Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚጠቀሙበትን የድንጋይ ከሰል በዕፅዋት ምርት ለመተካት ታቅዷል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በማገዶነት የሚጠቀሙበትን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ  ከውጭ የሚገባውን የድጋይ ከሰል፣ በአገር ውስጥ የዕፅዋት ምርት ለመተካት እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በድንጋይ ከሰል ምትክ የዕፅዋት ምርት እንዲጠቀሙ የሚያስችል ጥናት ማካሄዱን አስታውቋል፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በአብዛኛው ከደቡብ አፍሪካ የሚያስገቡትን የድንጋይ ከሰል፣ ሲሚንቶ ለማምረት እንደ ዋነኛ ግብዓት የሚያገለግለውን የኖራ ድንጋይ ለማቃጠል ይጠቀሙበታል፡፡ በአገር ውስጥ የሚገኙ 17 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዓመት ለድንጋይ ከሰል ግዥ 220 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጡ ታውቋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዮሐንስ ድንቅአየሁ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የኖራ ድንጋይ በሚያቃጥሉበት ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦን ወደ አካባቢ ይለቃሉ፡፡ የፋብሪካዎቹን የካርቦን ልቀት መጠን ለመቀነስና የድንጋይ ከሰል ለማስገባት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማዳን፣ በዕፅዋት ምርት ለመተካት የሚያስችል ጥናት በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት መካሄዱን አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡ ረዥም ርቀት ተጉዞ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል ወደ ፋብሪካዎቹ ለማድረስ ብዙ ውጣ ውረድ እንዳለው የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ በአፋር ክልል በስፋት የሚበቅለውን የአረም ተክል በማቀነባበር ለማገዶነት ለመጠቀም ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የዕፅዋት ምርቱ ከካርቦን ልቀትና የውጭ ምንዛሪ ከማዳን በተጨማሪ፣ ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡

‹‹የአዋጪነት ጥናቱ ተጠናቋል፡፡ የዕፅዋት ምርቱን በፋብሪካ ለማቀነባበር ሰፊ መሬትና መዋዕለ ንዋይ የሚፈልግ በመሆኑ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ራሳቸው ኢንቨስት ያድርጉ? ወይስ ሌሎች ባለሀብቶች ይግቡበት? በሚለው ላይ ከተስማማን ሥራው በ2012 ዓ.ም. ሊጀመር ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሃላላ፣ ኢንስቲትዩቱ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ፈንድና አውሮፓ ኅብረት ድጋፍ በዕፅዋት ምርት ሒደት ላይ የአዋጪነት ጥናት ማካሄዱን ገልጸዋል፡፡ በአፋር ክልል በተለምዶ የወያኔ ዛፍ በሳይንሳዊ ስሙ ፕሮፌሲስ ኒውፎራ ተብሎ የሚታወቀው ተክል፣ በፋብሪካ ወደ ማገዶነት እንዲለወጥ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር ለፕሮጀክቱ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ከአፋር ክልላዊ መንግሥት ጋር በመምከር ላይ እንደሆኑ አቶ ሳሙኤል አስረድተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ በዓመት 2.2 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ካርቦን እንደሚለቅ የተናገሩት አቶ ሳሙኤል፣ የኢትዮጵያ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዓመት ስድስት ሚሊዮን ሜትር ኩብ ካርቦን እንደሚለቁ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አገራችን የነደፈችውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት መርሐ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ፣ ይህን የካርቦን ልቀት መጠን መቀነስ ወሳኝ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለድንጋይ ከሰል ግዥ በዓመት 220 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጡ የገለጹት አቶ ሳሙኤል፣ 40 በመቶ የሚሆነውን የድንጋይ ከሰል ፍጆታ በዕፅዋት ምርት መተካት ቢቻል 88 ሚሊዮን ዶላር ማዳን እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

የዕፅዋት ምርት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እስከሚሆን የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል እንዲጠቀሙ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እያበረታቱ ነው፡፡ የድንጋይ ከሰል ክምችት በጅማ አካባቢና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሺ ዞን በስፋት እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

የዳንጎቴና የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የዕፅዋት ምርቱንና የአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ለመጠቀም ያሳዩትን ተነሳሽነት አቶ ዮሐንስ አድንቀዋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የዳንጎቴና የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካዎችን በማስተባበር፣ ሰፊ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. አስጀምረዋል፡፡ በዕለቱ የድርጅቶቹ ሠራተኞች 1,500 ችግኞችን በምዕራብ ሸዋ አዳበርጋ ወረዳ ሙገር ከተማ አቅራቢያ ተክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች