Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊግንባታው የተቋረጠው የኢትዮ አሜሪካ ዶክተሮች ቡድን ሆስፒታል ዳግም ተጀመረ

ግንባታው የተቋረጠው የኢትዮ አሜሪካ ዶክተሮች ቡድን ሆስፒታል ዳግም ተጀመረ

ቀን:

የኢትዮ አሜሪካን ዶክተርስ ቡድን ከአራት ዓመት በፊት ያስጀመረውና ግንባታው ወዲያው የተቋረጠው ተርሸሪ ሆስፒታል ግንባታ ዳግም ተጀመረ፡፡

ኢትዮ አሜሪካን ዶክተርስ ቡድን፣ 110 ሚሊዮን ዶላር በሚገመት ወጪ ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟላ ተርሸሪ ሆስፒታል በአዲስ አበባ ከተማ ለመገንባት የመሠረት ሥራ ቢያስጀምርም ሥራው ግን ሊቀጥል አልቻለም ነበር፡፡

የግንባታውን ዳግም መጀመር አስመልክቶ ሰሞኑን በተሰጠ መግለጫ፣ ከሆስፒታሉ መሥራቾች አንዱ፣ የቡድኑ ቦርድ ሰብሳቢና የደም ሥር ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ግርማ ተፈራ (ፕሮፌሰር) እንደገለጹት፣ ለግንባታው መቋረጥ ከምክንያቶች መካከል ሕንፃው የሚያርፍበት መሬት ከተገኘ አራት ዓመት ቢሆነውም፣ ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የሰነድ ስምምነትና የሊዝ ውል ያለቀው የዛሬ ሁለት ሳምንት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡

‹‹በእኛ በኩል ለሆስፒታሉ ግንባታ ያለን ቁርጠኝነት ከፍ ያለ ነው፡፡ በምንም ዓይነት መልኩ ወደኋላ አላልንም፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ምንም ነገር ቀጥ ብሎ የሚሄድ አልነበረም፡፡ በዚህም የተነሳ ግንባታውን አስመልክቶ መከናወን ባለባቸው ተግባራትና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ የታዩት መንገጫገጮች መጓተትን አስከትለዋል፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ እንቅፋት ባያጋጥመንና በወጣው ፕላን መሠረት በቀጥታ ቢከናወን አብዛኛው ግንባታ እስካሁን ወደ መጠናቀቁ ይደርስ እንደነበር አመልክተው፣ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ ግን ግንባታውን መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ሒደት የሆስፒታሉን ሕንፃዎች ተሸክሞ የሚቆመው መሠረት ከመገንባቱ ጋር የተያያዙ፣ እያንዳንዳቸው ከ20 እስከ 30 ሜትር ጥልቀት ያላቸው በአሸዋና በአርማታ ብረት የሚሞሉ 740 ጉድጓዶች መቆፈራቸውንም ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

የቡድኑ ፕሬዚዳንት፣ ከመሥራቾቹ መካከል አንዱና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ተስፋዬ ደምሴ (ዶ/ር)፣ አገርንና ሕዝብን በሕክምና ዘርፍ ለማገልገል የሚያስችለው የዚህ ሆስፒታል ፕሮጀክት ትልቁ ጥንካሬ 339 ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስፔሻሊስቶችን፣ ሐኪሞችንና ልዩ ልዩ ጤና ባለሙያዎችን ማቀፉን ገልጸዋል፡፡

በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያና በካናዳ ከሚኖሩ ከእነዚሁ ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል 300ዎቹ ሐኪሞችና ልዩ ልዩ ጤና ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ የቀሩት 39ኙ ደግሞ በተለያዩ ሕክምናዎች ስፔሻላይዝድ ያደረጉና ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው መሆናቸውን አክለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ተስፋዬ፣ ይህን የመሰለ ክህሎት ያላቸው ሐኪሞች ወደ አገር ቤት እየመጡ አገርንና ሕዝብን በማገልገል፣ የሕክምና ክፍተቶችን በተቻለ መጠን በመሸፈን፣ ከኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግና የዕውቀት ሽግግር በማካሄድ የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡

ግንባታው ሲጠናቀቅ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የሕክምና ልህቀት ማዕከል በመሆን የውጪ ምንዛሪን በማዳን የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው፣ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ብሎም ከሌሎች አኅጉራት የሚመጡ ሕሙማን የሚታከሙበት ተቋም ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

የማሕጸንና ፅንስ ሐኪም፣ የሕግ ባለሙያና ከመሥራቾቹ መካከል አንዱ የሆኑት ሠናይት ፍሥሐ (ፕሮፌሰር)፣ የሆስፒታሉ ግንባታ ካለቀ በኋላ የአቅም ማነስ ችግር ላለባቸው ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ለመገንባት የሚያስችል ዝግጅት መከናወኑን አክለዋል፡፡

ለከፍተኛ ሕክምና ቤተሰቦቻቸውንም ጭምር ይዘው ወደ ህንድና ታይላንድ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣና ይህ ዓይነቱም ጉዞ ለከፍተኛ ኪሣራ እንደዳረጋቸው ፕሮፌሰር ሠናይት ገልጸው፣ ቡድኑ የሚያስገነባው ተርሸሪ ሆስፒታል ሲጠናቀቅ ይህን ዓይነቱን ጉዞ በማስቀረት ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት እዚሁ እንዲያገኙና ለኪሳራም እንዳይዳረጉ ያስችላል ብለዋል፡፡

የሆስፒታሉ የመጀመርያው ዙር ግንባታ ታኅሳስ 2013 ዓ.ም. ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ከፍት እንደሚሆን፣ በዓመቱ ደግሞ አጠቃላይ ግንባታው አልቆ በሙሉ አቅም ወደ ሥራ እንደሚገባም ተነግሯል፡፡

ሆስፒታሉ 300 አልጋዎች እንደሚኖሩት፣ ዘላቂ ልማትን ዳር ለማድረስ አገሪቷ ለምታካሂደው እንቅስቃሴ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ፣ የምሁራን ፍልሰትንና ወደ ውጭ የሚሄደውን የሕክምና ቱሪዝም እንደሚቀንስ፣ በአገር ውስጥ ላሉ የሕክምናና ተያያዥነት ላላቸው ሙያተኞች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...