Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማክሰኞ ሐምሌ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት የሲዳማ ዞን መስተዳደር ምክር ቤት ውሳኔን መሠረት በማድረግ፣ ኅዳር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ለመወሰን ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅለት ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡን አስታወሶ፣ በሌላ በኩል ምርጫ ቦርድን እንደ አዲስ የማደራጀት፣ ሥልጣንና ተግባሩን የሚወስነውን ሕግ የማርቀቅና በተወካዮች ምክር ቤት የማፀደቅ፣ የምርጫ ሕጎችን የማሻሻልና ተቋማዊ ለውጦችን የማከናወን እንቅስቃሴ ሲደረግ መቆየቱን ገልጿል፡፡

ከእነዚህ ተቋማዊ ለውጦች መካከል የቦርዱን ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት አድርጎ የተከናወነው የምርጫ ቦርድ አባላት መረጣ ዋነኛው መሆኑን፣ በዚህም መሠረት ከዚህ የቦርድ አባላት መረጣ ሰፊ ምክክርና ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጐበት ከተለየ በኋላ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ተጨማሪ አራት የቦርድ አባላት ሹመት ተከናውኖ ቦርዱ አባላት ተሟልተውለት ሥራውን መጀመሩን አስረድቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ቦርዱ ተሟልቶ ሥራ በጀመረበት ባለፈው አንድ ወር በእንጥልጥል የሚገኙና አስቸኳይ ናቸው ያላቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በቦርዱ አለመሟላት ምክንያት በእንጥልጥል ከቆዩት ጉዳዮች አንዱ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ለቦርዱ የቀረበው የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ ማደራጀት ነው፤›› ሲል አክሏል፡፡

ቦርዱ ሥራ ከጀመረ አንስቶ የሲዳማ ዞን ክልልነትን የሚመለከቱ በተለያዩ ጊዜያት የቀረቡትን ጥያቄዎች ከመመልከቱም በላይ፣ ከክልሉና ከዞን መስተዳድር አመራሮች ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት ማድረጉን አውስቷል፡፡

‹‹እንደሚታወቀው የሲዳማ ዞን የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ የማደራጀት ጥያቄ ከክልሉ ምክር ቤት ለቦርዱ የደረሰው ኅዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲሆን፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/3/ለ/ ለክልሉ የተሰጠው ‹ጥያቄው ከደረሰበት ቀን ጀምሮ በአንድ ዓመት› የሚለው የማደራጀት ጊዜ ገደብ ለቦርዱም ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡ በመሆኑም በሕገ መንግሥቱ የተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ በቀሩት አምስት ወራት ውስጥ፣ ሕዝበ ውሳኔውን ለማከናወን የመጀመሪያ ደረጃ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፤›› ብሏል፡፡

ሕዝበ ውሳኔ የሚከናወነው የሕዝብን ፍላጐትና ውሳኔ ሕጋዊና ነፃ በሆነ አግባብ መሰጠቱን ለማረጋገጥ ነው ያለው ምርጫ ቦርድ፣ በመሆኑም ተገቢና በቂ ዝግጅት አድርጐ ሕዝበ ውሳኔውን ማካሄድ ይችል ዘንድ የሚያደርጋቸው ዝግጅቶች እንዳሉት ገልጿል፡፡
በዚህም መሠረት የሕዝበ ውሳኔ አካሄድ የሚመራበት የሥነ ሥርዓት መመርያ ማዘጋጀት፣ የሕዝበ ውሳኔ አጠቃላይ ጊዜ ሰሌዳና በጀት ማዘጋጀት፣
በሕዝበ ውሳኔ ዝግጅትና ድምፅ መስጠት ሒደት ስለሚኖረው የፀጥታ አጠባበቅ ሁኔታ ግብረ ኃይል ማደራጀትና ዕቅድ ማፅደቅ፣ ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚዎች መመልመል፣ ማሠልጠንና ማሰማራት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መድረክ ማዘጋጀት፣ የድርጊት መርሐ ግብር ማውጣት፣  በሕዝበ ውሳኔ አፈጻጸምም ሒደቱ ላይ የጋራ ምክክር መርሐ ግብሮችን አውጥቶ መተግበር፣ የሰነድና ቁሳቁስ ዝግጅትና ኅትመት ሥራዎች ማከናወን፣ ድምፅ መስጫ ወረቀቶችና ፖስተሮች ማዘጋጀት፣ ማሳተም፣ ማሠራጨት፣ሕዝበ ውሳኔ ድምፅ ማሰጠት፣ ቆጠራና ውጤት ማሳወቅ 
ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል ሒደቱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚኖርባቸው አስታውቋል፡፡ 

በዚህም መሠረት አንደኛ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ከክልሉ መንግሥትና ከዞኑ መስተዳድር ጋር በመመካከር፣ በአሁኑ ወቅት የክልሉም የዞኑም አስተዳደር ዋና ከተማ ሆና የምታገለግለው የሐዋሳ ከተማ የሕዝበ ውሳኔው ውጤት የሲዳማን ክልል መሆን የሚያረጋግጥ ቢሆን፣ በከተማዋ ላይ ሁለቱ አካላት የሚኖራቸውን መብትና ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚነሱ የሀብት ክፍፍል ጥያቄዎች የሚያስተናግዱበትን አሠራር አዘጋጅተው ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ጠይቋል፡፡

ሁለተኛ በአዋጅ 532/1999 አንቀጽ 107 በተጠቀሰው የትብብር ድንጋጌ መሠረት የሕዝበ ውሳኔው ፀጥታና ደኅንነትን (Electoral Security) ማስጠበቅን አስመልክቶ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ፖሊስና የዞኑ ፖሊስ በትብብር የሚሠሩበትን ዝርዝር ዕቅድ እንዲያወጡና ከቦርድ ጋር ተባብረው እንዲሠሩ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ሦስተኛ የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሲዳማ ዞን የሚኖሩ የተለያዩ የሌሎች ብሔር ብሔረሰብ አባላት ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ የሚኖራቸውን ሕጋዊ የመብቶች ጥበቃ አስመልክቶ ግልጽ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲያዘጋጅና ለቦርዱ እንዲያሳውቅ ምርጫ ቦርድ የወሰነ መሆኑን፣ ከዚህም በተጨማሪ የሚመለከታቸው አካላት ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ምላሽ እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2011 .ም. በጽሑፍ እንዲያሳውቁ መወሰኑን ቦርዱ አስታውቋል፡፡ 

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕገ መንግሥቱና በምርጫ አዋጁ የተሰጠውን ኃላፊነትዓለም አቀፍ የምርጫ መሠረታዊ መርሆዎች ጋር በማጣመር ለመወጣት፣ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ በመግለጽ መግለጫውን ቋጭቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...