Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች እኔን አላሳመኑኝም

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች እኔን አላሳመኑኝም

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ዕትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2011 ዓ.ም. የኢኮኖሚ አፈጻጸም ሪፖርትን አስመልክቶ፣ የተገነዘብኩትንና ጉድለት ይታይባቸዋል ያልኳቸውን ሐሳቦች መጻፌ ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2012 ዓ.ም በጀትን ለማፀደቅ ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፓርላማው ባቀረቡበት ወቅት፣ በሚቀጥሉት ዓመታት ሦስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞችን ለማድረግ እንደታቀደ ገልጸው፣ እነዚህ ማሻሻያ ፕሮግራሞችም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የመዋቅር ማሻሻያና የተቋም ማሻሻያ ተብለው በሦስት ዓብይ ጉዳዮች እንደሚከፈሉ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ጽሑፌ ያለኝን አመለካከት ልገልጽ የምፈልገው ከሦስቱ በአንዱ ላይ ብቻ በማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ዛሬ ድረስ ጥቅል ፍላጎት (Aggregate Demand) ላይ አተኩረን የሕዝባችንን ፍላጎት አሳድገናል በማለት፣ የገጠሩ ሕዝብ ‘ቡናን በጨው’ ከመጠጣት አልፎ በስኳር መጠጣት ጀምሯል ያሉበትን በ2011 ዓ.ም. ሪፖርት ላይ ያቀረቡትን አጠናክረው በማቅረብ፣ ከእንግዲህ ግን ጥቅል አቅርቦት (Aggregate Supply) ላይ አተኩረን ምርትን ለማሳደግ እንተጋለን ብለዋል፡፡

እኔ እሳቸው ከተናገሩት ተቃራኒ አመለካከት ነው ያለኝ፡፡ ይህ አመለካከቴም ዛሬ በውስጤ የፈለቀ ሳይሆን፣ ለብዙ ጊዜ በብዙ ጽሑፎቼ ሳስተጋባው የነበርኩት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ባለፉት በርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እንዳደገ የታወቀ ቢሆንም፣ እንደ እኔ አመለካከት የሕዝብ ቁጥር ዕድገትና የዘመኑን ሰው የሸቀጦች ጣዕም ለውጥ ተከትሎ የመጣ የፍላጎት ዕድገት እንጂ፣ መንግሥት በተከተለው ፍላጎትን የማሳደግ ፖሊሲ ምክንያት የመጣ አይደለም፡፡

ከዚህ ቀደም ባቀረብኳቸው ጽሑፎች በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት ታላላቅ የዓለማችን ኢኮኖሚስቶችም በአቅርቦት ጎን (Supply Side) እና በፍላጎት ጎን (Demand Side) የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማራጮች ላይ፣ ብርቱ ክርክርና አሳማኝ ትንታኔዎችን ሰጥተዋል፡፡ ከጥንት ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች አንስቶ እስከ አሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ኒዮ ክላሲካል ብሎም እስከ ዘመናችን ኒው ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች በአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚክስ ሲያምኑ፣ ኬንስና የእሱ ፍልስፍና ተከታዮች ኒው ኬንሽያንስ ደግሞ በፍላጎት ጎን ኢኮኖሚክስ ያምናሉ፡፡ ሁለቱንም ማጣመር ይቻላል የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የእያንዳንዳቸውን ጽንሰ ሐሳብ፣ ትንታኔና ለአገራችን አንድምታ ቀንጨብ ቀንጨብ እያደረግሁ ስጽፍ ኖሬአለሁ፡፡ በዚህም ለታዳጊ አገሮች የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሕግጋትና ጽንሰ ሐሳቦች ምን ይሠራላቸዋል በልማት ኢኮኖሚክስ ላይ ብቻ ቢያተኩሩ ይበቃቸዋል? ከሚሉ ኢኮኖሚስቶች እለያለሁ፡፡ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳቦች ትንታኔዎችና ሕግጋት ለአደጉትም ላላደጉትም ለሁሉም የሚሠሩ ዓለም አቀፋዊ (Universal) ናቸው እላለሁ፡፡

