Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ማንኛውም ሐሳብ ቀርቦ ፍጭት ከተደረገበት በኋላ ጭሱ በዚህ ምክር ቤት በኩል መውጣት አለበት›› አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ

ከ2007 ዓ.ም. አገር አቀፍ ምርጫ ውጤት በኋላ በ2008 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ የሥራ ዘመኑን የጀመረው አምስተኛው የምርጫ ዘመን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሥራ ዘመኑን ከጀመረበት የመጀመሪያ ዓመት አንስቶ በአገሪቱና በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥ የተስተዋሉና እየተስተዋሉ የሚገኙ የፖለቲካ ለውጥ ንቅናቄዎች የተንፀባረቁበት እንደነበር መናገር ይቻላል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታዎች ላይ ማብራሪያ ካልሰጡ የሕዝብ ውክልናም ሆነ የሕግ ማውጣትና ቁጥጥር ኃላፊነታቸውን ላለመወጣት ገሚሱ የምክር ቤት አባላት በፓርቲያቸው መስመር ተሰባስበው አቋም የያዙበት፣ በምክር ቤቱ የተመረጠ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፉት 27 ዓመታት ባልተለመደ ሁኔታ በሕይወትና በሙሉ ጤንነት ላይ እያለ በፈቃዱ ከሥልጣን የለቀቀበት፣ ይኼው የአምስተኛው ዘመን ምክር ቤት የሥራ ዘመኑ አጋማሽ ላይ ሦስተኛውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የመረጠበት፣ ለአምስት ዓመታት የሥራ ዘመን ብቻ የተመረጠው ይኼው ምክር ቤት እስከ አራተኛው ዓመት ድረስ በነበረው ቆይታ ሦስት አፈ ጉባዔዎችን (አቶ አባዱላ ገመዳን፣ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚልና አቶ ታገሰ ጫፎ) የቀያየረበት መሆኑ፣ በምክር ቤቱ የተገለጡ የአገር አቀፍ የፖለቲካ ለውጥ ንቅናቄዎች ነፀብራቆች ናቸው። እነዚህ የፖለቲካ ለውጥ ንቅናቄዎች በምክር ቤቱ አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን (2011 ዓ.ም.) መጀመሪያ አንስቶም መንፀባረቃቸውን ቀጥለዋል። በአራተኛው ዓመት የሥራ ዘመን የፖለቲካ ለውጥ ንቅናቄው መገለጫ ሆኖ በምክር ቤቱ የተንፀባረቀው መሠረታዊ ጉዳይ ደግሞ፣ በርካቶቹ የምክር ቤቱ የሕግ ማውጣትና የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቶች ጥልቅ ልዩነቶች የታዩባቸውና ከሞላ ጎደል የምክር ቤቱ ውሳኔዎችም በከፍተኛ ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ያለፉበት ነበር። ምክር ቤቱ ማክሰኞ ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. የዓመቱን የሥራ ዘመን አገባዶ ለሦስት ወር ዕረፍት ተበትኗል። በዚሁ በአራተኛው የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን መጀመሪያ ላይ ለአምስተኛው የምርጫ ዘመን ምክር ቤት ሦስተኛው አፈ ጉባዔ በመሆን የደቡብ ክልል ተመራጩና የደኢሕዴን ከፍተኛ አመራር የሆኑት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ መመረጣቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ በዚህ ዓመት ውሳኔዎቹን ከሞላ ጎደል ያሳለፈው በአብላጫ ድምፅ መሆኑ እንደሆነ፣ ወደ ትክክለኛው የፓርላማ ዴሞክራሲ ለመሸጋገርም መሠረት ሊሆን እንደሚችል ተስፋ አድርገውበታል። አፈ ጉባዔ ታገሰ የምክር ቤቱን አራተኛ ዓመት ማለትም የ2011 ዓ.ም. የሥራ ዘመን አፈጻጸምን በተመለከተ ሐሙስ ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። አፈ ጉባዔ ታገሰ ከጋዜጠኞች ጋር ያደረጉትን ቆይታ የተከታተለው ዮሐንስ አንበርብር፣ የምክር ቤቱ ዓመታዊ የሥራ ክንውንን በተመለከተ ያቀረቡትን መግለጫና ለተነሱላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ እንደሚከተለው አሰናድቶታል።

ጥያቄ፡- ምክር ቤቱ ሰሞኑን በተጠናቀቀው አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ያከናወናቸው የሕግ ማውጣት፣ አስፈጻሚውን መንግሥት የመከታተልና የመቆጣጠር ተግባሩ ምን ይመስል ነበር?

አፈ ጉባዔ ታገሰ፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘንድሮውን የሥራ ዘመኑን የጀመረው በቅድሚያ በራሱ አደረጃጀት ላይ ማስተካከያ በማድረግ ነበር። ቀደም ሲል በምክር ቤቱ አደረጃጀት ውስጥ 21 ቋሚ ኮሚቴዎች የነበሩ ሲሆን፣ ይህንን የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት ከሥራ አስፈጻሚው መንግሥት አዲስ አደረጃጀት ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የቋሚ ኮሚቴዎቹን አደረጃጀት በማሻሻል፣ አሥር ቋሚ ኮሚቴዎችና 33 ንዑስ ኮሚቴዎች ለአሥሮቹ ቋሚ ኮሚቴዎች ተጠሪ ሆነው እንዲደራጁ ተደርጓል። በዚህ የአደረጃጀት ለውጥ፣ በቋሚ ኮሚቴዎችና በንዑስ ቋሚ ኮሚቴዎች አመራሮች ለውጥና ድልድል በማድረግ የሥራ ዘመኑን የጀመረው ምክር ቤቱ የ2011 በጀት ዓመት ተግባሩን እስካጠናቀቀበት ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ሕግ የማውጣት፣ የሥራ አስፈጻሚውን የመከታተልና የመቆጣጠር ተግባሩን አከናውኗል። በዚህ ጊዜ ውስጥ 67 አዋጆች ቀርበው በረቂቅ አዋጆቹ ላይ በሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች፣ እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን በመጋበዝ ሰፊ ውይይትና ምርመራ ተደርጎባቸው 62 ረቂቅ አዋጆች ፀድቀው ተግባራዊ በመደረግ ላይ ናቸው፡፡

     በተጨማሪም ሁለት ምክር ቤቱን የተመለከቱ ደንቦች ፀድቀው ወደ ሥራ ገብተዋል። አስፈጻሚ ተቋማት ምን ያህል እየሠሩ እንደሆነ ቋሚ ኮሚቴዎቹ በየዘርፋቸው ቁጥጥርና ክትትል የማድረግ ኃላፊነቶቻቸውንም ተወጥተዋል። ሁሉም ቋሚ ኮሚቴዎች የአስፈጻሚ ተቋማትን የሥራ ዕቅድና የአፈጻጸም ሪፖርት በየሩብ ዓመቱ በመገምገም፣ በመስክ በመገኘትም የአገልግሎት አሰጣጣቸውንና ፕሮጀክቶቻቸውን እየገመገሙ ግብረ መልሶችን ቁጥጥር ለሚደረግባቸው ተቋማት ሰጥተዋል። የዘንድሮው የፓርላማ ክርክር ካለፉት ጊዜያት በይዘቱ ለየት የሚያደርገው፣ በአጀንዳዎች ላይ ሁሉም የምክር ቤት አባላት ያመኑበትንና የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት በሚያስችል ደረጃ ምክንያታዊ ክርክር በማድረግ ሚናቸውን በሚገባ የተወጡበት በመሆኑ ነው። ይህ አዲስ ጅማሮ ጤናማ በመሆኑ ሊበረታታና ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባም ፅኑ እምነት አለኝ። የፌዴራል ዋና ኦዲተር ለምክር ቤቱ የሚያቀርበው የሀብት አጠቃቀምና የሥራ አፈጻጸም ኦዲት ሪፖርት ምክር ቤቱ ለሚያደርገው አስፈጻሚውን የመከታተልና የመቆጣጠር ተግባር ወሳኝ መሣርያ በመሆኑ፣ ኦዲተሩ የሚያቀርባቸውን ሪፖርቶች በመንተራስ ችግር ያለባቸውን ተቋማት በመጥራት ውይይት ተደርጓል።

