Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትኢትዮጵያ ሆይ ደግሞ እንደምን አለሽ!?

ኢትዮጵያ ሆይ ደግሞ እንደምን አለሽ!?

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

የሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ግድያ በባህር ዳርና በአዲስ አበባ የተፈጸመው ይኼንን ጽሑፍ ከግማሽ በላይ ከገፋሁ በኋላ ነበር፡፡ የግድያው ምክንያትና ዓላማ ምንም ይሁን ምን ሰኔ አጋማሽን ሁላችንም እንደተጨነቅነው፣ ብሔር ከብሔር፣ አካባቢ ከአካባቢ ወደሚያበላላ መተላለቅ ሊከተን የሚችል ፈንጂ ነበር፡፡ ከዚህ ያመለጥነው ከመተላለቅ ማንኛችንም እንደማናተርፍ፣ ሁላችንም ዘንድ (የፌዴራልና የአካባቢ መንግሥታት፣ መከላከያና ፖለቲከኞች ዘንድ ሁሉ) ልብ ሊባል በመቻሉ ነው፡፡ በጊዜው የታየው ልብ መግዛትና አደጋውን ለማስወገድ የተደረገው ርብርብ ሁሉ ሊመሠገን ይገባል፡፡ ይህ ጽሑፌም ይህንን ኃላፊነታቸውን ለተወጡና ሲወጡ ለወደቁ ሁሉ መታሰቢያ ይሁንልኝ፡፡

በጽሑፎቼ ደጋግሜ ለማስገንዘብ እንደሞከርኩት መጨራረስን የሚያስከትሉ የፈንጂ ዓይነቶች እኛ ላይ መሥራት አለመሥራታቸውን ለማወቅ እያፈነዳን መክሰል አይኖርብንም፡፡ በቅርብና በሩቅ ጎረቤቶቻችን ላይ ከደረሰው ሲኦል መማርና መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ እናም እንደምንም ካመለጥነው የሰኔው ፈንጂ የማይረሳ ትምህርት መቅሰም ልባምነት ነው፡፡ የሽግግር ጊዜ የስኬት ክንዋኔዎችና ነፃነት፣ እንደ ጨቅላ ሰውነት ገና ያልፀና በቀላሉ ተሰባሪ ነውና ካሰቡት ለመድረስ በየወቅቱ ሁነኛ ጉዳይ ላይ የሕዝብን ትኩረት አሰባስቦ ወደፊት መራመድን ይጠይቃል፡፡ ባልፀና የንግግር ነፃነት ላይ በጥላቻ፣ በደም ፍላትና በበቀል የሚንጨረጨር ፖለቲካ መልቀቅ፣ ጨቅላውን ነፃነት ብቻ ሳይሆን ራሳችንንም እየለመጠጠ ከአመድ ይቀላቅላል፡፡ የሰኔ አጋማሹ ጥፋትም ሆነ በሶሻል ሚዲያ ላይ የሚታየው መረንነት የተማረረ ፖለቲካችን ውጤት ነው፡፡ ፖለቲካችንን የመረዙትን ችግሮች በእርጋታና በብልኃት ማስወገድ አለብን፡፡ ለዚህም እየተለፋ ሽግግሩ እንዳይጨነግፍ እያንዳንዳችን የምንበትነውን ሐሳብ በኃላፊነት ልጓም ልንገራው ግዳችን ነው፡፡ ወደ ዴሞክራሲ የምናደርገው ጉዞ ተዋክቦ እንዳይቀጭ ብቻ ሳይሆን፣ የተዋጣ ፍሬ እንዲሰጥ አንድ ጋር የገጠመ ርብርብ (ሶሊዳሪቲ) ያስፈልገናል፡፡ የሐሳብ ክርክራችንና ፉክክራችን ሁሉ በዚህ የሶሊዳሪቲ የትግል አንድነት ግቢ ውስጥ እንዲሆን መሥራት አለብን፡፡ ይህንን ጽሑፌንም በዚሁ ግቢ ውስጥ እንደምትረዱልኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ለለውጥ የምንብከነከነው የሚያብከነክን ዕጦት ስላለብን ነው፡፡ መሸካከርን፣ ጥላቻን፣ በብሔር መንጓለልንና መጠቃቃትን ያራገፈ ጤናማ የልሂቃንና የሕዝቦች ግንኙነትን፣ በሁሉም ዓይነት ማንነቶች ሳያፍሩና ሳይሳቀቁ በተግባቡ መብቶች ውስጥ መኖር፣ በአጠቃላይ ሶሲዮ ኢኮኖሚያዊ ግስጋሴ ለማካሄድ የሚያስችል የፖለቲካ ሰላምንና የሥራ ባህልን መቀዳጃት እንሻለን ብንል የብዙዎቻችንን ፍላጎት እናንፀባርቃለን፡፡ መልካም ፍላጎቶችን መደርደር ብዙም ላያስቸግር ይችላል፡፡ ዋናው ጉዳይ ፍላጎቶቻችን ሊጨበጡ የሚችሉ መሆናቸውና ለተጨባጭነት የሚያሿቸውን ነገሮች ጥርት አድርጎ መረዳትና በእነሱ ላይ ለመሥራት መቻል ነው፡፡

ዛሬ ኋላቀር አገሮች ያሉበት ወቅት የቋፍ (ሰበበኛ) ዘመን ሊባል የሚችል ነው፡፡ የመነጠል እንቅስቃሴ የሚጎትተው የመጠፋፋት ቀውስ ‹‹ልነጠል›› ባይንም፣ ‹‹ሞቼ ነው ቆሜ!›› ባይንም (ከተነጠሉ በኋላ እንኳ ቢሆን) የሚቀረጣጥፍ አይምሬ ጅብ ሆኗል፡፡ እንኳን የአብሮነት ግንኙነት ተናግቶ ይቅርና ከዚያ በመለስ አፋኝ አገዛዝን በጠመንጃዊ ነውጥ አፈራርሶ ለውጥ ለማምጣት መሞከር እንኳ (ማባሪያ የሌለው የፍጅት መንጋጋ ውስጥ በተደጋጋሚ ሲከት ታይቷልና)፣ በሩቁ ይቅርብን የሚባል ሆኗል፡፡ ይህንን ልብ ካልን ዛሬ አብሮ መኖር ለፍላጎቶቻችን ተጨባጭነት የቅድመ ሁኔታ ያህል ወሳኝ ሰበዝ መሆኑን ተረድተናል ማለት ነው፡፡

አብሮ መኖርን የጋራ ዕጣችን ያደረገው ከአብሮ መኖር ውጪ ያለ የትርምስ አዝቅት ብቻ አይደለም፡፡ የጋራ ዕጣ ያጎናፀፉን ብዙ የረዥም ታሪክ ሰበዞች አሉን፡፡ የረዥም ዘመን ጦርነቶች፣ አዝጋሚና ማዕበላዊ የማኅበረሰቦች እንቅስቃሴዎች፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከአንዱ ወደ ሌላው አፍስሰውናል፣ አሸማምነውናል፡፡ የምንጋራቸው ብዙ የሰቆቃና የትግል ታሪኮች፣ የጋራ ድሎች፣ የጋራ ኩራቶች፣ የጋራ የባህል ቅርሶችና እሴቶች አሉን፡፡ እነሱን በአግባቡ ለመንከባከብና ለማበልፀግ መቻል አለመቻልም ዕጣችንን ይወስናል፡፡ ለምሳሌ የመላ ኢትዮጵያ መሰባሰቢያ እንብርት የመሆን ታሪክ ያላትን አዲስ አበባን ለአዲስ አበቤዎች ማለት፣ ወይም በሕዝብ በተመረጠ ከንቲባ መተዳደርና የራስን ዕድል በራስ መወሰን ያላቸውን ልዩነት ሳያውቁ አዲስ አበባ የራሷን ዕድል ትወስን ብሎ ማለት አባ ዘባራቂነት ነው፡፡ አማራ ክልል በሚባለው ውስጥ ልዩ አስተዳደር ሆኖ ከዚያ ውስጥ ባይተዋር ለማውጣት መሞከር ጭልጥ ያለ የፖለቲካ ስካር ማሳያ ነው፡፡ በአማራ የፖለቲካ ቡድን/‹‹ንቅናቄ›› አማካይነት በየክልሉ ያለ አማራን መብትና ጥቅም አስከብራለሁ ማለት ሌላ ፖለቲካዊ ቅዠት ነው፡፡ ኦሮሞ በታሪክ ሒደት በየአቅጣጫው ተቀላቅሎ ሶማሊኛ ተናጋሪ፣ ሐረሪኛ ተናጋሪ፣ አፋርኛ ተናጋሪ፣ አማርኛ ተናጋሪ፣ ትግሪኛ ተናጋሪ፣ ጉራጊኛ ተናጋሪ፣ ወዘተ መሆኑን ሲረዱ የኦሮሞነትን ጉዳይ የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ አድርጎ አመለካከትን በማስተካከል ፋንታ፣ የኦሮሚያ ካርታ ወሎን ውጦ እስከ ትግራይ እንዲጠልቅ መቃበዝ መጠፋፋትን የሚሻ ዕብደት ነው፡፡

ከዚህ ዓይነቶቹ ዕብደቶች ለመመለስ ብንችልም የለውጥ ጉዟችን የፖለቲካ ጤናችንን ሊያስጠብቅ በሚችል አኳኋን ካልተዋቀረና በሁሉም ሕዝባችን ዘንድ በእኩልነት፣ በነፃነትና በፍትሐዊ ልማት ውስጥ የመኖር ስሜትን በመፍጠር ረገድ ስብራት ከደረሰ፣ የማኅበራዊ ሰላምና የመጣጣም ፍላጎቶቻችን ተጨባጭነትና ዘላቂነት ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ለውጣችን ምን መጣልና ማጥብቅ እንዳለበት ከወዲሁ መመርመር ተገቢያችን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ አስተዳደር የመቀየር ሥረ መሠረታዊ ቁም ነገር፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዴሞክራሲ መብቶች ውስጥ ነፃነትና እኩልነት ተሰምቷቸው በአንድ አገር ማዕቀፍ ውስጥ ዕምቅ አቅማቸውን በአግባቡ ፈልቅቀው የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ኑሯቸውን እንዲያራምዱ የሚስማማ አስተዳደራዊ ሥርዓት ማጎናፀፍ ነው፡፡ ይህም የቡድንና የግል ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአግባቡ በተረጋገጡበት አኳኋን፣ የአገሪቱን ሕይወት በፌዴራላዊና በአካባቢያዊ ሥልጣኖች ማሳለጥን የተመለከተ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የ1983 ዓ.ም. ቻርተርና የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥትን ተመርኩዞ በኢትዮጵያ የተደራጀው ሥርዓት የአገሪቱን ሕዝቦች ሰላም፣ ኅብረትና የግስጋሴ አቅም በእኩል ባለመብትነት ስሜት ማሳለጥ ያቃተውና ዴሞክራሲ የተሰለበበት ሥርዓት  ነበር፡፡ ብዙ ብልሽትም አድርሷል፡፡ አንድ ሁለት ብለን እንያቸው፡፡

  • ሁሉን ማኅበራዊ ሥፍራ አገሬ/ወገኔ ባይነትንና እኩል ዜግነትን ነስቷል፡፡ በየክልሉና በየክልሉ ውስጣ ውስጥ የቤተኛና የባይተዋር ግንኙነት ፈጥሯል፡፡ ዋና ባለመብትና በችሮታ መብት የሚያድር አድርጎ ኅብረተሰብን ለያይቷል፡፡ በብሔረሰብ ማዳላትንና ማበላለጥን ተገቢ አድርጓል፡፡
  • በዚህም ምክንያት በየክልሎች ውስጥ የብሔረሰብ መብቶች በሁለት መልክ እንዲጎሳቆሉ ተደርገዋል፡፡ በየክልሉ ‹‹ባለቤት›› የተባሉ ብሔረሰቦች ራሳቸውን ዋነኛ ባለመብት አድርገው እንዲያዩ፣ ከእነሱ ውጪ ያሉትን በመብት አሳንሶና ባይተዋር አድርጎ መቁጠርን ከመብት አለማስነካት ጋር ባሳከረ እሳቤ የጭቆና አመለካከት ተቋዳሽ እንዲሆኑ ተድርገዋል፡፡ ከባለቤትነት ውጪ የሆኑ ብሔረሰቦችና የብሔረሰብ አባላት ላይ አድልኦ ከማድረግ አንስቶ፣ የአካባቢውን ብሔረሰባዊ ባለቤትነት በባህልና በቋንቋ ሴመኝነት ብልጫ ለማስተማመን ሲባል በቋንቋቸው የመማር መብታቸውን የመደፍጠጥ፣ ክምችታቸውን በስግሰጋና በማፈናቀል የማደብዘዝ ጥቃት በተለያየ ደረጃ ደርሶባቸዋል፡፡ የዚህ ዓይነቱ በዳይነትና ከዚህ የሚፈልቅ ቅያሜና ጥላቻ፣ አንጓላይ ብሔርተኛ ገዥነት ከመጣበት ጊዜ አንስቶ በሁሉም ሥፍራ ድፍን ፈቃድ ተሰጥቶት ቆይቷል፡፡

የሕወሓት መሪዎች በግንባር ልምድ ራሳቸው የኢትዮጵያ ዋና ገዥ ሲያደርጉና የደርግን ሠራዊት በትነው በራሳቸው ሠራዊት መከላከያን፣ ደኅንነትንና ፖሊስን ሲያዋቅሩ የትግራይ ሕዝብን መስዋዕትነትና የመላውን ሕዝብ የዴሞክራሲና የእኩልነት ተስፋ ነበር የረገጡት፡፡ በዚህ ድርጊታቸው ራሳቸውን ባስጠመዱ ጊዜም ለመገኛቸው የትግራይ ሕዝብም መጠመድን አጋርተዋል፡፡ ያረቧቸው ጭፍራ ቡድኖች በየ‹ርስታቸው› አድሏዊ ገዥነትን ሲዘረጉም፣ ጥላቻዊ ግንኙነትን ሕዝቤ ለሚሉት ሳይቀር በተግባራቸው አድለዋል፡፡ በየአካባቢዎች ሕዝቦች ባለቤትና መጤ (ባይተዋር) ተደርገው ከተከፈሉበት ጊዜ አንስቶ ሁሉም ብሔረሰቦች በአንድ ጊዜ ባለቤትና መጤ፣ በአንድ ጊዜ አንጓላይና ተንጓላይ ተደርገዋል፡፡ በክልላቸው ውስጥ ባለቤት፣ በሌላ ክልል ውስጥ ደግሞ በመጤነትና በመገፋት ዕጣ ውስጥ እንዲወድቁ ተደርገዋል፡፡ በብሔር መጠቃት፣ መገደልና መፈናቀል ፈቃድ የተሰጠው ያኔ ከ1984 ዓ.ም. አካባቢ ጀምሮ፣ አማሮች ነፍጠኛ እየተባሉ ጥቃት ሲደርስባቸውና የሁሉ በደል ምንጭና ማላከኪያ ያደረገ ፕሮፓጋንዳ ይለቀቅ በነበረ ጊዜ ነበር፡፡ ለትግሬዎች፣ ለኦሮሞዎች፣ ለሶማሌዎች፣ ለጌዴኦዎች፣ ለወላይታዎች፣ ለጉራጌዎች፣ ወዘተ መፈናቀል በሩ የተከፈተውም ያኔ ነበር፡፡ ያ በር እስከ ዛሬ አልተዘጋም፡፡ ብሔረሰቦች በአንድ ጊዜ ይዞታቸው በተባለ ሥፍራ በስመ ጥቅማቸው አንጓላይ የበደል ሥራ የሚነገድባቸው፣ የሌላ በተባለ ይዞታ ውስጥ ደግሞ ተንጓላይ የሚሆኑበት ባለሁለት ገጽታ ጭቆና ዛሬም ገና አልተወገደም፡፡

  • ሥርዓቱ ሰዎች ላይ የፈጠረው ብሔርተኛ ግንኙነትና የሚያባዝተው ፖለቲካ፣ የሰዎችንም አዕምሮ ቃኝቷል፡፡ ሰዎች ብሔረ ብዙ ተራክቧቸው እንዲኮማተር፣ በጥርጣሬ፣ በመፈራራትና በመሸካከር እንዲሳሳ አድርጓል፡፡ የተዝናና ልባዊ የፖለቲካ ጨዋታና ባልንጀራነት ጭምር የብሔር ቢጤን ወደ መፈለግ እንዲያደላ፣ ከቤት ሠራተኛ ጀምሮ እስከ ፖለቲካ ሰው ምርጫ ወደ ብሔር ቢጤ እንዲጠመዘዝ አድርጓል፡፡ የብሔር ፓርቲዎችም ብሔርተኛነታቸው እንደተጠበቀ ግንባር ቢሆኑምና አገራዊ ሥልጣን ላይ ቢወጡም፣ አካባቢያዊ ተልዕኳቸው ከአገራዊ ኃላፊነታቸው ጋር እየተፎካከረና እየተጋጨ የሕዝቦችን አመኔታ በጥያቄ ውስጥ ሲያስገባ ቆይቷል፡፡

ይህ ሁሉ ለብዙ ሰው እንግዳ ያልሆነና ብዙ የተባለለት የጊዜያችን ኑሮ እንከን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ብሔርተኞች ዛሬም የእነዚህ ችግሮች ምንጭ፣ ብሔርተኛ ፖለቲካቸው አግላይ የፓርቲ አደረጃጀታቸውና ብሔርተኛ የመሬት ቅርጫቸው  መሆኑን፣ መፍትሔያቸውም በዚያው በብሔርተኛ መቃን ውስጥ እንደማይገኝ መረዳት ቀላል አልሆነላቸውም፡፡ ዕውን ይኼንን መረዳት ከባድ ሆኖ!?

ብሔርተኛ ፖለቲካና አግላይ ገዥነቱ ጭርንቁሱ ከወጣ በኋላ፣ የአማራን ጥቅም ለማስጠበቅ በብሔር መደራጀት ግድ ሆኖብኝ ተደራጀሁ ባይ አፍላ ብሔርተኝነትን እንደ ምሳሌ ታክኬ ነጥቦቼን ላፍታታ፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥቅም የተባለው ነገር ሁለመናው የመሬት ጉዳይ ካልሆነ በቀር፣ ከላይ እንደገለጽኩት ብሔርተኛነት የየቱን ብሔረሰብ መብት ሲያስከብር ታይቶና ተቀንቶ ይሆን አዲስ ወረትና አፍላ ጉልበት ያገኘው? የትኛው የብሔር ቡድን ብሔረሰቡን አግላይ ገዥነት ከሚያራባው ቅራኔ አዳነ? የትኛው ቡድን ብሔረሰቡን ከቂም፣ ከጠይነትና ከተጠይነት፣ ከአፈናቃይነትና ከተፈናቃይነት ሲያድን ታየ? በብሔረሰብ ማንነት ተለይቶ መደራጀትና ብሔሬ ተበደለ፣ ተገፋ ብሎ ለብቻ ስለራስ ብሔረሰብ መጮህ ኃይል አጠንክሮ ውጤት ሲያመጣ የት ታየ? ‹‹አብን››ም ሆነ ‹‹ሳልሳዊ ወያነ›› ከብቻ ጩኸት ይልቅ ለየትኛውም ብሔረሰብ በደልና መፈናቀል መጮህና መተባበር፣ ግዙፍ የፀረ ጭቆና አቅም እንደሚያጎናፅፍ እንኳ የሚያስተውል ዓይን አላቸው? የአገራችን የትግል ታሪክ ለግማሽ ምዕተ ዓመታት ግድም ይህንኑ ትምህርት ቅሰሙልኝ እያለ ሲማፀን መኖሩ ንፋሱ እንኳ ደርሷቸው ይሆን?

አንጓላይ አወቃቀርንና ገዥነትን ተገቢ ያደረገው ሥርዓት እስከ ቀጠለ ድረስ፣ አዲስ አበባ ወይም ክልላዊ የብሔር ቤቱ ውስጥ ዋና መቀመጫውን ያደረገ የብሔር ፓርቲ፣ በየክልሉ ያሉ የብሔር ወገኖቹን ‹‹ለጥቅማችሁ የምታገል…›› እያለ በፓርቲ አባልነት ስለመለመለና ብሶታቸውን ስለጮኸ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም፡፡ ለፌዴራል መንግሥት አቤት ብሎ ሰብዓዊና የዜግነት እኩል መብትን ላስከብር አይባል ነገር፣ ባለቤትና ባይተዋር ተደርጎ መከፋፈል (በሕገ መንግሥት) የተቋቋመ ሥርዓት ሆኖ ሳለ፣ ፌዴራል መንግሥት የተለየ ባህርይ ከሰማይ ሊያመጣ ነው?! ለየብሔሬ ቆሜያለሁ ባይ ብሔርተኛ ፓርቲ ራሱን በብሔር ለይቶ (ሌላውን አንጓሎ) እስከተደራጀ ድረስና ከሥርዓቱ አወቃቀር ጋር ስምም እስከሆነ ድረስ፣ መንጓለልን ለመታገል የሚያስችል የአመለካከት እውነተኛ አንጀት ከየት ሊያመጣ? አንጀት እንደ ምንም አግኝቶ የብሔሩን ሰዎች ባይተዋር በተደረጉበት ክልል ውስጥ ለመብታቸው በሠልፍና በስብሰባ እንዲጮሁ ቢያደርግ፣ ጭራሽ አጎንብሶ በማደር እንኳ ሊያገኙት የሚችሉትን ጥቅም እስከ ማጣትና በተለያየ ሥልት እስከ መፈናቀል ለሚደርስ የበቀል ጥቃት ሊያጋልጣቸው ይችላል፡፡ ትጥቅ አንስቶ ወደ መታገል ቢመራቸው የባሰ በጥቃት ለመሟጠጥ አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ የ‹‹ሀ›› ብሔር ፓርቲ በሚገዛበት ክልል ውስጥ ባሉ የእኔ ብሔር ሰዎች ላይ በደል ሠርቷልና በራሴ ክልል ውስጥ ባሉ የእሱ ብሔር አባላት ላይ ሒሳብ ላወራርድ ማለትም፣ በቀልን በበቀል እያራቡ ተያይዞ ወደ ገደል መንጎድ ነው፡፡ እነዚህ የገደል መንገዶች ተሞካክረዋል፡፡ በየአካባቢው የመብት መበላለጥና መንጓለል ውስጥ የከተተንን ሥርዓት አቅፎና አክብሮ የሚደረግ የትኛውም መፍጨርጨር ውጤት አያመጣም፡፡

በ‹‹አሥራት›› ቲቪ የ‹‹አብን›› የስትራቴጂ ጥናት ኃላፊና የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ ግንቦት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው ቃለ መጠይቅ ድርጅቱ አካታች እንደሆነና ቅማንት፣ አገው፣ ኦሮሞንም ሆነ ክርስቲያንና ሙስሊሙን ሁሉ እንደ አማራ ሕዝብ እንደሚመለከት ነግሮናል፡፡ በግንቦት ማለቂያ ወይም ሰኔ መጀመርያ ላይ ይመስለኛል፣ የአብን ሊቀ መንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በአማራ ቴሌቪዥን በሰጠው ቃለ መጠይቅ ደግሞ የ‹‹አብን›› ትኩረት አማራ እንደሆነ፣ በአማራነት ጥላ ሥር ሆነው ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ ወንድሞቻቸው ጋር ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንደሚታገሉ ተናግሯል፡፡ የሁለቱን አነጋገር አንድ ላይ ወስደን ስለአማራነት ያላቸውን ግንዛቤ ለመረዳት እንቸገራለን፡፡ በክልሉ ያሉት ማኅበረሰቦች በብዙ ፈርጅ የተወራረሱ እጅግ ዘመዳሞች መሆናቸው አያከራክርም፡፡ ዘመዳምነትና ኅብርነት (ዥንጉርጉርነት) የአካባቢው ኅብረተሰብ ገጽታ ነው፡፡ በመወራረስ ታሪኩ ጥልቀትና ስፋት ላይ በተለይ ጎጃም፣ ወሎ፣ ጎንደር በሚባሉት አካባቢዎች ዘንድ አገውነት የተጫወተው ሚና ከሌላው ሳይልቅ፣ አይቀርምና ዛሬ ‹‹አማራ›› የሚል ስም ለተሰጠው ክልል ‹‹አገዋዊ›› መባል ይበልጥ የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡ አብን ‹‹አማራ›› የተሰኘውን ቃል የሚጠቀመው አካባቢው አማራ ክልል የሚል ስያሜ የተሰጠው ስለሆነ ከሆነና በ‹‹ክልሉ›› ውስጥ ካሉ ማኅበረሰቦች ውስጥ አባላቱን የሚመለምል ከሆነ፣ የተሻለ መጠሪያ እስኪወጣ በአማራ ክልል ስላለ መላ ሕዝብ እያወራ ስለመሆኑ አጥርቶ መናገር ይኖርበታል፡፡ በክልሉ ውስጥ አማርኛ ተናጋሪነት መግዘፉን መሠረት አድርጎና ሌሎቹን ያው የአማራ ያህል ቆጥሮ ከሆነ አማራነትን የሚጠቀምበት፣ ፖለቲካው ችግር ይገጥመዋል፡፡ የአብን የፖለቲካ ትኩረት መላ የክልሉን ሕዝብና ከክልሉ ወጥቶ በተለያየ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተሠራጨውን የሚመመለከት ከሆነ፣ ‹‹አማራ›› በአማራነት ጥላ ሥር የሚል አባባል አደናጋሪ ይሆናል፡፡ ‹‹አብን›› አሁን በተጨባጭ ያለው የአባልነት ጥንቅር የአካባቢውን አገው/ቅማንቴ፣ አማራ፣ ኦሮሞና ትግሬ ሁሉ እስከ አመራር ድረስ ያዘለ ከሆነም፣ ከ‹‹ብሔራዊ›› ንቅናቄ ይልቅ ኅብረ ብሔራዊ ንቅናቄ ነኝ ቢል ይሻለዋል፡፡ ‹‹አብን›› እንብርታዊ ጉዳዬ የሚለው የአማራ ብሔርን ከሆነና አካታችነቱ ከአማራ ብሔር መቆጠር ለወዳደችሁ ሁሉ በራችን ክፍት ነው ከማለት ያላለፈ ከሆነም፣ ይህንኑ ጥርት አድርጎ ማሳወቅ ከመምታት ያድናል፡፡

የ‹‹አብን›› ሊቀመንበር በአማራ ቲቪ ላይ በሰጠው ቃለ መጠይቅ የትግራይ ሕዝብ፣ የአማራ ሕዝብ ወገንና ወንድም መሆኑን አስረግጦ፣ ሕወሓት ግን የአማራ ጠላት/አማራን ሲያጠቃ የኖረ ስለመሆኑና እንዲታገድ ስለመጠየቃቸውም ነግሮናል፡፡ ይህ አቋም ንቅናቄው የግንዛቤ ችግሮች እንዳሉት ይጠቁመናል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ‹‹አማራ›› ለክርስቲያንነት ልዋጭ ስም ሆኖ ሲሠራበት የቆየ ነው፡፡ ከዚያ በስተጀርባ ደግሞ ከአማራ፣ ከትግሬ፣ ከአገው፣ ከኦሮሞ፣ ከጉራጌ፣ ወዘተ ሁሉ የወጣ ዘማችና ሠፋሪም ‹‹አማራ›› ይባል ነበር፡፡ ነፍጠኛ እያዘመተ፣ እያሠፈረ የገባር ሥርዓትን ከጠቅላይነት ጋር ያስፋፋው አፄያዊ ገዥነት የአማራ መንግሥት ይባል ነበር፡፡ አማራ ጠል ስሜት ይህን መሰል ከበደል ጋር የተወራረሰ ታሪካዊ ሥር እንደነበረው አብን አጣርቶ መረዳቱ ያጠራጥራል፡፡ አሉታዊ ስሜቱ ተዘመተብኝ፣ መሬቴን ተነጠቅሁ፣ በነፍጠኛ ባለርስትና መልከኛ ተደቆስኩ ያለ ሕዝብ ውስጥ ሁሉ የገባ ነበር፡፡ ይህንኑ ይዘው ‹‹የአማራ›› ነፍጠኛነትንና ትምክህትን ያባዘቱ ፖለቲከኞችና ቡድኖች ጥቂት አልነበሩም፡፡ ከሕወሓት የበለጠ መራራ ስሜትና በቀል የነበራቸውንም ፖለቲካዎች በቅርብ ታሪካችን ውስጥ ዓይተናል፡፡ ‹‹አብን›› አማራ ጠልነትን ከሕወሓት ጋር አዛምዶ ማየቱ አሳሳች ነው፡፡ ሕወሓትን በማሳገድ የሚገላገለው አድርጎ ከተረዳም የባሰ በስህተት መንጎድ ነው፡፡ በብሔር እየተደራጁ የተዛባ ገዥነት በየአካባቢም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ መትከል እስካልተወገደ ድረስ፣ ከገዥ የብሔር ቡድኖች ወደ ተገዛን ባዮች የሚተላለፍ የጥላቻ ስሜት መፍለቁ አይገታም፡፡ ‹‹አብን›› ይህ ግንዛቤ ያለው ከሆነ በጊዜ ኅብራዊ ሆኖ የጥላቻና የመቃቃር መፍለቂያን ሊዘጋ ለሚችል አዲስ ሥርዓት የሚታገል መሆኑን ሊያሳየን ይገባል፡፡

በኢትዮጵያዊነት መቃን ውስጥ አማራን ነፃ የማውጣት ዓላማ ያለው ‹‹አብን›› ላይ ከነካካናቸው የባሰ የቦዙ ዕይታዎችም አሉበት፡፡ የንቅናቄው ሊቀመንበር ቀደም ብለን በጠቀስነው ቃለ መጠይቅ እንደነገረን፣ ከአማራ ክልል ባሻገር በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ያለ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአማራ ድጋፍን መሠረት አድርጎ በአገር አቀፍ ፓርላማ ውስጥ አብላጫ ወንበር የማግኘት፣ ያ ቢጎድል በጥምረት የቁጥር ብልጫን አረጋግጦ መንግሥት የመሆን ዕቅድም አለው፡፡ የኢትዮጵያንም የራሱንም ድርጅታዊ እውነታ በቅጡ ያለመገንዘቡ ምርጥ ማሳያ ይህ ሥሌቱ ነው፡፡ ‹‹አብን›› በፓርላማ ውስጥ ብልጫ ቁጥር ቢያገኝ በአማራነት ተለይቶ የተደራጀ ቡድን ብሔረ ብዙ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ሞራላዊ ሥልጣን እንደምን ሊኖረው ይችላል!? በብሔር ተለይቶ የተደራጀ ቡድንን ያለ አድልኦ ያስተዳድራል ብለን እንደምን ልናምን? ከሰማይ የተቀባ ስለሆነ? ለዚህ ነው ‹‹አብን›› በፓርላማ ውስጥ አብላጫ ቁጥር ተቆጣጠረ ማለት የኢትዮጵያ መበታተን የሚሆነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ሰምሮ መቀጠልም ሆነ የአማራ ‹‹ነፃ መውጣት›› ከዚህ ዓይነት ሥሌት ውጪ እንደሆነ ያልገባው ፖለቲካ ከጮርቃነት የተሻለ ስም የሚገኝለት አይመስለኝም፡፡

በሰላማዊ መንገድ እስከ መነጠል ድረስ ሊሄድ የሚችል ትግል አደርጋለሁ ስለማለቱ፣ በርቀት የሰማንለት ‹‹ሳልሳዊ ወያነ››ነትም ሰኔ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በናሁ ቲቪ ሁለት የቡድኑ ሰዎች በሰጡት ቃለ መጠይቅ አማካይነት፣ የትግራይ ክልል ወሰን የማይነካካ እንዲሆን፣ ፍርጥ ባለ አነጋገር አገራዊ ድንበር እንዲሆን የሚታገል መሆኑን ነግሮናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰላምና ህልውና አስተማማኝነት በቀጣናዊና በአኅጉራዊ ተዛምዶ ውስጥ መታቀፍንና በዚያ ውስጥ ሆኖ በጠንካራ አገርነትና በግስጋሴ እንብርትነት የዙሪያቸው ሙጫ በመሆን አለመሆን የሚወሰን መሆኑን አለመገንዘብ፣ እናም ከ2008 ዓ.ም. አንስቶ የደመቁ ብሔር ጠቀስ ጥቃቶችንንና መፈናቀሎችን በትግራዊ ላይ ብቻ የወረዱ እያስመሰሉና የእነ ጄኔራል ክንፈን በካቴና ታስሮ በቲቪ መታየትን የትግራይ ጥቃት አድርጎ እያራገቡ አገርን ወደ ቁርጥራጭነት የመቀየር ፊት መሪ መሆን ሌላ በጮርቃነት የመግለብለብ መገለጫ ነው፡፡

የክርክሬን ውሎች በአጭሩ ባስቀምጣቸው፣ አሁን ያለው አንጓላይ አወቃቀርም ሆነ የብሔር ፓርቲ እንጓላይ ምልመላና ገዥነት እስከቀጠለ ድረስ፣ ብሔረሰቦችና ዜጎች በአንድ ጊዜ ለአንጓላይነት ለተንጓላይነትም ድጥ ይጋለጣሉ፣

የመሬት ቅርጫ ባለቤትነትን ለማስተማመን ሲባል የ‹‹ክልል›› ኅብረተሰብን በአንድ ብሔር ቀለም የማቅለም ጥረት አይመክንም፡፡ በዚህ ድርጊትም የቁርጥራጭ ብሔረሰቦች መዳመጥ ይኖራል፣

የመሬት ስስት በሚያነሳሳው ፍትጊያና ግጭት የተጎራባች ሕዝቦች ሰላምና ኑሮ መረበሹ በአግባቡ አይደርቅም፣

መማረርና ስስት የያዝኩትን ሳላስነጥቅ በምን ላምልጥ እስከ ማለት ድረስ ሊሄድና የትልቅ ቀውስ በር ከፋች ሊሆን ይችላል፡፡

በየአካባቢው አንጓላይ ገዥ ሆኖ ያለ ወይም ለአንጓላይ ገዥነት የሚፎካከር ብሔረተኛ ፓርቲ እዚያ ማዶ ክልልና ወዲህ ማዶ ክልል ውስጥ ያሉ የብሔረሰብ ወገኖቹን በአባልነት ስለመለመለና ተበደሉ ብሎ ስለጮኸ የሚያመጣው ውጤት የለም፡፡ ሌላው ክልል ውስጥ ያለው ማጥ እሱም ቤት ስላለ፡፡

በዚህ ማጠቃለያ የማይስማሙ የሕገ መንግሥቱና የአወቃቀሩ አምላኪዎች፣ የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ሕገ መንግሥታዊ ግንኙነቶች በደንብ ከተረጋገጡና ዴሞክራሲ ከተቋቋመ ዛሬ የሚታዩት ጣጣዎች ሁሉ ይቃለላሉ፣ ችግሮቹን ያመጣቸው አሀዳዊ ገዥነትና ዴሞክራሲ አልባነት ነው ይሉናል፡፡ የአገሩ ባለቤትነትና ገዥነት የዚህ ብሔር/ብሔረሰቦች ነው ከሚል (ቤተኛ የሆነና ያልሆነ አድርጎ ከሚለይ) ግንኙነት እንዴት ነው ዴሞክራሲያዊ እኩልነት ሊፈልቅ የሚችለው? ወሳኙ እንቆቅልሽ እዚህ ላይ ነው፡፡ እንቆቅልሹም በአንድ ቅፅበት እየከለከሉ ለመስጠት እንደ መሞከር ያለ ነው፡፡

እንቆቅልሹን ሳንረሳ የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ተፈጥሮ መፈናቀል ተገታ፣ ቤት ንብረት የማፍራትና ተዘዋውሮ የመሥራት መብትም በመንግሥት የሚጠበቅ፣ ቢጣስ የሚያስጠይቅ ሆነ እንበል፡፡ ይህ ስለሆነ ግን ቢጤና ባይተዋር አድርጎ የሚያንጓልል (የሚጨቁን) ግንኙነት ይወገዳል?

