Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየታሪክ ጠባሳ

የታሪክ ጠባሳ

ቀን:

ጃፓን ከባድ ሰቆቃ ያስተናገደችበትን 74ኛ ዓመት ነሐሴ 6 ቀን 2019 (ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም.) ታከብራለች፡፡ እነዛ ሁለት ቀውጢ ቀናት ማለትም እ.ኤ.አ. ነሐሴ 6 እና 9 ቀን 1945 በጃፓናውያን ሕይወትና ሥነ ልቦና ላይ እጅግ ከባድ ለውጥን ያስተናገዱ ነበሩ፡፡ በቅድሚያ በሄሮሺማ ቀጥሎ ደግሞ በናጋሳኪ ላይ የተጣሉት የአቶሚክ ቦንቦች ለጃፓንያውያንም ሆነ ለመላው ዓለም ዘመን ተሸጋሪ ሰቆቃና ጠባሳን አሸክመው ነበር ያለፉት፡፡

በወቅቱ የጥፋት ኃይሉ ላቅ ያለ ቦንብ በሄሮሺማ ከሦስት ቀናት በፊት መውደቁን ከመስማት በስተቀር ዝርዝር ግንዛቤው ያልነበራቸው የናጋሳኪ ነዋሪዎች በጥቃቱ ሙሉ ለሙሉ ነበር የተናጉት፡፡ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት፣ ከአክሲስ ኃያላት ጋር ለተሸነፈችው ጃፓን ሕዝቧ ለአየር የቦንብ ድብደባ አዲስ ያልነበረ ቢሆንም፣ የነሐሴዎቹ ግን የተለዩ ነበሩ፡፡

በዚች የተረገመች ዕለት ከአቶሚክ ቦንቡ ፍንዳታ አንድ ሰዓት ተኩል በፊት ማለትም ከጠዋቱ 3፡30 ላይ በናጋሳኪ ከተማ የተለመደ የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደውል ተደውሎ እንደነበር ይነገራል፡፡ በዚህ ደውል ምክንያት ወደ የቦንብ ጥቃት መሸሸጊያ የገባው ሠራተኛ የናጋሳኪ ነዋሪ የአደጋው ማለፍን የሚያመላክት ሁኔታ ደውሉ 4፡15 ሲጠፋ አገር ሰላም ብሎ ወደየሥራው ይበተናል፡፡ ነገር ግን ከባድ ዱብ ዕዳ ከተፍ ሊል ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነበር የቀሩት፡፡

የታሪክ ጠባሳ

 

ከረፋዱ 5 ሰዓት ገደማ በወቅቱ የሚትስቡሺ የጦር መሣሪያ ፋብሪካ አዲስ ተለማማጅ ቅጥር የነበረው የ14 ዓመቱ ኢኖሱሴ ሀያሳኪ ወደ ፋብሪካው ሌላኛው ክፍል ማቅናት ይጀምራል፡፡ የዕድል ነገር ሆኖ ዕቃ እንዲያወጣ የተላከበት የፋብሪካ ክፍል በትላልቅ ቋሚ ኮንክሪት የተሞላ መሆኑን የሚያስታውሰው ሀያሳኪ በቅጽበት ውስጥ የፈጠረውን ነገር በቅጡ ለማብራራት ዛሬም ይቸገራል፡፡

‹‹በወፍራም ግድግዳና ትልቅ ፍሪጅ መካከል የተላክሁበትን ጉዳይ ልፈጽም ስገባ ትዝ ይለኛል›› የሚለው ሀያሳኪ በደቂቃዎች ልዩነት ከዚያ በፊት አይቶ የማያውቀው ፈዛዛ ሰማያዊ፣ እጅግ ኃይለኛ፣ ከብልጭታ አለፍ ያለ ብርሃን አየሁ ይላል፡፡ ብርሃኑ ደግሞ የጆሮ ታንቡር የሚበጥስ ፍንዳታ ያስከትልና ሀያሳኪ ከመቅጽበት ከፍሪጁ ጀርባ ይወረወራል፡፡ ‹‹ከወደቅኩበት ቀና ስል ለማየት በሚያስቸግር ጥቁር ጥቀርሻ የነበርኩበትን ክፍል ስለሞላው ለደቂቃዎች ማየት ተስኖኝ ብቆይም ቀስ በቀስ ግን በጥቂቱ ወገግ አለልኝ፡፡ በቅድሚያ ያየሁት የራሴን የተራቆተ እግርና ሰውነት ነበር፣ አለመጎዳቴን ግን አረጋገጥኩ፡፡ ከሃያ ደቂቃ ላላነሰ ጊዜ ካለሁበት አንድ ሜትር አርቄ ማማተር ተስኖኝ ቆየሁ፣ ሁሉ ነገር ጨለማ ነበር፤›› ሲል ሁኔታዎች የሚያስታውሰው ሀያሳኪ ቀስ በቀስ ከነበረበት ተነስቶ የደረሰውን ጉዳት መመርመር ይጀምራል፡፡

