የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ባለፈው ሳምንት ባወጡዋቸው መግለጫዎች፣ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ መጀመርያ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ረቡዕ ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው ባለ ሰባት ነጥብ መግለጫ፣ አገርን እየበታተነ ያለውን ከየአቅጣጫው የተሰበሰበ የትምክህት ኃይል እንደፈለገው እንዲሆን እያደረገ ያለው አዴፓ ነው ብሏል፡፡ በአጠቃላይ በተፈጸመው ጥፋት በተለይ ደግሞ በድርጅቱ አመራሮች ላይ ያጋጠመውን ግድያ በጥልቀት በመገምገም፣ ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግና ግልጽ አቋም በመውሰድ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አዴፓ ይቅርታ መጠየቅ አለበት ብሏል፡፡ አዴፓ የውስጥ ችግሮቹን በመሸፋፈን ጥፋቱን በሦስተኛ ወገን ማሳበብና ሕዝቡን ማወናበድ እንደሌለበት፣ በሁሉም ጉዳዮች የውስጥ ችግሮቹን በዝርዝር በመገምገም ግልጽ አቋሙን እንዲያሳውቅ፣ ይህ ሊሆን ካልቻለ ግን ሕወሓት ከእንዲህ ዓይነት ኃይል ጋር አብሮ ለመሥራትም ሆነ ለመታገል እንደሚቸገር መታወቅ አለበት ሲል አስታውቋል፡፡ የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በበኩሉ ሐሙስ ሐምሌ 4 ቀን ባወጣው መግለጫ፣ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ክልል መንግሥት ላይ ተሞክሮ ሙሉ በሙሉ በከሸፈው መፈንቅለ መንግሥትና በከፍተኛ አመራሮቹ ላይ በተፈጸመው የግፍ ግድያ ምክንያት፣ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴው ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ላይ ተመሥርቶ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ባለበት የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ መውጣቱን አውስቷል፡፡ የአማራ ሕዝብና የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከጥልቅ ሐዘናቸው ሳይላቀቁና በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ተሁኖ ‹‹በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት›› እንዲሉ፣ የትሕነግ/ሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ የትሕነግ/ሕወሓትን የነበረና እየቀጠለ ያለ አሳፋሪ የሴራ ፖለቲካ ዕርቃኑን በአደባባይ ያጋለጠ ነው ብሏል፡፡ አገሪቱ አሁን ለምትገኝበት የፖለቲካ ብልሽት ራሱ ዋና ተጠያቂ ሆኖ ሳለ፣ የአማራ ሕዝብን ህልውናና ክብር የማይመጥን መግለጫ አውጥቷል ሲል አዴፓ ሕወሓትን ኮንኖታል፡፡ በተጨማሪም ራሱ ሲጥሰው የነበረውን ሕገ መንግሥታዊና የፌዴራል ሥርዓት ጠበቃ በመምሰል የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን በማደናገር ለዳግም ሰቆቃ እንዲዳረጉ እያደረገ መሆኑን፣ በፀረ ለውጥ እንቅስቃሴው አገራዊና ክልላዊ ለውጡ በጥርጣሬ እንዲታይ ከጥፋት ኃይሎች ጀርባ መሽጎ አመራር እየሰጠ መሆኑን አዴፓ አስታውቆ፣ ትሕነግ/ሕወሓት ሕዝብና አገር በድፍረት የዘረፉ ሌቦችን፣ በብሔር ብሔረሰቦች ልጆች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ደብቆ በያዘበት ሁኔታ፣ ራሱን ብቸኛ የኢትዮጵያ ጠበቃ አስመስሎ ማቅረቡ የሞራልና የተግባር ብቃት የሌለው ድርጅት እንደሆነ ማሳያ ነው ሲል አዴፓ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ የሁለቱ ድርጅቶች ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ተስተናግዷል፡፡
ከሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው የአንድ ቀን አስቸኳይ ስብሰባ በቅርቡ ባጋጠመው የከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎችና የአማራ ክልል አመራሮች ላይ ያጋጠመውን ግድያ መነሻ በማድረግ በአገሪቱ እየተባባሱ በመጡት ሁለንተናዊ ችግሮች ይህንን ተከትለው ወደፊት ሊኖር ከሚችለው አጠቃላይ ሁኔታ ለአገራችንም ሆነ ለክልላችን ከሚኖራቸው ትርጉም አንፃር በመገምገም በአስቸካይ ሊፈጸሙ የሚገባቸው ወሳኝ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች አስቀምጧል፡፡
በዚህ ወቅት የአገራችን ህልውና ከከፋ ወደ ባሰ ደረጃ ሊወስድ የሚችል በመጠኑና ስፋቱ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ በየጊዜው እየተከማቸ የመጣው በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታ እየተበራከተ የአደጋው ፍጥነት በየቀኑ እየጨመረ በመሄድ በቅርቡ በከፍተኛ የአገሪቱ ወታደራዊና የክልል አመራሮች ላይ ያጋጠመው በግፍ የመግደል ደረጃ ደርሷል፡፡
ትናንት የአገሪቱ ህልውና ክብር አሳልፈው የሰጡና ኢትዮጵያን ለመበታተን ሌት ከቀን የማይተኙ ኃይሎች በስመ ለውጥ ግንባር በመፍጠር አሠላለፍ ባለየ መልኩ ተደበላልቆ አንድ ላይ እንዲሆኑ በመደረጉ በጥፋት ላይ ጥፋት እየተደራረበ አሁን ላለንበት ደረጃ ላይ በቅተናል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለዚህች አገር ክብርና ህልውና ሲሉ ዕድሜያቸውን ልክ የታገሉትን የሚታደኑበት፣ የሚታሰሩበትና ጥላሸት የሚቀቡበት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡
ሕዝቦች በሰላም ዕጦት ሳቢያ እንዲሰቃዩ፣ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ሕይወትና ንብረታቸው የሚያጡበት፣ እንዲሸማቀቁ፣ መጠለያ አጥተው ብርድና ፀሐይ እየተፈራረቀባቸው እንዲጣሉ፣ በአገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የግጭትና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የመፈናቀል አደጋ የተበራከተበት፣ ከምንም ጊዜ በላይ ሕግና ሥርዓት ማክበር ያልተቻለበት አገር ጠባቂ አጥታ ፅንፈኛ ኃይሎች የሚፈነጥዙባት እየሆነች ፀረ ሕገ መንግሥትና ፌዴራላዊ ሥርዓት የሆኑ ፅንፈኛ የትምክህት ኃይሎች እንዳሻቸው የሚሆኑበት ሁኔታ ተፈጥረዋል፡፡
ሕወሓት የትምክህት ኃይሎች ሲል የሕዝብ መብትና ጥቅም ረግጠው የግል ፍላጎታቸውና ያሻቸውን ለመፈጸም የሚጓጉትን ጥቂት ኃይሎች እንጂ ሕዝብን ፈርጆ አያውቅም አይችልምም፡፡ በማንኛውም መመዘኛ ትምክህተኛ ተብሎ የሚጠራ ሕዝብ የለም፡፡ የሁሉም ሕዝቦች ፍላጎትና መሻት አንድና ተመሳሳይ ነው፡፡ ሰለሆነ ወዳጅም ጠላትም ማወቅ ያለበት ሕወሓት ትናንት፣ ዛሬም ሆነ ነገ ለሕዝብ የላቀ ክብር የሚሰጥና ሕዝባዊ እምነትም አንግቦ የሚታገል ድርጅት መሆኑ ነው፡፡ ባለፉት ጊዜያት ከአማራ ሕዝብ ጎን በመሠለፍ ፀረ ትምክህተኛና ገዥ መደቦች የታገለና የላቀ መስዋዕትነት የከፈለ ድርጅት ነው፡፡
ስለሆነም የአማራ ሕዝብ ትምክህተኛ ብሎ ሊጠራ አይችልም፡፡ ሆኖም እነዚህ ፀረ ሕዝብ የትምክህት ኃይሎች የቆየውን ኋላ ቀር ህልማቸውን ለማስፈጸም እንደ ሕዝብ ትምክህተኛ ተብለሃል በማለት ሕዝብን እያደናገሩ ይገኛል፡፡ በአማራ ሕዝብ ስም እየነገዱ በአሉባልታ ወሬ ሕዝቡ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ደሙን ለመምጠጥ አኮብኩበው እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ ቢሆንም ግን እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የአማራ ሕዝብም ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ሲል መስዋዕት በመክፈል አዲሲቷን ኢትዮጵያ በመፍጠር የራሱ ሚና የነበረውና ያለው ሕዝብ ነው፡፡
ተጀምሮ የነበረው ተስፋ ሰጪ ልማትና ዕድገት በአሁኑ ወቅት መሪ አልባ ሆኖ ቁልቁለት መውረድ የጀመረበት ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት ከምንም ጊዜ በላይ የአገሩቱን ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ አልቻሉም፡፡ የጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ግድያ የሚያረጋግጠው እውነትም መንግሥት የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ማስከበር ተስኖት በግፍና ጭካኔ የሥልጣን ፍላጎታቸውን ማርካት የሚፈልጉ የትምክህት ኃይሎች እንዳሻቸው የሚፈነጩበት፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ መሽገው የሕዝቦች አለኝታ የሆነውን ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓት ለማፍረስ በግላጭ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታም በየቀኑ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለመገመት አዳጋች የሆነበት ደረጃ ላይም ተደርሷል፡፡ የአገሪቱ ሁኔታ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ እየታወቀም ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በማስወገድ በቀላሉ ሥርዓት የማፍረስ ተግባር በይፋ የሚያወግዝና የጠራ አቋም በመያዝ የሚደረግ ትግል አልታየም፡፡ በተቃራኒው ሁሉንም የለውጥ መሪዎች ነበሩ በማለት ይህንን እኩይ ተግባር ቀጣይነት እንዲኖረውና በዚህ ተግባር ላይ እጅ የነበራቸው አካላት ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ ሆን ተብሎ ያለ ኃፍረት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ የአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት እንዲጠበቅ ኃላፊነት የተሸከሙ የፀጥታና የደኅንነት አካላት በተፈጸመው ጥፋት ላይ ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መንገድ እየተሠራበት አይደለም፡፡ በመሆኑም የአገሪቱን ህልውና የከፋ አደጋ ላይ መሆኑን በመገንዘብ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀደም ብሎ ያስቀመጣቸውን የትግል አቅጣጫዎች በማጠናከር በቅርቡ ከተፈጠረው ሁኔታ በመነሳት የሚከተሉትን አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡
በጀግኖች የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ላይ የተፈጸመው የግድያ ወንጀል ከሐሳብ ጀምሮ እስከ ተግባር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተሳትፎ የነበራቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች በገለልተኛ አገራዊ ወገን በፍጥነት እንዲጣራ፣ የፀጥታና ደኅንነት አመራሮች በዚህ ሴራ ላይ የነበራቸውን ሚና ይሁን ግዴታዊ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ለተፈጸመው ጥፋት ተጠያቂ እንዲሆኑና የማጣራት ሒደቱና ውጤቱ በየጊዜው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ እንዲደረግ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
በዚህ ወቅት አገርን እየበታተነ ያለው ከዚህም ከዚያም የተሰበሰበው የትምክህት ኃይል ነው፡፡ ይህ ኃይል ዕድል አግኝቶ እንደፈለገው እንዲሆን እያደረገ ያለው ደግሞ አዴፓ ነው፡፡ በመሆኑም አዴፓ በአጠቃላይ በተፈጸመው ጥፋት በተለይም ደግሞ በድርጅቱ አመራሮች ላይ ባጋጠመ ግድያ ላይ በጥልቀት በመገምገም ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግና ግልጽ አቋም በመውሰድ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡
ከዚህ ውጭ የውስጥ ችግሮችን ለመሸፈን ጥፋቱን ሦስተኛ ወገን አለበት በማለት ማሳበብና ሌሎች ረዣዥም እጆች አለበት ወዘተ. በማለት ሕዝቡን ማወናበድ መቆም አለበት፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መኖር እንደማይቻል ሕዝቡም ተገንዝቧል፡፡ ስለዚህ አዴፓ በሁሉም ጉዳዮች ላይ የውስጥ ችግሮችን በዝርዝር በመገምገም ግልጽ አቋሙን እንዲያሳውቅ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ይህ ሊሆን ካልቻለ ግን ሕወሓት ከእንደዚህ ዓይነት ኃይል ጋር አብሮ ለመሥራትና ለመታገል እንደሚቸገር መታወቅ አለበት፡፡
እስካሁን ያጋጠመው መሠረታዊ ችግር በኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠረው የጎራ መደበላለቅና በግልጽ ወገንተኝነት ላይ በተመሠረተ ትግል እየታገዘ ሁሉንም ጥገኛና ደባል አስተሳሰቦች ተሸክሞ የሚኖር ድርጅት እየሆነ በመምጣቱ ነው፡፡ በመሆኑም የአገራችንን ህልውናና ደኅንነት ዋስትና እንዲኖረው ኢሕአዴግ ወደ ነባሩና የሚታወቅበት መለያው የሆነ ባህሪና እምነት ተመልሶ ከጎራ መደበላለቅ በጠራና ግልጽ ወገንተኝነት የተመሠረት ትግል እንዲካሄድና በቀጣዩ ዓመት በሕገ መንግሥቱ መሠረት መካሄድ ያለበትን አገራዊ ምርጫ እንደ ግንባርና መንግሥት አቋሙን ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ግልጽ እንዲያደርግ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያሳስባል፡፡
የአገር መከላከያ ኃይል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና የአገሪቱን ሉዓላዊነት ከማንኛውም አደጋ ለመከላከልና ለመጠበቅ የተሰጣችሁን ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት ከምንም ጊዜ በላይ ውስጣዊ አንድነታችሁን በማጠናከር የአገራችሁን ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅ ረገድ ኃላፊነታችሁንና ግዴታችሁን እንድትፈጽሙ ጥሪ በማቅረብ ይህን ለመፈጸም በምታደርጉት ትግል ላይ ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ ዛሬም እንደ ትናንቱ ከጎናችሁ በመሆን በፅናት እንደሚታገል ያረጋግጥላችኋል፡፡
ሕወሓት ሕገ መንግሥታዊና ፌዴራላዊ ኃይል እንደ መሆኑ መጠን ሕዝብና አገር ካለውና ለወደፊትም ከተጋረጠባቸው አደጋ ለማዳን ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ሕገ መንግሥታዊና ፌዴራላዊ ኃይሎች ጋር ሰፊ መድረክ በመፍጠር ለመታገልና በአስቸኳይ ወደ ተግባር እንዲሸጋገር የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ወስኗል፡፡
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እየተነሱ ያሉትን ክልል የመሆን ጥያቄዎች ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ሊፈቱ ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ የሕዝብን ጥያቄ በኃይል ወይም በሌላ መንገድ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ የፌዴራል መንግሥት በዚህ አገር ውስጥ አስተማማኝ ሰላም እንዲያረጋግጥ፣ ሕግና የሕግ የበላይነት እንዲያከብር፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊያረጋግጥና ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ሳይሸራረፍ እንዲተገብር የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በድጋሚ ያሳስባል፡፡
የተከበርክ የትግራይ ሕዝብ
በመስመርህና ድርጅችህ ዙሪያ ተሠልፈህ በየጊዜው ላጋጠመህ ቁጥር ስፍር የሌለው ሴራና ተግዳሮት በመበጣጠስ ወደፊት እየተራመድክ ትገኛለህ፡፡ በፅናትህ፣ ትዕግሥትህና ብልኃትህ አማካይነት ከያዝከው መንገድ ዝንፍ ሳትል በዓላማህና መስመርህ ፀንተህ እየታገልክ ትገኛለህ፡፡ ተስፋ እንድትቆርጥ፣ እንድትንበረከክና አንገትህ እንድትደፋ በማሰብ ኮትኩተህና አንፀህ ያሳደግካቸውን ምርጥ ታጋዮችህ እንድታጣ አድርገዋል፡፡ ቢሆንም ግን መስዋዕት ለአንተ አዲስ አይደለም፡፡ ምርጥ ታጋይ ልጆችህን ከፍለህ ለዚህ በቅተሃልና፡፡ አሁንም ቢሆን ያጋጠመህን ችግር አልፈህ ለበለጠ ትግልና ለማይቀር ድል ተዘጋጅ፡፡ እውነተኛና ፍትሐዊ ትግል እስኪካሄድ ድረስ በዓላማ ላይ የተመሠረተ ጽኑ አንድነትህን እስካረጋገጥክ መጪዉ ጊዜህ በአንፀባራቂ ድል የታጀበ ነው፡፡ በመሆኑም አንድነትህ አጠናክረህ ከመስመርህና ከድርጅትህ ጎን ተሠለፍ፡፡ በየጊዜው የሚፈጠሩትን ሁኔታዎች በንቃትና በትዕግሥት ተከታተል፡፡
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች
ትናንት በድህነትና ኋላ ቀርነት ተቆራኝተን እንድንኖር ፈርዶብን የነበረውንና በሕዝቦች መስዋዕትነት ያስወገድነውን የትምክህት ኃይልና በእሱ የሚመራው አኃዳዊ ሥርዓት ዳግም አፈሩን አራግፎ በመነሳት በሕዝብ ልጆች መስዋዕትነት የተጻፈ የሕዝቦች ቃል ኪዳን የሆነውን ሕገ መንግሥትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማፍረስ በውስጥና በውጭ ኃይሉን አጠናክሮ ላይና ታች እያለ ይገኛል፡፡ ስለዚህም ሰላማችንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታችንን በመጠበቅ በዋነኝነትም ደግሞ የአገራችንን ህልውና በማረጋገጥ ረገድ በጋራ እንድንታገል የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ክብርና ሞገስ ለጀግኖች ሰማዕታት
የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. መቐለ
ከአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
የድርጅታችን አዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በክልላችን መንግሥት ላይ ተሞክሮ ሙሉ በሙሉ በከሸፈው መፈንቅለ መንግሥትና በከፍተኛ አመራሮቻችን ላይ በተፈጸመው የግፍ ግድያ ምክንያት የማዕከላዊ ኮሚቴያችን ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ላይ ተመሥርቶ በወቅታዊ ጉዳይና ቀጣይ የትግል አቅጣጫዎች ግምገማ ለማድረግ ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. እየመከረ ባለበት፣ የአማራ ሕዝብና የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከጥልቅ ሐዘናችን ባልተላቀቅንበት በዚህ ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታ ውስጥ ሆነን፣ ‹‹በሰው ቁስል እንጨት ቢሰዱበት›› እንዲሉ፣ የትሕነግ/ሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የትሕነግ/ሕወሓትን የነበረና እየቀጠለ ያለ አሳፋሪ የሴራ ፖለቲካ ዕርቃኑን በአደባባይ ያጋለጠ የአቋም መግለጫ ማውጣቱ ‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል እንዲሉ›› አገራችን አሁን ለምትገኝበት የፖለቲካ ብልሽት ራሱ ዋና ተጠያቂ ሆኖ ሳለ፣ የአማራን ሕዝብ ህልውናና ክብር የማይመጥን መግለጫ አውጥቷል፡፡
ምንም እንኳን የድርጅታችን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለስብሰባ የተቀመጠው ካጋጠመን ወቅታዊ ችግር በፍጥነት እንዴት መውጣት እንዳለብንና የለውጡን ቀጣይነት ጠብቀን መዝለቅ እንደሚገባን ለመምከር ቢሆንም፣ የትሕነግ/ሕወሓት መግለጫ ከሐዘን ባልወጣንበት ሁኔታ ከአንድ እህት ፓርቲ የማይጠበቅ አሳፋሪ ድርጊት በመሆኑ፣ ድርጊቱን ለማውገዝ፣ ለአብሮነትና ለትግራይ ሕዝብ ባለን ክብር እያየን እንዳላየን የታገስነውና ያለፍነውን ነገር ሁሉ፣ ትሕነግ/ሕወሓት በመግለጫው ‹‹ራሱ ነካሽ፣ ራሱ ከሳሽ›› ሆኖ በመቅረቡ ይህ የአዴፓ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ አስፈላጊና ወቅታዊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
የትሕነግ/ሕወሓትን መሰሪና አሻጥር የተሞላበት የዘመናት ባህሪውን በማጋለጥ፣ የአማራ ሕዝብን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባደረጉት ቆራጥ ትግል የተገኘውን ሕዝባዊ ድል ደግሞ ደጋግሞ በማንኳሰስና ፈፅሞ አክብሮት የማያውቀውንና ራሱ ሲጥሰው የነበረውን ሕገ መንግሥታዊና የፌዴራል ሥርዓት ጠበቃ በመምሰል፣ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ጭቁን ሕዝቦችን በማደናገር ለዳግም ሰቆቃ እንዲዳረጉ እያደረገ ባለበት፣ በፀረ ለውጥ እንቅስቃሴው አገራዊና ክልላዊ ለውጡ በጥርጣሬ እንዲታይ፣ ከጥፋት ኃይሎች ጀርባ መሽጐ አመራር እየሰጠ ባለበት ሁኔታ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የለውጥ ፍላጐት መነሻ ተደርገው የተወሰዱ አሳሪና ደብዳቢ ፀረ ዴሞክራቶችን፣ ሕዝብና አገር በድፍረት የዘረፉ ሌቦችን፣ በብሔር፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ልጆቹ ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ፣ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አቅፎና ደብቆ በያዘበት ሁኔታ የትሕነግ/ሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያወጣው መግለጫ የዘመናት አስመሳይነቱን ያጋለጠ፣ ራሱን ብቸኛ የኢትዮጵያ ጠበቃ አስመስሎ መቅረቡ የሞራልና የተግባር ብቃት የሌለው ድርጅት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
ትሕነግ/ሕወሓት ከምሥረታው ጀምሮ በ1968 ዓ.ም. ማኒፌስቶው የአማራን ሕዝብ በጠላትነት የፈረጀ፣ ከሌሎች ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር ተከባብሮና ተሰናስሎ በፍቅር እንዳይኖር፣ ‹‹ትምክህተኛና ሌሎችን አግላይ ስያሜዎችን እየሰጠ፣ ለዘመናት የፈጸመው ግፍና በደል ሳያንሰው ዛሬም ከለውጥ ማግሥት በአደባባይ ተሸንፎ ሕዝባዊ ዕርቃኑ በተጋለጠበት በዚህ ሰዓት፣ አጠቃላይ ትግሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የትሕነግ/ሕወሓትንና የጥፋት ኃይሎችን እኩይ ድርጊት መፋለም ሆኖ ሳለ፣ ትግሉ በትሕነግ/ሕወሓትና በአዴፓ መካከል የሚካሄድ በማስመሰል፣ ወቅታዊ ጉዳታችንን እንደ ዘላቂ ሽንፈትና ውድቀት በመቁጠር፣ ዛሬም የአማራን ሕዝብ አንገት ለማስደፋት ‹‹የተቀበረውን የትምክህት ትርክቱን ዳግም ይዞ ብቅ ማለቱ ድርጅቱ መቼም ቢሆን መፈወስ የማይችል በሽታ ያለበት መሆኑን ያጋለጠ ተግባር ነው፡፡ በእርግጥም ትሕነግ/ሕወሓት በዚህ ባህሪው ይታወቃል፡፡ በፅናት የሚታገሉትንና ከእኔ ጎን አይሠለፉም የሚላቸውን ኃይሎች ሲሻው ትምክህተኛ፣ ሲሻው ጠባብና አሸባሪ በማለት ታርጋ እየለጠፈ የሚያሸማቅቅ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት መሆኑ መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል፡፡ በመሆኑም የትሕነግ/ሕወሓት መግለጫ አዲስ ነገር ይዞ የመጣ ሳይሆን፣ የተለመደ ፖለቲካዊ ሴራ ማሳያ ነው፡፡
ትሕነግ/ሕወሓት ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሁለት አገረ መንግሥት ዕይታ ያለው፣ አንድም ቀን ለሕዝቦች አንድነት የማይጨነቅ፣ በሥልጣን ላይ እስከቆየና እላፊ ጥቅም እስካገኘ ድረስ ብቻ አስመሳይ የአንድነት ኃይል ሆኖ መቀጠል የሚፈልግ፣ ነገር ግን እንደ ዛሬው በሥልጣን ላይ ሆኖ በአድራጊ ፈጣሪነት ሁሉንም ማሳካት ሳይችል ሲቀር፣ በቁም ቅዥትና ከትግራይ ሕዝብ ሥነ ልቦና ባፈነገጠ መልኩ ‹‹የዥዋ ዥዌ ፖለቲካን›› የሙጥኝ ያለ እምነት የማይጣልበት ድርጅት ነው፡፡
የአማራ ሕዝብና መሪ ድርጅታችን አዴፓ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ለሀቀኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት፣ ለእውነተኛ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትና ለእውነተኛ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እኩልነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ ለጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት ፅኑ እምነት ይዞ የሚታገል ሕዝብና ድርጅት እንጂ ትሕነግ/ሕወሓት ደጋግሞ እንደሚከሰው ሳይሆን ለአገር አንድነት የሚተጋ፣ በሌሎች ጉዳት ላይ የተመሠረተ ተናጠላዊ ጥቅምን ማረጋገጥ የማይፈልግ፣ ሀቀኛና ሕዝባዊ ድርጅት ነው፡፡
አሁን በምንገኝበት የለውጥ መድረክም የአማራ ሕዝብና ድርጅታችን አዴፓ ሆን ተብሎ የተበላሸውን አገራዊ ፖለቲካዊ ሁኔታችን እንዲታረም፣ ከሌሎች የለውጥ ኃይሎች ጋር ሆኖ ፊት ለፊት የተፋለመና የለውጡን ውጤቶች ጠብቆ ለመዝለቅ ሌት ከቀን የሚታትር ድርጅት እንጂ፣ እንደ ትሕነግ/ሕወሓት በከፋፋይት በሽታ የተጠመደ ድርጅት አይደለም፡፡
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በክልላችን ከፍተኛ አመራሮችና የኢትዮጵያን አንድነት መስዋዕትነት እየከፈለ ለማስቀጠል በሚተጋው የመከላከያ ኃይላችን የጦር ጄኔራሎች ላይ ያነጣጠረው ግድያና የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በድርጅታችን አዴፓ፣ በአማራ ሕዝብና በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የተፈጸመ ጥቃትና የለውጣችን ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በመሆኑም የጥፋት ድርጊቱን ከሕዝባችንና ከፀጥታ መዋቅራችን ጐን ተሠልፈን በፅናት የተፋለምነውና ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈልንበት ነው ብለን እናምናለን፡፡ በሒደቱም ለኢትዮጵያ አንድነት ያለንን ቁርጠኝነት ዳግም ያሳየንበትን ታሪካዊ ወቅትና የትግላችን አንድ አካል የሆነውን ጥረታችንን እንደ ሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሪ ድርጅቶች መደገፍና ማገዝ ሲገባ ትሕነግ/ሕወሓት ድርጊቱን ለራሱ በሚጠቅመው መንገድ በመረዳት ይቅርታ እንድንጠይቅበት መግለጫ ማውጣቱ ተደማሪ ታሪካዊ ስህተት ከመሆኑም በላይ የተከበረውን የትግራይ ሕዝብ ባህልና እሴት የማይመጥን፣ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳዘነ መግለጫ ነው ብለን እናምናለን፡፡
በእርግጥም ትሕነግ/ሕወሓት ይህንን ወቅታዊ ሁኔታ የራሱን የዘመናት ወንጀሎች ለመሸፋፈን ተጠቅሞበታል፡፡ እውነትና ፍትሕ ቢኖር ኖሮ ባለፉት ዘመናት በትሕነግ/ሕወሓት የሴራ ፖለቲካ ምክንያት ለተለያየ ጥፋትና እንግልት በተዳረገው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ቅርቃር ውስጥ በወደቀው አገራዊ አንድነታችን ምክንያት ከወገቡ ዝቅ ብሎና ከልቡ ተፀፅቶ የተበደለውን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ የነበረበት ዋነኛው ተጠያቂ ትሕነግ/ሕወሓት መሆኑን እንረዳለን፡፡ በተጨማሪም ትሕነግ/ሕወሓት ድርጅታችን አዴፓን በዚህ ደረጃ ጥርስ ውስጥ ያስገባበት መሠረታዊ መነሻ ለዘመናት ሲሠራው የነበረውን ፀረ ሕዝብና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባር ከሌሎች የለውጥ ኃይሎች ጋር ሆነን በግንባር ቀደምትነት አምርረን በመታገላችንና ጥፋቱ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ፊት በመጋለጡ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ድርጅታችን አዴፓ፣ በኢሕአዴግ ግንባር ውስጥ ከትሕነግ/ሕወሓት ጋር አብሮ እየታገለ መቆየቱን የመረጠው ለትግራይ ሕዝብ ካለን ክብር፣ እንዲሁም ትሕነግ/ሕወሓትም ራሱ ተፀፅቶ ራሱን ያርማል በሚል ተስፋ ቢሆንም ትሕነግ/ሕወሓት በነበረበት ተቸክሎ የሚዳክር ድርጅት በመሆኑ፣ ድርጅታችን አዴፓን ይቅርታ እንዲጠይቅና ከአዴፓ ጋር አብሮ ለመሥራትም የሚቸገር እንደሆነ አድርጐ መቅረቡ ‹‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ›› የድርጅቱ የሴራ ፖለቲካ መገለጫ ነው፡፡
ትሕነግ/ሕወሓት መቼም ቢሆን ከብልሹ ፖለቲካ የማይፈወስ ድርጅት በመሆኑ በተደጋጋሚ የሕዝባችን የጎን ውጋት ሆኖ በተለያዩ የክልላችን አካባቢዎችና አጎራባች ክልሎች ከግጭቶች ጀርባ መሽጐ እንደሚያዋጋ እያወቅንም፣ ለዚህም በርካታ ማስረጃዎች በእጃችን ላይ እያሉ ለሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትና ለኢትዮጵያ አንድነት ስንል በሆደ ሰፊነት ብንመለከተውም፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሌሎች ወንድምና እህት ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከችግርና ሰቆቃ ባልተላቀቁበት ነባራዊ ሁኔታ፣ የራሱን እኩይ ወንጀል ለመሸፋፈን፣ በትግራይ ሕዝብ ሲምልና ሲገዘት የሚውል ሕዝቡን ለጥቃት በሚያጋልጡ ተንኮሎች የተጠመደ፣ የማይማርና የማይድን ድርጅት ነው፡፡ በመሆኑም ትሕነግ/ሕወሓት ጥርሱን ነቅሎ ባደገበት የሴራ ፖለቲካ እየተመራ፣ ከልክ በላይ በእብሪተኝነት ተወጥሮ በየአካባቢው ጦር እየሰበቀና በበሬ ወለደ አሉባልታ ወንድም የሆነውን የትግራይ ሕዝብ በተለይም ወጣቱን ለጥፋት እያነሳሳ ለተለያዩ አደጋዎች ተጋላጭ እንዲሆን እየገፋፋው ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ ድርጅታችን አዴፓና የአማራ ሕዝብ እንደ ወትሮው ሁሉ ለኢትዮጵያ አንድነትና ለሕዝቦች እኩልነት፣ እንዲሁም ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ለእውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓትና ለእውነተኛ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በፅናት የሚታገል እንጂ ተንኳሽና ጦር ሰባቂ እንዳልሆነ እየታወቀ፣ በተሳሳተ መረጃ ጭቁኑን የትግራይ ሕዝብ፣ የኢትዮጵያን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሌለ ሥጋት በመፍጠር አዴፓንና የአማራን ሕዝብ ተጠርጣሪ ለማድረግ የሚያደርገው ተከታታይ ቅስቀሳ መወገዝ ያለበት መሆኑን በፅኑ በማመን የሚከተሉትን የአብሮነትና የአጋርነት ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
- ለመላው የድርጅታችን አዴፓ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች
አዴፓ ሕዝባዊነቱን እንደ ያዘ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ለብሔር፣ ብሔረሰቦች እኩልነት የታገለና የሚታገል የዛሬና የነገ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ነው፡፡ በመሆኑም ለዓላማዎቹ ግብ መሳካት መስዋዕትነት የከፈሉትን ጓዶች ዓላማ ዳር ለማድረስ በፅናት የሚታገል የአማራ ሕዝብ ፓርቲ እንጂ፣ እንደ ትሕነግ/ሕወሓት ላሉ የሴራ ኃይሎች የሚያጎበድድ ፓርቲ አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው በሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በደረሰብን አደጋ ጉዳታችን ጥልቅ ቢሆንም፣ መላ መዋቅራችንን፣ ሕዝቡንና የፀጥታ ኃይሉን ከጎናችን አሠልፈን እኩይ ሴራውን መቆጣጠራችንናና ማክሸፋችን የሚታወቅ ነው፡፡ ክልላችን ከደረሰብን አደጋና ችግር ፈጥኖ እንዲወጣ ሰፊ የማረጋጋት ሥራ በመሥራት አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ላቀ ጥንካሬያችን እየተመለስን ሲሆን፣ በወንጀል ድርጊቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተሳተፉ አካላትን ለሕግ በማቅረብ ላይ ስንሆን፣ የምርመራ ሥራውም በጥብቅ ዲሲፕሊንና በተቀናጀ አግባብ እየተመራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም አጠቃላይ የምርመራ ሥራውንና የሕግ ተጠያቂነትን የማረጋገጡን ተግባር በቁርጠኝነት ዳር የምናደርሰው ሲሆን፣ በዚህ ወቅት አደጋውን ለመቀልበስ ከጎናችን ተሠልፎ ሊታገል የሚገባው እህት ድርጅት ትሕነግ/ሕወሓት በድርጅታችንና በአማራ ሕዝብ ላይ የከፈተውን የጥፋት ዘመቻ በፅናት በመመልከት ለአማራ ክልል ሕዝቦች እኩል ተጠቃሚነትና ለጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት የጀመርነውን አገራዊ ለውጥ አጠናክረን እንድንቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ - ለክልላችን ሕዝቦች፣ እንዲሁም በኢትዮጵያና በመላው ዓለም የምትገኙ የአማራ ተወላጆች አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን ጠብቀንና ኅብረታችንን አጠናክረን፣ የቀደመ ታሪካችንን ሳንሸራርፍ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ለብሔር፣ ብሔረሰቦች እኩልነት በአብሮነት መንፈስ በፅናት የምንታገልበት ታሪካዊ ወቅት ላይ መሆናችን፣ የበለጠ የሚያስተሳስረንና የሚያዋህደን እንጂ፣ ከውስጥም ሆነ ከውጭ በሚሸረብ ሴራ የማንለያይና የማንነጣጠል በመሆናችን፣ የትናንት እኩይ ሴራቸውን ዛሬም ሳይረሱ ወቅታዊ ችግሮቻችን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም አንገት ሊያስደፉን ከሚፈልጉ ትሕነግ/ሕወሓትና መሰል የጥፋት ኃይሎች የማንበገር መሆናችንን በፅናት እየገለጽን ከድርጅታችን አዴፓ ጎን ተሠልፋችሁ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም፣ ቀጣይነት ለሚኖረው ልማትና ዋስትና ላለው ዴሞክራሲ በአንድነት እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
- ለተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣
ድርጅታችን አዴፓና የአማራ ሕዝብ ባጋጠመው ፈተና ሁሉ ከጎናችን በመሠለፍ አጋርነታችሁን ስላረጋገጣችሁልን በዚህ አጋጣሚ ምሥጋናችንን እያቀረብን፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ ለኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ ለእውነተኛ ዴሞክራሲና የፌዴራሊዝም ሥርዓት፣ እንዲሁም ለሀቀኛ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ከጎናችሁ ሆነን በፅናት የምንታገል መሆኑን እያረጋገጥን፣ ትሕነግ/ሕወሓት የዘመናት ወንጀሎቹን ለመሸፈንና ድርጅታችን አዴፓና የአማራ ሕዝብን የሌሎች ሕዝቦች ጠላት በሚያደርግ የተሳሳተ አስተምህሮ ዛሬም በጥርጣሬ እንድንተያይ የሚነዛውን የማደናገሪያ ትርክት መሠረተ ቢስ መሆኑን እንደምትገነዘቡ ፅኑ እምነት ያለን