Wednesday, February 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገርን የማያስቀድም አጀንዳ ፋይዳ የለውም!

‹‹አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ›› እንዲሉ፣ ፋታ የማይሰጡ የአገር ትልልቅ ጉዳዮችን ወደ ጎን ብለው ጥቃቅን ነገሮች ላይ የሚያተኩሩ አፍለኞች እየበዙ ነው፡፡ በተለይ በፖለቲካው ምኅዳር ውስጥ የሚርመሰመሱ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ግለሰቦችና ድኖች፣ ከአገር ደኅንነትና ጥቅም በላይ በመረማመድ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡ የረባ አገራዊ አጀንዳ ሳይኖራቸው በአጋጣሚ ራሳቸውን ያገዘፉ ግለሰቦች፣ ሚዲያውን ጭምር የጥላቻና የቂም በቀል መወጫ አድርገውታል፡፡ የወጣቶችን ደካማ ጎን በመጠቀም በስሜት ኮርኳሪ ቅስቀሳዎች፣ አገሪቱን ከዕለት ወደ ዕለት ሰላምና እረፍት እየነሷት ነው፡፡ ለአገር የሚጠቅም አማራጭ ሐሳብ ሳያቀርቡ፣ በሌሎች ሐሳቦች ላይ በመንተራስ የጥላቻ ቅስቀሳ ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡ መንግሥት ሲሳሳት በበሰለ ሐሳብ መተቸት፣ አላስፈላጊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ወቀሳ ማቅረብና ትክክለኛውን መስመር ማስያዝ ሲገባ፣ የሚቀድመው ስድብና ዛቻ ሆኗል፡፡ በአገሪቱ ሐሳብ የነጠፈ ይመስል ልዩነትን ማክበር ብርቅ እየሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚታወቁባቸው መልካም ሥነ ምግባሮችና እሴቶች እየተጣሱ፣ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ አሳፋሪ ስድቦችና ዘለፋዎች ይሰማሉ፡፡ ለአገር የማይጠቅሙ አጀንዳዎች እየተመዘዙ፣ ከዕለት ወደ ዕለት ወደ ቀውስ መንደርደር ልማድ ሆኗል፡፡ ለአገር የማይጠቅሙ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡

አንድ ሰው የፈለገውን ሐሳብ በነፃነት የማራመድ ተፈጥሯዊ መብት አለው፡፡ ይህ መብት ደግሞ ለሌሎችም ጭምር እንደሚሠራ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ አገር ወደ ተሻለና የሚያስደስት ሥርዓት መንደርደር የምትችለው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲከበሩ ነው፡፡ እነዚህ መብቶች እንዲከበሩ አንዱ ለማኝ ሌላው ተለማኝ መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም ይህንን ሥርዓት በጋራ ለማቆም በልዩነት ውስጥ የጋራ የሆነ ነገር መፍጠር ይገባል፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች የሚደምቁበት ማዕድ እንደሆነ የጋራ ግንዛቤ ሊኖርም ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ አንዱ ጉልበተኛ ሌላው ተንበርካኪ፣ አንዱ ሕግ አክባሪ ሌላው ሕገወጥ ለመሆን መሞከር ከባድ ጥፋት ያስከትላል፡፡ በሌላ በኩል ሕዝብ አገለግላለሁ የሚል ማንም ወገን መጀመርያ ራሱን ከሐሜት፣ ከአሉባልታ፣ ከሴራና ከቂም ነፃ ማውጣት አለበት፡፡ በሕዝብ ስም እየነገዱ ራስን አጉል ነፃ አውጪና አርበኛ በማድረግ፣ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ውስጥ መገኘትም ትክክል አይደለም፡፡ ለአገር የማይጠቅም ድርጊት ውስጥ የሚገባው ለዴሞክራሲ ባህል ባዕድ ሲሆኑ ነው፡፡

  የአገር ጉዳይ ሲነሳ የእያንዳንዱ ዜግነት ኃላፊነት ከባድ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የአገር ሰላምና ፀጥታ ሲደፈርስ ጉዳት የሚደርስባቸው ንፁኃን ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ቀን በሰላም ተውሎ የሚታደርበት እንዲሆን ደግሞ የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ የእያንዳንዱ ዜጋ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሰላም የሚገኘው ከመንግሥት ከፍተኛ ሹማምንት ጀምሮ በእያንዳንዱ ዜጋ ሕግ ሲከበር ነው፡፡ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቱን ሲጠቀም፣ በተቻለ መጠን ለሌሎች ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል፡፡ ይህ ማለት ግን ሌሎች ከራሳቸው ፍላጎትና ዓላማ አንፃር የግለሰቡን ንግግር እየተረጎሙ ጥቃት ይፈጽሙ ማለት አይደለም፡፡ መብትና ግዴታ ተነፃፃሪ ናቸው ቢባልም፣ ግለሰባዊ ነፃነትን ሰፋ አድርጎ ማየት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይረዳል፡፡ በዚህ መንፈስ የሐሳብ ልውውጦች ሲኖሩ፣ ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅም በላይ የአገር ይቀድማል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አልታይ ያለው ይህ ዓይነቱ የጋራ ግንዛቤ ነው፡፡ ጥቃቅንና ተልካሻ ጉዳዮች ታላላቅ አገራዊ ጉዳዮችን እየሸፈኑ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት 16 ወራት በርካታ ክስተቶችን አስተናግዳለች፡፡ መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም የመተባበርና የመተጋገዝ ስሜት ቢዳብር ኖሮ፣ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በመሻገር ብሩህ ተስፋ ማየት አይከብድም ነበር፡፡ ከሥልጣን ወዲያ ማዶ ያለውን የሕዝብ የጋራ አማካይ ፍላጎት ገሸሽ በማድረግ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚደረገው ሽኩቻ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ አሁንም እያደረሰ ነው፡፡ ለዘመናት በሕዝቡ መካከል የሰፈነውን አብሮነት የሚገዳደሩ የጥላቻ ቅስቀሳዎች በየጎራው ይነዛሉ፡፡ የሕዝቡን የጋራ እሴቶች የማይወክሉ አፀያፊ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡ እርግማን ያለ ይመስል የአገሪቱ ልሂቃን መናናቅና መጣላት ይቀናቸዋል፡፡ ከሴረኝነትና ከአሻጥር ውስጥ መውጣት አቅቷቸው የጎሪጥ ይተያያሉ፡፡ ከዚህ በፊት የተሠሩ ስህተቶችን ለመድገም ይሯሯጣሉ፡፡ የመነጋገርና የመደማመጥ ፍላጎት ስለሌላቸው በሴራ ንድፈ ሐሳብ ትንተና ተወጥረው፣ ወጣቶችን ግራ እያጋቡ የነገን ተስፋ ያጨልማሉ፡፡ ይህ ሁሉ ለኢትዮጵያ ምን ይጠቅማል ተብሎ ሲጠየቅ መልሱ ምንም ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም መልካም አጋጣሚዎች እያመለጡ ነው፡፡ አገርን የማያስቀድሙ አጀንዳዎች እየበዙ ብዙዎችን ተስፋ እያስቆረጡ ነው፡፡

አሁን ሰከን ባለ መንገድ መነጋገር ይገባል፡፡ የዓመታት ቁርሾዎችና ጥላቻዎች የሚለዝቡት በመነጋገር ነው፡፡ ትኩረት ለብሔራዊ መግባባት መባል ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ መካን ከሚያደርጉት ችግሮች መካከል ዋነኛው፣ ለመግባባት ሳይሆን ለመጣላት ቅርብ የመሆን አባዜ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው አካልም ሆነ ሌሎች የብሔርተኝነት ካርድ እየመዘዙ መበሻሸቁን ያቁሙ፡፡ ትልልቅ አገራዊ ችግሮች ፋታ እያሳጡ፣ የመበሻሸቂያ አጀንዳዎች መፍጠር ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባና በባህር ዳር የተፈጸመው የከፍተኛ ባለሥልጣናት ግድያ፣ በቅጡ ተቀምጦ ለመነጋገርና የጋራ መፍትሔ ካለመፈለግ የተከሰተ መሆኑን ማመን የግድ ይላል፡፡ ፖለቲካው ውስጥ ከሐሳብ ልውውጥ በላይ ጠመንጃ እንዳይነግሥ ጠንክሮ መሥራት የግድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጉልበትና የሕገወጥነት መንገድ አንገሽግሾታል፡፡ ታሪኩም ከጦርነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ስለሆነ በሚገባ ያውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የብልፅግና መናኸሪያ እንድትሆንለት ይመኛል፡፡ በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊነት መተዳደር ይፈልጋል፡፡ አገርን የማያስቀድሙ አጀንዳዎች ፋይዳ ቢስ ለመሆናቸው ደግሞ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ ምስክር የለም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በኢትዮ ቴሌኮም ላይ ላደረሰው ኪሳራ ክስ ተመሠረተበት

ኩባንያው በግማሽ ዓመት ስምንት ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ገልጿል ኢትዮ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጠጠር ገለልተኛ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

ከ70 በላይ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ዘርፉን ሊቀላቀሉ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...

እስቲ አንገፋፋ!

እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስንነት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው...

ሆድና የሆድ ነገር (ክፍል አንድ)

በጀማል ሙሀመድ ኃይሌ (ዶ/ር) "ሆድ ባዶ ይጠላል..." "ከሆድ የገባ ያገለግላል…” ከጥቂት ዓመታት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገር ሰላም እንዳይናጋ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ!

የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንዲገታ ተደርጎ ጠባሳው ሳይሽር፣ አገርን ሌላ አስከፊ ቀውስ ውስጥ የሚከት የሃይማኖት ውዝግብ ተፈጥሯል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም አግኝታ...

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...