ወ/ሮ ማርታ ሙሉና ባለቤቷ በአሥር ዓመት ልጃቸው የንባብ ፍላጎት ምክንያት የሱፐር ሪደርስ ዲጂታል (ኦንላይን) ቤተ መጻሕፍት እንዳቋቋሙ ይናገራሉ፡፡ ልጃቸው አዳቤል ቢንያም የትምህርት ቤቷ ተማሪዎች እንዲያነቡ በሚደረገው ክትትልና እገዛ እንዲሁም ካነበቡት መጻሕፍት በሚጠየቁት ጥያቄ ተሳታፊ ነበረች፡፡ በአሥራ አንድ ወራት ውስጥም 366 መጻሕፍት በማንበብ ከትምህርት ቤቷ ከሦስት ተሸላሚዎች አንዷ ሆናለች፡፡ ሕፃን አዳቤል በ18 ወራት ውስጥ 500 መጻሕፍት እንዳነበበች ወላጆቿ ይገልጻሉ፡፡ ትምህርት ቤት የምታገኘውንና ቤተሰብ የሚገዛላትን መጻሕፍት የምታነበው አዳቤል፣ ትምህርት ቤት ሲዘጋ መጻሕፍት የማግኘት ዕድሏ ግን ጠባብ ነው፡፡ ይህንን ያዩት ቤተሰቦቿ ለራሷና እሷን መሰል ሕፃናት መፍትሔ ይሆናል ብለው ከዘጠኝ ወራት በፊት ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት ከፍተዋል፡፡ በቤተ መጻሕፍቱና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሔለን ተስፋዬ ወ/ሮ ማርታን አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት ምንድነው?
ወ/ሮ ማርታ፡- ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት መጻሕፍትን በወረቀት መልኩ ተጠርዘው ከምናገኛቸውና በአብዛኛው ከተለመደው በተለየ በኦንላይን የሚስተናገድበት ነው፡፡ መጻሕፍቱ ኮምፒዩተሮች ላይ ተጭነው በተፈለገ ጊዜ በቀላሉ ልንጠቀመው የምንችለው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ብክነት ሳይኖር፣ በአነስተኛ ወጪና ቦታ ሳንይዝ ልንገለገልበት የምንችለው ቴክኖሎጂ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የሱፐር ሪደርስ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው? ማንበብ የሚፈልጉ ልጆች ምን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል? የመጻሕፍቱ ይዘት ምን ይመስላል?
ወ/ሮ ማርታ፡- የሱፐር ሪደርስ ተጠቃሚዎች ማንበብ ከሚችል ሕፃን እስከ 18 ዓመት ድረስ ነው፡፡ ማንበብ የፈለገ ልጅ በመጀመሪያ ከቤተሰቦቹ ጋር በመምጣት መመዝገብ ይችላል፡፡ ከተመዘገበ በኋላ መመዘኛ ፈተና እንሰጣለን፤ ፈተናውን ካለፉ ዕድሜያቸውንና የትምህርት ክፍላቸውን ያገናዘበ መጻሕፍት እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ይህም ከአቅም በታች ወይም በላይ የሆኑ መጻሕፍት እንዳያነቡ ለማድረግ ነው፡፡ መጻሕፍቱ የተለያዩ ይዘቶች አሏቸው፡፡ በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ቤተ መጻሕፍት ታሪክ፣ ኬሚስትሪና ሌሎችም እንደሚቀመጡት ሁሉ፤ በሱፐር ሪደርስም በተለያየ መልኩ የተዘጋጁ መጻሕፍት በኦንላይን አካቷል፡፡ እንደ ልጆቹ ፍላጎትና ዝንባሌ የፈለጉትን እንዲያነቡ ይፈለጋል፡፡ ባላቸው ፍላጎትና ተሰጥኦ አድገው የተሻሉ እንዲሆኑ በእነሱ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ንባብ መሆን አለበት፡፡ እስካሁን ስድስት ሺሕ ያህል መጻሕፍት አሉን፡፡ ፕሮግራማችን መሠረት ቁጥሩ የሚጨምር ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ልጆቹ የቤተ መጻሕፍቱ ተጠቃሚ ለመሆን ሲመዘገቡ ምዘና እንደምትሰጡት ሁሉ፣ በየጊዜው ለውጣቸውን የምታዩበት አሠራር አለ?
ወ/ሮ ማርታ፡– መጽሐፉ መቼ መነበብ እንደጀመረ፣ ምን ያህል ሰዓትና ምን ያህል ቃላት እንደተነበበ ፕሮግራሙ ያሳያል፡፡ በሥዕልና በድምፅ የታገዘ ስለሆነም አንባቢዎችን በአማራጭ ዕውቀት ያስቀስማል ብለን እናምናለን፡፡
ቤተ መጻሕፍቱ በዘጠኝ ወር ዕድሜው እስካሁን ከ100 በላይ አባላት አሉት፡፡ የልጆቹ ቤተሰቦች የልጆቻቸውን ለውጥ እያዩ የሚሰጡን ምላሽ አዎንታዊ ነው፡፡ የበለጠ እንድንሠራ የሚገፋፋ ነው፡፡ ለጊዜው የመጻሕፍቱ ቋንቋ እንግሊዝኛ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ለወደፊቱ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲሆን እናስባለን፡፡ ንባቡ ድምፅ ስላለው የእንግሊዘኛ ሰዋስው በቀላሉ እንዲረዱ ያግዛቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዓለም ከወረቀት ነፃ እየሆነች የመጣችበት ጊዜ ስለሆነ ትውልዱን ለዚህ ማዘጋጀት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ታሪኮች ተረቶችና ሌሎችም የተጻፉት በአብዛኛው በአማርኛ ነው፡፡ ልጆች ደግሞ የአገራቸውን ታሪክ እያወቁ ማደግ አለባቸው፡፡ አማርኛ ቋንቋ እንዴት ፕሮግራሙ ውስጥ አልተካተተም?
ወ/ሮ ማርታ፡- እኛም ይኼን ሳናስብ ቀርተን አይደለም፡፡ ሁሉም ልጆች ታሪካቸውን እያወቁ ቢያድጉ እኛን ጨምሮ ሁሉንም የሚያስደስት ነው፡፡ ነገር ግን ትልቁ ችግር አብዛኛው የልጆች መጻሕፍት በተለይ ለኦንላይን ገበያ የሚጻፉት በእንግሊዝኛ ነው፡፡ እንደ አገርም የኦንላይን የመገበያያ ዘዴው ዘመናዊ አለመሆኑ በአማርኛም ሆነ በሌሎች የአገራችን ቋንቋዎች የተጻፉ የልጆች መጻሕፍትን ለማስገባት ክፍተት በመኖሩ የተነሳ እንጂ ሳናስብበት ቀርተን አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ዲጂታል ቤተ መጻሕፍቱ በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ ነው ወይስ ክልሎችንም ያማክላል?
ወ/ሮ ማርታ፡- እስካሁን ፕሮጀክታችን የሚተገብረው በአዲስ አበባ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ ወኪል በመክፈት በስፋት ለመሥራት እያሰብን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ ፕሮጀክት ምናልባት ቤታቸው ውስጥ ኮምፒዩተር፣ ታብሌት ላላቸው ቤተሰቦች ወይም አቅም ላላቸው ብቻ መሆኑ ተደራሽነቱን አይገድበውም?
ወ/ሮ ማርታ፡- እንደ አገር ካየን አሁን ያሉት ተማሪዎች ነገ ለሚመጡት ትውልዶች መንገድ ጠራጊዎች ናቸው፡፡ ችግሩን ቀስ በቀስ ይቀረፋል፡፡ ተጠቃሚዎቹ ጥቂቶች ብቻ ናቸው ብለን ያሉትንም የምንገታ ከሆነ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ነው የሚሆነው፡፡ ብንችል ለሁሉም የሚደርስ ቢሆን ደስ ይለን ነበር፡፡ ነገር ግን ችግሩ እንደ አገር ስለሆነ ቢያንስ እኛ እነዚህን የተሻለ ብናደርግ እነሱ ደግሞ ብዙ የተሻለ ማፍራት ይችላሉ ብለን አስበን ነው፣ የቴክኖሎጂ አማራጭ ያላቸውን ልጆች የንባቡ ተጠቃሚ እያደረግን ያለነው፡፡
ሪፖርተር፡- አንድ አንባቢ በዓመት እስከ ስንት ብር ሊያወጣ ይችላል?
ወ/ሮ ማርታ፡- በዓመት 1,650 ብቻ ነው የምናስከፍለው፤ በፈለጉት ሰዓት መጻሕፍት ማንበብ ይችላሉ፡፡ ለዓመት የሚከፈለው ያለምንም ገደብ ማንበብ እንዲችሉ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የማንበብ ባህል እናምጣ በሚባልበት ጊዜ ዋጋው አልተወደደም?
ወ/ሮ ማርታ፡- ልጆች የተመጣጠነ ምግብ መመገብ እንዳለባቸው ሁሉ አዕምሮአቸውን በንባብ መመገብ አለብን፡፡ ወጪውን በተመለከተ አልበዛም፡፡ አንድ ቤተሰብ የልጅ ልደት ለማክበርና ለስጦታ ብለው የሚያወጡት ምን ያህል እንደሆነ ቢታሰብ በዓመት አንድ ሺሕ ስድስት መቶ ሃምሳ ብር አይጎዳም፡፡
ሪፖርተር፡- በሥራው ምን ችግር አጋጠማችሁ?
ወ/ሮ ማርታ፡- ትልቁ ችግር የኔትወርክ ችግር ነው፡፡ ችግሩ እንደ አገር ነው፣ በሒደት ይፈታል ብለን እናስባለን፡፡ ሌላው አንዳንድ ቤተሰቦች ለንባብ ያላቸው አመለካከት ያነሰ ነው፡፡ ያው እርሱም በጊዜ ይፈታል ብለን እናስባለን፡፡ በመጨረሻም ልጆቻችን እኛ በሄድንበት ውጣ ውረድ መሄድ ስለሌለባቸው አስተካክለን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ ያን ለማድረግ ደግሞ በዕውቀትና በቴክኖሎጂ የታገዘ መንገድ መከተል ተገቢ ነው፡፡ ልጆች እንዲያነቡ ማገዝ፣ ቀርቦ ፍላጎታቸውን መገንዘብ መጪውን ትውልድ የተሻለ ለማድረግ ያግዛል፡፡