Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልዕውን የሆነው አዲሱ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ቤተ መጻሕፍት ሕንፃ

ዕውን የሆነው አዲሱ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ቤተ መጻሕፍት ሕንፃ

ቀን:

“የሪቻርድ ፓንክረስት ቤተ መጻሕፍት” ስያሜ የት ደረሰ?

በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት (ላይ ግቢ) ሕንፃ ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ጉዞው በሥሩ ያቀፈው፣ አብያተ መጻሕፍት፣ የኢትኖ ግራፊክሙዚየም፣ የጥናትና ምርምር ማዕከልን ነው፡፡ በጉያውም በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጻሕፍት፣ ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብት፣ የዳግማዊ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱን ጨምሮ የድምፅና የምሥል ቅጂዎች፣ ከመጀመርያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ የጥናት ድርሳኖች፣ ጆርናሎችና ረዥም ዕድሜን ያስቆጠሩ የብራና መጻሕፍትንም አቅፏል፡፡

ይህ ሁለገብ ጥናታዊ ነገሮች ያቀፈው ተቋም ያሉትን ሀብቶች ተደራሽ ለማድረግ ያለበት ብቸኛ ሕንፃ በቂ ባለመሆኑ በ1990ዎቹ የመጀመርያ ዓመታት ከአጠገቡ በሚገኝ ሥፍራ አዲስ ራሱን የቻለ ዘመናዊ የቤተ መጻሕፍት ሕንፃ ለማስገንባት ተንቀሳቅሷል፡፡

- Advertisement -

በቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አንድርያስ እሸቴ (ፕሮፌሰር)፣ ዘመን፣ የጥናት ተቋሙ መሥራችና የመጀመርያ ዳይሬክተር ሪቻርድ ፓንክረስት አቀንቃኝነት የተወጠነው፣ ከሙዚየሙ ተነጥሎ ራሱን የቻለ ቤተ መጻሕፍት ለመገንባት እንቅስቃሴ ሲጀመር ሕንፃውን አሠርተው ለማስረከብ ቃል የገቡት የሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባለቤትና ሊቀመንበር ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ናቸው፡፡ ሼህ ሙሐመድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በተቀበሉበት ወቅት ከፕሮፌሰር አንድርያስ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት አዎንታዊ ምላሽ መሠረት፣ በ116 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ዘመናዊ ሕንፃ ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ዩኒቨርሲቲው ተረክቧል፡፡ በሼህ መሐመድ አሊ አል አሙዲን ስም የተሰየመውን ሕንፃ ቁልፍ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደ ሐና (ፕሮፌሰር) ያስረከቡት፣ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋ ይርዳው (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ዕውን የሆነው አዲሱ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ቤተ መጻሕፍት ሕንፃ

 

በሥርዓተ ምረቃው ዲስኩር ያሰሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደገለጹት፣ በ6,240 ካሬ ሜትር ጠቅላላ የወለል ንጣፍ የተገነባው ሕንፃ በምድር ወለልና ሁለት ፎቆቹ የሚገኙት ዘመናዊ ክፍሎችና መገልገያዎቹ የጥናትና የምርምር ተቋሙን ወደ ላቀ ዕርከን እንዲያሸጋግር የታለመ ነው፡፡

ሕንፃው የስብሰባ አዳራሽ (ኦዲቶርየም) ከሙሉ 250 መቀመጫዎች ጋር፣ ከአራት በላይ የተገልጋዮች የማንበቢያ አዳራሾች ከአስተናጋጅ ካውንተር ጋር፣ የተለያዩ የስብሰባ አዳራሾችና ቢሮዎች፣ የመጻሕፍት ክፍል ከ365 ታላላቅ የመጻሕፍት መደርደሪያ ጋር፣ የማኑስክሪፕት፣ የፎቶ ኮፒ፣ የዕቃ ማስቀመጫዎች፣ የውኃ፣ የመብራት፣ የእሳት ማጥፊያ፣ ሁለት ሊፍቶች፣ የማቀዝቀዣ ሲስተሞች፣ የሠራተኞችና የላይብረሪው ተጠቃሚዎች የሚገለገሉባቸው የተለያዩ የምግብ አዳራሾች፣ የምግብ ማዘጋጃ/ኪችን ቦታዎች አካቶ ይዟል፡፡

በዩኒቨርሲቲው አመራር ውስጥ በነበሩበት ዘመን የተጀመረው ግንባታ በተጓተተበት ወቅት ከሚድሮክ አመራሮች ጋር ይነጋገሩ እንደነበር ያስታወሱት የዕለቱ የክብር እንግዳ  የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሒሩት ወልደ ማርያም (ፕሮፌሰር)፣ አዲሱ ሕንፃ “ስለ ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ ውስጠ ምስጢር ምንነትና ማንነት፣ ታሪኳንና ባህሏን፣ የጽሑፍ ቅርሶቿን ፈትለን ለማወቅ የሚረዳን ትልቅ ፋይዳ ያለው መሠረተ ልማት ነው፤” ብለዋል፡፡ ሌሎች ባለሀብቶችም በእንዲህ አይነት አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዕውን የሆነው አዲሱ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ቤተ መጻሕፍት ሕንፃ

 

የሪቻርድ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ቤተ መጻሕፍት ስያሜ የት ደረሰ?