መናጢ ወላጆች ያለ የሌለ ገንዘባቸውን ከስክሰው ልጃቸው ደህና ትምህርት እንዲያገኝ ባለፀጎች የተከማቹበት ትምህርት ቤት ቢያስገቡት መደባዊ አየሩ (በጨዋታ፣ በወሬ የሚራጨው ኑሮና ምኞት ሁሉ) ያንን ወጣት ያንጓልለዋል፡፡ እዚያ ውስጥ የገባው ወጣት ከልብስ አንስቶ ለማስመሰል እየሞከረ የእነሱ ዓይነት አኗኗር እሱም ቤት ውስጥ እንዳለ አድርጎ እየዋሸ የመኖር፣ ወይም ተሸማቆ የመገለል ፈተና ውስጥ ይወድቃል፡፡ በፈረንጆቹ አገሮችም በአፍሪካም ውስጥ ‹‹ጥቁርነት ውበት ነው፣ … በጥቁርነታችን አንፈር…፣ ጥቁርነታችንን ለመካድ አንሞክር…›› ይባላል፣ ግን ዓለማችን የነጭ የበላይነት ዓለም ነውና የሥልጣኔና የውበት መለኪያው ከነጮቹ ጋር የተያያዘ ነውና ነጭ ለመምሰል መሞከር ዛሬም ድረስ ያልተወጡት ፈተና ነው፡፡ አማርኛ ብቸኛ የአገሪቱ መታወቂያና ይፋዊ ሥራ ማካሄጃ ቋንቋ በነበረት ዘመን አማርኛን በደንብ ያልቻለን ሰው ሸርድዱ/እንደ አላዋቂ ቁጠሩ የሚል አዋጅ አልነበረም፡፡ የባህልና የቋንቋ እኩልነት መጓደል ራሱ ግን በማንነት ማፈርንና በማላገጥ የሚገለጽ ጭቆናን ያመነጭ ነበርና በዚያ ምክንያት ማንነትን መሸሽና ሌላውን መምሰል መከተሉ አይቀሬ ነበር፡፡ የዛሬው ብሔርተኛ ተንጓላይነት እልሁንና ውርጭቱን ሲጨርስ (መንጓለል የተለመደ መደበኛ እውነታ ሲሆን) ቤተኛ ለመሆን ብሔረሰባዊ ቋንቋን ወደ መተው ብቻ ሳይሆን፣ ብሔረሰባዊ ምንጭን የሚጠቁም ባህልንና ስምን እየጣሉ ‹‹የባለቤት›› ብሔረሰባዊ ማንነትን ወደ መምስል መውሰዱ አይቀርም፡፡ ሒደቱም የተጀመረ ይመስለኛል፡፡

ከዚያ አቅጣጫ መለስ እንበልና ጥያቄ እናንሳ፡፡ ለመሆኑ የዚህ አካባቢ ባለቤት ይኼ ብሔር ነው ብሎ ማወጅና በዚያ ብሔር በተውጣጣ የብሔር ፓርቲ የአካባቢ ኅብረተሰብን መግዛት ውስጥ ለምን ተገባ? የሚገዙ የብሔር ፓርቲዎች (አንድ ግንባር ነን የሚሉ ጭምር) ለምን በየክልሉ ያሉ የብሔር ቢጤዎቻቸውን የእኔ እያሉ በየፊና መመልመል አስፈለጋቸው? ክልሎች ዕጩ አገሮች ስለሆኑ ከወዲሁ ዜጎቻቸውን ለማወቅ እንዲችሉ? ወይስ ብሔረሰባዊ ማንነት ሊደባበቅ የማይችል ጥሬ ሀቅ ስለሆነ እንጂ፣ ዜጋ ለማንጓለል ተብሎ አይደለም ይባልን ይሆን?

ብሔርተኛ ፖለቲካ የፈጠረውን ወለፈንድ ለማየት እንድንችል ዛሬ ያሉ ክልሎችን ራሳቸውን የቻሉ አገሮች የሆኑ አድርገን በማሰብ እንመልከታቸው፡፡ በነሲብ ምሳሌነት ኦሮሚያን እንውሰድና ‹‹ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች›› ከሚል አዋጅ ጋር፣ ኦሮሞዎችን ብቻ በሚያሰባስብ ፓርቲ የመንግሥት መሪነት ቀጠለ እንበል፡፡ ከኦሮሞነት ውጪ የሆኑ በኦሮሚያ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችንና አባላትን ሥርዓቱ ምን ያደርጋቸዋል? የእኔ ዜጎች አይደሉም ብሎ ወደ ብሔር አገራቸው እየጠረዘ ይሰዳቸዋል? ከዚሁ ጎን ለጎን በየክልሉ የኦሮሞ ፓርቲ አባል እያደረገ ይመዘግባቸው የነበሩ ኦሮሞዎችን፣ አገሮች ቢሆኑ ካልናቸው ‹‹ክልሎች›› እየጠራ ወደ ኦሮሚያ ያሰባስባል? በ21ኛ ክፍለ ዘመን እነዚህ ሲፈጸሙ ዓለም ቢያይ ጉድ ዓየሁ ሳይል አይቀርም፡፡ ጤና በሆነ የፖለቲካ ዓይን አገሩ የኦሮሞ ነው ማለትም ኦሮሞን ብቻ ለይቶ በሚያደራጅ ፓርቲ መግዛትም አላስፈላጊና ትርጉመ ቢስ ነው፡፡ ይኼ ዓይነቱ አካሄድ የጤናም አይደለም፡፡ ጥሬ ሀቁ በኦሮሚያ ውስጥ ኦሮሞ ብዙኃን መሆኑ ነው፡፡ ይህ ጥሬ ሀቅ የኦሮሞን የብዙኃን (ራስ በራስ) አስተዳደርን ለማረጋገጥ፣ የአገሩን የኦሮሞ መሆንንና ኦሮሞ ያልሆኑን ያገለለ ፓርቲ ማቋቋምን አይሻም፡፡ ኦሮሞ ያልሆኑ ወገኖችንም የኦሮሚያ ልጆች (እኩል ዜጎች) አድርጎ በብሔር ማንጓለልን ቢሰርዝ፣ ‹‹የኦሮሞ›› የሚል ቅጥያ እንኳ በሌለባቸው ፓርቲዎች የሚሠራና ለየትኛው የሥልጣን ደረጃ ብሔረሰባዊ ገደብ የማያደርግ የፖለቲካ ሥርዓት ቢዘረጋ፣ ተንጓለልኩ ባይ ስሜት ከሌለበት ብሔረሰባዊ መጣጣም ጋር የኦሮሞ ብዙኃናዊ አስተዳዳሪነት ደምቆና አምሮ ይወጣል እንጂ አይደበዝዝም፡፡ ክልሎችን አገሮች ቢሆኑ በሚል ሐሳባዊ ሁኔታ ውስጥ ኅብረተሰብን ባለቤትና ባይተዋር አድርጎ መለየትና ብሔር በለየ ፓርቲ መግዛት ጤናማ አለመሆኑ ከተጤነ፣ ያንጓለሉትን የኅብረተሰብ ክፍል አገርህን ፈልግ ቢሉ፣ ዜግነት ቢነፍጉና በፊት በክልልነት ጊዜ ወገኔ እያሉ በየፓርቲ ይመለምሉት የነበርን የብሔር ወገን ከክልልነት ወደ አገርነት ከተሸጋገሩ ሥፍራዎች እንለቀም ቢሉ፣ የጤና ማጣት ያህል ሥራ መሆኑን ማየት ይከብደናል? ይህንን ማድረግ ኬንያ ላለ ኦሮሞ የዜግነት መታወቂያ ልስጥ ከማለት ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡ የዚህን ወለፈንድነት መረዳት ከቻልን፣ በአንድ ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ አገር ልጅነት፣ ታሪካዊ ዝምድናና ማኅበራዊ ትስስር ባልፈራረሰበት ሁኔታ ውስጥ ይህንን መሰል አድራጎት መፈተም የበለጠ ጤና ማጣት እንደሆነ ሊጤነን ይገባል፡፡

ብሔር ለይቶ የተደራጀ ፓርቲ የብሔር ቤቴ ባለው ክልል ውስጥ ገዥ ቢሆን፣ አውቆም ሳያውቅም የመንጓለል አየር ንብረትን የማያስቀር ከሆነ፣ ሳት ብሎት ንቁ አንጓላይነት ውስጥ ከተነከረም፣ በሌላ ክልል ባሉ የብሔር ቢጤዎቹ ላይ የበቀል መነሳሻ የሚሆን ከሆነ፣ ከክልል ቤቱ ተሻግሮ በሌላ ክልል ውስጥ ያሉ የብሔር ‹‹ዘመዶቹ››ን በፓርቲ ማሰባሰብም መንጓለልን ለማስቀረት ዋስትና ካልሆነ፣ በሥራ ላይ የመቀጠሉ ዕርባና ምንድነው ብለን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ የትኛውም የኢትዮጵያ ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም አካባቢ የአካባቢ ልጅነት፣ ስሜትና ግንኙነት መነፈግ አይኖርበትም፡፡ አንድ ኩባንያ በፖለቲካ አቋም ወይም በሃይማኖት/በብሔር መርጦ ሠራተኛ ቢያሰባሰብ ሊጠየቅ እንደሚገባ ሁሉ፣ በብሔር ለይቶ የሚያደራጅ ፓርቲም እንዲገዛ መፍቀድ ፍትሐዊ አይሆንም፡፡

በየክልሉ ያለ ኅብረ ብሔራዊ ጥንቅር ብዙኃኑም ንዑሳኑም በየአካባቢው እኩል ቤተኛ ተደርጎ ከታየ፣ አካባቢያዊ መንግሥታት የየአካባቢ ኅብረተሰባቸውን በአንድ ዓይን ካዩ፣ ፓርቲዎችም በብሔር የማይንጓልሉ ከሆኑ መጀመርያ ላይ አንስተነው የነበረው እንቆቅልሽ ይፈታል፡፡ አንጓላይ ሁኔታ ቢኖርም ‹‹አላንጓልልም››፣ ‹‹ፓርቲዬ ብሔር መርጦ የተሰባሰበ ቢሆንም፣ በእኩልነት ያስተዳድራል›› ባይ ግጭት ይቃለላል፡፡ በሁሉም ክልሎች የሁሉም ብሔረሰቦች መብትና እኩልነት በዴሞክራሲ የመረጋገጥ ተስማሚ ሁኔታ ያገኛል፡፡ በኅብረ ብሔራዊ የብዙኃን አስተዳደር ውስጥ ሴመኛ ማኅበረሰቦች የራስ በራስ አስተዳደር ሊስተናገድ ይችላል፡፡ በሆነ አካባቢ የበለጠ ታሪካዊ ነባርነት ያላቸው ማኅበረሰቦች ንዑሳን ቢሆኑም እንኳ፣ በብዙኃን ዴሞክራሲ ውስጥ የእነሱን ታሪካዊ ልዩ ሥፍራ ማስተናገድ ይቻላል፡፡ ባይተዋር ብሎ ማፈናቀል ይቅርና የማዳላት ሥራን እንኳ አጋልጦና ከሶ መብት ማስከበር የሚቻልበት ሁኔታ በሁሉም አካባቢ ይለማል፣ ያድጋል፡፡ ለምን ቢባል በየአካባቢው የሚኖር ሰው እንደ ወንዝ ልጅ ራሱን ለማየትና ለመላላስ ዕድል ስላለው፡፡ ዕድሉን የሚነፍገውና በመጤነት ማራቅን ተገቢ የሚያደርግና የሚኮተኩት የፓርቲ ፖለቲካና መዋቅር ስላልተሾመ፣ ማለትም በብዝኃነት የተገነባ አካባቢያዊና አገር አቀፋዊ ፓርቲነት ከዴሞክራሲ ጋር ሲገናኝ የብሔረሰቦች እኩልነትን ያለንቁሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ይመቻል፡፡

‹‹የቡድን መብት ከተከበረ የግል መብት ይከበራል››?