     በተለይም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ ያለውን የሀብት ብክነት በተመለከተ ከዋና ኦዲተር ጋር በመሆን ችግሮቹ ላይ ጥልቅ ውይይት ከዩኒቨርሲቲዎቹ ጋር  ለችግሮቹ መንስዔ የነበሩ ሕጋዊ የአሠራር ማዕቀፎች ተለይተው እንዲታወጁ በማድረግ ሕጋዊ የአሠራር ሥርዓት እንዲፈጠር ተደርጓል። የአገር መከላከያና የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጄንሲ በሚያደርጉዋቸው ግዥዎች ግልጽነት በተላበሰና ብሔራዊ የደኅንነት ጥቅምን ባረጋገጠ መንገድ መከናወን እንዲችሉ ውይይቶች ተደርገው፣ በዚህ አግባብም የሕግ ማሻሻያ ተደርጓል። በቀጣይም ሕግ ከማውጣት አኳያ አንገብጋቢና ወሳኝ ሥራዎችን ሊያከናውኑ የሚችሉ ሕጎች ትኩረት ተስጥቷቸው እንዲወጡ ለማድረግ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው። እስካሁን የወጡ ሕጎችን ተፈጻሚነት በተመለከተ በቀጣይ መሠራት ያለበት ወሳኝ ጉዳይ፣ እስካሁን የወጡ ሕጎችን ኦዲት ማድረግ ይሆናል። በአገሪቱ የተጀመረውን ሪፎርም ለማስቀጠል ቀጣይ በሚኖረው አንድ ዓመት የሪፎርም ፕሮግራም ዶክመንት በማዘጋጀት፣ የተለያዩ ምሁራንና የፓርላማ አባላት የተሳተፉበት መድረክ በመፍጠር እንዲበለፅግ ተደርጓል። ሕዝቡን ለማርካት ተቋማት ሊያሻሽሉ የሚገባቸውን ድክመቶች ለይተው በማስቀመጥ፣ የፓርላማ ዴሞክራሲ አሠራር ሒደቶች ተለይተው የድርጊት መርሐ ግብር ተነድፏል።

ጥያቄ፡- የዘንድሮ ፓርላማ በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አቋም ያልተንፀባረቀበትና ውሳኔዎች በአመዛኙ በአብላጫ ድምፅ ያለፉበት ቢሆንም፣ የአባላቱ የክርክር ሐሳቦች ምክንያት ላይ የተመሠረቱ ከመሆን ይልቅ የወከሉትን ፓርቲና ብሔር የሚሸቱ ከመሆናቸው አንፃር፣ የክርክሩ መንፈስ ዴሞክራሲን የሚያጎለብት ነው ማለት ይቻላል?

አፈ ጉባዔ ታገሰ፦ በምክር ቤቱ የሚደረጉ የሐሳብ ሙግቶች የብሔር ወይም የፓርቲ ቅርፅ መያዝ የለበትም የተባለው ትክክል ነው። ከዚህ መውጣት አለብን። አባላቱ ከተመረጡና የምክር ቤቱን ወንበር ከያዙበት ዕለት አንስቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወኪሎች ናቸው። የደቡብ ክልል ተመራጭ ስለትግራይ ሕዝብ ፍላጎቶች ተቆርቁሮ መሟገት አለበት፡፡ ከትግራይ ክልል የተመረጠም ስለትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ስለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች መሟገት ይኖርበታል። የምክር ቤቱ አባላት ከየአካባቢያቸው ተወክለው የተገኙ ቢሆንም እንኳ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ከሆኑ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካይ በመሆናቸው መከራከር ያለባቸው፣ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማዕከል አድርገው መሆን ይገባዋል። በምክር ቤቱ የሚደረግ ክርክርና ውይይት በበሰለ መንገድ በምክንያትና በሐሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ትኩረት በማድረግ፣ የአቅም ግንባታ ሥራ ማከናወን ይኖርብናል። የወደፊት የትኩረት ሥራችን ይኼ ይሆናል። ምክንያቱም የፓርላማ አባላት የክርክር ይዘት ምክንያታዊነት ላይ ብቻ በመመሥረት፣ አባላቱም ለህሊናቸውና ለሕገ መንግሥቱ ብቻ ታማኝ በመሆን አቋም ሲወስዱ ነው ዴሞክራሲ የሚጎለብተው። የአገራችን የምርጫ ሥርዓት ሁሉም ብሔሮችና የፖለቲካ አስተሳሰቦች በፓርላማ እንዲወከሉ የሚያስችል ሆኖ ሳለ፣ ያለፉት ዓመታት ልምድ ግን በተፅዕኖ ምክንያት የልዩነት ሐሳብ የማይሰማበት ነበር። ይህ አካሄድ ትክክል አይደለም። የዴሞክራሲ ባህል እዚህ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ነው ጎልቶ መውጣት ያለበት።

ጥያቄ፡- ዘንድሮ በምክር ቤቱ ጎልተው ከወጡ አከራካሪ ጉዳዮች አንዱ የአስተዳደርና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ይህ አዋጅ ትልቅ የተቃውሞ ሙግት የገጠመው ቢሆንም፣ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል። ይህንን የተቃውሞ ሐሳብ ያነሳው ወገን በኮሚሽኑ መቋቋም ላይ ባለመስማማቱ፣ ኮሚሽኑ ተልዕኮውን ለመፈጸም በሚንቀሳቀስበት ወቅት እክል ሊፈጥርበት አይችልም ወይ? ተቃውሞውን ያቀረበው ክልል ለኮሚሽኑ ትብብር ባያደርግስ? ከዚህ አንፃር የውሳኔዎች በአብላጫ ድምፅ መፅደቅ ብቻውን ዴሞክራሲን ያጎለብታል ሊባል ይችላል? በዴሞክራሲ ግንባታ ሒደት ላይ ሌላ ተግዳሮት አያመጣም?

አፈ ጉባዔ ታገሰ፦ የምክር ቤቱ አባላት ያለ ማንም ተፅዕኖ ምክንያታዊ አቋም የያዙበት ዓመት ነው ከሚያስብሉት ጉዳዮች አንዱ፣ በዚህ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የተደረገው ክርክር ነው። ይህ እጅግ ጤናማ ውይይትና ክርክር ነው። በሥጋት መታየት የለበትም። የፓርላማ አባላት ከዚህ ቀደም የዴሞክራሲ ልምምድ ስላልነበራቸው፣ ትንሽ የልዩነት ድምፅ ስለተሰማ ሌላ ነገር የተፈጠረ ተደርጎ መታየት የለበትም። የኮሚሽኑ መቋቋም የተለየ ነገር አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደምም በክልሎች መካከል የሚነሱ የአስተዳደር ጉዳዮችን፣ የአስፈጻሚው መንግሥት አካል የነበረው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሲያጠናና ምክረ ሐሳብ ሲያቀርብ ነበር። ኮሚሽኑም የአስፈጻሚ መንግሥት ቋሚ አካል ሳይሆን፣ ለግጭት መንስዔ በሆኑ የአስዳደር ወሰን ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን በማከናወን፣ የግጭት መንስዔዎችን በመለየት፣ ምክረ ሐሳቦችን ለአስፈጻሚው መንግሥት፣ ለፌዴሬሽንና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያቀርብ ነው ሥልጣን የተሰጠው። የሚቀርበው ምክረ ሐሳብ ጠቃሚ ከሆነ ውሳኔ የሚሰጥበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በመሆኑ፣ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ምንም የሚያጣርሰው ነገር አይኖርም። በዚህ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ሰፊ ክርክር ተደርጎ በአብላጫ ድምፅ እንዲፀድቅ ተደርጓል። ሕገ መንግሥቱ እንደሚደነግገው ከተወሰኑ ጉዳዮች በስተቀር የምክር ቤቱ ውሳኔዎች የሚያልፉት በ50+1 የአብላጫ ድምፅ መርህ ነው። ይህም ማለት የልዩነት ሐሳቦች ተነስተው ክርክር ይደረግባቸዋል፣ ነገር ግን አብላጫው በተስማማበት ጉዳይ ላይ አገር ይቀጥላል ማለት ነው። ነገር ግን ይህ የምክር ቤቱ ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ ነው የሚል አቋም ለያዘ ወገን፣ መፍትሔ የሚፈልግበት ሌላ ሥነ ሥርዓት የለም ማለት አይደለም። ልክ ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርቦ የተዛባ ውሳኔ ነው የተሰጠኝ ብሎ የሚያምን አቤቱታ አቅራቢ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ ይህ ካልሆነም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚያቀርበው በዚህ ጉዳይ ላይ ያልተመለሰ የሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄ ካለ፣ አቤቱታውን ለሕገ መንግሥት ትርጉም አጣሪ ጉባዔ ማቅረብ የሚችልበት ሥርዓት በመኖሩ ይህንን አማራጭ መከተል ይችላል።

ጥያቄ፡- ምክር ቤቱ በአስፈጻሚው መንግሥት ላይ የሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር ዋነኛ መገለጫ ባህሪው፣ አስፈጻሚውን ጠርቶ በሚነሱ ቅሬታዎች ወይም ምክር ቤቱ ራሱ በለያቸው ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ማንሳት ሲሆን፣ የአስፈጻሚው መንግሥት ባለሥልጣንም ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቶ ይሄዳል። በዚህ ሒደት ውስጥ እውነት የት ዘንድ እንዳለ ማወቅ አይቻልም። እውነቱ ያለው በቀረበው ጥያቄ በኩል ነው? ወይስ በተሰጠው ምላሽ? ምክር ቤቱ ይህንን ለይቶ ካልሄደ አስፈጻሚውን ተቆጣጥሯል ማለት ይቻላል? በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በአስፈጻሚው መንግሥት ላይ የሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር ተጠያቂነት የማረጋገጥ ጉድለት እንዳለበት ይተቻል፡፡ ካለፉት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችን በመፍታት ረገድ ምክር ቤቱ ለግጭቶች መነሻ ምክንያት በሆኑት ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ በግጭቶች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ያሉበትን ሁኔታ ተከታትሎ ሪፖርት ማድረግ ላይ ብቻ ማተኮሩ ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም የሚል ጥያቄን አያጭርም ወይ?

አፈ ጉባዔ ታገሰ፦ ምክር ቤቱ አስፈጻሚውን የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነቱን በሚወጣበት ወቅት ለሚነሱና ለሚስተዋሉ ቅሬታዎች በአስፈጻሚው በኩል የሚቀርቡ ማብራሪያዎችን አድምጦ ማለፍ ብቻ ሳይሆን፣ እውነትን መመዘን አለበት፣ እውነት የቱ ጋ ናት የሚለውን መለየት አለበት የሚለው ተገቢ ጥያቄ ነው። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ሪፖርቶች ላይ ነው የምንወያየው ማለት ነው። ስለዚህ በአስፈጻሚው ከሚቀርቡ ሪፖርቶችና ማብራሪያዎች በዘለለ የምክር ቤቱ አባላት አደረጃጀቶችን በመጠቀም፣ በአካል ተገኝተው የማረጋገጥና የመቆጣጠር ተግባር ላይ ሰፊ ትኩረት ማድረግ አለባቸው። ይህንንም እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን የበለጠ ትኩረት በመስጠት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በተመለከተ በአካል በመገኘት፣ በመታዘብና ተገልጋዮችን በማነጋገር መቆጣጠር ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ቋሚ ኮሚቴዎች በአስፈጻሚ ተቋማት ፕሮጀክቶችና አገልግሎት ላይ በአካል፣ በመስክና በተቋማት ተገኝተው የሚያደርጉትን የክንውን ምልከታ አስመልክቶ የሚያቀርቡትን የግምገማ ሪፖርት ሁሉንም በአንድ ላይ አጠናቅሮ በመጽሐፍ መልክ በማሳተም፣ ለአስፈጻሚው መንግሥትም ሆነ ለአጥኝዎች ተደራሽ ለማድረግ አስበናል። ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል።

     ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አኳያ በፓርላማው ላይ ጥያቄዎች መነሳታቸው ተገቢ ቢሆንም፣ አንድ መስተዋል ያለበት ጉዳይ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ በተመለከተ የተዛባ አረዳድ መኖሩ ነው። ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ማለት የሕዝብን ጥቅም ማረጋገጥ ነው? ወይስ የአስፈጻሚው መንግሥት አካል የሆነ ተቋም ኃላፊን እንዲነሳ ማድረግ ነው? በማኅበረሰቡ ዘንድ አንድ የመንግሥት ኃላፊን ከአመራርነት እንዲነሳ ማድረግ ተጠያቂነትን ለማስፈን የመጀመሪያም የመጨረሻም እንደሆነ አድርጎ የመረዳት አዝማሚያ አለ። ይህ ትክክል ነው ብዬ አላምንም። አንድ ተቋም ሥራውን አለከናወነም ለማለት መለኪያ መሥፈርቶቹ ምንድን ናቸው? አንደኛው የበጀት አጠቃቀሙ ነው፣ ሌላኛው ሕጋዊ ሥርዓትን መከተሉ ነው፣ ሌላው ደግሞ የፊስካል ሥራዎች አፈጻጸሙ ነው። የፊስካል ሥራዎች ላይ ያሉ ጉድለቶች ወይም መጓተቶች እንዳይኖሩ በመከታተልና በመቆጣጠር እንዲፈጸሙ ማድረግ ለማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት ወሳኝነት ያላቸው በመሆኑ፣ ምክር ቤቱ ይህንን ተግባር በማከናወን ተፈጻሚነታቸውን ለማረጋገጥ ከሠራ ተጠያቂነትን እያረጋገጠ እንደሆነ መታወቅ አለበት። ፕሮጀክቶች በዕቅዳቸው መሠረት ባለመፈጸማቸው ምክንያት ሊታጣ ለሚችለው የማኅበረሰብ ተጠቃሚነትና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ቅድሚያ መስጠት ይሻላል? ወይስ ፕሮጀክቶቹን ያጓተተ የመንግሥት ተቋም ኃላፊን በማንሳት የማኅበረሰብን ተጠቃሚነት ከማዘግየት አንፃር ሚዛኑን የጠበቀ ተጠያቂነትን ማስፈን ነው የሚያስፈልገው? ይህ ቢሆንም ምክር ቤቱ የሚሰጠውን ምክረ ሐሳብ ተቀብሎ ማስተካከል የተሳነው ኃላፊ መነሳት ብቻ ሳይሆን በሕግም መጠየቅ አለበት። ከዚህ አኳያም ምክር ቤቱ በዚህ ዓመት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሳወቅ ከኃላፊነት እንዲነሱ ያደረጋቸው የተቋማት አመራሮች አሉ።

     በተጨማሪም ዋና ኦዲተር ያቀረበውን የሀብት አጠቃቀምና የክዋኔ ኦዲት መሠረት በማድረግ ሕጋዊ ተጠያቂነት ሊወድቅባቸው ይገባል ብለን የለየናቸውን ተቋማት በመዘርዘር፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠረትባቸው ተልኮለታል። ከሚስተዋሉ የፖለቲካ ቀውሶችና ግጭቶች ጋር በተያያዘ የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ገምግሞ አስፈጻሚው ፈጣን ዕርምጃ እንዲወስድ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ወደ ቀዬአቸው ከተመለሱ በኃላም የሚገኙበትን ሁኔታ ምክር ቤቱ በአካል በመገኘት ገምግሟል። የግጭቶችን መንስዔ ለይቶ እንዲቀረፉ ማድረግን በተመለከተም እንደተባለው አይደለም። ምክር ቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያገለግሉትን ተቋማት ማለትም በቀጥታ ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑትን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምኖ በመጠቀም፣ ለግጭት መንስዔ የሆኑ ጉዳዮች እንዲጣሩ በማድረግ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል እንዲቀርብ ተደርጓል። ለአብነት ያህል የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በለገጣፎ ከተማ የተካሄደውን ነዋሪዎችን የማፈናቀል ተግባር እንዲመረምር በማድረግ፣ የምርመራ ግኝቱ ለመንግሥት እንዲቀርብ ተደርጓል። በማረቆ እንዲሁም በጌዴኦ አካባቢዎች የተነሱ ግጭቶችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲመረምር በማድረግ፣ የግኝት ሪፖርቱ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ተሠራጭቷል።

ጥያቄ፡- በቀጣዩ 2012 ዓ.ም. አገር አቀፍ ምርጫ መካሄድ የሚኖርበት ቢሆንም፣ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ምርጫው መተላለፍ አንደሚገባው የሚያሳስቡ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ መካሄድ አለበት የሚሉ ቢኖሩም፣ በቀጣዩ ዓመት ለሚደረገው ምርጫ እየተደረገ ያለው ዝግጅት አነስተኛ ነው። በቀጣዩ ዓመት ምርጫ ይካሄዳል ወይ? ካልተካሄደ የምክር ቤቱ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? ይበተናል?

አፈ ጉባዔ ታገሰ፦ በሕገ መንግሥቱ መሠረት አንድ የምርጫ ዘመን አምስት ዓመት ነው። በሥራ ላይ የሚገኘው ምክር ቤትም የሥራ ዘመን በቀጣዩ ዓመት ያበቃል። በእኛ በኩል በቀጣዩ ዓመት የሚጠበቀው ምርጫ እንደሚካሄድ ነው የምናውቀው። ለዚህም ከምክር ቤቱ የሚጠበቀውን ተግባር እየፈጸምን ነው። እንደምታውቁት ቀጣዩ ምርጫ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ምርጫውን የሚያስፈጽመው የምርጫ ቦርድ ገለልተኛና ብቃት ያለው ሆኖ ማደራጀት አስፈላጊ በመሆኑ፣ በዚሁ አግባብ ቦርዱን በድጋሚ ተቋማዊ አደረጃጀት የሚያሻሽል አዋጅ ቀርቦልን ውይይት ተካሄዶበት ፀድቋል። በፀደቀው አዋጅ መሠረትም የቦርድ አባላት ሹመት ተከናውኖ የምርጫ ዝግጅት በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ቦርዱን በአዲስ መልክ ከማደራጀት በተጨማሪ፣ የምርጫ አዋጁ ምርጫው የሚፈጸምበትን ሥነ ሥርዓት የሚገዛ ነው። በዚህ ላይም ሰፊና ዝርዝር ረቂቅ የምርጫ አዋጅ፣ ምክር ቤቱ የዓመቱን የሥራ ዘመን ሊያገባድድ ሁለት ቀን ሲቀረው ቀርቦለት ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል። ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት ዕረፍት ላይ ቢሆንም፣ ይህ የምርጫ አዋጅ የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ ግን ረቂቅ አዋጁ ላይ ምልከታ እያደረገ ይገኛል። ምክር ቤቱ ዕረፍት ላይ ቢሆንም ይህንንና ሌሎች በአስቸኳይ መፅደቅ የሚጠበቅባቸው አዋጆችን ጭምር የሚፀድቁበት የአስቸኳይ ጊዜ ስብሰባ በመጥራት ማፅደቅ ይቻላል። በመሆኑም በቀጣዩ ዓመት ለሚካሄደው ምርጫ አስፈላጊ ዝግጅቶች በምክር ቤቱም ሆነ በመንግሥት በኩል እየከናወኑ ነው። ወቅቱ ደርሶ ምርጫውን ለማካሄድ የማያስችል ሁኔታ ከተፈጠረና የሚመለከተው ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ይህንን አስመልክቶ የሚያቀርበው የውሳኔ ሐሳብ ካለ፣ በወቅቱ የሚታይና መንግሥትና ሕዝብ መክረውበት ሲስማሙበት ሊወስኑ ይችላሉ።

