Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚን ጨምሮ አሥር ከፍተኛ ኃላፊዎች ተከሰሱ

የኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚን ጨምሮ አሥር ከፍተኛ ኃላፊዎች ተከሰሱ

ቀን:

ከ295.2 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸው  በክሱ ተጠቁሟል

የኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ አማረ አምሳሉንና በእስር ላይ የሚገኙትን አቶ ኢሳያስ ዳኘውን ጨምሮ፣ አሥር ከፍተኛ ኃላፊዎች ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተከሳሾቹ ሥልጣናቸውን ያላግባብ ተጠቅመው ተፈጽሟል ከተባለው ወንጀል ድርጊት ከሚገኘው ጥቅም ቀጥተኛ ተካፋይ በመሆን 295,586,120 ብር ጉዳት አድርሰዋል በማለት፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ያቀረበው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ሁለት ክሶች አቅርቧል፡፡ በወንጀል ድርጊቱ ተሳትፈዋል በማለት በክሱ ያካተታቸው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩትን አቶ አማረ አምሳሉ፣ የኤንጂፒኦ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ወልዱ፣ በእስር ላይ የሚገኙትና የአፕሊኬሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ኢሳያስ ዳኘው፣ የኔትወርክ ኢንፍራስትራክቸር ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አብዱልሀፊዝ አህመድ፣ የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ፕሮጀክት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ማስረሻ ጥላሁን፣ የኢንተርፕራይዝ ማኔጅመንት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሰይፈ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የኦፕሬሽን ሰፖርት ኦፊሰር የነበሩት አቶ ፀጋዬ መኮንን፣ የኤንጂፒኦ ምክትል ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አይተንፍሱ ወርቁ፣ የሲቪል ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ጌታሁን ያሲንና የኤንጂፒኦ ሞባይል ፕሮግራም ኃላፊ የነበሩት አቶ ሳሙኤል ፈጠነም በክሱ ተካተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንዳብራራው ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም. የወጣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ) እና 407 (1ሀ እና ለ) እና (3) ላይ ተደነገገውን በመተላለፍ፣ ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል፡፡ ከአቶ አማረ እስከ አቶ አይተንፍሱ ወርቁ ድረስ ያሉ ስምንት ተከሳሾች የኢትዮ ቴሌኮም የኤንጂፒኦ ማኔጅመንት ኮሚቴ ሆነው ሲሠሩ፣ የመንግሥትን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር መፈጸማቸውን አስረድቷል፡፡ ያደረሱት ጉዳትም የኢትዮ ቴሌኮም የግዥ ፖሊሲና መመርያ በመተላለፍ የዕቃና አገልግሎት ግዥ ሲፈጸም በውድድር መሆን ሲገባው፣ ያለ ውድድር በቀጥታ ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ብቻ እንዲሆን በማድረግ፣ ለራሳቸው ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘትና ለኮርፖሬሽኑ ለማስገኘት በማሰብ ድርጊቱን እንደፈጸሙ የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ተከሳሾቹ በኢትዮ ቴሌኮም የግዥ ፖሊሲና መመርያ አንቀጽ 2.5 (1ረ) መሠረት ከ50,000 ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ግዥዎች ከአንድ ድርጅት መፈጸም እንደማይቻል፣ በመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 430/97 አንቀጽ 27 (1 እና 2ሀ) ድንጋጌ መሠረት፣ ከአንድ ድርጅት መግዛት የሚቻለው ተፈላጊው ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚገኘው በዚያ ድርጅት ውስጥ ብቻ መሆኑን እያወቁ፣ ሥልጣናቸውን በመጠቀም ግዥው ከሜቴክ ብቻ እንዲፈጸም ውሳኔ ማስተላለፋቸውን ገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ ከላይ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ ጉዳት አድርሰዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው፣ በሶማሌ ክልል ከሚደረገው የሞባይል ማስፋፊያ ግንባታ አገልግሎት ግዥ ውል ጋር በተያያዘ ነው፡፡ እንደ ዓቃቤ ሕግ ክስ ለፕሮጀክቱ ግንባታ፣ በወቅቱ የነበረው የከተማ ልማት ሚኒስቴር የሲቪል ሥራ በኮንትራክተሮች በምን ያህል ዋጋ እንደሚከናወን መጠየቁን ዓቃቤ ሕግ ጠቁሟል፡፡

ሚኒስቴሩም ተቀራራቢ የመሬት አቀማመጥ ላለው የአፋር ክልል ለዞን አምስት የሰጠው ዝቅተኛ ዋጋ 99,905,731 መሆኑን የገለጸ ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ ግን ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ያቀረበውንና የ221,804,693 ብር ልዩነት ያለውን 321,710,424 ብር ተቋራጭ ሆኖ እንዲሠራ ማድረጋቸውን አብራርቷል፡፡