‹‹የግል መብት ከተረጋገጠ የቡድን መብት ይከበራል››? የቡድንና የግል መብት ተገናዛቢና ተዛማጅ ናቸው፡፡ ስለግል መብት ስናወራ ስለተጨባጭ ግለሰቦች ሳይሆን፣ ስለረቂቅ ግለሰቦች (ወላዊ ግለሰብነት) ነው የምናወራው፡፡ ስለተጨባጭ ግለሰብ መብት ብናወራ ስለአንዳንድ አካላዊ ሰዎች፣ ስለአየለ፣ ስለአልማዝ፣ ወዘተ ይሆናል፡፡ ስለሴቶች መብት ስናወራ በጥቅሉ በሴትነት ስለተገኘ ግን በተጨባጭ ሴቶች ላይ ተግባራዊነቱን ስለሚያሳይ መብት መናገራችን ነው፡፡ ስለሰብዓዊ መብትና ስለዜጎች መብት ስናወራም፣ በሰውነትና በዜግነት ስለምንጋራቸውና በእያንዳንድነታችን ልናገኛቸው ስለሚገቡ መብቶች መናገራችን ነው፡፡ በሌላ አባባል የግል የምንላቸው መብቶች ተጨባጭ ግሰለብነትን እንደሚጠቅሱ ሁሉ ቡድናዊ ገጽታም አለባቸው፡፡ ስለቡድን ስናወራም በጋራ ማኅበራዊ ክሮች ስለተያያዙ ግለሰቦች ማውራታችን ነው፡፡ እንደ ትኩረት አመራረጣችን ስለቡድኑ አባላት ወይም ቡድን ለመሰኘት ስላበቃቸው የጋራ ትስስር ልናወራ እንችላለን፡፡

የግል መብቶች ካልተገሩ ወይም ልክ ካልተበጀላቸው ማኅበራዊ ጉዳት እስከ ማድረስ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ የመናገር ነፃነት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ኅብረተሰብ እግዜር የለም እያሉ እስከ መጻፍ ቢሄድ፣ ማኅበራዊ  ሰላምን እስከ ማፋለስ ድረስ ውጤት ሊኖረው ይችላል፡፡ መሬትን መሸጥ ሕጋዊ መብት በሆነበት ሁኔታ ውስጥ መሬት በማግበሰብስ መልክ የሚካሄድ ንብረት የማካባት መብት ልክ ካልተበጀለት፣ ማኅበራዊ ህልውናን እስከ መቦርቦርና እስከ መንፈግ ሊሄድ ይችላል፡፡

በምዕራብ ዴሞክራሲ ውስጥ ለሁሉም ግለሰብ ክፍት የሆኑ የግል መብቶች አሉ ማለት ይቻላል፡፡ አውስትራሊያ ውስጥ አቦሪጅኖችን ለይቶ ከመማር፣ ከማደግና ንብረት ከማፍራት የሚገድብ ሕግ የለም ሊባል ቢችልም ሱሰኝነት፣ የኑሮ ድቀትና ድንቁርና ዑደታዊ ሆኖ አቦሪጅኖችን እየበላቸው ይገኛል፡፡ የእነሱ ከአማቃቂ ኑሮ የመውጣት ጉዳይ ማኅበራዊ መላ (ልዩ እንክብካቤ) ይሻል፡፡ አሜሪካ ውስጥ ዘረኛ ጥቃት ማድረስ መብት አይደለም፡፡ ማስረጃ ተገኝቶ ከተፈረደበት በሕግ ይቀጣል፡፡ ያም ሆኖ ዘረኝነት በአሜሪካ ውስጥ ተግባራዊ ሕይወት አለው፡፡ በዘረኝነት፣ በኑሮ ድቀት፣ በቤተሰብ መናጋትና በሱሰኝነት ወፍጮ ውስጥ የወደቀው የአሜሪካ ጥቁሮች ሕይወት ከግል መብት ባሻገር ልዩ ማኅበራዊ መብት (መፍትሔ) የሚሻ ነው፡፡ በአሜሪካ ውስጥ የወሲብ ጥቃት ደረሰብኝ የሚል የሴት ልጅ አቤቱታ በሕግ ጥበቃን የሚሻ ነው፡፡ እንዲሁም የሴቶች መደፈር በሕግ ፊት ጠንካራ ተሰሚነት አለው፡፡ የዚህም ዓላማ ሴቶችን ከጥቃት መጠበቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ወንዶችን እንደ ወሲብ ኮርማ የሚያማልልና የሴቶችን የወሲብ መገልገያነት የሚያባዛ የወሲብ ንግድ (በዘፈን፣ በፊልም፣ በኢንተርኔት፣ በራቁት ዳንስ ቤት፣ ወዘተ) እንደ ልቡ ማኅበራዊ ጥቃት እንዲያደርስ ተፈቅዶለት እናያለን፡፡ ታዳጊዎችን በተመለከተም ጨምላቃ ባህል ማኅበራዊ ጥቃት እንዲያደርስ (እንዲያላሽቅ) ፈቅዶ፣ በግል ደረጃ ጥቃት እንዳይደርስና ጥቃት ሲደርስ ለመቅጣት የመሞከር ቅራኔን እናገኛለን፡፡

የግል መብትን በተግባር የመተንፈስ ዕድል ከቡድን ህልውና ጋር የተሳሰረ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ አምስት ኦሮሞዎች መቀሌ ነዋሪ ቢሆኑ እንደ ማንኛውም ዜጋ ታክስ ከፋዮች ነንና ልጆቻችን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር መብት ስላላቸው ትምህርት ቤት ይከፈትላቸው ቢሉ፣ ጥያቄያቸው ተግባራዊ መሆን አይችልም፡፡ የዚያ ዓይነት ጥያቄ ተሰሚነት የግድ ትርጉም ካለው ማኅበረሰባዊ ክምችት ጋር የሚገናዘብ ነው፡፡ ይህ ይደረግልኝ ብሎ መንግሥትን ግድ መጠየቅ የማያሻቸው ቋንቋንም ሆነ ባህልን የማበልፀግ እንቅስቃሴዎች፣ በሆነ አካባቢ በቡድን መገኘትን ወይም በተለያየ ሥፍራ ሆኖ በተለያዩ የመስተጋብርና የመደራጃት ዘዴዎች ሕይወት መፍጠርን ይሻሉ፡፡ የቋንቋና የሥነ ጽሑፍ ሕይወት በአንድ ጊዜ ቡድናዊም ግለሰባዊም ነው ማለታችን ነው፡፡

የቡድን መብት ከግል መብት ጋር እንዲመጋገብ ተደርጎ በዴሞክራሲ ካልተዋቀረ ማኅበራዊም፣ ግለሰባዊም የአፋኝነት ባህርይ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ለአካባቢ የራስ በራስ አስተዳደር መነሳሻው እንቶኔ የሚባል ብሔረሰብ ክምችት ሊሆን ይችላል፡፡ የራስ በራስ አስተዳዳሩ ግን ብሔር አይለይም፣ ወይም የእንቶኔ ብሔር አባላት ንብረት አይሆንም፡፡ የአካባቢውን መላ ኅብረተሰብ የሚመለከት ነው፡፡ በብሔረሰብ ማንነት ለማንጓለል/ለማበጠር መሞከር፣ ወይም የመመረጥና ሥልጣን ላይ የመውጣት ዕድልን ከብሔር ማንነት ጋር ማጣበቅ በምንም መመዘኛ መብት ከማረጋገጥ ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው ሥራ ዝምድናው ከጭቆና ጋር ነው፡፡ በማኅበራዊ  መጣጣም ፈንታ ቅሬታ፣ ቅራኔና መሸካከር የሚያራባውም ለዚህ ነው፡፡

ቀደም ሲል ለማሳየት እንደተሞከረው፣ የተወሰነ አካባቢ ማኅበረሰቦችን  በተመለከተ ባለቤትና መጤ ብሎ መለየትና በባለቤት ነን ባይነት አገዛዝን መቆጣጠር፣ በቀጥታ እኩል ዜግነትን ይተናኮላል፡፡ የዜግነት እኩልነትን በመተናኮል የጀመረ የመብት ጥሰት ባለቤት በሚባለው ብሔር ውስጥም የግል መብትን እስከ መጉዳት ድረስ ጥፍሩ መርዘሙ አይቀርም፡፡ በብሔሩ ውስጥ የተገኙ ንዑስ ቡድኖችን በቡድንም በግልም መብትን ሊደፈጥጥ እንደሚችል ሁሉ፣ የገዛ ብሔሩን አባላት ቡድናዊና ግላዊ መብቶች በሌላ ቦታ እንዲረገጥ ይዳርጋል፡፡ በሌላ አነጋገር ይህን ዓይነት ኢዴሞክራሲያዊ ግንኙነት ደርቶ በቀጠለበት ሥፍራ ዴሞክራሲ ራሱ ስለመሰለቡ አያጠራጥርም፡፡ ይህንን የመሰለ እኩልነት አልባ ግንኙነትን የፈቀደ ‹‹ዴሞክራሲ››ም፣ በዴሞክራሲ አልባነት ተበልቶ የመጥፋት መንገድን ገና ከመነሻው ጀምሯል ማለት ነው፡፡

