Wednesday, October 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናደኢሕዴን የክልል እንሁን ጥያቄዎችን ለመፍታት በምሁራን ጥናት ግኝት ላይ መግባባት ተፈጥሯል አለ

  ደኢሕዴን የክልል እንሁን ጥያቄዎችን ለመፍታት በምሁራን ጥናት ግኝት ላይ መግባባት ተፈጥሯል አለ

  ቀን:

  የሲዳማና የወላይታ ዞኖች ሰንደቅ ዓላማዎቻቸውን ሰቅለዋል

  የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአሥር ተከታታይ ቀናት ካካሄደው ስብሰባ በኋላ ባወጣው ባለ ስድስት ነጥብ መግለጫ አገራዊ የሰላምናፀጥታ ሁኔታን ከአኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ መገምገሙን በመግለጽ፣ የክልል እንሁን ጥያቄዎችን ለመፍታት በምሁራን ባስጠናው ጥናት ላይ ተወያይቶ መግባባት ላይ መድረሱን አስታወቀ፡፡

  ሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ድርጅታችን የክልሉን ሕዝቦች ጥያቄ በበቂ መረጃና ዕውቀት ላይ ተመሥርቶና ሕዝቡን ባሳተፈ መንገድ ለመመለስ ላለፉት ሰባት ወራት ባስጠናው ጥናት መሠረት ምላሽ ለመስጠት የተወያየ ሲሆን፣ የሁሉንም ሕዝቦች ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ውሳኔም አስተላልፏል፤›› ብሏል፡፡ ‹‹የክልል እንሁን ጥያቄዎችን ለመፍታት ሳይንሳዊ ጥናት በምሁራን ቡድን ያስደረገው ድርጅታችን፣ በጥናቱ ግኝት ላይም ሰፊ ውይይት በማካሄድ መግባባት ፈጥሯል፤›› በማለት በመግለጫው አስረድቷል፡፡

  ጥናቱ ደረጃውን የጠበቀ አሳታፊና ትክክለኛ ውሳኔ ላይ ለመድረስ በሚያግዝ አግባብ መመራቱን ማረጋገጡን፣ በጥናቱ ደኢሕዴን የደቡብ ክልልን ሕዝብ መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተገኙ ትሩፋቶች፣ ተግዳሮቶች፣ መንስዔዎችና የመፍትሔ አማራጮችን የያዘ ስለመሆኑ በጥልቀት በመፈተሽ ለቀጣይ የድርጅት የመሪነት ሚና፣ እንዲሁም የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን በጥንካሬ መውሰዱን ገልጿል፡፡

  በመሆኑም በወቅታዊ አገራዊና ክልላዊ የፖለቲካና የፀጥታ ሁኔታ፣ እንዲሁም በክልሉ የሚነሱ ተጨማሪ ክልል ሆኖ የመደራጀት ጥያቄዎች ላይ ጊዜ ወስዶ በጥልቀት ኃላፊነት በተሞላበትና በሰከነ ሁኔታ መምከሩን ደኢሕዴን አስታውቋል፡፡

  በክልል የመደራጀት ጥያቄ የሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን ድርጅቱ እንደሚገነዘብ፣ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ሲነሳ የነበረው ከአንድ አካባቢ ብቻ ባይሆንም ጥያቄውን በጥናት ላይ ተመሥርቶ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት በድርጅቱ አሥረኛ ጉባዔ በተወሰደው አቋም መሠረት በዝርዝር ሕዝቡን ያሳተፈ ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን፣ በጥናቱ የቀረቡ አማራጮችን በጥልቀት በመመርመር የሕዝቡን የጋራ ዘላቂ ጥቅም የሚያረጋግጠውን አማራጭ በመውሰድ የክልል አደረጃጀት ጥያቄዎች በሚመለሱበት አግባብ ላይ አቋም መወሰዱን ጠቁሟል፡፡ ‹‹በክልላችን መላው ሕዝብ ምክክርና ውይይት የሚያደርግበት ሆኖ በአንድ በኩል በጥናቱም የተገኘውን የክልሉ ሕዝቦች አብሮ የመቀጠል ፍላጎትን ባከበረ፣ በሌላ ጎኑ ደግሞ የጉባዔውን ውሳኔ ተግባራዊ ባደረገ መንገድና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የመምራት ኃላፊነት ለመወጣት ማዕከላዊ ኮሚቴው ተስማምቷል፤›› ሲል አክሏል፡፡

