በተሾመ ብርሃኑ ከማል
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. አገር አቀፍ የመንዙማ ጉባዔ ለማካሄድ ተዘጋጅቶ በነበረበት ጊዜ እኔም በባህልና ቱሪዝም በኩል ተጋብዤ የበኩሌን አስተዋጽኦ እንዳደርግ በቦታው ተገኝቼ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በወቅቱ የተከሰተውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ለበረራ በተዘጋጀሁበት ደቂቃዎች ብሰማም ጉባዔው ይደናቀፋል የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ ዳሩ ግን ጠዋት ላይ ደሴ ስደርስ ጉባዔው ለሌላ ጊዜ መዛወሩን ሰማሁና በሄድኩበት እግሬ ተመለስኩ፡፡
ሆኖም በተነገረኝ አጭር ጊዜ መጠነኛ ዝግጅት አድርጌ ስለነበር ከሁሉ አስቀድሞ የኢትዮጵያ ረቂቅና ተጨባጭ ቅርስ አካል ስለሆነው ስለኢስላማዊ ረቂቅና ተጨባጭ ቅርሶች የምርምር ሥራቸውን ለሚያከናውኑ መጠነኛ ሐሳብ ለመፈንጠቅ፣ የጋዜጣው አንባቢ መንዙማ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እኔ ካየሁት አኳያ እንዲያይ፣ ምናልባት ጉባዔው ወደፊት የሚካሄድ ቢሆን ጥናታቸውን ለማቅረብ ተዘጋጅተው የነበሩ ተመራማሪዎች ተጨማሪ ሐሳብ ቢያገኙበት ተጨባጭና ረቂቅ ቅርሶቻችን ለማሳወቅ ለማፈልጉ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ቱሪስቶች አመቺ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ለመጠቆም በማሰብ ካጠናሁት ሰፊ መረጃ የሚከተለውን ጥናት ለዚህ ጋዜጣ አንባቢ በሚሆን መልኩ አቅርቤያለሁ፡፡ በዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ውስጥ ግጥምና ዜማ በኢትዮጵያውያን ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያላቸው መሆኑን እንደ መግቢያ በመውሰድ መንዙማ ምንድነው? የመንዙማ ዜማስ? ከዓረብኛ ውዳሴ፣ ምሥጋና፣ እንጉርጉሮ ግጥም ጋር ሲነፃፀር በምን ይመሳስላል ወይም በምን ይለያል? ለመሆኑ በአገራችን መንዙማ መች ተጀመረ? እነማንስ ጀመሩት? በኢትዮጵያውያን ሕይወት ምን ሚና አለው? የሚሉትን ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡ ከመጨረሻው ጥያቄ እንነሳ፡፡
ግጥምና ዜማ በኢትዮጵያውያን ሕይወት ምን ይመስላል?
ቀደም ያሉ ኢትዮጵያውያን አድናቆታቸውን ሐዘናቸውን፣ ደስታቸውን ለአምላካቸው፣ ለጌታቸው፣ ለጀግና፣ ለፃድቃንና ለቅዱሳን ወዘተ. እንደሚገልጹ ሥራቸውን በግጥምና ዜማ ጋር እንደሚያከናውኑ በሕይወት ዘመናችን የምናውቀው ነው፡፡ በዚህም መሠረት እናቶቻችን ወፍጮ ሲፈጩ፣ ውኃ ከሩቅም ሆነ ከቅርብ ወንዝ፣ እንጨት ከሩቅም ሆነ ከሩቅ ሲያመጡ፣ ከጥሬ ላይ ትንንሽ ድንጋዮችንና ሌሎች ጉድፎችን ሲለቅሙ፣ አንዳች ነገር ሲወቅጡ፣ ጥጥ ሲፈትሉ፣ ድር ሲያደሩና ሲዳውሩ፣ እርሻ ሲያርሙና ሲጎለጉሉ ድካም እንዳይሰማቸው የወዳጆቻቸውን፣ የዘመዶቻቸውን፣ የሥራቸውንና የዕጣ ፈንታቸውን በዜማና በግጥም ይገልጹ ነበር፡፡ ወንዶችም ሲያርሱ፣ ሲቆፍሩ፣ እህል በአውድማ ሲያበራዩ፣ ሲሸምኑ፣ ጥልፍ ሲጠልፉ፣ ከብት ሲጠብቁ፣ ረዥም መንገድ ሲጓዙ፣ ለተመሳሳይ አገልግሎት ያውሉት እንደነበር ከ50 እና 60 ዓመታት በላይ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን፣ እንዲሁም ዛሬም ቢሆን በገጠር የሚኖሩ ሁሉ የሚያውቁት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው
‹‹ዕድሌ ነው እንጂ እኔ የሰው አላማ፣
የአህያ ልጅ በቅሎ ወርቅ ተሸልማ››
የሚል ሥነ ቃል ቢያገኝ በተለይ የመኪናው ትውልድ በቅሎዋ ወርቅ ተጭና የምትሄድ ሊመስለው ይችላል፡፡ ነገር ግን የነገሥታት፣ የመሳፍንት፣ የመኳንንት፣ የባላባቶችና የቱጃሮች የጭን በቅሎ ወይም በዘመናዊ አገላለጽ ተሳፍረው የሚጓዙባት በቅሎ ልጓም፣ ልባብ፣ ግላስና እርካብ ወዘተ. በወርቅ ጌጥ የተለበጠ፣ የተሸለመ፣ ያማረ፣ የተዋበ፣ ሊሆን ስለሚችል ‹‹በቅሎዋ እንኳ በወርቅ የተጌጠ ኮርጫና ዕቃው ሲኖራት እኔ ዕድለ ቢሱን ግን አጥቼ፣ ነጥቼ፣ አበሳየን አያለሁ፡፡ ስለዚህም ዕድሌ የሰጠኝን መቀበል እንጂ ሰው አልሰጠኝም፣ አላደረገልኝም፣ በድሎኝ ነው ብዬ ማማረር አይኖርብኝም፤›› የሚል አንድምታ እንዳለው ለባለ መኪናው ትውልድ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡
‹‹ኮምቦልቻ ዝንጀሮ አላሻ ላይ ዝሆን
ጊምባ ላይ አንበሳ የሰፈረ እንደሆን፣
ይሉታል ያ አውሬ፣ ምን ይሆን ምን ይሆን፣
ያለ አቀማመጡ፣ ያለ ስፍራው ሲሆን››
የሚለውን የሼክ ሁሴንን ኮምቦልቻ የመንዙማ ግጥምን ላይ ላዩን (በግርድፉ) ስንመለከተው ሦስት የተለያዩ ሥፍራዎችና ሦስት የተለያዩ እንስሳት፣ በውስጠ ታዋቂም በሦስቱ ስፍራዎች ይኖሩ የነበሩ ሰዎችን እናገኛለን፡፡ ሦስቱም እንስሳት የተገኙት መገኘት በማይገኝባቸው ቦታና ዘመን መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ በዚህ የመንዙማ ግጥም መሠረት እንስሳቱ ዓይተዋቸው በማያውቁ ሰዎች ይዞታ አካባቢ በመገኘታቸው ምክንያት ‹‹ምን ይሆኑ?›› ብለው በአድናቆት ወይም በመገረም የሚመለከቷቸው ይሆናሉ፡፡ ሆኖም የግጥሙ ደራሲ ሦስቱን የእንስሳት ዝርያዎችና የታዩባቸውን ሥፍራዎች ከነዋሪዎቹ ሰዎችና ዘመን ጋር በማያያዝ ሰው መገኘት በማይገባው ስፍራ ሲገኝ ጥርጣሬ ላይ እንደሚወድቅና በተለየ ስሜት እንደሚታይ ይተርካል፡፡ ግጥሙና ዜማው ከዚህም ባሻገር ልብን እየመረመረ ያለ ቦታው የተቀመጠውና እንደ አውሬ የሚታየው ሰው ማን እንደሆነ ይጠይቃል፡፡ በአጭሩ ግጥምና ዜማ ያለበትን ሁኔታ፣ የነበሩበትን ዘመንን፣ ፍልስፍና፣ እምነትና ስለትምህርት የሚያንፀባርቅ ነው፡፡
ለመሆኑ መንዙማ ምንድነው?
‹‹መንዙማ›› የዓረበኛ ቃል ሲሆን የተገኘውም ነዞመ፣ ከተሰኘው ሥርወ ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም አዘጋጀ፣ አደረጀ፣ ትክክለኛ ቦታ ላይ አስቀመጠ፣ አስተካከለ፣ ተስተካከለ፣ አልሺዕር የሚል ቃል ሲጨመርበት ነዞም አልሺዕር ግጥም መደርደር፣ መግጠም፣ ቃላትን ሐረጎችን፣ ስንኞችን በትክክለኛ ቦታቸው ማስቀመጥ መደርደር ይሆናል፡፡ ኢንተዞመ፣ ተነዞመ፣ ተናዞመ፣ ሲሆን ደግሞ አዘገጃጀት፣ አደረጃጀት፣ አደራደር የሚል ስሜት ይሰጣል፡፡ ተንዚሙል ሺዕር ሲሆን ግጥምና ቅኔ የግጥምን ሥነ ጽሑፋዊ ውበት በተከተለ ሥልት፣ ሥርዓት፣ አካሄድ በቅደም ተከተል ማስቀመጥ፣ መደርደር፣ ለወጣለት ዜማ ወይም ለሚወጣለት ዜማ እንዲሆን አድርጎ መድረስ የሚል አንድምታ አለው፡፡ መንዙማ ከሌላው ግጥም የሚለየው ከእስልምና እምነት ጋር የተያያዘ መንፈሳዊ ግጥም በመሆኑ ነው፡፡ እስካሁን ሲነገር የነበረው የመንዙማ ትርጉም በዚህ የሚተካ ከሆነ ዜማውንና ግጥሙን፣ እንዲሁም ውዝዋዜውንና የምት መሣሪያውን የሚያጠቃልል ገላጭ ስም ማውጣት አስፈላጊ ይሆናል፡፡
ግጥምና ዜማ እንዳይሰበሩ ጥንቃቄ ስለማድረግ
ከመንዙማ ጋር ግጥምና ዜማ አብረው የሚኖሩ ሲሆን ገጣሚዎቹና ዜማ አውጭዎቹም በሚያውቁት፣ በታያቸው፣ በበራላቸው፣ በተረዳቸው መንገድ ሐሳብ የሚያመነጩና የሚያዜሙ ሲሆኑ የግጥምና የዜማ ደራሲዎቹም ዘመን አይሽሬ ሥራ ሊያበረክቱ እንደሚችሉት ሁሉ ለጊዜው አንጎራጉረው የሚተውት ሊሆን ይችላል፡፡
ከመንዙማ ግጥምና ዜማ ጋር የሚነሳው ዋናው ቁም ነገር ደራሲዎቹ እነማን ናቸው? ከየት ናቸው? በኅብረተሰቡ የነበራቸው ወይም ያላቸው የላቀ ደረጃ እስከ ምን ድረስ ነው? ከዚህም በተጨማሪ በግልጽም ሆነ በረቀቀና በጠለቀ ሚስጥራዊ መንገድ የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድነው? ጥልቀቱና ምጥቀቱ ምን ያህል ነው? ቅርፁ ምን ያህል ማራኪ በሆነ ውበት ይዘቱን ገልጾታል? ብሎ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ መንዙማውን ሰምተን ምን አገኘን? ደረጃችንን ከፍ አደረግን ወይስ የጨመርነው ነገር የለም? ከዚህም በላይ የመንዙማ ግጥሞቹ በእንጉርጉሮም ሆነ በሌላ መንፈስ ቀስቃሽና ስሜት ኮርኳሪ ዜማ ተቀናብረው ሲቀርቡ ምን ያህል ቀና ናቸው? ምንስ ያህል የሰውን ልቦና ይማርካሉ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡
ወንድሜ ሼክ ኑረዳኢም አወል ከሐሸንጌ (ደቡብ ትግራይ) እንዳስረዳኝ መንዙማ ጥንታዊ የፈጣሪ ማመስገኛ፣ የነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ማወደሻ፣ የፈጣሪ አሀድነትን ማስተማሪያ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ በሰሜን ኢትዮጵያና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የንጉሥ (ወሎ) ሙጃሂዱ በግንባር ቀደምነት እንደሚጠቀሱ፣ ቀጥሎም የአና ሸኾች እንደሚመጡ፣ ከአናም ወደ ዳና፣ ከዳና ወደ ጫሌና ወደ ሌሎች እንደ ተዛመተ አስረድቶኛል፡፡ በራያ (አና) እነ ጀማሉዲን አንይ፣ ሼክ ኢብራሂም ሪሓና፣ ሼክ አዋሎዎ፣ ሼክ ዓብዱሶመድ፣ ሼክ ዓብዱራሕማን፣ ሼክ መሐመድ ዓረቡ ሲራጅ፣ ሼክ ዓብዱረዑፍ፣ ሼክ ቡሰይሪል አንይ፣ ሼክ ሚስባህ አንይ፣ አባታቸው ሼክ አወል እንደሚጠቀሱ አብራርቶልኛል፡፡ በዚህ ዓይነት የዳናውን፣ የጫሌውን፣ የሾንኴን፣ የዳባቱን፣ የጎንደሩን፣ የጎጃሙን፣ የቀጥባሬውን፣ የአልከሶውንና የአብሬቱን መግለጽ ይቻላል፡፡
የወንድሜ ልጅ መሐመድ ዓረብ ዓብዱራህማንም፣ በራያ መንዙማ የሚደረሰውም ሆነ የሚዜመው በመርህ ላይ ተመሥርቶ እንደሆነ ጠቅሶ በተለይ በአና ወጣት ዓሊሞች ትክክለኛውን አቅጣጫ ተከትለው እንዲጓዙ የሼኮች ክትትል ይደረግ እንደነበረ፣ ነገር ግን ጉዳዩ ጠለቅ ያለ ጥናትና ምርምር እንደሚያስፈልገው አስረድቶኛል፡፡ ይህን ሐሳብ ሼክ ኑረዳኢም አወልም መንዙማ በተጠና ሕግ፣ በሥነ ሥርዓት የሚመራ እንደሆነና መንዙማ ማን ማቅረብ እንደሚኖርበት፣ እንዴት ሥርዓቱን ጠብቆ ማቅረብ እንደሚገባ፣ መንዙማ መሪው በዜማ በሚያቀርብበት ጊዜው ሌላው ምን ማድረግ እንዳለበት፣ ለምሳሌ አንዱ መንዙማውን አውቀዋለሁ በሚል ጣልቃ እንዳይገባና እንዳያደናቅፍ፣ ዜማው በትክክል እንዲባል፣ ግጥሙ እንዳይሰበር፣ ሥርዓት ይበጅለት እንደነበረ አብራርተውልኛል፡፡
ይህም ሆኖ ኢስላም ወደ ኢትዮጵያ በተለይም በሰሜንና ማዕከላዊ የአገራችን ክፍል የገባው መዲና ከመግባቱ በፊት ከሆነ፣ ለምን ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት እንደመጣ ተደርጎ ይወሰዳል? በተለይም እንደሆጂራ ፎቂሳ፣ አራ፣ ቢሌት ከ500 እስከ 1000 በሚቆጠር ዓመት ኢስላም የሚሰበክባቸው ቦታዎች ከሆኑ መንዙማ ለምን ኋላ መጣ? ከነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ሕልፈት ጀምሮ ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጡ ዓረቦች በአገራችን ያለማቋረጥ እንደመጡ፣ ከዚህም በላይ የንግድ ግንኙነታቸው ጥንታዊ እንደሆነ ይታወቃልና እንደምን በዓረቢያ ለረዥም ጊዜ የነበረው ‹‹መንዙማ›› ወደ አገራችን ሳይገባ ቀረ? ሌላው ይቅር ነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) በሕይወት እያሉ ኢትዮጵያውያን በዜማ ያደንቋቸው እንደነበረ በተለያዩ የዓረብ ጸሐፊዎች ተገልጾ ሳለ እንደምን በአገር ውስጥ ይህ ባህላዊ እሴት ድምጥማጡ ጠፋ? ለአንድ ትውልድ ያህል ወይም ከዚያ በላይ የጠፋ ታሪክ ይኖር ይሆን? የሚል ጥያቄ እዚህ ላይ ማንሳት በእጅጉ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
እናም ለጊዜው በሰሜኑና በማዕከላዊው የአገራችን ክፍል ስለመንዙማ ሲነሳ ከ200 ዓመት ያልበለጠ ታሪክ ስለሚጠቀስ ተጨማሪ ጥናቶችን አጥንቶ ወደ ትክክለኛው ዘመን መድረስ እስከሚቻል ድረስ ባሉት ላይ ማተኮር የግድ ይሆናል፡፡
ይህም ሆኖ የሶማሌ፣ የኦሮሚያና የሐረሪ መንዙማ ታሪክ መኖሩና ከአናም ሆነ ከዳና ሊቀድም እንደሚችል ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ የባሌና የአርሲው ሰይድ ኑርሁሴን እስካሁን ድረስ ውብ በሆነ ዜማና ውዝዋዜ መቅረቡ ምስክር ነው፡፡ አይኤም ሌዊስ የተባለ ተመራማሪ ‹‹ሴይንትስ ኤንድ ሱማሊስ›› በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1998 ባሳተመው መጽሐፍ፣ በተለይም በምዕራፍ ሁለት ‹ቃዲሪያና በድቢ ያጀበው ዚክር›› በሚል ንዑስ ርዕስ በሶማሊያም ከዘይላ ጀምሮ እስከ ደቡብ ሶማሊያ ያሉት ቃሲዳ የተሰኘ መንዙማ ከጥንት ጀምሮ እንደነበራቸውና እሱም መጽሐፉ ከመታተሙ 40 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር የነበሩ የቃዲያ ጠሪቃ ተከታዮች በመንዙማ ፈጣሪን ያመሠግኑ እንደነበረ ጠቅሷል፡፡ ሐረሪዎች ከአው አባድር ጀምሮ ሰፊ ኢስላማዊ ታሪክ ስላላቸው የመንዙማ ታሪክም ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚቀርብ ሲሆን ‹‹አውበርኸሌ›› የተባሉት የሰሜን ሶማሌው ታዋቂ ሊቅ ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ኢስላም ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የታወቀ ነው፡፡
መንዙማ ከግጥምና ከዜማ አኳያ ሲፈተሽ
መንዙማ ከግጥምና ከዜማ አኳያ ሲፈተሽ የተደረሰው በየትኛው ዘመን ነበር? ወይም የትኛውን ዘመን ያንፀባርቃል? ዘመን አይሽሬ ነው ወይስ የአንድ ዘመን ብቻ እያሉ መተንተን ሊጠይቅ ይችላል፡፡
ለምሳሌ፡- ‹‹እንዴት አደርክ ብለው እንዴት አደርክ አለኝ
አልሃምዱሊላሂ ሊቀር ነው መሰለኝ››
የሚል እንጉርጉሮ ቢገጥመን የትኛውን ጊዜ እንደሚያንፀባርቅ መገመት ይቻላል፡፡
ስለሆነም መንዙማ ከዘመኑ ጋር የሚያድግ፣ አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር በሚኖራት ግንኙነት የሚጎለምስ ስለሆነ ግጥም በወዲያኛዎቹ አያቶቻችን ዘመን፣ ግጥም በአባቶቻችን ዘመንና ግጥም በእኛ ዘመን ብሎ መተንተን ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የዛሬ 70 ዓመት ገደማ ሐጂ ባደረገበት ጊዜ መካንና መዲናን ዓይቶ የድንጋይና የአሸዋው ክምር፣ ስለአነስተኛዎቹ የመኖሪያ ቤቶች፣ ፅዳት ስለጎደላቸው ምግብ ቤቶች፣ ስለዓረብ ምጽዋት ፈላጊዎች፣ ስለተላላፊ በሽታዎች ቢቃኝ፣ በዚህ ዘመን የሚቃኘው ደግሞ ስለፎቆቹና መንገዶቹ ውበት፣ ስለመብራቱና በመብራት ስለተሠሩት ውብ ጌጦች፣ ስለመኪኖችና ስለሌሎች አስገራሚ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሊጽፍ ይችላል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በወጣቶች የሚቀርበው መንዙማ በዓረብ አገሮች ከሚቀርበው ነሺዳ የተቀዳ ወይም የተዳቀለ፣ አንዳንዱም ከዓለማዊው ዘፈን የተወሰደ መሆኑን ስናጤን መንዙማንና ዘመንን አብሮ የማየት አስፈላጊነት እንገነዘባለን፡፡
መንዙማ የሚተነተነው ከላይ ለማቅረብ በተሞከረው ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቅርፅና ይዘትን ተመርኩዞ መገለጥ የሚገባቸው ነገሮች አሉና እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ጸሐፊው ስለመንዙማ ባቀረበው ጥናት ቀርቧል፡፡ ይህን ያህል ስለአገራችን መንዙማ ካየን ስለዓረቡ ዓለም ሥነ ጽሑፍ ገጽታ መጠነኛ ግንዛቤ ይኖረን ዘንድ ደግሞ የሚከተለውን እንመልከት፡፡
የዓረበኛ ሥነ ጽሑፍ አጠቃላይ ገጽታ ከመንዙማ አኳያ
ምክነር ቢ ትራዊንክ የተባለ ጸሐፊ፣ ወርልድ ሊትሬቸር በሚል ርዕስ በ1953 ዓ.ም. ባሳተመው መጽሐፉ እንደገለጸው፣ የዓረብ ሥነ ጽሑፍ ከሰባተኛው ክፍለ ዘመን በፊት እምብዛም አይታወቅም ነበር፡፡ ከዚያ በፊት በነበረው ታሪክ ሲጠናም ዓረቦች ከብቶቻቸውን ይዘው እስከ ግብፅና ሜሶፖታሚያ ድረስ የሚንቀሳቀሱ ዘላኖች ነበሩ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ እርስ በርሳቸው በጦርነት ይቆራቆሱ ስለነበር ኅብረት አልነበራቸውም፡፡ ይሁንና ከ622 እስከ 630 በነበረው ጊዜ የተወለዱት ነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ይዘውት በተነሱት የኢስላም እምነትና በነበራቸው ኃይል ጠንካራዋን የዓረቢያ መንግሥት መሠረቱ፡፡ በዚህም መሠረት ፋርስን፣ ታናሿ እስያን፣ ሰሜን አፍሪካን፣ ስፔንና ከፊል የህንድ ግዛት፣ አፍጋኒስታንና ፓኪስታንን ለመያዝ በቁ፡፡ ከ650 እስከ 1300 ባለው ጊዜም በእነዚህ አገሮች መካከል ከፍተኛ የባህል፣ የዕውቀትና የማኅበራዊ ሕይወት ውህደት ተፈጠረ፡፡ የዓረብኛ ሥነ ጽሑፍ በተለይም ከሃይማኖትና ከፍልስፍና እንዲሁም ከሳይንስ ጋር ቁርኝት ያለው ሥነ ጽሑፍም በዚህ አጋጣሚ ለማስፋፋት ዕድል አገኘ፡፡ በዚህም ምክንያት ልዩ ልዩ የግጥም ዓይነቶች በብዛት ተገጥመዋል፡፡ ታሪኮች፣ ሀተታዎችና አፈ ታሪኮች ተጽፈዋል፡፡ የዓረብኛ መንዙማዎች መዲህ ነባዊ (ነብዩ ሙሐመድንና ቤተሰቦቻቸውን የሚያሞግሱ)፣ መቃም (ሰዎች በአንድ ላይ ሆነው የሚያቀርቡት)፣ ማዕሉፍ (በሰሜን አፍሪካ)፣ ድር (በግብፅ)፣ ሙወሸሽ (በሶሪያና በኢራቅ)፣ እና መቃም አል ኢራቂ ተብለው የሚታወቁ መንዙማዎች አሉ፡፡ በቱርክ ‹‹ነዓት››፣ በኅብረት የሚቀርብ የመውላዊ ዚክር፣ ሰምዓ በተባለው የአጦለሌ ውዝዋዜ የሚቀርብ ዓዩን የተባለ መንዙማና ሌሎች ስሞች ያሉዋቸው የመንዙማ ዓይነቶች ሲኖሯቸው፣ ዓረቦች የመንዙማ ወይም የዜማ መጽሐፍ (ኪታቡ አቃኒም) አላቸው፡፡ የሆነ ሆኖ መንዙማ አጥኝዎች በቃሲዳ (በዓረብኛ አጠቃላይ ሥነ ጽሑፍ ላይ) የበለጠ ትኩረት እንደሚያደርጉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የዓረብ የግጥም ቅርጾች በርካታ ቢሆኑም ዋና ዋናዎቹ መዲህ (አሞጋሽ፣ አሞካሽ፣ አግናኝ)፣ ሒጃ (አጥላይ፣ ተሳዳቢ፣ አሽሟጣጭ፣ ሸርዳጅ)፣ ቐዛል (የፈጣሪ፣ የነብይ፣ የሰው ፍቅር የሚገለጽበት)፣ ቂጣህ (በተራ አጋጣሚ የሚገጠም)፣ ማስናዊ (ድርብ ትርጉም ያለው)፣ ወስፍ (ገላጭ)፣ ሪጣ (እንጉርጉሮ፣ ወዮ እኔ፣ ዓይኔ)፣ ኺምሪያ (ወይን ወይም በወይን የሚመሰል አስካሪ፣ መንፈስን የሚለውጥ ምሳሌ የሚያሰክር ፍቅር)፣ ተርዲያህ (የአደን ግጥም)፣ ፈኽር (የፉከራ ግጥም)፣ ሙወሸሻ (ስለአገር ፍቅር)፣ ሐመስ (የጦርነት ግጥም) ናቸው፡፡
ወደፊት በመጠኑም ዝርዝር አድርገን እንደምንመለከተው በዓረብ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ በደንብ ዳብሯል የሚባለው ስል መቐማህ የተባለው አሽሙር ነክ ዝርው ጽሑፍ ሲሆን፣ የዚህም ሥነ ጽሑፍ ሰው ሥራ ከ969 እስከ 1008 የነበረው አል ሐማድሐኒ የተባለ ደራሲ ነው፡፡ ምንም እንኳን መቃማህ አጻጻፍ ዘዴ በአል ሐማድሐኒ ይፈጠር እንጂ ሥልቱን አንድ ዕርምጃ ወደፊት እንዲገፋ አድርጎታል የሚባለው ግን ከ1054 እስከ 1122 የኖረው፣ ኢራቃዊው መሐመድ አልቃሲም ኢብ ዓሊ አልሐሪሪ ነው፡፡ ይኸው አንባቢውን በማዝናናት ሳይወሰን ምጥቀትና ጥልቀት ባላቸው ቃላት ይጠቀም የነበረው ጸሐፊ የቃላት ጎተራ እንደነበረ በሥራዎቹ አስመስክሯል፡፡ መልሀት አልሂራብ ፊአናዋህዋ በሚል ርዕስ የደረሰው የሰዋስው መጽሐፉ የዓረቡን ሥነ ጽሑፍ በማዳበር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ዳሩ ግን የዓረብኛ ‹‹መንዙማዎች›› ወይም ኢስላማዊ መንዙማዎች መሠረት ምንድነው? ብለን ስንጠይቅ ጠለቅ ወዳለ ምክንያታቸው መግባት የግድ ይሆናል፡፡
የዓረብኛ ‹‹መንዙማ›› ምንጮች
የዓረብኛ መንዙማዎች መሠረታቸው ፈጣሪን ከማመስገን ከማወደስ፣ ለፈጣሪና ለነብዩ መሐመድ (ሱዓወ) ያላቸውን ፍቅርና አድናቆት ከመግለጽ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ሲሆን፣ ወደ ፈጣሪ የሚወስዱት መንገዶች ከቁጥር በላይ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የሀቅ መረጃ ሳይንስ የሆነው ሱፍያ በውስጡም ተጓዡ ለጉዞው የሚያስፈልጉትን ምግብ፣ ብርሃንና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሲሆኑ መድረሻ ወደቦቹም መንፈሳዊ ሥርዓቶቹ ማለትም ጠሪቃዎቹ ናቸው፡፡
የሀቅ መንገዶችም በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ሲከፈሉ፣ የመጀመርያው ተጓዡ ከመጓዙ በፊት የሚሰጠው ወይም የሚማረው ነው፡፡ ይህም ትምህርት ትንሽ መብላት፣ ትንሽ መጠጣት፣ ትንሽ መተኛት፣ ዚክርን ማብዛትና አስፈላጊ ካልሆኑ ማኅበራዊ ግንኙነቶች መገታትን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ዚክሮቹም ሰባት ሲሆኑ አንዱ ከፈጣሪ (ከአላህ) በስተቀር ሌላ የለም፤ ፈጣሪ፣ እርሱ፣ ሀቁ፣ ዘለዓለማዊው፣ የተብቃቃው የሚሉት ናቸው፡፡ እነዚህን የፈጣሪ ስሞች ደጋግሞ በማውሳት ሰባት የመንፈስ ደረጃዎችን ያልፋል፡፡ እነዚህም ሰባት የመንፈስ ደረጃዎች እርኩስ መንፈስ አዛዥ፣ ራስን የማውገዝ መንፈስ፣ የዕረፍት መንፈስ፣ የፍሥሐ መንፈስ፣ የመንፃት ማለትም እንከን የለሽ የመሆን መንፈስ ናቸው፡፡ ይህንን መንገድ የሚከተሉት ሁሉንም ነገር ዓለማዊ ነገር ሁሉ ትቶ ሸሪዓው በሚፈቅደው መሠረት መሪዎቻቸውን ወይም አስተማሪዎቻቸውን እየተከተሉ በፈጣሪ ፍቅር ማለትም በዓሽቅ ተሞልቶ ወደ ሀቅ መጓዝ ነው፡፡ ዓሽቅ ማለት ጥሬ ትርጉሙ ከፍተኛውን ደረጃ የያዘና ፍፁም የሆነ ፍቅር ውበት ወይም አካላዊ ወዘና ሲሆን፣ ሱፊዎች እንዲህ ያለውን ከፍተኛ ፍቅር የሚሰጡት ለዘለዓለማዊው ንጉሥ፣ ለግርማዊነቱና በግርማዊነቱ ለሚገለጽ ውበቱ ነው፡፡
ሙላ ጃሚዕ የተባለ ሰው ስለፈጣሪ አስገራሚና አስደናቂ ውበት ሲገልጽ፣ ‹‹የግብፅ ሴቶች የዩሴፍን ውበት ሲመለከቱ ከመደነቃቸው የተነሳ ይዘውት በነበረው ሳንጃ እጃቸውን ከቆረጡ፣ ጌታ ሆይ ያንተን ግሩም ድንቅ ውበት ቢመለከቱ ኖሮ በያዙት ሳንጃ ልባቸውን ይሰነጥቁ ነበር፤›› ብሏል፡፡ ይህም ከፍተኛ ዓይነት ውበትና ፍቅርን (ዓሽቅን) ይፈነጥቃል፡፡ ለመሆኑ መንዙማ ሳያቋርጥ የሚፈልቅበት ዓሽቅ ምንድን ነው?
ዓሽቅ (ከፍተኛው ዓይነት ፍቅር)
እውነተኛው ከፍተኛውን ደረጃ የያዘው ፍቅር በራሱ በፈጣሪ የተሰጠና ወደ ራሱ የሚያደርስ ከብርሃን የተሠራ ክንፍ ነው፡፡ ሱፊዎች ፈጣሪ ዓለምን የፈጠረው ህልውናው እንዲታወቅና እንዲፈቀር ብሎ እንደሆነና ሀቁን ለመረዳት የነቁ መንፈሶችም የእሱን መገለጫ ባህሪያት ለመረዳት ያስችላቸዋል ብለው ያምናሉ፡፡ ዓሽቅ ከራሱ ከፈጣሪ የሚመነጭ እንጂ በአፍቃሪው ቁጥጥር ሥር ባለመሆኑ የግል ፍላጎት ጣልቃ ገብነት አያሻውም፡፡ ዓሽቅ የመጨረሻውን ከፍተኛውን ደረጃ የያዘና ፍፁም የሆነ የፈጣሪ ፍቅር በመሆኑ ከእሱ ወዲያ ሌላ ፍቅር የለም፡፡ የዚህ ፍቅር የመጀመርያ ደረጃ መገለጫ ‹‹ፈጣሪን ለመረዳት የሚያስችል የፈጣሪ መገለጫ ዕውቀት›› ነው፡፡ የዓሽቅን ውዴታ ካገኙ በኋላ የህልውና ላዕላዊ ሽፋን ከዕይታቸው ይጠፋል፡፡ ማለትም የእነሱ ህልውና ከውስጣቸው ይጠፋና ፍፁም አሐድነት ይሰማቸዋል፡፡ የፈጣሪና የተፈጣሪ አንድነትና ልዩነት ሳያደናግራቸው ጉዟቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡ የሁለተኛው መንገድ ያለማቋረጥ ማምለክ፣ ማፍቀር፣ ከፈጣሪ ጋር በመንፈሳዊ ስበት መሳብ፣ ያለማቋረጥ ቁርዓንን ማንበብ፣ ከመሪ ጋር ግንኙነትን ማጠናከር ናቸው፡፡
ባሲራና ፊራሳ (ውስጣዊ ዕይታና ግንዛቤ)
ባሲራና ፊራሳ የሚለው የዓረበኛ ቃል ግንዛቤ፣ ዕውቀት፣ መረዳት፣ መረጃ፣ ምስክር፣ ማለትም ኃላፊንና መጭን ክስተት በልብ ማየት የሚሉትን ያጠቃልላል፡፡ ፈጣሪ መንፈሱን በተከታዮቹ ልብ ውስጥ እንደሚሞላ ነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ዓይነተኛ ምሳሌ ናቸው፡፡ በቅዱስ ቁርዓን ውስጥም በምዕራፍ 11 ክፍል 12 ቁጥር 108 ‹‹እነዚያ ዕድለኞቹማ፣ ጌታህ ከሻው (ጭማሬ) ሌላ ሰማያትና ምድር እስካዘወተሩ ድረስ በውስጧ ዛውታሪዎች ሆነው በገነት ውስጥ ይኖራሉ፤ የማያቋርጥ ስጦታንም ተሰጡ፡፡ (የነሐጂ ሳኒ ሐቢብ ትርጉም) ‹‹እነዚያ የፈጣሪ ፀጋን የተቸሩ በገነት ይሆናሉ፣ መሬትና ሰማይ እስከ ቻሉ (እስከ ፀኑ) ድረስም በዚያው ይቆያሉ፤ ፈጣሪ ከፈቀደው በስተቀር ፀጋው (ስጦታውና በረከቱ) አይቋረጥም፡፡
በመሠረቱ፣ ግንዛቤ የዕውቀት ምንጭ በሆነ ጊዜ ግንዛቤና መረዳት ውስጣዊ ዕይታ ጥልቅ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ የፈጣሪን፣ የሀቁን ብርሃን የሚረዱ፣ ሁሉን ጉዳይ፣ ሁሉንም ነገር በሙሉ ግልጽነት ለማየት የሚያስችል ውጋጋን (ጨረር) ይኖራቸዋል፡፡ በተመሳሳይነቱ ፍፁም አደናጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ እንኳን አይደናገሩም፣ ወይም በመለየቱ ግር አይሰኙም፡፡
ዳህሻና ሐይራ (የላቀ መገረምና መደነቅ)
በእንግሊዘኛው መደነቅና መገረም (Astonishment and Amazement) ተመሳሳይ ቃላት እንደሆኑት ሁሉ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ሲፈቱም የትኛው ቃል መደነቅ የትኛው ደግሞ መገረም እንደሆነ ማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይሁንና ወደ ሀቅ ተጓዡ በፍቅር ተሞልቶ፣ በፍቅር ተቃጥሎ፣ ከተፈቃሪው በሚሰጠው የዘለዓለማዊነት ወይም ስካር ከሚገባው በላይ ፈንጥዞ ሰክሮ ይጓዛል፡፡ በቅዱስ ቁርዓንም ‹‹አረንጓዴ የሆኑ የቀጭን ሀር ልብሶችና ወፍራም ሀርም በላያያቸው ላይ አለ፡፡ ከብርም የሆኑ አምበሮችም ይሸለማሉ፡፡ ጌታቸውም አጥሪ የሆነን መጠጥ ያጠጣቸዋል›› 76፡21 (የነሐጂ ሳኒ ሐቢብ ትርጉም) ‹‹በላያቸው ላይም ያማረ አረንጓዴ ሀርና የተጠለፈ (በጥልፍ ያጌጠ) ልብስ ይደረጋል፡፡ ከብር በተሠራ አምባርም ያጌጣሉ፡፡ ጌታቸውም የሚያጠራ መጠጥ ይሰጣቸዋል›› (የጸሐፊው ትርጉም)፡፡ አፍቃሪው የፈጣሪ ዕውቀቱ እየፈለገ፣ እያንዳንዱ መለኮታዊ ስጦታ ፍላጎቱን እንዲጨምር እያደረገ ይሄዳል፡፡ ፍላጎቱ በጨመረ ቁጥርም አዲስ ስጦታ በልቡ ውስጥ ይንቆረቆርለታል፡፡ ንብ ከአበባ ቅስም ወስዳ ማር በመሥራት አበባን የማር መገኛ ምንጭ እንደምታደርገው፣ አፍቃሪውም የፈጣሪን የዕውቀት ቅስም በመቅሰም ከመለኮታዊ ስሞችና ከእርሱ ዘንድ ከሚመነጩ ባህሪያቱ የዕውቀት ማመንጫ መስክ ያደርገዋል፡፡ ይህም ከመለኮታዊ ህልውና ጋር ለመገናኘት የነበረውን ህልም ዕውን ስለሚያደርገው አፍቃሪው በከፍተኛ አድናቆት ይሞላል፡፡ ይህንንም በሚመለከት ‹‹ጉሊስታን›› (የጽጌረዳ የአትክልት ሥፍራ) በሚል ርዕስ የጻፈው ሰው ስሜቱን እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ታሳያለህ ውብ መልክህን፣
ዳሩ ግን የተሸፈነ ነው፣ ፍፁም የሚታይ ሳይሆን፡፡
ስለሆነም ሁለ መናህን እንድናይህ፣
በሚያቃጥል ስሜት ታነሳሳናለህ፣
እሳታችንንም እንዲጨምር አድርገህ፡፡
የተገለጠውን ተፈቃሪ ስመለከት፣
ከእርሱ ጋር በፍቅር የወደቅሁለት፡፡
እንዲህም ይሆንና በመንገድ ላይ ግራ የተጋባሁ ይመስለኛል፣
የተፈቃሪው ብርሃን በልቤ ውስጥ እሳት ያቀጣጥላል፣
እንደ ጨረር ሆኖ ተፈነጣጥቆ ይወጣል፡፡
ለዚህም ነው ተቃጥየ ያገኘኸኝ፣
በውቅያኖስ ውስጥ ሰምጬ ያየኸኝ፡፡
ኢስማዒል ሐቂ ቡርሳዊ የተባለው ‹‹ተፍሲር ሩሁል በያን›› በሚል ሥራው (ቅጽ 10) ‹‹ተጓዦቹ ያለማቋረጥ የሰከሩ›› መሆናቸውን በቅዱስ ቁርዓንም ውስጥ (76፡21) ቅዱሳን ጌታቸው በሚሰጣቸው ንፁህ ውኃ እንደሚሰክሩ የሰፈረውን ዋቢ በማድረግ ያብራራል፡፡ ይህም ሆኖ ተጓዡ ልቦናውን መንፈሳዊ ጉዞ ለማድረግ የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት ካላደረገና በሸሪዓ ትዕዛዛት ካልተመራ የሚያጋጥመው ነገር ቢኖር ውድቀት፣ መደናገር፣ መወናበድና ከሸሪዓው ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን መናገር ነው፡፡
ፊራራና ዒጢሳን (ስሜትና መጠለል)
ፊራራ ማለት በዐውዳዊ ትርጉሙ ከአንዳች ነገር ራስን ማራቅ ሲሆን በሱፊዎች ደግሞ ከተፈጥሮ ወደ ፈጣሪ መጓዝ ማለት ነው፡፡ ከዋነኛው (ከምንጩ) ጥላ ጥላ ተጠልሎ ጠብታን ትቶ ባህር ውስጥ መጥለቅ ማለት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ፣ በፀሐይ ጨረር አማካይነት ብርሃንን ከሚያንፀባርቅ መስታወት ራስን አላቆ ወደ ፀሐይ ወደ ራሷ ፊትን ማዞር (በእርሷ መጠቀም) ነው፡፡ በመዞርም ከራስ መተማመን ተላቆ (አፈትልኮ በመውጣት) በእውነተኛው ጨረር መቅለጥ ነው፡፡ ወደ ፈጣሪ ብረሩ የሚለው ግጥም (51:50) የአማኞችን በልብና በመንፈስ መጓዝ የልብን ድርጊትና የመንፈሳዊነት ችሎታን የሚያመለክት ነው፡፡
ከሚያጨናንቀው ተጨባጭ እውነታ ዓለም ድባብና ከሥጋዊ ፍላጎት አድማስ የበለጠ የራቁ ሰዎች ወደ ፈጣሪ የበለጠ በቀረቡ ቁጥር ለራሳቸው የበለጠ ክብር ይሰማቸዋል፡፡ በደግነት፣ በታማኝነት፣ በቅዱስነት ወደ ፈጣሪ በመሸሽ በውጫዊ ስሜታቸው ከማሰብ በልቦናቸው፣ ታይታ ከተሞላበት አምልኮ ወደ ውስጣቸው፣ ከዓለማዊ ስሜታቸው ወደ መንፈሳዊ ስሜታቸው የተለዩ ይሆናሉ፡፡ ይህም ‹‹ፈጣሪ ሆይ፣ ከቁጣህና ከቅጣትህ ምሕረትን አገኝ ዘንድ ከአንተ እጠለላለሁ፤›› ይላል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱ ስሜታቸውን እንዴት እንደሚገልጹ ሩሚ በሁለት ስንኞች ሲገልጽ
እነዚህ የሐሳብ ትዕይቶች የቅዱሳን ወጥመዶች፣ ነገር ግን በእውነታው፣