‹‹ብዙ ቶን የሚመዝኑ ማሽኖች ሳይቀሩ በሥፍራቸው የሉም፣ ተወርውረዋል፣ ግድግዳው ወደ ፍርስራሽነት ተቀይሯል፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ግን በትንሹ በግማሽ ሰዓታት አንድም ነፍስ ያለው ፍጡር ያለማየቴ ፍርኃቴን ጨመረው፤›› ሲል በፍርስራሽ መሀል በግራ መጋባት ያሳለፈውን ጊዜ ያስታውሳል፡፡

የሞት ሞቱን ሙሉ በሙሉ የወደመ የፋብሪካውን ቅጥር ለቆ ሽሽት የጀመረው ሀያሳኪ ጥቂት ከተጓዘ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ያየው ሰው ከፍንዳታው በላይ ያስደነገጠው ነበር፡፡ ‹‹ሰውየው የለበሰው ልብስ ሙሉ ለሙሉ የተቃጠለ መሆኑ ይታያል፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ቆዳው ተተልትሏል፡፡ ምን እንደሆነ ጉዳቱ ስጠይቀው አየት አድርጎኝ እየተንገዳገደ አልፎኝ ከመሄድ ውጪ የሚናገርበት ኃይል አልነበረውም፤›› የሚለው ሀያሳኪ በድንጋጤና ግራ መጋባት ውስጥ ሆኖ ዕርምጃውን ቀጠለ፡፡

ወደ ፋብሪካው የሚገባውን የባቡር መሥመር ይዞ ሲገሰግስ ብዙ እንቅልፍ የሚነሱት ሰቆቃዎችን መታዘብ ችሏል፡፡ ‹‹ከሁሉም በይበልጥ የረበሸኝ ነገር በየመንገዱ ላይ ተዘርረው በደከመ ድምፅ ውኃ እንድሰጣቸው የሚለምኑኝ ተጎጂዎች ነገር ነበር፡፡ በወቅቱ ውኃ መጠጣቱ አደገኛ እንደሆነ አንድ ተጎጂ ቢነገረኝም ሰዎቹን ከመርዳት ግን አላቆመኝም፡፡ በአቅራቢያ ውኃ ከነበረበት ወንዝ በሸማ ቅዳጅ ውኃ እየነከርኩ ከሃያ በላይ ለሚሆኑ ላንቃቸው ለማራስ ሞከርኩ፤›› የሚለው ሀያሳኪ፣ ከአፍታ ቆይታ በኋላ አልሰማ ያለውን ማስጠንቀቂያ እውነትነት መረዳቱን ይገልጻል፡፡ ‹‹ውኃ ማድረሴን ገታ አድርጌ ስመለከት ያጠጣኋቸው ሰዎች በብዛት በሕይወት የሉም፡፡ በእጅጉ አዘንኩ፣ የገዳይነት መንፈስ ተሰማኝ፤›› ይላል፡፡ በዚህ መሀል በሚሠራበት ፋብሪካ የሚያውቀው ሰው በናጋሳኪ ላይ የተጣለው ከሦስት ቀናት በፊት በሄሮሺማ ላይ ትልቅ ጥፋት ያደረሰው ዓይነት ቦንብ መሆኑን እንደነገረው ያስታውሳል፡፡

የታሪክ ጠባሳ

 

‹‹አዲስ ዓይነት ቦንብ ነው፤ በሄሮሺማ ላይ የወደቀው በዚህ ዓይነት ናጋሳኪ አብቅቶለታል፣ የተረፈ ነገር የለም፣ ሁሉ ነገር ወድሟል፡፡ ብሎኝ ራሱን ስቶ የወደቀው ባልደረባዬ ግን በጣም ፍርኃቴን ጨመረው፤›› የሚለው ሀያሳኪ በወቅቱ የታዘበው ሰቆቃ ሕይወቱን እንደቀየረው ይናገራል፡፡ ‹‹ፀጉራቸውና ቆዳቸው ከፍንዳታው በተለቀቀው እሳት አዘል አየር የተቃጠለባቸው ሰዎች ውኃ ፍለጋ ሲዳክሩ አይ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ የቆዳ ቀለማቸው በጥቁርና ወይን ጠጅ መካከል ሆኖ ነበር፡፡ ፈጽሞ አይቼው የማላውቀው ሰቆቃ ነበር የተደቀነብን፡፡ አደጋው ብዙዎቹን አስፈሪ ፍጥረት አስመስሏቸው ነበር፡፡ በጣም የሚያስፈራ ትዕይንት ነበር፤›› ይላል ሀያሳኪ፡፡

በዚህ ሁሉ መሀል ባልደረባዬ ‹‹ናጋሳኪ አልቆለታል፣ ወደ ቤተሰቦችህ ሂድ›› ያለኝን እያሰላሰልኩ በርቀት የባቡር ድምፅ ስሰማ፣ የዕርዳታ መምጣትን አበሰረኝ በማለት የሚተርከው፣ የአቶሚክ ቦምብ በጥቃቱ ያጣውን ነገር ሲያሰላው በእጅጉ ያዝናል፡፡ ‹‹ጓደኞቼ የሥራ ባልደረቦቼ፣ የትምህርት ቤት እኩዮቼን በአንድ ቅጽበት ማጣቴ ሳስበው ብሎም ከዚያ በኋላ ሕይወቴን ለማስቀጠል ያየሁትን ፈተና ሳስበው በእጅጉ አዝናለሁ፤›› ይላል፡፡

ሀያሳኪ ዛሬ የ88 ዓመት አዛውንት ነው፡፡ እንዳለውም የናጋሳኪ ቦንብ ሕይወቱን በእጅጉ ለውጦታል፡፡ ለዘመናት ‹‹ናጋሳኪ ፋውንዴሽን ፎር ዘ ፕሮሞሽን ናኦ ፒስ የተሰኘ›› ኅብረት አባል ሆኖ በዓለም እየዞረ የሰላምን አስፈላጊነት ሰብኳል፡፡ አሁን ላይ ናጋሳኪ በተገነባው የሰላም ፓርክ ውስጥ በአንድ ጥግ ላይ የሰላም መልዕክቱን ለጎብኚዎች ማሰማቱን ቀጥሏል፡፡ ሀያሳኪ የማይጠፋበት በቦንብ ጥቃቱ የጠፉ ሰዎች ሐውልት የጎብኚ ቀልብን በእጅጉ ትስባለች፡፡ ምክንያቱም ሀያሳኪ በብዙ ጥቅም ላይ የዋሉ የውኃ ፕላስቲኮች ውኃ ቀድቶ ጎብኚዎችን ስለሚጠባበቅ ነው፡፡ ከውኃ በተጨማሪ አንዲት አበባ አብራ ትታያለች፡፡ ታድያ የሱን ታሪክ ለመስማት ጎራ የሚል ጎብኚ በሙሉ በዚች አበባው ውኃ ቀድቶ ማጠጣት አለበት፤ ይህ የሀያሳኪ ሕግ ነው፡፡ ‹‹አበባዋ በዛ የሰቆቃ ሰዓት ውኃ እንዳጠጣቸው የለመኑኝን ያለፉ ሰዎች ሕይወት ማስታወሻ ናት›› የሚለው ይህ አዛውንት በቀን ውስጥ ወደሱ ጎራ ለሚሉ ጎብኚዎች በሙሉ ያለመታከት ታሪኩን ያወራል፤ በዚያውም የነዛን የሰቆቃ ሰዓታት ደጋግሞ ይኖራቸዋል፡፡

በፍንዳታው ቅጽበት 74,000 ወገኖቻቸውን እንዳጡ የሚናገሩት ናጋሳካውያን (አንዳንድ መረጃዎች ከመቶ ሺሕ በላይ ሞተዋል ይላሉ) ለዚህ ጠባሳ በከተማው ትልቅ ማስታወሻ የሰላም ፓርክና የሰላም ሙዚየም ተክለዋል፡፡ የሰላም ፓርኩ በዋነኝነት ያረፈው በፍንዳታው እምብርት ቦታ ላይ ሲሆን፣ ሀያሳኪ የሚሠራበት ማትስቢኢ ፋብሪካን ጨምሮ በፍንዳታው 100 ሜትር ዙርያ ገባ ላይ የሚገኙ አንድ ማረሚያ ቤት፣ እንዲሁም የጥንት ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ መውደማቸው ይወሳል፡፡ አንዳንዶች እስከ 600 ሜትር ራዲየስ ውስጥ የነበሩ ሰዎችና ሕንፃዎች እንደጠፉም ይመሰክራሉ፡፡

በቅጽል ስሙ ‹‹ፋትማን›› (ወፍራም ሰው) ተብሎ የሚታወቀው ይህ የአቶሚክ ቦንብ በናጋሳኪ አምሳያ ሞዴል ማስታወሻነት ተሠርቶለት ይጎበኛል፡፡ ጃፓናውያን በአቶሚክና ኒኩለር ቦንብ ዙሪያ ሰፋ ያለ መረጃ በሙዚየማቸው አሰባስበዋል፡፡ የተሠራበት ንጥረ ነገር (ፕሉቶኒየም)፣ ክብደቱ፣ የተፈበረከበት ቦታ፣ የሠራው ሰው በናጋሳኪ ላይ የጣለው የጦር አውሮፕላን እንዲሁም አብራሪ ፓይለቱ ዝርዝር ታሪክ በሙሉ የዚህ ሙዚየም አካላት ናቸው፡፡

ከሁሉም በላይ የሰላም ፓርኩን ያስዋበው ከመሬት 13 ሜትር ርዝማኔ ያለው የሰላም ሐውልት ሲሆን፣ እጆቹን በሁለት አቅጣጫ የዘረጋው ይህ የነሐስ ሐውልት በቀኝ እጁ ወደ ሰማይ የአቶሚክ ቦምብ የመጣበትን አቅጣጫ፣ በግራ የተዘረጋ እጅ ሰላምና መቻቻልን የሚያሳይ መሆኑ ነግሯል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የአቶሚክ ቦንብ ታሪካቸውን ጃፓናውያን ስለ ሰላም አስፈላጊነት መስበኪያነት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡

የታሪክ ጠባሳ

በአስራት ሥዩም፣ ናጋሳኪ፣ ጃፓን

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...