ጥያቄ፡- የምክር ቤቱ ቀጣይ የሪፎርም ፕሮግራሞች በምን ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ?

አፈ ጉባዔ ታገሰ፦ በዋናነት ያቀድነውና እየሠራንበትም የምንገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሐሳብ ልዩነቶች የሚስተናገዱበት የክርክር ቤት ማድረግ ነው። የምክር ቤት አባላት ያለ ማንም ተፅዕኖ ምክንያት ላይ ቆመው የሚሟገቱበት መድረክ መሆን አለበት። የዴሞክራሲ ባህል እዚህ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ጎልቶ መውጣት አለበት። የፓርላማ አባላት የማኅበረሰቡን ችግሮች ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደም የዴሞክራሲ ልምምድ ስላልነበራቸው ታፍነው ቆይተዋል። ይህ መቀየር አለበት። እዚህ ምክር ቤት ውስጥ የሐሳብ ፍጭት ቢደረግ ኖሮ አሁን አገሪቱ የገጠማት ቀውስ ውስጥ ላትገባ ትችል ነበር። ቀደም ብሎ የሐሳብ ፍጭት የሚደረግበት ምክር ቤት ቢሆን ኖሮ የገጠመን ቀውስ በዚህ በኩል ይቀጣ ነበር። ማንኛውም ሐሳብ ቀርቦ ፍጭት ከተደረገበት በኋላ ጭሱ በዚህ ምክር ቤት በኩል መውጣት አለበት። ይህንን ሁኔታ በቀጣይ እንፈጥራለን። ለዚህም ሲባል በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል የሚደረጉ ክርክሮች ጭምር፣ ምክር ቤቱ በሚያቋቁመው ቴሌቪዥን በቀጥታ ለሕዝብ ይተላለፋል። የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በምክር ቤቱ የክትትልና ቁጥጥር ተግባር ላይ በቀጥታ እንዲሳተፉ ይደረጋል። ለዚህም ሲባል የወረዳ ኔት የመረጃ መረብን በመጠቀም ከጫፍ ጫፍ ያሉ የአገሪቱ ነዋሪዎች፣ ቅሬታዎቻቸውን በቪዲዩ ኮንፈረንስ በቀጥታ ለሚመለከተው የመንግሥት ኃላፊ የሚያቀርቡትና ኃላፊውም ከምክር ቤቱ ሆኖ በቀጥታ ምላሽ የሚሰጥበት አሠራርን እንዘረጋለን።

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...