የተግባቡ የቡድንና የግለሰብ መብቶች መሠረታዊ መብቶች ናቸው፡፡ እነዚህን መብቶች የመቀዳጀት ነገር መብቶቹን የሚንከባከብና የተለመዱ የኑሮ ሁኔታዎች የሚያደርግ ሥርዓት የማደራጀት ጉዳይ ነው፡፡ መብቶቹ የሥርዓተ መንግሥት ጥበቃና እንክብካቤ ካገኙና የኅብረተሰብ ኑሮ ከሆኑ ምንም ዓይነት የፓርቲ አስተዳዳሪነት ቢቀያየር፣ የአገርን ድንበር እንደማስጠበቅና የሕዝብ ጤናን እንደ መንከባከብ ኃላፊነት የእዚህን መብቶች ሕይወት ማስቀጠል መደበኛ ግዴታው ነው፡፡ ግለሰብ፣ ሹም፣ ቡድን፣ መንግሥት (የፌዴራል/የክልል) በእነዚህ መብቶች ላይ ጥሰትና ጉዳት ቢፈጽሙ ሥርዓተ ማኅበሩ አጋልጦ ያርማቸዋል፣ ይቀጣቸዋል፡፡ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሕዝብ፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የመብት ተከራካሪ ተቋማት፣ መብቶችን መንከባከብና ማስከበር ሥራቸው የሆኑ አገረ መንግሥታዊ አካላት ሁሉ አሉበት፡፡

መብቶችን የማስከበርና የመንከባከብ ሥልቶች ውስጥ ከጊዜ ጊዜ ክፍተት ሊታይ ይችላል፡፡ እነዚያን ክፍተቶች ከመንግሥት ይልቅ ግለሰቦች፣ የመብት ተከራካሪዎች፣ ወይም ፓርቲዎች ሊያዩ ይችሉ ይሆናል፡፡ ወይም በጊዜ ሒደት አዳዲስ የመብት ጥያቄዎች (የቡድን/የግል) ሁሉ ብቅ ሊሉ ይችላሉ፡፡ የትኞቹም ጥያቄዎች ትግል ተደርጎባቸውና ድጋፋቸውን አባዝተው ተቀባይነት ሲያገኙ፣ በማኅበራዊ ሥርዓቱ ውስጥ እንዲካተቱ ይደረጋሉ፡፡ እናም መደበኛ የኑሮ ዘይቤ ወደ መሆን ይሸጋገራሉ፡፡

በዚህ አኳኋን የማኅበራዊ ሥርዓቱ አካል የሆኑና ሥርዓቱ የሚንከባከባቸው መብቶች አላዛኝ አይሹም፡፡ በሌላ አባባል የቡድን መብቶች፣ የዜግነት መብቶች፣ ሰብዓዊ መብቶች የኅብረተሰብ ኑሮ አካል እንዲሆኑ የሚያሻቸው እነሱን ኃላፊነቱ አድርጎ የሚያስተናግድ ሥርዓተ መንግሥትን ማደራጀትና የዴሞክራሲ ባህልን መገንባት ነው፡፡ ይህ ሥራ እንደማይቀለበስ ሆኖ ከአነሳሱ ከተዋጣ ሥርዓቱ  ራሱ ዕንከኖቹን እየነቀሰ ወደ ፊት መራመድ ይችላል፡፡ የእነዚህ መብቶች መከበርና መቀጠል፣ ‹‹ለብሔር መብት የቆምኩ ነኝ፤››፣ ‹‹ለዜግነት/ለሰብዓዊ መብቶች የቆምኩ ነኝ፤›› የሚሉ ፓርቲያዊ ጩኸትንና ጠባቂነትን ወይም ለእነሱ የቆምን ባይ ፓርቲዎችን በተከታታይ ሥልጣን ላይ መውጣትን አይፈልግም ማለታችን ነው፡፡ የእነዚህ መብቶች ተከባሪነት ከፓርቲና ከመስተዳደር አልፎ የዘለቀ፣ የአገረ መንግሥት መደበኛ ሥራና የኅብረተሰብ እስትንፋስ እንዲሆን ተደርጓል እንደ ማለት ነው፡፡

ብሔርን መውደድ፣ ማድነቅ፣ በብሔር ማንነት መኩራት መብት ነው፡፡ እሰየው ነው፡፡ አገርን መውደድ፣ አገርን ማድነቅና በኢትዮጵያዊነት መኩራት መብት ነው፡፡ እሰየው ነው፡፡ የሁለቱን ተመጋጋቢነት ለማየት አለመቻል ወይም ሁለቱን ተቀናቃኞች አድርጎ መረዳትና የብሔር ተቆርቋሪነትንና የአገር ተቆርቋሪነትን ጎራ የለየ ፓርቲያዊ ቅርፅ ሰጥቶ መላፋት ቦዞ ማቦዝ ነው፡፡ የትውልድ ሥፍራን፣ ብሔረሰብን፣ አገርን፣ ጥቁርነትን፣ አፍሪካዊነትን መውደድና ማክበር ገጽታችንን መንከባከብ ነው፡፡ ይህ የሁላችንም ግለሰባዊና ቡድናዊ ግዴታችን ነው፡፡ የፓርቲ ሥራና ኃላፊነት መደበኛ ግዴታ የሆኑ መብቶችን መታወቂያ ካርድ ማድረግ/ማናፈስ ሳይሆን ዓለማዊ፣ አኅጉራዊ ክፍለ አኅጉራዊ አዝማሚያዎችን ነቅቶ መከታተል፣ በውጪያዊና ውስጣዊ ሰበዞች መስተጋብር የሚመጡ/ሊመጡ የሚችሉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጉዳይ ፈተናዎችን እያዩ ማሳየትና ፈተናዎቹን ለመወጣት የሚያስችሉ መላዎችን መቀመር ነው፡፡

የግለሰቦች ፈጠራ የቡድን ሀብትን፣ ታሪክን፣ ቋንቋንና ሥነ ጽሑፍን ያበለፅጋል፣ ይቃኛል፡፡ ዛሬ በባህል አልባሳት፣ በሙዚቃ፣ በሥነ ጽሑፍና በቋንቋ ብልፅግናና ሕይወት ውስጥ ግለሰቦች ምን ያህል አሻራ እያሳረፉ እንደሆነ ለመረዳት የአገራችን እውነታ ያስችላል፡፡ የ‹‹ሀ›› ማኅበረሰብ ሀብት የተባለ ነገር ህልውናው በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ ተወስኖም አይቀርም፡፡ በኅብረተሰብ ተራክቦ ውስጥ የማኅበረሰቦች የባህል ሀብት ከአንዱ ወደ ሌላው ይዛመታል፡፡ መስተጋብራቸው የጋራ ታሪክና ማንነት እያበጀ ይሄዳል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የማንነት፣ የባህልና የታሪክ መወራረስ በአንድ አገር ውስጥ ያለ ብዝኃነት የመላ ሕዝቡ ነው ከሚል አገላለጽ በላይ የጠለቀ ነው፡፡ ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ባህልን፣ አለባበስንና ቋንቋዎችን የዚህ የዚህ ብሔረሰብ ብሎ መለያየት ከባድ ነው፡፡ በሥነ ልቦና ያለው መወራረስም የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት የሚፈጥረውን ልዩነት ጥሶ ያለፈ ነው፡፡ የእንሰት ባህልን በሚጋሩ አካባቢዎች፣ በመሀል ኢትዮጵያ፣ በሰሜን ምሥራቅ፣ በሰሜን፣ በምዕራብ ግድም ስላለ መወራረስም እንደዚያው ማውራት ይቻላል፡፡ ከአካባቢያዊ ምንጫቸው አልፈው የመላ ኢትዮጵያ የሆኑና እየሆኑ ያሉ ሀብቶችም ብዙ ናቸው፡፡ ጥሬ ሥጋ መመገብ፣ ክትፎ፣ ጭኮ፣ በሶ፣ ቆጮ፣ አብሽ ወጥ፣ እንጀራና ወጥ፣ አምባሻ፣ ድፎ ዳቦ፣ ሳምቡሳ፣ አንጮቴ፣ ዳጣ፣ ቆጭቆጫ፣ ጥህሎ፣ ወዘተ፡፡ ሰፊ ተለማጅነት እያገኘ ያለው የምግብ ዝርዝር ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ሙዚቃዎችና ውዝዋዜዎች ከመላ ኅብረተሰብ ሀብትነት ባሻገር የእያንዳንዱ ዜጋ መቀረጫ ሆነዋል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ባለ ኅብር ባህል እየሆነ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእዚህ ላይ ደግሞ በተለያየ መልክ ከውጪ የሚቀዳው ባህልና አስተሳሰብ ሙዚቃና ውዝዋዜም ተደርቦ ይገኛል፡፡ ፈንረንጆቹ ከየትም ቦታ ለንግድና ለባህላቸው ብልፅግና የሚሆን ቅርስ አስሶ መውሰድ ያውቁበታልና ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚሻገርም አለ፡፡ አመጋገባችን፣ ሙዚቃችን፣ አልባሳታችን የፈረንጅ ቀልብ ውስጥ ከገባ ሰነባብቷል፡፡