ሌላው ተከሳሾቹ ከኮርፖሬሽኑ ጋር የኮንትራት ውል ሲዋዋሉ የግንባታ ሥራውን ከኢትዮ ቴሌኮም የጽሑፍ ስምምነት ካልተሰጠው በስተቀር ለንዑስ ተቋራጭ መስጠት እንደማይችል የውል ግዴታ ውስጥ የገባ ቢሆንም፣ ውሉን በማፍረስ ወይም በመጣስ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ለንዑስ ተቋራጮች በ44,333,306 ብር በመስጠት እጅግ የተጋነነ የ277,377,118 ብር ጥቅም ማግኘቱንም አክሏል፡፡ ተከሳሾቹ የሞባይል ማስፋፊያ ግንባታ ግዥውን ማስቆም ሲገባቸውና ለግዥው የሚያስፈልገውን የስፔስፊኬሽን ዝርዝር መሥፈርቶችን የያዘ ሰነድ ተዘጋጅቶ አገልግሎቱን ለሚያቀርበው ለኮርፖሬሽኑ መላክ ሲገባው፣ ባልተላከበትና ግዥው እንዲፈጸም የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አመራር ቦርድ የተፈቀደበት ወይም የፀደቀበት ሰነድ ሳይኖር፣ ተከሳሾቹ ግዥው በኮርፖሬሽኑ እንዲፈጸም ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር አስረድቷል፡፡

አቶ አማረ የመጀመርያውን የ204,981,630,630 ብር ውል ሲፈራረሙ፣ አቶ ኢሳያስ ደግሞ የ289,827,072 ብር የተሻሻለውንና ሁለተኛውን እንዲሁም የ321,710,424 ብር ሦስተኛውንና የተሻሻለውን ውል መፈረማቸውንም ገልጿል፡፡ አራተኛውንና የተሻሻለውን የ322,628,124 ብር ውል ደግሞ አቶ አይተንፍሱ ወርቁ መዋዋላቸውን አክሏል፡፡   

ሜቴክ የግንባታ ዕቃዎችን ከጅግጅጋ ወደ ግንባታ ጣቢያዎች በራሱ ትራንስፖርት እንዲሚያደርስ በውሉ የተካተተ ቢሆንም ከጅግጅጋ እስከ ጎዴ፣ ጊነርና ነገሌ ድረስ ያጓጓዘበትን 397,716 ብር ኢትዮ ቴሌኮም እንዲከፍል አቶ አይተንፍሱ በመስማማታቸው፣ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ጠቁሟል፡፡

የሞባይል ፕሮጀክቱ በትክክል ከተሰጠው የግንባታ ስፔስፊኬሽን ጋር አስተያይቶና በመሐንዲስ ተረጋግጦ ርክክብ ማድረግ ሲገባ፣ ርክክብ ላልተፈጸመባቸው 51 ሳይቶች 69,027,085 ብር ክፍያ እንዲፈጸም ያደረጉት አቶ ኢሳያስና አቶ አብዱልሀፊዝ መሆናቸውንም ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በገባው ውል መሠረት ፕሮጀክቱን ማስረከብ ሲገባው በአምስት ዓመታት ዘግይቶ በማስረከቡ በውሉ መሠረት 4,356,626 ብር ከሚከፈለው ላይ ቀንሰው መክፈል ሲገባቸው ሳይቀንሱ መቅረቱንም ጠቁሟል፡፡

በአጠቃላይ የመፀዳጃና የጥበቃ ሠራተኞች ቤት ግንባታ ጋር ተደማምሮ ተከሳሾቹ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም፣ በመንግሥት ላይ 295,586,120 ብር ጉዳት በማድረሳቸው የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ አቶ አማረ አምሳሉ፣ አቶ ወልደ ጊዮርጊስ ወልዱ፣ አቶ ሰይፈ ኃይለ ሥላሴ፣ አቶ ፀጋዬ መኮንን፣ አቶ ጌታሁን ያሲንና አቶ ሳሙኤል ፈጠነ በሌሉበት የተከሰሱ ሲሆን፣ በማረሚያ ቤት የሚገኙት አቶ ኢሳያስ ዳኘውና አቶ አብዱልሀፊዝ አህመድ፣ አቶ ማስረሻ ጥላሁንና አቶ አይተንፍሱ ወርቁ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በችሎት ለተገኙት ተከሳሾች ክሱን በማንበብ፣ የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...