ሲሆን፣ ይኼን ፀረ ዴሞክራሲና አስመሳይነት ከጎናችን ተሠልፋችሁ በፅናት እንድትታገሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ - ለተከበርከው የትግራይ ሕዝብ፣ የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ታሪካዊ አንድነትና ውህደት ያላቸው፣ ባህላዊና ጥንታዊ ሃይማኖታዊ እሴቶችን የሚጋሩ፣ በጋብቻና በደም የተሳሰሩ፣ በፀረ ጭቆና ትግል ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ሆነው በአንድ ጉድጓድ ክቡር መስዋዕትነት እየከፈሉ አሁን ላለንበት የአገረ መንግሥት ምሥረታ ጉልህ አሻራ ያሳረፉ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ሆኖም ትሕነግ/ሕወሓትና መሰል እኩይ ድርጅቶች በሕዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ፣ በትግራይ ሕዝብ ስም እየነገዱ ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ የዘለቀውን የአብሮነት ታሪካችንን በአራት አሥርት ዓመታት የበሬ ወለደ ትርክቶች ለመሸርሸርና ሕዝባዊ አንድነታችንን አደጋ ላይ ለመጣል የሚያደርጉት ሴራ መሆኑን አውቃችሁ ከአማራ ሕዝብ ጋር ያላችሁ ወንድማዊና ቤተሰባዊ ግንኙነታችሁ ሳይቋረጥ ሁለቱን ሕዝቦች የሚያለያዩ ሙከራዎችን በፅናት እንድትታገሉ የከበረ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡
- ለእህትና ለአጋር የፖለቲካ ድርጅቶች እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችን ኢትዮጵያ ካሏት ዘርፈ ብዙ ፀጋዎችና እሴቶች መካከል ብዝኃነታችን የምንደምቅበት ጌጣችን መሆኑ ለአፍታም ቢሆን አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ትሕነግ/ሕወሓት ይህን የብዝኃነት ፀጋ ጠብቆ ለማስቀጠል ብቸኛ ተቆርቋሪ በመምሰል፣ ሲያሻው ደግሞ በሕዝቦች መካከል የጥርጣሬ አጥር በመፍጠር፣ ሕዝባዊ አንድነታችንን ለማላላት የከፋፋይነት ፖለቲካውን ሲያራምድበት በመቆየቱ ምክንያት በለውጥ መድረካችን በአንድነት የረገምነው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ዛሬም እንደ ትናንቱ ለብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ የተለየ ትኩረት የሰጠ በመምሰል ይህንኑ የአስመሳይነት ድራማውን በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ሲተውን የሚስተዋል ስለሆነ፣ ይህን መሰል እኩይ ተግባር በአንድነትና በፅናት በመፋለም ሕዝባዊና አገራዊ አንድነታችንን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ አጠናክረን እንድናስቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
- ለኢፌዴሪ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ለክልላችን የፀጥታ ኃይሎች
ድርጅታችን አዴፓና የአማራ ሕዝብ የአገር መከላከያ ሠራዊታችንና የክልላችን የፀጥታ ኃይሎች ሕዝባዊነታችሁን ጠብቃችሁ ለአንዲት ሉዓላዊት አገር መከበርና ቀጣይነት ክቡር መስዋዕትነት በመክፈል ላይ መሆናችሁን እንገነዘባለን፡፡ ጥንትም ቢሆን ኢትዮጵያ የተመሠረተችውና ፀንታ የቆየችው በጀግኖች አርበኞቻችን ተጋድሎና መስዋዕትነት በመሆኑ፣ በቅርቡም አጋጥሞን በነበረው አደጋ ፈጥኖ ደራሽነታችሁን በማረጋገጥ ክልላችንና አገራችንን ከጥፋት በመታደጋችሁ ምሥጋናችንን እያቀረብን ወደ ፊትም የአገራችንን ሉዓላዊነትና የክልላችንን ሁለንተናዊ ደኅንነት በማስጠበቅ ሒደት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ሁሉ በፅናት በማለፍ ሕዝባዊነታችሁን እንድታረጋግጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
በመጨረሻም በክልላችንም ሆነ ከክልላችን ውጪ በአማራና በክልሉ ሕዝቦች ስም የምትንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች እየሰፋና እየጠነከረ በመጣው የፖለቲካ ምኅዳር አዎንታዊ ሚና እድትጫወቱ ጥሪያችንን እያቀረብን፣ በሌላ በኩል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የትሕነግ/ሕወሓትን የፖለቲካ ደባ የምታስፈጽሙ ተላላኪ የፖለቲካ ኃይሎችና ቡድኖች ከእኩይ ድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ በጥብቅ እያሳሰብን ድርጅታችን አዴፓም ሆነ የአማራ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔሰቦች ጋር ሆነን ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የሚደረገውን ትግል አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን በድጋሚ እናረጋግጣለን፡፡
የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም.