንደተጠቀምን እንጃ! ራሴን የመታዘብ አመሌ ሲነሳብኝ ግን ይኼንኑ ጥያቄ ለራሴ አቀርባለሁ። እንግዲህ ብዙ ጊዜ እንደምላችሁ ምድራችን የጥያቄዎች ጎተራ ስለሆነች ራሴን ለጠየቅኩት ጥያቄ ሁሉ መልስ በማሰላሰል እንዳትወጠሩ አደራ! የዘመኑ ሰው ለአደራ ባይታመንም እኔና እናንተ ግን ሽርክ ነን ብዬ እገምታለሁ። እንዲህ እየተባባልን ጊዜውን ካልገፋነው ፀብ በደላላ ብለን እንጋጫለን! እኔና እናንተ ከምንጋጭ የቀረው ቢቀር ይመረጣል!
ታዲያ የባሻዬ ልጅ ከተፍ ከማለቱ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹አንበርብር ከዓለት ፍልፈላ ሥልጣኔ ወደ ጭቃ ምረጋ እንደ ወረድን አስበኸው ታውቃለህ?›› ነበር ያለኝ። የደላላ አዕምሮዬ ያለ ትንታኔ ስለማይኮረኮር ‹‹ምን ለማለት ፈልገህ ነው?›› አልኩት። ‹‹ከአክሱም ሐውልቶች እስከ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ድረስ የጥበብ ችሎታችን የት ሄዶ ነው ወደ ጭቃ ረጋጭነትና ወደ ጭሰኝነት ሕይወት ወርደን የተሰቃየነው እያልኩህ ያለሁት፤’›› ብሎኝ አረፈው፡፡ ድብርትና ጭንቀት ፈጠረብኝ ካልኳችሁ ከሰሞነኛው የወሬ ቱማታ ይልቅ ይኼኛው ትንታኔ ብሶኝ አረፈዋ! ጉድ እኮ ነው! ‘ርቃለሁ እያልኩ ከአንቺ እሸሸጋለሁ፣ ዕድሜዬን በሙሉ ወንዝ እሻገራለሁ፣ ዳሩ ምን ያደርጋል ወንዙን አቋርጬም ስምሽ ትዝ ይለኛል፤’ አለ ያገሬ ሰው። ይኼ የአገሬ ሰው ስንቱን ችሎ፣ በስንቱ ገጥሞ፣ ከስንቱ ታግሎ እንደኖረ ይገርማል፡፡ ኋላ ቡናዬን ፉት እያልኩ አስቤ አስቤ (ማሰብ እንኳ አያስፈልገውም ነበር) ‹‹ማን እርስ በርስ ይጋደልልን ታዲያ?›› አልኩት። ለሦስት ሺሕ ዘመናት የድሎት ታሪክ የተነገረው ትውልድ፣ ከዚህ የተሻለ ጠይቆ ካለበት የተሻለ ምን ምን ማግኘት ይችላል ታዲያ? አይደለም እንዴ! ከዓለም ግንባር ቀደም የነበረ ሥልጣኔ ብን ብሎ ጠፍቶ፣ በቀን ሁለቴ የረባ ምግብ ማስገኘት ያልቻለች አገርን ጭራሽ ወደ ኋላ ለመጎተት የተጀመረው ትንቅንቅ አያሳዝንም ወይ! በጣም ያበሳጫል!
ቡናዬን አጣጥሜ ዕድሜ ለባሻዬ ልጅ ስሜቴ እንደተነካ ወደ ሥራ ልሰማራ ብድግ አልኩ። ይሸጣል የተባለ ቪላ ቤት ነበረኝና ጥቂት ከማይባሉ ወዳጆቼና ደንበኞቼ ጋር ስደነቋቆር ቆይቼ (ኔትወርክን ልብ ይሏል)፣ አንድ ሰው ወዲያውኑ ቤቱን ማየት እንደሚሻ አስታወቀኝ። ከደንበኛዬ ጋር ለመገናኘት ቤቱ ያለበትን ሥፍራ እየነገርኩት ሳለሁ በቆምኩበት አንድ ለግላጋ ወጣት ክፉኛ እያየ ሲታከከኝ አስተዋልኩ። ሞጭላፋ መስሎኝ፣ ‹‹አንዴ መልሼ ልደውል›› ብዬ ስልኩን ዘጋሁ። መልሼ ስደውል በስንት መከራ የሚገኘው ኔትወርክ እንዴት እንደሚያማርረኝ ሳስብ ንዴቴ ተባባሰ። በደም ፍላት ወደ ወጣቱ ዞሬ ‹‹ምን ፈለግክ?›› ብዬ መጮህ። እርሱም፣ ‹‹ጉድ ሆኜ ነው!›› ማለት፣ ጉድ መሆንና ጉድ መሠራት ብርቃችን ይመስል።
አላስችለኝ ብሎ ምን እንደሆነ ጠየቅኩት። የከተማ ልጅ አለመሆኑና ብላቴናነቱ አሳሳኝ። ‹‹ክፉ መካሪ ጋሼ! ክፉ መካሪ ነው እዚህ ያደረሰኝ፤›› አለኝ ዓይኖቹ እንባ አቅረው። ‹‹ሰው እንኳን አዲስ አበባ አሜሪካ ካልሄድኩ ብሎ ፍዳውን ያያል፣ አንተ የተወለድክበት አገር አድገህ አርጅተህ እስክትሞት ታጠብቃለህ ብሎ ካገሬ ክፉ መካሪ አስኮብልሎኝ ነው። እዚያ ሆኜ የተወራልኝ ሌላ እዚህ የማየው ሌላ። እባክዎ መሳፈሪያ ይሙሉልኝና አገሬ ልግባ፤›› አለኝ አስተዛዝኖ። እሱን እንዲህ ሳነጋግር በአጠገቤ የሚያልፉ በአለባበሳቸው ሥልጡን (የአስተሳሰባቸውን አላውቅም) የሚባሉ ወጣቶች ስለሩሲያና አሜሪካ ፖለቲካዊ ፍጥጫ እየተጨቃጨቁ ነበሩ፡፡ ልመነው አልመነው? እያልኩ አመነታለሁ። መቼም ዘንድሮ የሌብነት ታክቲክ አልተቻለም። ወዲያው ደግሞ ሦስት የሚሆኑ ወጣቶች (አንደኛዋ ሴት ናት) ስለማንቸስተር ዩናይትድ የተጫዋቾች ዝውውር ተጋግለው እየተነጋገሩ ባጠገቤ አለፉ። ማሰብ፣ መወሰንና ማመን ከበደኝ። ከልጁ ይበልጥ እኔ ችግረኛ መስዬ ሳልታይ አልቀረሁም። መልሼ ልደውልልህ ያልኩት ደንበኛዬ ቆይቼበት መልሶ ሲደውል ከቁም ቅዠቴ ነቃሁ። ለልጁ ሦስት ብር ጀባ ብዬው “ሃሎ!” አልኩ። የእንጀራ ነገር ሆነና ሦስቱን የጎዳና ትዕይንት አገጣጥሜ ሳልተነትን ተፈተለኩ። በየት በኩል? ለነገሩ ሁሉም ከሊቅ እስከ ደቂቅ ተንታኝ በሆነበት አገር፣ ማን አዳማጭስ አለና ነው ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ትንተና ውስጥ የምገባው!
ከደንበኛዬ ጋር የተቀጣጠርንበት ሥፍራ እኩል ደረስን። ወደ ተባለው ቪላ የሚወስደው መንገድ ውኃ ለመሰለችው የደንበኛዬ አዲስ መርሰዲስ መኪና ተስማሚ አልነበረም። ስለሆነም ማቆሚያ ፍለጋ ቁም ስቅሌን አየሁላችሁ። አይ ደላላ መሆን አልኩ ቢቸግረኝ። ደንበኛዬ መኪናውን እንደ ዓይኑ ብሌን ከማየቱ የተነሳ ለምን አንዳንድ ዕቃዎች ጨማምሮ እዚያው አይኖርም ያሰኛችኋል። ቤቱን ዓይተን ስናበቃ ሻጭና ገዥ ጥግ ይዘው ማውጋት ጀመሩ። እኔ ቤቱን ከጠቆመኝ አንድ ሌላ ሰው ጋር አወራለሁ። ‹‹ለመሆኑ ቤቱ የዚህች አንድ ፍሬ ልጅ ነው?›› አልኩ ደንበኛዬ ወደሚያናግራት ልጅ እያየሁ። ‹‹የውርስ ንብረት ነው፡፡ ከወንድሞቿ ጋር አልስማማ ስላሉ ሸጠው ለመካፈል ወስነው ነው፤›› ብሎኝ፣ ‹‹እናት አባት ላይ ታች ብለው ያፈሩትን ንብረት ይኼውልህ የዛሬ ልጅ ፍቅር አጥቶ ይጫወትበታል፤›› ብሎኝ በረጅሙ ተነፈሰ። ውሎ አድሮ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በተገኙበት ቤቱ ሲሸጥ እኔም ኮሚሽኔን ተቀበልኩ። ቤቱን የሸጡት ወንድምና እህቶች ገንዘብ ተከፋፍለው ሲያበቁ ዳግመኛ ዞረው የሚተያዩ አይመስሉም ነበር። እንዲህ የሚበታተነው ቤተሰብ መብዛት ይሆን አገሩንና ምድሩን ጀርባና ሆድ ያደረገው? እኔማ ፈራሁ! የአንዳንዶቻችን ሁኔታ አገርንም እንደነዚህ ቤተሰቦች የሚያስበትን ይመስላል፡፡
በሉ እስኪ እንሰነባበት። ከመሰነባበታችን በፊት ‘አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስገርሙኛል’ የሚለውን የዝነኛውን ጥሎዬ ዜማ ጋብዣችሁ ሳበቃ፣ አንድ ያስገረመኝን ነገር ደግሞ ላውጋችሁ። ባሻዬ ሰሞኑን ዘመድ ከገጠር ካመጣላቸው ሁለት ዶሮዎች አንደኛዋ ለሰኔ ፆም ፍቺ ከመታረዷ ከሰዓታት በፊት ጠፍታ ነበር። ሞትን ሽወዳ በሉት ከፈለጋችሁ። ብቻ ተጠልፋ፣ ታርዳም ሆነ ወይም ራሷን አጥፍታ ሳይታወቅ ውላ አድራ ከትናንት በስቲያ ቂን ቂን እያለች መጣችላችሁ። ባሻዬ በጣም ተገርመው አስተውለዋት ሲያበቁ፣ ‹‹እህ ምን ላድርጋት እንግዲህ?›› ብለው ጎረቤቱን ሐሳብ አዋጣ አሉት። በዚህ መሀል ነገር አዋቂ ነን የሚሉት ሁለት ጎራ ፈጥረው፣ በዓይን ጥቅሻ የሚግባባው ጎረቤት በሁለት ወገን ተከፈለላችሁ። የአንደኛው ወገን ስብስብ ዶሮዋ ልታወጣ የምትችለውን ዋጋ እያሰላ (ልክ ከኪሱ አውጥቶ እንደ ገዛት ሁሉ)፣ ‹‹ባሻዬን የሚያህል በአገር ምድሩ የተከበሩ ታላቅ ሰው ከድታ መጥፋቷ አንሶ በፍጥነት ታርዳ እዚሁ መብላት ሲገባን፣ በሕይወት ትኑር ማለት ምን ማለት ነው?›› ይላል። ሌላው ጎራ ደግሞ ተቀብሎ፣ ‹‹ይህች ዶሮ ተልዕኮ ቢኖራት ነው እንጂ ልዩ ተሰጥኦ እንዳላት እንደ ውሻ አነፍንፋ ስትመለስ አንገትዋን ጠምዝዞ ወንዝ መጣል ነው!›› በማለት አስደንጋጭ መፍትሔ አቀረበ። ባሻዬ ካሰቡት በላይ ጎረቤት በዶሮዋ ጉዳይ ለሁለት ተከፍሎ ቢያዩት፣ ‹‹ወይ ጉድ! እውነትም አብረን እንኖራለን እንጂ ልባችን ከተለያየ የቆየ ይመስላል፤›› አሉኝ በጆሮዬ። አይ ባሻዬ ፈላስፋ ናቸው እኮ!
አመሻሽ ላይ እኔና ማንጠግቦሽ አልጋ ልንወጣ ስንዘገጃጅ ነገሩን አንስተን ተጫወትን። ‹‹አንቺዬ እውነት ጎረቤቱ በሁለት ጎራ በመከፈል ጠፍታ የመጣችው ዶሮ ጉዳይ የምር አሳስቦት ነው? ወይስ ከጀርባ ሌላ ነገር አለ?›› ብዬ ከእኔ እሷ ታውቅ ይሆናል በማለት ብጠይቃት፣ ‹‹አንተ ደግሞ ባሻዬ የሰውን ሁኔታ ለመለካት ‘ወስኑባት’ ሲሉ፣ አዳሜ አጋጣሚውን በመጠቀም የልቡን ክፋት አውጥቶ እንዲያ ዓይኑ ደም እስኪመስል የተጠዛጠዘው እኮ በአሉባልታና በሐሰተኛ ወሬ ስለተካነ ነው፤›› አለችኝ። ‘በዚህ ዓይነት ሕዝብ ስለራስህ ራስህ ታውቃለህ የተባለ ቀን፣ ምርጫው ለራሱ የተተወለት ቀን ምን ሊሆን ነው? እያልኩ አሰብኩ። በአንድ ወቅት የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ለነገሩ ሕዝብ በራሱ ለራሱ ቢወስን የዴሞክራሲ መገለጫ ነው፡፡ ሕዝብ ወስን ተብሎ ሒደቱ ሲጀመር እንደ ጥንብ አንሳ አሞራ የሚከቡት ያዋክቡታል እንጂ፡፡ የገዛ አዕምሮውን በመጠቀም ያሻውን መምረጥ ሲኖርበት፣ እነ አውቅልሃለሁ ይግተለተሉበታል፡፡ እኛ ነን ምኞትህን የምናውቅ ብለው ድምፁን ይሰርቁታል. . .›› ያለኝ ትዝ አለኝ፡፡ የጎረቤት ሰዎቻችን በነገረ ሠሪዎች ጣልቃ ገብነት በጎራ ተከፍለው የደረሱበት ውሳኔ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ትውስታ ጋር ሲዛመድብኝ፣ ሁሉም ነገር አስጠልቶኝ በመሀል እንቅልፌ መጥቶ ህልም ጀመረኝ። በህልሜ ያየሁት ደግሞ በገሃድ የማየውን እየመሰለኝ በቅዠት ያወላግደኛል፡፡ የሆነስ ሆነና በስንቱ እንወለጋገድ? መልካም ሰንበት!