በ2012 በጀት ዓመት 248.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዟል
ገቢዎች ሚኒስቴር የኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ የቫትና የቁርጥ ግብር አዋጆችን በረቂቅ ደረጃ ማዘጋጀቱንና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የ2011 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ አፈጻጸምን በሚመለከት ዓርብ ሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ በሥራ ላይ የሚገኙት የኤክሳይስ ታክስ፣ የቫትና የቁርጥ ግብርን በሚመለከት የሚታዩ የአሠራር ክፍቶችንና የንግዱ ማኅብረሰብ ቅሬታዎችን በመገንዘብ፣ በማጥናትና በመመርመር ነባር አዋጆችንና አሠራሮችን ማሻሻልና እንደ አዲስም መሥራት በማስፈለጉ፣ ረቂቅ አዋጆች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ኤክሳይስ ታክስን በሚመለከት እንደተናገሩት፣ የሚደረገው ማሻሻያ መሠረቱን ማስፋት ነው፡፡ ኤክሳይስ ታክስ ሊጣልባቸው የሚገባ ተመሳሳይና ተቀራራቢ ዕቃዎች (ምርቶች) ሆነው ሳለ፣ የተወሰኑ ላይ ተጥሎ የተወሰኑት ላይ አልተጣለም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በአንዳንድ ገቢ ዕቃዎች ላይ መጣል ባለበት ደረጃና ልክ ያልተጣለበት ሁኔታ ሲኖር፣ በሌሎች ላይ ደግሞ ከሚገባው በላይ መጣሉን አስረድተዋል፡፡ በአልኮል፣ በትምባሆና በመሳሰሉት ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ላይም መጣል አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ልምዶችን በማየት፣ የአገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባትና ጥናት በማድረግ፣ እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ከዓመት በላይ ጊዜ ተወስዶ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀታቸውን ወ/ሮ አዳነች ተናግረዋል፡፡
የቫት አዋጁም በተመሳሳይ ሁኔታ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ መሠረቱ እንዲሰፋ ሲደረግ ግብር እየከፈለ በሚገኘው የንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ሌላ ጫና መጨመር ሳይሆን፣ ተጨማሪ ግብር እንዳይጫንበት ማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የግብር ምጣኔውን ለማሳደግ ሳይሆን የማይከፍለውን ወደ ግብር ሥርዓቱ ለማስገባትም ጭምር መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ ታክስ እየከፈለ ያለው የንግዱ ማኅበረሰብ ጥያቄም በትክክለኛው አሠራር ሁሉም እኩል እንዲዳኝ በመሆኑ፣ አዋጁ ፀድቆ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ እንደሚስተካከል አስረድተዋል፡፡
ቁርጥ ግብር (ግምት)ን በሚመለከትም ማብራሪያ የሰጡት ወ/ሮ አዳነች፣ የዚህ ዓይነቱ ግብር የሚጣለው በክልሎች፣ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮች መሆኑን ጠቁመው፣ የሚጣለው ግምት ወይም ቁርጥ ግብር ግን ተገማችና ፍትሐዊ መሆን እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡ ቁርጥ ግብር በምን ሁኔታ መሠራት አለበት በሚለው ላይ ከክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውንና የአገማመት ሥርዓቱ መሻሻል እንዳለበት ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡ በዋናነት ወደ ሥርዓት መግባቱ የሚጠቅመው ወይም የተፈለገው የንግዱ ማኅበረሰብ ሒሳብ በትክክል መያዙን፣ ደረሰኝ በአግባቡ መቁረጡንና በአግባቡ መሠራት አለመሠራቱን ለማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይኼንን ካደረገ ማንም እንደፈለገ ሊገምትበት እንደማይችልም አክለዋል፡፡
ሚኒስትሯ ሌላው የገለጹት፣ ከቀረጥ ነፃ መብትን በሚመለከት ነው፡፡ ከቀረጥ ነፃ መብትን በሚመለከት ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከቀረበ በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን ጠቁመው፣ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ እንደሚፀድቅም ተናግረዋል፡፡
ከቀረጥ ነፃ መብት ጥሩ ቢሆንም እስካሁን ባለው አሠራር ግን ከታለመለት ዓላማ ጋር አብሮ እንዳልሄደም ጠቁመዋል፡፡ በየትኛውም ዓለም የሚደረግ ማበረታቻ መሆኑንና በአገር ኢኮኖሚ ውስጥ ገብቶ የለውጡ አካል እንዲሆን፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጥርና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ቢሆንም፣ እስካሁን መብቱን መፍቀድ ላይ ብቻ ትኩረት በመደረጉ ላልተገባ ዓላማ መዋሉን አስረድተዋል፡፡ ሆን ተብሎ ለዘረፋ የተመቻቸና ሲዘረፍበት እንደቆየም አክለዋል፡፡ ይኼ እንዲሆን የተደረገው ሕጉ በራሱ ክፍተት ስለነበረውና አገራዊ ጥቅም ያመጣሉ ተብለው የተዘረጉ ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና መመርያዎች ላይ ቁጥጥር ባለመደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ከ35 በላይ ተቋማት ከቀረጥ ነፃ መብት ይፈቀድላቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ዋናው ተቋም ጉምሩክ ግን የነበረው ሥልጣን ማስፈጸም ብቻ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይኼ የተዝረከረከ አሠራር ተስተካክሎና ቁጥጥር ተደርጎበት ውጤታማ የአሠራር ሥርዓት ውስጥ እንዲገባ፣ በግልጽ ማሻሻያ እንደተደረገበት አስረድተዋል፡፡ በየሴክተሩ ላሉ የኢንቨስትመንት ዓይነቶች የተለያየ አለካክ ማስቀመጥ ሳይሆን፣ ለሁሉም እንደ ዓይነታቸው ተመሳሳይ አሠራር ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ እስካሁን የሚሠራባቸው ሕጎችና መመርያዎች ከ40 በላይ በመሆናቸው፣ ሰብሰብ ብለው አንድ አዋጅ ሆነው እንደሚፀድቁ ተናግረዋል፡፡
የክትትል ሥርዓቱና ቁጥጥሩ በየትኛው ተቋም ሥር ይሁን የሚለውም አዋጁ ሲፀድቅ እንደሚታወቅና ከዚያ በኋላ፣ ‹‹አንድ ሆቴል እገነባለሁ ተብሎ 28 ጊዜ ብረት ሲያስገቡ መቆየት ይቆማል፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ አዋጅ በኋላ ብረትም ሆነ ሌላ ከቀረጥ ነፃ የሚገባ ነገር ያለው ፕሮጀክት ታይቶና በልኩ እንዲሆን ቁጥጥር እንደሚደረግበት አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ ዜጎች ግብር መክፈል ያለባቸው በፈቃደኝነት መሆን እንዳለበት ለማድረግ እንጂ፣ በንግዱ ማኅበረሰብም ላይም ሆነ በማንኛውም ዜጋ ላይ ጫና ለመፍጠር እንዳልሆነ ወ/ሮ አዳነች ተናግረዋል፡፡
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የ2011 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምን በሚመለከት እንደገለጹት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 213 ቢሊዮን ብር እንዲሰበስብ ያወጀውን ገቢ፣ ተቋሙ ወደ 241 ቢሊዮን ብር ከፍ በማድረግ አቅዶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ላይ ግን 198.1 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ከ2007 እስከ 2009 በጀት ዓመታት ዕቅድ ጋር ሲነፃፀር የ70፣ የ54 እና የ38 ቢሊዮን ብር ዕድገት ማሳየቱንም ጠቁመዋል፡፡
በ2011 በጀት ዓመት ዕቅድን በተሳካ ሁኔታ መፈጸም መቻሉን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ለዚህም ተቋሙ ስትራቴጂክ ዕቅድ ክለሳና መዋቅራዊ ለውጥ ማድረጉ፣ በአሠራር ሥርዓትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ማሻሻያ በማድረጉና የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ሥርዓት በመዘርጋቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በተደረገ የግብር ንቅናቄ ኩነቶች፣ የግብር ሥርዓቱ ላይ መነቃቃት በመጨመር፣ ከግብር ከፋዩ ጋር ተቀራርቦ መሥራት በመቻሉ፣ በኅቡዕ ይንቀሳቀሱ የነበሩ 12 ሺሕ ነጋዴዎችን ወደ ግብር ሥርዓቱ ማስገባት መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የታቀደውን በሙሉ ማሳካት ያልተቻለው የአገራዊ ፖለቲካዊና የሰላም ሁኔታ፣ የወጪ ንግድ መቀዛቀዝ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ግብር ሥወራና ማጭበርበር የመሳሰሉ ተግዳሮቶች ስላጋጠሙ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ በ2012 በጀት ዓመት 224 ቢሊዮን ብር ገቢ እንዲሰበሰብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢነገረውም፣ ነገር ግን ዕቅዱን በመለጠጥ 248.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብስብ ዕቅድ ነድፎ እንቅስቃሴ መጀመሩን ወ/ሮ አዳነች አስታውቀዋል፡፡