በፈጣሪ የአትክልት ስፍራ (በገነት) የሚያበሩ ፊቶች ነፀብራቆች ናቸው፡፡
በዚህ ቅኔ የፈጣሪ የአትክልት ሥፍራ የሚለው በዓለም ያለውን መለኮታዊ አንድነትን፣ አሐድነትን፣ ብዙንና ሁሉን መገለጫ ሲሆን፣ አብራሂ ገጾች ደግሞ መለኮታዊ ስሞችን፣ በአንድ ነገር ላይ ያለ ነገር ባህሪን የሚወክል ሲሆን፣ የሁለቱ ስንኞች ድምር ትርጉም መለኮታዊ እውነታን ለማይገነዘቡ የሐሳብ ትዕይንት (የቀን ሕልም፣ ቅዤት) ሆነው የሚገለጡ ለቅዱሳን ደግሞ በዓይነ ልቦናቸው ወለል ብለው የሚታዩ፣ በቅዱሳኑ ልቦች የሚንፀባረቁና የሚገለጡ ናቸው፡፡ ፈጣሪም ልዩ ልዩ ስሞቹን (99) ለቅዱሳን ገልጧል፡፡
ማጠቃለያ
ውድ አንባብያን መንዙማ መጠናት፣ መተንተንና መታወቅ ያለበት የኢትዮጵያ ረቂቅ ቅርስ ነው፡፡ የዓረብኛው የመንዙማ አቅጣጫ በዚህ ጽሑፍ ማካተት ያስፈለገበት ምክንያት፣ ወጣቶች መንዙማን ከምን አኳያ ሊያዩት ይገባል ለሚለው መጠነኛ ሐሳብ ለመፈንጠቅ ነው፡፡ ይህም ሆኖ መንዙማ ከተደረሰበት፣ ከተዜመበት፣ ከተማሩበት፣ ከደረሱበትና ከደራሲያኑ ጋር የተሰናሰለ ስለሆነ ከተጨባጭ የኢትዮጵያ ቅርስ ጋር በጥብቅ የተያያዘ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም ሆነ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ለዚህ አገራዊ ሀብት ትኩረት ማድረጋቸው የሚመሠገኑ ሲሆን፣ ወደፊትም የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ጥልቅ ጥናት ማድረግና ጥናቱን ማሳተም ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኢስላሚክ ቱሪዝምን በማስፋፋት የአገር ልማት አጋር ማድረግ ይቻላል፡፡
በመጨረሻም የባህል ሚኒስቴር በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ የፈጸመውን አኩሪ ሥራ በመጠቆም ወደ መንዙማው በማተኮር ሐሳቤን ላጠቃልል፡፡ ጊዜው እንደተጠቀሰው በ1960ዎቹ መጨረሻ ሲሆን ከአብዬ መንግሥቱ ለማ ጋር እንደተለመደው ስንገናኝ የግዕዝ ቅኔዎችን ከሌሎች ጋር እየሰበሰቡ በመተርጎም ላይ እንደሆኑ ገለጹልኝ፡፡ ያን ሲገልጹልኝ ከፍተኛ ደስታ እየተሰማቸው ነበር፡፡ ‹‹አየህ በዚህ አጋጣሚ የአገርን ሀብት መሰብሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ መንግሥት ለዚህ ሥራ የሚከፍለን አነስተኛ የውሎ አበል ነው (የነገሩኝን ካልዘነጋሁት በቀን ከአምስት ብር አይበልጥም ነበር)፡፡ በነፃስ ቢሆን! ዋናው እኛ ይህን እንድናደርግ ዕድል ማግኘታችን ነው፡፡ ነገ የሚሆነው አይታወቅም፤›› አሉኝ፡፡ አዎን በዚያ አጋጣሚ ሁለትም ሦስትም ቅጽ የሚወጣው የግዕዝ ቅኔ ተሰባስቦ ተተረጎመ፡፡ ታተመም፡፡
በ2010ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ በዶክተር ሥርግው ገላው አርታኢነት ‹‹የግዕዝ ቅኔ መንገዶች ቅጽ አንድ›› ታትሞ ለንባብ በቅቷል፡፡ ይህም ሌላው የሚያስደስት ነገር ነው፡፡
ታዲያ መንዙማ እንደ ግዕዝ ቅኔ ሁሉ በውስጡ ያካተታቸው ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና፣ ኢትዮጵያዊ ታሪክ፣ ኢትዮጵያዊ ማኅበራዊ ኑሮ፣ ኢትዮጵያዊ ባህል ወዘተ. ስላሉ ትልቅ የአገር ሀብት ነውና ባህልና ቱሪዝምም ሆነ ዩኒቨርሲቲዎች ትኩረት ሊሰጡበት ይገባል፡፡ ነገር ግን ‹‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም›› እንዲሉ ባለቤቶቹ ሙስሊሞች የላቀ ትኩረት ሊያደርጉበት ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