  ወቅታዊ አገራዊ የፖለቲካና የፀጥታ ሁኔታን በተመለከተ በእስካሁኑ ሒደት የታዩ አዎንታዊ ውጤቶችን የሚፈታተኑ ጉዳዮች መኖራቸውን መገምገሙን ማዕከላዊ ኮሚቴው ገልጾ፣ በመሪ ድርጅቱ ኢሕአዴግ መሪነትና በሕዝቦች ተሳትፎ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳይቀለበስ ሁሉም አካላት በጋራ የኃላፊነት መንፈስ እንደሚገባቸው አስምሮበታል፡፡

  በአገር ደረጃ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ተስፋ የፈነጠቁ ጅምር ውጤቶች የታዩበት መሆኑን፣ በጥንቃቄ ካልተያዘ የአገርን ህልውና የሚፈታተኑና ሕዝቡን ሥጋት ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉ ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ መሆናቸውን መገንዘቡን ጠቁሟል፡፡ በቅርቡ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችንና የአገሪቱን የጦር መኮንኖች እስከ ሕይወት ማጥፋት ድረስ የደረሰውን ጥቃት ድርጅቱ በፅኑ እንደሚያወግዝና በፅኑም እንደሚታገል አስታውቋል፡፡

  ማዕከላዊ ኮሚቴው ያነሳው ሌላው ነጥብ በእህት ድርጅቶች መካከል ከድርጅታዊ ዲሲፕሊን ውጪ የሚወጡ መግለጫዎችና ይህንንም ተከትሎ እየተደረሱ ያሉ ድምዳሜዎች ከኢሕአዴግ መርህ ውጪ መሆናቸውን በመገምገም፣ የትኛቸውንም ዓይነት የሐሳብ ልዩነቶችን እንደ ወትሮው ሁሉ በድርጅቱ ባህል መሠረት ማስተናገድ እንደሚገባ መገምገሙን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደኢሕዴን በውስጡ ያሉ ችግሮችን ታግሎ የሚያርምና የሚያጋጥሙ ችግሮችና ፈተናዎችን ከሕዝቡ ጋር በመሆን የመፍታት ባህልና ልምድ ያለው ድርጅት መሆኑን ገልጾ፣ ከዚህ ውጪ እኔ አውቅልሃለሁ በሚመስል መንገድ ከሩቅ የሚሰነዘርና ሒደቱን ያልተከተለ አመራር የማይቀበል መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው ያስገነዝባል ብሏል፡፡

  ክልላዊ ወቅታዊ ፖለቲካና የፀጥታ ሁኔታ ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው በዝርዝር መገምገሙን አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት አገራዊ የፖለቲካና የፀጥታ ድባብ ተከትሎ በክልሉ ውስጥ የሚታዩ አዝማሚያዎች የሕግ የበላይነት አደጋ ውስጥ በመግባቱ፣ የኢመደበኛ አደረጃጀቶች እንቅስቃሴዎች ሥርዓት መያዝ እንዳለባቸው ተሰምሮበታል በማለት ገልጿል፡፡

  ‹‹በዚህ ሒደት ለታዩ ጉድለቶች አገራዊ ሁኔታ የራሱ አሉታዊ አስተዋጽኦ ያለው ቢሆንም፣ ዋናው ችግር የድርጅታችን ውስጣዊ ሁኔታ መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው በጥልቀት ተወያይቷል፡፡ ከድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ በየደረጃው ያለው አመራር ድርሻ ሰፊ መሆኑም ታይቷል፡፡ ስለሆነም እንደ አገርና እንደ ክልል ከገባንበት ያለመረጋጋት ለመውጣት የድርጅቱ ውስጣዊ ጥንካሬ ወሳኝ መሆኑን፣ የድርጅቱ አመራሮች በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስና ሕዝባዊ ውግንና መንቀሳቀስ የሚጠይቀን ወቅት ላይ መሆናችንን መተማመን ላይ ተደርሷል፡፡ በመብት ጥያቄ ሽፋን የሚደረጉ ማናቸውንም ኢመደበኛ እንቅስቃሴዎችን ሥርዓት ማስያዝ፣ እንዲሁም የሕዝቦችን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥና የሕግ የበላይነትን ማስከበር ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው ድምዳሜ ላይ ደርሷል፤›› ብሏል፡፡

  የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኅብረ ብሔራዊነት ላይ እየተገነባ ባለው የፌዴራል ሥርዓት ትሩፋቶችን ያስመዘገበ መሆኑን፣ በሒደቱ የታዩ ተግዳሮቶችን በማረም አገሪቱ በደረሰችበት የዕድገት ደረጃ በማሻሻል ለፌዴራል ሥርዓቱ ይበልጥ መጎልበትና ቀጣይነት ድርጅቱ የሚታገል መሆኑን አቋም አስታውቋል፡፡ ከሁሉ በላይ ኅብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጎልበት ማዕከላዊ ኮሚቴው አጽንኦት መስጠቱን ገልጿል፡፡

  በእያንዳንዱ አካባቢ ያለውን የልማት ሁኔታ በተመለከተ በድርጅቱ መሪነት በክልሉ የተመዘገቡ የልማት ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ የመልካም አስተዳደርና የአመራር ሥርዓት ላይ የሚታዩ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው አቋም መያዙን አስረድታል፡፡ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በክልሉ ውስጥ ያሉ ሕዝቦች በጋራ መልማት እንዳለባቸው በመግባባት፣ ሕዝቡን ባሳተፈ ሁኔታ የክልሉን ሕገ መንግሥት ከማሻሻል ጀምሮ ሌሎች ዝርዝር የሕግ ማዕቀፎች እንዲዘጋጁ አቋም መወሰዱን ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

  ለድርጅቱ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች፣ ለክልሉ ሕዝቦች፣ ለአርሶና አርብቶ አደሮች፣ ለወጣቶችና ሴቶች፣ ለምሁራን፣ ለባለሀብቶችና ለንግዱ ማኅበረሰብ፣ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ለእህት ድርጅቶችና አጋሮች፣ እንዲሁም ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ገንቢና አዎንታዊ ሚናቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል፡፡

  ይህ በዚህ እንዳለ በደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄያቸውን አፅድቀው ለክልሉ መንግሥት ካቀረቡት 11 ዞኖች ውስጥ፣ የሲዳማና የወላይታ ዞኖች የራሳቸውን ሰንደቅ ዓላማ በሐዋሳና በሶዶ ከተሞች ሰቅለዋል፡፡ ደኢሕዴን ባወጣው መግለጫ ይፋ ባያደርገውም፣ የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል በማለት የሲዳማ ዞን ወጣቶች በሐዋሳና በአካባቢው ከተሞች ደስታቸውን እየገለጹ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በወላይታ ዞንም ለሁለት ቀናት ስብሰባ ከተካሄደ በኋላ በተደረሰበት ስምምነት መሠረት፣ የወደፊቱን የወላይታ ክልለ ይወክላል የተባለለት ሰንደቅ ዓላማ ተውለብልቧል፡፡

  ሃምሳ ስድስት ብሔርና ብሔረሰቦች ባሉበት የደቡብ ክልል በክልልነት ጥያቄ ምክንያት ችግር እንዳይፈጠር ሥጋት የገባቸው ዜጎች፣ ሁኔታውን የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱ እንዲያጤኑት እያሳሰቡ ነው፡፡ ከኃይል ይልቅ ሕጋዊነት እንዲቀድምም ጠይቀዋል፡፡ በተለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርቡ ክልል መመሥረት ሕገ መንግሥዊ መብት በመሆኑ ተቀባይነት እንዳለው፣ ሕጋዊ መንገድ የማይከተል ከሆነ ግን የፌዴራል መንግሥት በሶማሌ ክልል ያደረገውን ጣልቃ ገብነት እንደሚደግም ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡

  ያም ሆነ ይህ ደኢሕዴን ለጉዳዩ በምሁራን የጥናት ግኝት ላይ መግባባት መፈጠሩን ቢገልጽም፣ ከጥናቱ በላይ የተራመደ እንቅስቃሴ መታየቱ ግራ መጋባት ፈጥሯል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img