አጀማመሩ በመንግሥት የተቋቋመ ኤጀንሲ ሆኖ አሁን ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀሰው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ‹‹ከሊፋ ፈንድ ፎር ኢንተርፕራይዝ ዴቨሎፕመንት›› በኢትዮጵያ በተለይ ለአነስተኛና ጥቃቅን፣ እንዲሁም ለጀማሪ የንግድ ተቋማት ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ተፈራረመ፡፡ ለዚሁ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚሆን የ2.8 ቢሊዮን ብር (100 ሚሊዮን ዶላር) የረዥም ጊዜ (የኮንሴሽናል) ብድር ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡
የፈንዱ ሊቀመንበር ሁሴን ጃሲም አል ኖይስ በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ካሊፋ ፈንድ ምሥረታው በአገር ውስጥ (በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ) የሚፈጠሩ አነስተኛና ጥቃቅን፣ እንዲሁም ጀማሪ የንግድ ተቋማትን ለመደገፍና በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ ለማስቻል ቢሆንም፣ በተለይ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ግን ተመሳሳይ ድጋፉን ወዳጅ ለሚላቸው አገሮችና ተቋማት ለመለገስ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ በዚህ ረገድ ‹‹ከሊፋ ዓለም አቀፍ›› በአሁኑ ጊዜ በ20 አገሮችና በሦስት አኅጉራት ፕሮጀክቶችን እየደገፈ መሆኑን የሚናገሩት ሚስተር አል ኖይስ፣ ኢትዮጵያም በዚህ ወቅት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ትራቴጂክ አጋር አገር ስለሆነች፣ ድጋፉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
የብድር ድጋፉ በተለያዩ የአቅም ግንባታዎችና የአሠልጣኞች ሥልጠና ፕሮግራሞች ላይ ፈሰስ የሚደረግ ቢሆንም፣ በዋነኝነት ግን ኢትዮጵያዊ አነስተኛና ጥቃቅን፣ እንዲሁም ጀማሪ የንግድ ተቋማትን ለመደገፍ በሶፍት ብድር (ርካሽ ወለድ የሚታሰብበት ብድር) መልክ የሚቀርብ መሆኑን ሊቀመንበሩ አስረድተዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በዋነኝነት ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ጋር በጋራ ተፈጻሚ እንደሚሆን፣ ለቀጣይ የፕሮጀክቱ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በጋራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በ20 አገሮች ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የሚያደርገው ከሊፋ ፈንድ አሁን ከታሰበው የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አኳያ ኢትዮጵያ ከጥቂት ከፍተኛ ድጋፍ የሚያገኙ አገሮች መካከል መሆኗም ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል እንደ ሚስተር አል ኖይስ ከሆነ ቢያንስ ለአምስት ዓመታት የሚከናወን ፕሮጀክት ፈሰስ የሚደረግለትን 100 ሚሊዮን ዶላር እንደ ተዘዋዋሪ ፈንድ በመጠቀም፣ ድጋፍ የሚደረግላቸው ተቋማት ብድራቸውን ሲመልሱ ለቀጣይ የድጋፍ ብድር ማዋል ይችላል፡፡ ይህም ፕሮጀክቱ በተቻለ መጠን ዘላቂነት እንዲኖረው ያደርጋል ተብሏል፡፡
ቢያንስ በአራት ትልልቅ ምሰሶዎች ላይ የሚመረኮዘው ይህ ፕሮጀክት ሴቶችንና ወጣቶችን ማብቃት፣ ጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ተቋማትን እንዲበራከቱ ማድረግ፣ የሥራ ፈጠራ እንዲስፋፋ ማድረግና ድህነትን የመቀነስ ዓላማዎችን ለማስፈጸም እንደሚያግዝ ተናግሯል፡፡
በዚህ ረገድ ‹‹በከሊፋ ዓለም አቀፍ›› ሥር ቢያንስ 220,000 የአነስተኛና ጥቃቅን ፕሮጀክቶች ተፈጻሚ የሆኑ ሲሆን፣ ከዚህ ጋር በተያያዘም 400,000 አዳዲስ የሥራ ዕድሎችም መፈጠራቸውን ሊቀመንበሩ ይናገራሉ፡፡
‹‹በዚህ ፕሮጀክት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ዘርፎችን የመወሰኑ ኃላፊነት በሚኒስቴሩ ላይ ቢሆንም፣ በጥቅሉ ግን ከአገሪቱ የጀርባ አጥንት ግብርናና፣ ከግብርና ጋር ተያያዥነት ያላቸው የፈጠራ ሥራዎች (ኢኖቬሽን) ቅድሚያ እንደሚያገኙ መናገር ይቻላል፤›› ያሉት ሚስተር አል ኖይስ፣ በሌሎች አገሮች ተግባራዊ እንደሆነው ፕሮግራሙን ከአገራዊ ሁኔታ ጋር የማጣጣም ሥራዎች ከፈንዱ ጋር በመሆን እንደሚከናወን ይገልጻሉ፡፡
በሌላ በኩል ከአነስተኛና ጥቃቅንና ጀማሪ የቢዝነስ ተቋማት መካከል ያለው የድጋፍ ምጣኔም ቢሆን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚወሰን ሲሆን፣ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የተባለው ዘርፍ እስከ 90 በመቶ ድጋፍ ሊወስድ እንደሚችል ሊቀመንበሩ ያስረዳሉ፡፡
ዞሮ ዞሮ ለመንግሥት የሚደረገው የብድር ድጋፍም በጣም ቀላል የወለድ ምጣኔና ተስማሚ የአከፋፈል ሁኔታ እንደሚኖረው አስረግጠው የሚገልጹት ሊቀመንበሩ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከዚህ መሰል ድጋፍ ትርፍ ሳይሆን አገር ግንባታን የመደገፍ ዓላማ ብቻ አንግባ እንደምትንቀሳቀስ አስታውቀዋል፡፡