ከአቅርቦት ጎን ፖሊሲ መነሻ ሐሳብ ስንነሳ፣ የዚህ ፖሊሲ ደጋፊዎች ክላሲካል ወይም ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ሲሆኑ፣ ሞዴላቸውም በፈረንሣዊው ክላሲካል ኢኮኖሚስት ጂን ባፕቲስት ሴይ አቅርቦት የራሱን ፍላጎት ይፈጥራል ሥሌት ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ይህ ማለትም ሰው በአምራችነቱ ገቢ ያገኛል፤ በሚያገኘው ገቢም የሌሎች ሰዎችን ምርቶች ፈላጊ በመሆን ፍላጎትን ይፈጥራል፣ ስለዚህም አቅርቦት የራሱን ፍላጎት ስለሚፈጥር በፍላጎት እጥረትና በምርት መትረፍረፍ ምክንያት አምራቾች ቀጣይ ምርታቸውን ገተው ሥራ አጥነት ይፈጠራል ብለን መጨነቅ የለብንም የሚል ነው፡፡ አቅርቦትን የሚገዛው ሕግም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ስለሆነ፣ የሀብት ድልድልንና የምርት መጠንን የሚወስነው ለአምራቹ በሚያስገኘው ገቢና ትርፋማነት መጠን ነው፡፡ ለዚህም ነው የክላሲካል ኢኮኖሚስቶች አስተምህሮ የሆነው የአቅርቦት ጎን ማይክሮ ኢኮኖሚክስ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ጥበብ ነው የሚባለው፡፡

በሌላ ወገን የኬንስ ማክሮ ኢኮኖሚ ፍልስፍና የፍላጎት ጎን ኢኮኖሚክስ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን፣ አትኩሮቱ ጥቅል ገቢ ላይ ነው፡፡ ስለዚህም የኬንስ ኢኮኖሚክስ አስተምህሮ የሆነው ማክሮ ኢኮኖሚክስ የገቢ አወሳሰን ሥርዓት ጥበብ ነው፡፡ ኬንስ የክላሲካል ኢኮኖሚስቶችን የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ማይክሮ ኢኮኖሚክስ ጥናት፣ በገቢ አወሳሰን የማክሮ ኢኮኖሚክስ ጥናት ተክቶታል፡፡ ሰዎች ሁሉ በአምራችነታቸው ገቢ ያገኛሉ፣ ባለሀብቱ ትርፍ ያገኛል፣ ሠራተኛው ደመወዝ ያገኛል፡፡ የራሱን ሥራ የሚሠራው ገበሬና ሥራ ፈጣሪም ከካፒታሉ ትርፍና ከእጅ ደመወዝ ያገኛሉ፡፡ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ገቢ ውስጥ የባለሀብቱ ገቢ ድርሻና የደመወዝተኛው ገቢ ድርሻ፣ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ አላቸው፡፡

በእነዚህ ገቢዎች ሰዎች ምን ያህልና ምን ዓይነት የፍጆታ ሸቀጦችን ይሸምታሉ? ምን ያህሉን ይቆጥባሉ? የሰዎች ገቢ ሲያድግ የፍጆታቸው ዝንባሌ (Propensity to Consume) እና የቁጠባቸው ዝንባሌ (Propensity to Save) በምን መልክ ይለወጣል? የባለሀብቱ ገቢ ሲያድግ፣ የደመወዝተኛው ገቢ ሲያድግ ለያይቶ መተንተንና ማጥናት ዋናዎቹ የፍላጎት ጎን ኢኮኖሚክስ ጥናቶች ናቸው፡፡

በብሔራዊ ኢኮኖሚ ጥቅል ምርት ሥሌት አምራቾች ከፈጠሩት ተጨማሪ እሴት ወይም ምርት እኩል ገቢ ስለሚያገኙ፣ ተጨማሪ እሴት ወይም ምርትና ገቢ እኩል ናቸው፡፡ ሰዎች በአምራችነታቸው በሚያገኙት ገቢም የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ይሸምታሉ፡፡ የሸመታ ወጪዎችም ከገቢና ከምርት እኩል ይሆናሉ፡፡ ስለሆነም ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Gross Domestic Product – GDP) በምርት ዓይነትም፣ በገቢ ዓይነትም በወጪ ዓይነትም ቢሰላ መጠኑ እኩል ነው፡፡ በምርት ዓይነት የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ተጨማሪ እሴት በአጠቃላይ የምርት አቅርቦት ነው፡፡ በገቢ ዓይነት የሠራተኛው ገቢ ደመወዝና የባለሀብቱ ገቢ ትርፍ ሲሆኑ ለፍላጎት መሠረት ናቸው፡፡ በወጪ ዓይነት የግል ፍጆታ ወጪ፣ የመንግሥት ፍጆታ ወጪ፣ የግልና የመንግሥት መዋዕለ ንዋይ ወጪ፣ እንዲሁም ከኤክስፖርት ላይ ኢምፖርት ሲቀነስ ወይም የተጣራ ኤክስፖርት ወጪ በአጠቃላይ የምርት ፍላጎት ናቸው፡፡ ሆኖም የሰዎች ገቢ ወደ ገበያ ገብቶ የሸመታ ወጪ ከመሆኑ በፊት፣ ከገበያ ውስጥ በሁለት መንገድ ይጎድላል፡፡ አንዱ ጉድለት ከአምራቾችና ከባለ ገቢዎች ለመንግሥት በሚከፈል ግብር ሲሆን፣ ሁለተኛው ጉድለት በቁጠባ መልክ በባለ ገቢዎች በጓዳ ወይም በባንክ የሚያዘውና ለሸመታ ወደ ገበያ ተመልሶ የማይገባው ገቢ ነው፡፡