እዚህ ላይ በ‹‹አርትስ›› ቲቪ ሰኔ መጀመርያ (2011 ዓ.ም.) ውስጥ ታሪኩን ሲያወሳ ስለሰማሁት አንድ ኖርዌጂያዊ ፈረንጅ ለማንሳት እወዳለሁ፡፡ አባትና እናቱ ከአዲቬንቲስት ሚሲዮን ጋር ወደ ኢትዮጵያ ደብረ ታቦር ገብተው በዚያ ብዙ ቆይተዋል፡፡ አባቱ የሕክምና ባለሙያ ነበር፡፡ የማወሳው ፈረንጅ የተወለደው እዚያው ነው፡፡ ከደብረ ታቦር ኩታሮች ጋር እየተራገጠ፣ አህያ እየጋለበና እየተደባደበ ያደገ ነው፡፡ የሳማ ግርፊያንም ቀምሷል፡፡ ለእንጀራና ለበርበሬ ወጥ ያለው ፍቅርም ልዩ ነው፡፡ አትብላ ሆድህን ያምሃል ቢባልም ተደብቆ ከባልጀሮቹ ጋር ይበላና ጥጋቡን በጨዋታ አቅልሎ፣ ከቤተሰቡ ጋር እንደ አዲስ ገበታ ይቀርብ እንደነበር ተርኮልናል፡፡ በእናቱ አማካይነት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን ተምሮ ወደ ኖርዌይ ለተከታይ ትምህርት ሲላክም የባህልና የአስተሳሰብ ግጭት ደርሶበት ሁለቴ በመንፈስ መታወክ ተቸግሮ እንደነበር፣ ናፍቆቱ ሁሉ ከደብረ ታቦርና እዚያ ካሉት ወላጆቹ ጋር እንደነበር አውስቶናል፡፡ ኖርዌይ ገብቶ ተምሮ የሕክምና ባለሙያ ሆኖም፣ ጎልምሶም ከኢትዮጵያ ባልንጀሮቹና ካደገበት ጎንደሬነት ጋር አልተለያየም፡፡ ድርቆሽ፣ እንጀራና በርበሬ ያስልክ ነበር፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ደብረ ታቦር ተመልሶ የጎብኚ ማረፊያ (‹‹ሎጅ››) እና ትምህርት ቤት እያስገነባ ነው፡፡ ከሀብታሟ ኖርዌይ በጉልምስናው ወደ ኢትዮጵያ ያመጣው ሀብት ፍለጋ አይደለም፡፡ አባቱ የሰጠውን አደራ ሊያሟላና ከኢትዮጵያ ጋር ያቆራኘው ደብረ ታቦሬነትን ይዞት ነው፡፡ ዛሬም ድረስ አማርኛው ከዋናው ጎንደሬ የሚስተካከል ነው፡፡ ከሦስትና አራት ዓመት ፈረንጅ አገር ስለተቀመጥን ቋንቋዬ ተረሳን ለምንል፣ አማራነትን፣ ኦሮሞነትን ወይም የሌላ ብሔረሰብ አባልነትን ዘር አድርገን ለምናስብ፣ ወገናዊ ተቆርቋሪነትን በመወለድ ብቻ ለምንለካ ይህ ሰው ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ደገምገም አድርገው እንደሚያቀርቡት ተስፋ አለኝ፡፡

በዚህ ሰው ውስጥ ያለው ትውስታ አባቴ ከሥልጣኔ አካባቢ አውጥቶ ጨለማ አገር ውስጥ ከትቶ በጉስቁልና እንዳድግ አደረገኝ፣ ያልሠለጠኑ ጥቁሮች ልብሴን አስወልቀው በሳማ እስከ መግረፍ ጥቃት እንዲያደርሱብኝ አጋለጠኝ፣ ወዘተ የሚል ፅልመታዊ ትውስታ አይደለም፡፡ አገሬ ሕዝቤ ከምንል ሰዎች የማይተናነስ ፍቅርና ናፍቆት ነው ያለው፡፡ እኛ ግን የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል ሆነና በብሔርተኝነት የተባዛ የተበዳይነት ታሪክና ለቀስተኛ አስተሳሰብ እንደ ወረርሽኝ አዳርሶናል፡፡ ከዳር ዳር ተጠቃሁና ተገፋሁ ባይ አልቃሻነት ያልነካካው አንድም ብሔረሰብ የለም ብቻ ሳይሆን፣ መድረኩ ላይ እየተጋፋ ያለውም ይኼው አመለካከት ነው፡፡ ማኅበረሰባዊ ብሔረተኛነት አዲስ ወረት የሆነበት አማራም በበደል ለቅሶና ታሪክ ከሌላው እንዳያንስ፣ ‹‹በደሉን›› ከዘመነ ኢሕአዴግ አውጥቶ እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ዘርግቶታል፡፡ የብሔረሰብ ጠልነትና የብሔርተኛነት ግንዛቤ ያልነበረበት ዘመን፣ በዛሬ በደል አነፍናፊ አስተሳሰብ በግድ ብሔር እየለየ የሚያጠቃ ተደርጎ ሊሳል በቅቷል፡፡ አንዱ ተነስቶ ደግሞ የበደል ለቅሶውን እስከ ንግሥት ዮዲት ድረስ ያደርሰው ይሆናል፡፡ አንድ ወዳጄ እንዳለው ጋኖች አልቀው ምንቸቶች ጋን የመሆናቸው ታሪክ አልበቃ ብሎ፣ ከምንቸትነትም ተወረደና ቡጫሊቱ ሁሉ ታሪክ ለቅላቂና አስተማሪ ሆነ፡፡ የረባ የይዘት ነቀሳ ያላየው ግሳንግስና ጥንግርግሩ የወጣ ‹‹ሥራ›› ሁሉ ሕዝብ ላይ ይደፋል፡፡ የሊቃውንቱ የተጣራ ሥራ መቼ ይደርስልን ይሆን? ኢትዮጵያ ከከሰለች በኋላ?

ብሔርተኛ የሆነውም፣ ብሔረተኛ ‹‹አይደለሁም›› ባዩም የብሔር ሥርጭትና የድርሻ ሒሳብ ሲያሰላና ይህንኑ ሲያመነዥክ የሚውል ሆኗል፡፡ በየዕለት ንግግርና ጨዋታ ውስጥ ብሔረሰብ ነክ ሥውር ጉሽሚያና ሽርደዳን ማነፍነፍ፣ በመገናኛ ብዙኃን ዜና፣ ሐተታ፣ የባለሥልጣን ንግግርና ሹመት ውስጥ ሁሉ ብሔረሰባዊ መበለጥ ሰምቼ በተቃጠልኩና ሐሜት በነፋሁ እያሉ እስከ መናፈቅ ድረስ ጥርጣሬ ሱስ ሆኗል፡፡ ከዚህ ዓይነት የጥርጣሬ እስረኝነት ተላቆ አዲስ የአስተዳደር ቤት ግንባታ ላይ ማተኮር የነፃነት መንገድ መሆኑም የተዘነጋ መስሏል፡፡

አድልኦን ተጋፍቶና ተፋርዶ በነፃነትና በእኩልነት ስሜት ውስጥ ለመኖር የሚያስችል ቤተ አስተዳደር ሦስት ነገሮችን ያሟላ ሥርዓተ መንግሥት የመገንባት ጉዳይ ነው፡፡ የትኛውም መጪና ሂያጅ መንግሥትና ሹም በሕግ ሥር አዳሪ መሆኑ፣ ሕገ መንግሥትና ውላጅ ሕጎች ያልበደኑ/ህያው መሆናቸው፣ እነዚህ ሁለት ነገሮች ሁሌም እንዲሟሉ ደግሞ ዴሞክራሲን መሣሪያው ያደረገ የሕዝብ ልዕልና በብዙ መልክ (በሪፐብሊካዊ ሥልጣን፣ በውሳኔ ሕዝብ፣ የትጥቅና የፍትሕ አውታራትን ከፓርቲ መዳፍ በመጠበቅ፣ እንደራሴዎችን በመሳብ (መልሶ በመጥራት) ሥልጣን፣ በአድማና በቅዋሜ መብት) የሚገለጥ መሆኑ ናቸው፡፡

የዚህ ዓይነት ቤተ አስተዳደር ግንባታ ውጥኑ በአገራችን ተጀማምሯል፡፡ ትንንሽ ጉዳይን ትቶ በሰላምና በዚህ አዲስ ቤት ግንባታ ላይ በመረባረብ ፈንታ ዳር ቆሞ ‹‹ምሰሶው የተጣመመ ነው …ማገሩ ጭቃ አጥቅሷል…›› እያሉ ማሽሟጠጥ፣ አናፂውና ካቦው ከእንትና ብሔረሰብ ነው… ከእኔ ብሔረሰብ ግንበኛ የተመረጠው ስለምን?…›› እያሉ መርኮምኮምና ወሬ መቁላት እንደምን የጤና አድራጎት ይሆናል? እንዲህ ያለ የገዛ እርሻ ሥራን በእባብ የማስፈራራት ጅልነትን ተገላግሎ፣ ወደ ዴሞክራሲ ሕይወት በሚያስገባው ተግባር ላይ መረባረብ እንደምን ችጋር ይሆንብናል!?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...