ሃቻምና ያረፉት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ከአስተማሪነት እስከ ተመራማሪነት፣ እንዲሁም በኃላፊነት ያገለገሉ፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋምን ከመሠረቱት አንዱና የመጀመርያው ዋና ዳይሬክተር ነበሩ፡፡ ቤተ መጻሕፍቱን፣ ሙዚየሙንና የሥነ ጥበብ ጋለሪውን በማደራጀትና በማስፋፋት ይጠቀሳሉ፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ድምፁ የማይሰማው የኢትዮጵያ ጥናት ወዳጆች ማኅበር (ሶፊ) ለበርካታ ዓመታት ንቁ ተሳታፊና ሊቀመንበር በመሆን በሰጡት አገልግሎት፣ የተቋሙ ሙዚየምና ቤተ መጻሕፍት ስብስቦቹ በጥንታዊ ቅርሶች የተሞላ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በባህር ማዶ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች ከሽያጭ ለማዳን ገቢ ማሰባሰቢያ በማዘጋጀት ምሥሎችን፣ ሥዕሎችን፣ መስቀሎችና የሥነ ጥበብ ውጤቶች የማስመለሱን  ዘመቻ መርተዋል፡፡

ይህን ሁለገብ አገራዊ ተግባራቸውን ከግምት ውስጥ ያስገባው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በወቅቱ ፕሬዚዳንቱ አንድርያስ እሸቴ (ፕሮፌሰር) አማካይነት፣ በቅጥር ግቢው የመሠረት ድንጋዩ በ1993 ዓ.ም. በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የተጣለውንና ባለፈው ሐሙስ የተመረቀውን አዲሱን ቤተ መጻሕፍት በሪቻርድ ፓንክረስት ስም `The Richard Pankhurst Institute of Ethiopian Studies Library` ብሎ መሰየሙ በወቅቱ ተዘግቧል፡፡

ተቋሙ የእ.ኤ.አ. የ2007 የኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት ዕትሙ፣ እሳቸው ከባለቤታቸው ሪታ ፓንክረስት ጋር በመሆን ላበረከቱት አገልግሎትም የክብር መገለጫ እንዲሆን ያሳተመውና የተለያዩ ሊቃውንት ጥናቶቻቸው የታተመበት መድበል ሽፋኑም አሁን ዕውን የሆነውና በፋሲል ጊዮርጊስ የተሠራው ሕንፃ ዲዛይን ፎቶ የያዘ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ከሁለት አሠርታት ግድም በኋላ ዕውን የሆነው አዲሱ ቤተ መጻሕፍት የመነሻውን ስም አለመያዙ ተከትሎ፣ በሥርዓተ ምረቃው ላይ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የፓንክረስት ስም የት ደረሰ? በሚል ሪፖርተር የጠየቃቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደ ሐና (ፕሮፌሰር) የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ሕንፃውን የሠሩት ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ናቸው፡፡ ለላቀ አገልግሎታቸው የክብር ዶክትሬት የሰጠናቸው፡፡ በተለያየ ጊዜ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ተሰብስቦ የዚህ ሕንፃ ስም በስማቸው እንዲሰየም ሰጥቷል፡፡ በመጽሔቱ ውስጥ ዩኒቨርሲቲው የወሰነበት ጽሑፍ ይገኛል [ለምረቃው የቀረበው መጽሔት የተዘጋጀው በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሲሆን፣ በመጋቢት 16፣ 2008 ዓ.ም. በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አድማሱ ፀጋዬ (ዶ/ር) ፊርማ የወጣው ደብዳቤ የስያሜውን ውሳኔ ያስረዳል]፡፡

‹‹ለሪቻርድ ፓንክረስት ከፍተኛ ከበሬታ አለን፡፡ ለሙዚየሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ወደፊት ደግሞ የሳቸውን ስም እንዴት ነው የምሰጠው የምለውን ደግሞ ወደፊት ማኔጅመንት ዓይቶ ለእሳቸው ተመሳሳይ የሚሆን ነገር ማድረግ እንዳለብን ይሰማናል፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...