እነዚህ በግብርና በቁጠባ መልክ ከገበያ የሚወጡት ገቢዎች ተመልሰው ወደ ገበያው የሚገቡበት መንገድ አለ፡፡ ግብሩ የመንግሥት በጀት ወጪ በመሆንና ቁጠባው ከቆጣቢዎች በተበዳሪዎች ተወስዶ መዋዕለ ንዋይ በመሆን፣ ተመልሰው ወደ ገበያ ይገባሉ፡፡ ስለሆነም የፍላጎት ጎን ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትኩረት የገቢና የወጪ ዕቅድን ከክንውን ጋር ማጣጣም ነው፡፡ የሕዝቡ ገቢ ይታቀዳል፣ ግብር ይታቀዳል፣ የመንግሥት በጀት ይታቀዳል፣ ቁጠባ ይታቀዳል፣ መዋዕለ ንዋይ ይታቀዳል፣ ዕቅዶቹም ከክንውን ጋር ይነፃፀራሉ፡፡

የፍላጎት ጎን ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ተልዕኮ ማለትም የታቀደው ግብርና የተከናወነው ግብር እንዲጣጣሙ፣ የታቀደው የመንግሥት በጀትና የተከናወነው የመንግሥት በጀት እንዲጣጣሙ፣ የታቀደው ቁጠባና የተከናወነው ቁጠባ እንዲጣጣሙ፣ የታቀደው መዋዕለ ንዋይና የተከናወነው መዋዕለ ንዋይ እንዲጣጣሙ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የታቀደም ሆነ የተከናወነ ግብርና የታቀደም ሆነ የተከናወነ የመንግሥት በጀት እንዲጣጣሙ፣ እንዲሁም የታቀደም ሆነ የተከናወነ ቁጠባ ከታቀደም ሆነ ከተከናወነ መዋዕለ ንዋይ እንዲጣጣሙ ማድረግ ነው፡፡ 

በፍላጎት ጎን ኢኮኖሚክስ ዋነኞቹ የኢኮኖሚ ዕደገት መሠረቶች ቁጠባና መዋዕለ ንዋይ ስለሆኑም፣ ቁጠባንና መዋዕለ ንዋይን እኩል የሚያደርጋቸው በገበያ የሚወሰን የወለድ መጣኝና ይህንን የወለድ መጣኝ የሚያሰፍን የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲ ይቀረፃል፡፡ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲ የሸቀጦችን ዋጋ ስለሚወስንም፣ የሰዎች ገቢ ድልድል ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ሰዎች ገቢያቸው ሸቀጦችን የመግዛት አቅሙ ጠንካራ ሲሆን፣ ብዙ የፍጆታ ሸቀጦችን በመሸመት አምራቾችን ያበረታታሉ፣ ከገቢያቸው ውስጥ ለቁጠባ የሚሆን ጥሬ ገንዘብ ይተርፋቸዋል፣ በቁጠባቸው ንብረት ገዝተው የንብረት ባለቤት ይሆናሉ፣ ኑሯቸው ከዕለት ወደ ዕለት ይሻሻላል፡፡ በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መብዛት ምክንያት ሸቀጦች ከተወደዱባቸው ግን ባገኙት ገቢ ሁሉ ጥቂት ብቻ የፍጆታ ሸቀጦችን ስለሚሸምቱ ቁጠባም አይኖራቸውም፣ ንብረትም አያፈሩም፣ የዘወትር ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ብቻ ይሆናል፣ በአገር ደረጃም ቁጠባ ከሌለ መዋዕለ ንዋይም አይኖርም፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት የኢሕአዴግ አስተዳደር ዘመን ግብርናውንና ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ፣ ለገበሬውና ለከተማ ባለሀብቱ ድጋፍ በመስጠት በሚል ፍልስፍና ስትከተለው የነበረው የአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚክስ ፍልስፍናን ነበር፡፡ የአበባ እርሻ፣ ሰፋፊ እርሻ፣ የኤክስፖርት ምርቶች እርሻ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ልማት፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት፣ ወዘተ.፡፡ እነዚህ ሁሉ ያላጠገቡንና ያልረካንባቸው የነበሩና አሁንም ያሉ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ አዲስ ሊጀምሩት ያሰቡት የአቅርቦት ጎን ፖሊሲዎች ናቸው፡፡ 

የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን እንኳ ብንመለከት በዘርፍና በሴክተር ከፋፍሎ ስለምርት አቅርቦት ዕድገት ያወራል እንጂ፣ ስለገቢና ስለፍላጎት በአጠቃላይ ስለሸማቾች አቅምና ሁኔታ ትንታኔ የሰጠበት ምዕራፍና ገጽ የለም፡፡ ይህን አስመልክቶ ፍላጎትን አስቀርቶ ስለአቅርቦት ብቻ መናገርና መጻፍ፣ ሸማቹን ረስቶ አምራቹን ብቻ ማስታወስ በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ ነው ብዬ ብዙ ጊዜ ጽፌአለሁ፡፡

በመሠረቱ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ የአምራቹ ዋነኛ አዛዥ በሸመታው ቀጪና ሸላሚ የሆነው ሸማቹ እንጂ፣ የመንግሥት ድጋፍ አይደለም፡፡ መንግሥት የሸማቹን ገቢ በማስተካከልና ፍትሐዊ የገቢ ሥርጭት ፖሊሲን በመከተል፣ ሸማቹ የአምራቹ አለቃ እንዲሆን ማድረግ ይችል ነበር፡፡ በዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ሸማቹም ከአምራቹ እኩል የመደራደር አቅም እንዲኖረው ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ሆኖም በሸማቹ ላይ ምንም ዓይነት ሥራ ባለመሠራቱ ኪሱ ውስጥ በያዘውና በባንኮች እንደ ልብ በተረጨው የጥሬ ገንዘብ ብዛት የተነሳ፣ ነጋዴው ሸማቹን እርስ በራሱ አሻምቶ የተጠየቀውን ዋጋ እሺ ብሎ እንዲከፍል አደረገው፣ በዋጋ ንረት አንገበገበው፡፡

የመንግሥት አቅርቦት ጎን ፖሊሲ ውድድርን የሚያደናቅፉ መሰናክሎችን ማስወገድ፣ ለሁሉም ዕኩል ምቹ ሁኔታን መፍጠር፣ መሠረተ ልማትን መዘርጋት፣ ማኅበራዊ አገለግሎቶችን መስጠት፣ በታሪክ የተጎዱ ወገኖች እንዲያንሰራሩ ድጋፍ ማድረግ እንጂ፣ መንግሥትን የመጠጋት ዕድሉን ተጠቅሞ ለራሱ ብቻ ለመክበር የሚሻውን በሌሎች ትከሻ እንዲከብር መሣሪያ መሆን አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ የፍላጎት ጎን ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሆነውን የገቢ መጠንን በምርታማነት ልክ ለመገደብና የገቢ መመጣጠንን ፍትሐዊ ለማድረግ፣ የተስተካከለ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲ ባለመከተሏ አንዱ የመታጠቢያ ቤት ገንዳውን በወርቅ ሲለብጥ ሌላው የአካል ብቃትም እያለው፣ ተምሮ ዕውቀትም እያለው፣ የመንገድ ዳር ለማኝ ሆኗል፡፡ ምንም የማይሠሩ ጥቂት ወጣት ልጆች በወላጆቻቸው ሀብት ውድ መኪኖችን በየቀኑ ያለ ገደብ ለረጅም ሰዓታት ሲነዱ አገሪቱ የምታፈራው የውጭ ምንዛሪ ለነዳጅ ፍላጎት ብቻ የሚውል ሆነ፡፡ በውጭ አገሮች በሚያደርጉት ሽርሽር የውጭ ምንዛሪ ሀብታችን ተሟጠጠ፡፡ የቤትና የመኪና ደላሎች የሁለትና የሦስት ሕንፃዎች ባለቤት ሲሆኑ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች፣ ሐኪሞች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ለቤት ኪራይና ለወር አስቤዛቸው እንደሚጨነቁ በቅርቡ ሐኪሞች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን አቤቱታ እንደ አብነት ወስደን መመልከት ችለናል፡፡ ፕሮፌሰር ከመሆን በየበረንዳው የጀበና ቡና አፍልቶ መሸጥና በየጥጋጥጉ ሽሮ አንፈቅፍቆ መነገድ ተመራጭ የገቢ ምንጮች ሆነዋል፡፡ ንግድ ደጉ ይህች መናጢ ደሃ አገር በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተናጋጅነት በአምስት ሚሊዮን ብር አንድ ዕራት ሊበሉ የሚችሉ፣ በትንሹ ሁለት መቶ ሃምሳ ደጋግ ባለሀብቶችን አፍርታለች፣ የንፉጎቹ ቁጥር አይታወቅም፡፡

በአጠቃላይ አነጋገር ይህች አገር ባለፉት ዓመታት ለአቅርቦትም ሆነ ለፍላጎት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሳይንስ በሰጠችው ዝቅተኛ ትኩረት የዘራችውን እያጨደች ነው፡፡ ለወደፊትም ገና ብዙ ታጭዳለች፡፡ ከዚህ ቀደም ለውጤት ተኮር፣ ለቢፒአር፣ ለካይዘንና ለመሳሰሉት የመንግሥት አሠራር ማሻሻያ ፕሮግራሞች ከምንሰጠው ትኩረት ግማሹን እንኳ ለኢኮኖሚ ሳይንስ ዕድገት እንስጥ ብዬ ስሞግት የኖርኩት ባለመሰማቱ እዚህ ደረጃ ደርሰናል፡፡

ስለአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚክስና የፍላጎት ጎን ኢኮኖሚክስ ከዚህ ቀደም የልሂቃኑን ትንታኔዎች በስፋት የጻፍኩ ስለሆነ፣ እዚህ ላይ በድጋሚ ለማቅረብ አልፈልግም፡፡ አንዱን ብቻ ሳይሆን ሁለቱንም አመጣጥኖ መያዝም ስለሚቻል፣ ለዚህ ወገን አደላለሁ የምልበት ምክንያት የለኝም፡፡ ይኼኛው ከዚያኛው ይበልጣል ወይም ይሻለናል ብሎ ለማድላትም ወይም ለማመጣጠንም፣ ከዚህ በፊት እንደጻፍኩት በቅድሚያ ተጨባጭ ሁኔታን መተንተንና ማጥናት፣ ቀጥሎ ተስማሚ ጽንሰ ሐሳብን መምረጥ፣ ከዚያም ከጽንሰ ሐሳቡ ጋር የሚስማማ ፖሊሲ መቅረፅ፣ ፖሊሲውን የሚያስተገብር ዕቅድ መንደፍና ዕቅዱን መተግበር ያስፈልጋል፡፡

እያደግን እየመሰለን ከዓመት ዓመት፣ ከዘመን ዘመን የውጭ ሸቀጥ ምርኮኛ እየሆንን ዋናው የኢኮኖሚያችን ችግር የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየሆነ እንደመጣ ሁላችንም የምንመሰክረው ነው፡፡ የራሳችንን ምርት ለመጠቀምና በሸመታችን የራሳችንን አምራቾች ለማበረታታት የገቢ ድልድላችንን ማስተካከል ለነገ የማይባል የመንግሥት ኃላፊነትና የቤት ሥራ ነው፡፡ የውጭ ምርት ተጠቃሚ ማን ነው? የአገር ውስጥ ምርት ተጠቃሚ ማን ነው? ምክንያቶቹስ ምንድናቸው? ብለን ተንትነን ማጥናት የግድ ይለናል፡፡

ስለዚህም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በአቅርቦት ጎን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራማቸው እንደ ቀድሞው የብልጣ ብልጦች ምርኮኛ እንዳይሆኑ አጥብቄ ልመክር እሻለሁ፡፡ ይህ ጉዳይ የመቶ ሚሊዮን ሕዝብን ጉሮሮ የሚመለከት ስለሆነም በአቅራቢያቸው ባሉ ባለሟሎቻቸው ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቱ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የኢኮኖሚክስ ፋኩልቲዎች የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ለፖሊሲ መነሻ የሚሆኑ ግብዓቶች የሚሰበሰብበት እንጂ፣ በቀላሉ የሚፀድቅ ውሳኔ እንዳያደርጉት አሳስባለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...