Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየመፍትሔ አቅጣጫዎች ለዘላቂ አስተሳሰብ ለውጥ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን

የመፍትሔ አቅጣጫዎች ለዘላቂ አስተሳሰብ ለውጥ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን

ቀን:

(የመጨረሻ ክፍል)

በሺፈራው ሉሉና በእንግዳሸት ቡናሬ

አገራችን በከፍተኛ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኀበራዊ ቀውሶች ውስጥ ከገባች 50 ዓመታት (ግማሽ ምዕተ ዓመት) ሊሆነን ነው፡፡ ይህ አገራችን የገባችበት ቀውስ፣ ጊዜ በገፋ ቁጥር፣ ከመስከን ይልቅ እየተባባሰ ሲሄድ ይታያል፡፡ ለዚህ የተበላሸ ሁኔታ መባባስ መንስዔ የሚሆኑት ምክንያቶች ብዙ ናችው፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች ዋናዎቹ፣

- Advertisement -

1. የካርል ማርክስና ፍሪድሪክ ኤንግልስን (Karl Marx and Fridrich Engels) የኮሙዩኒዝም ፍልስፍና ያለአንዳች ጥያቄ የአገራችን መፍትሔ አድርገን መቀበላችን፣

2. የሶሺያል ዳርዊኒዝም የፖለቲካ ፍልስፍና ዋለልኝ መኮንን ከስታሊን ፍልስፍና ገልብጦ ባቀረበው የዘውግ ወይም የብሔር ጥያቄን ተገን አድርጎ በመግባቱና ይኼንንም የአገራችን መፍትሔ አድርገን መቀበላችን፣

3. አገራዊና መልካም አስተሳሰብ ያላቸው ልሂቃን ከፖለቲካው መገለልና እንዲጠፉ መደረጋቸው ናቸው፡፡

የነዚህም ውጤት በቅርቡ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅና፣ ለማመንም በሚቸግር ሁኔታ በሻሸመኔ፣ በቡራዩ፣ በሐዋሳ፣ በጭልጋ፣ በጌዲዮ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በከሚሴ፣ በካራቆሬ፣ በአጣዬ፣ ወዘተ. በሰላማዊ መንገድ በሚኖር ሕዝብ ላይ የተፈጸሙ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች የነበሩንን የጋራ እሴቶችና ፈሪኃ እግዚአብሔርን ያሳጡን መሆናቸውን ለማየት ተገደናል፡፡ ጄኔራል ዓብይ አበበ ‹አውቀን እንታረም› በሚል መጽሐፋቸው እንዲህ ይላሉ፣

‹‹አገር ምን እንደሆነች ሁላችንም እናውቃለን ነገር ግን አገር የምትኖርበትን ዘዴ ገና አጥርተን ያወቅነው አይመስለኝም፡፡ ስለዚህም የአንድ አገር ሰዎች መሆናችንን እንድናውቀውና ለአንድነታችን መጠጊያ የሆነችውን እናታችንን ኢትዮጵያን ለማገልገል፣ ለማኖርና ለኑሯችንም ለመሥራት የምንችለው በአንድ መንፈስ ስንሠለፍና በንፁህ ሕሊና ፀንተን ስንተባበር ብቻ ስለሆነ፣ ወደዚህም በቅንነት እንድንራመድ ስለሚያሻ የእያንዳንዳችን መንፈስ  ከደካማነት ወደ ፅኑነት መለወጥ አለበት፤›› ‹‹መተዛዘንን፣ መተሳሰብን፣ ጠንካራ መንፈስን፣ ቅን ባህሪን፣ ፍቅርን፣ እርስ በርሳችን መተዋወቅንና አለመናናቅን ማወቅ ይገባናል፡፡ ይህም በመካከላችን ከሌለ ምንም ሊኖር አይችልም፡፡ ወደ መጥፎ መንፈስ የሚመራ ሁሉ መጥፎ ነገሮችን እያራባ ሌላውን ሁሉ ከትቦ እንዳይጎዳ ያሠጋልና በኑሮ ውስጥ ምን ምን እንዳለ ተረድቶ ከአሁኑ መገታት ያስፈልግ ይመስለኛል፤›› በመቀጠልም እንዲህ ይላሉ፣ ‹‹ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት እንደሆነ ደህና አድርገን እናውቃለን፣ ስለዚህ ዞረን ዞረን የምንገባበትን አገራችንን፣ ቤታችንን፣ ኖረን ኖረን የምንቀበርባትን መሬታችንን እንደዋዛ አንያት፤››

‹‹ሁላችንም ነገ ጥለነው ለምንሄደው ነገር አንጓጓ፣ አገራችን ካልን የአገራችን ነገር ከሁሉ በፊት ይቅደም፣ አገራችንን ካልን ደግሞ ይዘን እናሻግራት፣ እንጠብቃት፣ ከልብም እንውደዳት፣ አንድነትም ሆነን እናገልግላት፣ ከእኛ በኋላ ለሚመጡትም አገራቸው ሆና እንድትቆይ፣  እንድትወራረስ  አድርገን  እንያዛት፤›› ‹‹ሰው በሰው ክፉ መሆን አይገባውም፣  በተለይም የአንድ አገር ሰዎች፣ የአንድ እናት ልጆች ማለት ነንና መተዛዘንን፣ መተሳሰብንና መፈቃቀርን ማወቅ ግዴታችን አድርገን እንያዘው፤›› ወንድም በወንድሙ ላይ በከንቱ አይነሳ የከንቱ ነገርንም ምንጮች አይቆፍር፡፡ ሊቅ አፉን ይክፈት፣ በጎ ምግባርንና የአገር ፍቅርን ከመናገር፣ ከመስበክ አይቦዝን፡፡ ‹‹ሁላችንም እናልፋለን፣ ይህንን የማያምን ቢኖር፣  የነበሩ እነማን አሉ? ማለፋችንን ካመንን ስለምን በቀና መንገድ አንሄድም? ስለምንስ ቅን ሠርተን አናልፍም?››

በመጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለው ተጽፏል

የጥበብ መጀመርያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፣ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሳፅን ይንቃሉ (መጽሐፈ ምሳሌ፣ ምዕራፍ፣ አንድ፣ ቁጥር፣ ሰባት)። ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትዕዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ ዕውቀትን ብትጠራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሳ፣ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፣ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም ዕውቀት ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና ከአፉም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፣ እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን ያከማቻል ያለ ነውር ለሚሄዱትም ጋሻ ነው፣ የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል የቅዱሳኑንም መንገድ ያፀናል። የዚያን ጊዜ ፅድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ። (መጽሐፈ ምሳሌ፣ ምዕራፍ፣ ሁለት፣ ቁጥር፣ 1 – 9)

ነገርን ከሥሩ ውኃን ከምንጩ

አሁን አገራችን የገባችበት ችግር በዋንኛነት በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ ዓለምን ያናወጠውን የዝግመተ ለውጥ ውላጅ የሆነውን የሶሺያል ዳርዊኒዝም (የዘውግ/ብሔር/ጎሳ) ፖለቲካ ሐሳብ ወደ አገራችን ያለአንዳች ጥያቄ መቀበላችን ነው፡፡ ይህ ዓለምን ያናወጠ ፍልስፍና የመጀመርያ መሥፈርቱ እግዚአብሔር/ፈጣሪን መካድ ነው፡፡ ይህን ፍልስፍና ወደአገራችን ያመጡልን ወይም ያሠራጩልን ወይም የተሠራጨው በመጀመርያ እግዚአብሔርን/ፈጣሪን በመካድ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በአውሮፓ ሰዎችን በተለያየ ደረጃ የመከፋፈያ ሥልት እንዲቀርፁ ምክንያት ሆኗል፡፡ የመከፋፈያ ሥልት በማውጣትም ሰውን የበላይና የበታች አድርገው ለመግዛት ተጠቅመውበታል፡፡ በመሆኑም ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን፣ ደቡብ አሜሪካንና ኤስያን በመውረር ሕዝቡን እንደ እንስሳ እንዲገዙት አስችሏቸዋል፡፡ ሆኖም ግን በአውሮፓ የከፍተኛ ቅራኔ መንስዔ በመሆኑ ከዚህ አስተሳሰብ በመውጣት በሰው መብት ላይ ብቻ ወደተመሠረተ ፖለቲካዊ ፍልስፍና እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል፡፡ ሆኖም ግን በዚህ ውስጥም ቢሆን የዝግመተ ለውጥ አስተሳሰብ መልኩን ቀይሮ እየሠራ ይገኛል፡፡

ይህ አስተሳሰብ በአውሮፓ ከተጀመረ ከ100 ዓመት በኋላ መነሻውን ሳንገነዘብ፣ የሚያስከትለውን ችግር ከሌሎች አገሮች እንኳን ሳንማር ወደ አገራችን አምጥተን፣ እግዚአብሔርን ክደን፣ እኛም እንስሶች እንኳን የማይፈጽሙትን ተግባር ልንፈጽም ችለናል፣ አሁንም እየፈጸምን እንገኛለን፡፡ ላለፉት 27 ዓመት እግዚአብሔር/ፈጣሪ መኖሩን የካደው ትውልድ ወደ እግዚአብሔር/ፈጣሪ መመለስ የጀመረ ቢሆንም፣ አብዛኛው የያዘውን ፍልስፍና አውልቆ አልጣለውም፡፡ ወደ እግዚአብሔር/ፈጣሪ የተመለሰ ሰው የእግዚአብሔር ያልሆነውን ከውስጡ አራግፎ መጣል ይጠበቅበታል፡፡ ያልተለወጠ ሰው የእግዚአብሔርን/ፈጣሪን ስም ይጠራል በዚያው አንደበቱ ደግሞ መለያየትንና ዘረኝነትን ይሰብካል፡፡

በእርሱ (አንደበት) ጌታንና አብን እንባርካለን፣ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፣ ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፣ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም (የያዕቆብ መልዕክት ምዕራፍ፣ ሦስት፣ ቁጥር፣ 9-10)። ነገር ግን መራራ ቅንአትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፣ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፣ ነገር ግን የምድር ነው፣ የሥጋም ነው፣ የአጋንንትም ነው፣ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ሥፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና። ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመርያ ንፅህት ናት፣ በኋላም ታራቂ፣ ገር፣ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፣ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት (የያዕቆብ መልዕክት ምዕራፍ፣ ሦስት፣ ቁጥር፣ 14-17)።

አሁንም ጊዜው አልመሸም፣ አሁን የተሸከምነውንና ትከሻችንን ያጎበጠውን የአጋንንት ፍልስፍና ከየት እንዳመጣነው፣ መሠረቱ ምን እንደሆነ ለመመርመርና ለመለወጥ ፈቃደኛ ከሆንን መታረምና መልካም ነገርን መፍጠር እንችላለን፡፡ ለአገራችን መፍትሔ በእውነት ካሰብን ቆም ብለን ራሳችንን መመርመር ያስፈልገናል፡፡ የምናምነው ምንድነው? የምንተገብረው ምንድነው? ከየትስ አመጣነው? ለትውልድ፣ ለአገርና በአጠቃላይ ለሰው ልጅ ይጠቅማል ወይ? ብለን ራሳችንን መመርመር መቻል አለብን፡፡

በአንድ ዘመን አዲስ አበባ ውስጥ ቄራ የሚባለው አካባቢ የሽታ ማስወገጃ መሣሪያዎች ከመተከላቸው በፊት በጣም ይከረፋ ነበር፡፡ በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ግን በአካባቢው ለረጅም ጊዜ በመኖራቸውና፣ አንዳንዶችም ተወልደው እዚያው አካባቢ በማደጋቸው ለእነሱ ክርፋቱ ብዙም አይታወቃቸውም ነበር፡፡ ምክንያቱም ለረጅም ጊዜ በአካባቢው ከመኖር የተነሳ የስሜት አካላቸው (አፍንጫቸው) ከመለማመዱ የተነሳ ነበር፡፡ ከሌላ አካባቢ ለሚመጣ ሰው ግን በአካባቢው እንኳን ለማለፍ ክርፋቱ ከባድ ይሆንበት ነበር፡፡ ልክ እንደዚሁ ላለፉት 45 ዓመታት የተቀበልነውን የዳርዊንና ማርክስን ፍልስፍና ተከትሎ የመጣውን የሶሺያል ዳርዊኒዝም የፖለቲካ ፍልስፍና ስለተለማመድነው ክርፋቱን መለየት አቅቶናል፡፡ ለዚህ ነው ሰው በዘር ተከፋፍሎ ሲገዳደል፣ ሲሳደድ፣ ሲወጋገዝ ቆመን እንደ ደህና የእግር ኳስ ዳኛ ፊሽካ ነፊ የሆነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ፍልስፍናችን የከረፋ መሆኑን መረዳት የሚቻለው ወጣ ብሎ በማሰብና ከየት አመጣሁት ብሎ በመጠየቅ ነው፡፡ አንድን ነገር ከመሠረቱ ፈልፍለን ለማወቅ የምናደርገው ጥረት ባለመኖሩ የአቶ እንዳለው ልጆችን በሽታ ተሸካሚ መሆናችን ሳያንስ፣ ለትውልድ አስተላልፈን ትውልድን በማለያትና በማጫረስ ላይ እንገኛለን፡፡ ‹‹ነገርን ከሥሩ ውኃን ከምንጩ›› እንደሚባለው ሁሉ፣ ከመሠረቱ መርምረን መልካሙን እየያዝን ክፉውን ልናስወግድ ይገባል፡፡

መዝራትና ማጨድ

በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፣ ብርድና ሙቀት፣ በጋና ክረምት፣ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም (ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ፣ ስምንት፣ ቁጥር፣ 22)። አትሳቱ፣ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና (ወደ ገላትያ ሰዎች ምዕራፍ፣ ስድስት፣ ቁጥር፣ ሰባት)፣ ኃጢአትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል፣ የቁጣውም በትር ይጠፋል (መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ፣ 22፣ ቁጥር፣ ስምንት)። አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኗልና (የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ፣ አራት፣ ቁጥር፣ 37)። የመዝራትና የማጨድ ሥርዓት እግዚአብሔር ለሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ ከሰጠው አንዱ ትልቁ ሥርዓትና ጥበብ ነው፡፡

የሰው ልጅ ዘርን ይዘራል ያጭድማልም፡፡ የሚዘራው ግን አብዝቶ ለማጨድ ነው፡፡ አንድ ቅንጣት ስንዴ የዘራ ገበሬ በብዙ እጥፍ እንደሚያጭድ ያውቃል፡፡ ነገር ግን ስንዴ ዘርቶ አተር እንደማያጭድ ያውቃል፡፡ የዘራውን ያንኑ እንደሚያጭድ ስለሚያውቅ አተር ከፈለገ አተር ይዘራል እንጂ አተር ፈልጎ ስንዴ አይዘራም፡፡ ሁሉም እንደ እግዚአብሔር ፍጥረትነታቸው በውስጣቸው ዘረመል ስለተቀመጠ ስንዴው አተር ሊሆን አይችልም ወይም አተሩም ስንዴ ሊሆን አይችልም፡፡ የእግዚአብሔር ቃልም ይህንን ለማስረዳት ዘሩ ያለበት ፍሬ ብሎ ይገልጸዋል፡፡

እግዚአብሔርም ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ እንዲሁም ሆነ (ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ፣ አንድ፣ ቁጥር፣ 11)። ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ (ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ፣ አንድ፣ ቁጥር፣ 12)። እንደዚሁ በተመሳሳይ ሁኔታ እግዚአብሔር በእንስሳትም ውስጥ እንደየ ወገኑ እንዲባዛ የየወገኑን ዘረመል አስቀምጧል፡፡ ዝንጀሮ ሰው ሊወልድ አይችልም፣ ሰውም ዝንጀሮን ሊወልድ አይችልም፡፡ የሰው ዘረመል ሌላ ነው የዝንጀሮውም እንደዚሁ፡፡

እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፣ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፣ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ አደረገ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ (ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ፣ አንድ፣ ቁጥር፣ 25)። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው (ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ፣ አንድ፣ ቁጥር፣ 27)። ዘረመል ውስጣዊና እግዚአብሔር ያስቀመጠው ሲሆን በአካባቢና፣ በአየር ፀባይ ሁኔታ የሚቀያየር አይደለም፡፡ ሰው ደጋማ አየር ፀባይ ቢቀመጥ ፈረስ አይወልድም ወይም ወደ በረሃ ቢወሰድ ግመል አይወልድም፡፡ ሰው አንታርክቲክ ቢወሰድ ፕንጉዊን (Penguin) አይወልድም ወይም ሰሜን ዋልታ ቢወሰድ ሲል (Seal) አይወልድም፡፡ ስለዚህ ሰው የትም ይሂድ፣ የትም ይኑር ሰው የሚወልደው ሰውን ነው፡፡ በዘረመል ከፍ ያለ ሰው የለም፣ ዝቅ ያለም የለም፣ ሰው ያው ሰው ነው፡፡

ይህ የመዝራትና የማጨድ ሥርዓት በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥም እንደሚገለፅ የእግዚአብሔር ቃል የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ ሰውም በተሞክሮው የሚያውቀውና የሚያረጋግጠው እውነት ነው፡፡ ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳል (ወደ ገላትያ ሰዎች ምዕራፍ፣ ስድስት፣ ቁጥር፣ ሰባት)፡፡ መልካምን የዘራ መልካምን ያጭዳል፣ ፍቅርን የዘራ ፍቅርን ያጭዳል፣ ክፋትን የዘራ ክፋትን ያጭዳል፣ መለያየትን የዘራ፣ መለያየትን ደግሞ ያጭዳል ኃጢአትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል፣ (መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ፣ 22፣ ቁጥር፣ ስምንት)፡፡

አገራችን ባለፉት 45 ዓመታት በተለይም 27 ዓመታት የዘራችውን እያጨደች ትገኛለች፡፡ የዝግመተ ለውጥ ውጤት የሆነው የሶሺያል ዳርዊንስቶች ፈሽስታዊ/ናዚያው/አፓርታይድ የዘረኝነትን የጎሳ ፖለቲካን በመዝራታችን ዛሬ ላይ በቅሎ ወጣቱ በማጨድ ለይ ይገኛል፡፡ ብዙ ሰው ወጣቱን ሲኮንን እንመለከታለን፡፡ ወጣቱ ምን አጠፋ? የዘራነው እኛ ከ55 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆነው ነን፡፡ አንዱ የዘራውን ሌላው ሊያጭድ እንደሚችል የእግዚአብሔር ቃል ያረጋግጣል፡፡ ታዲያ ዘረኝነትን ዘርተን ከወጣቱ ፍቅርን፣ አንድነትንና መተሳሰብን ለማጨድ ማሰብ ከንቱነት ነው፡፡ የዘረኝነትን የጎሳ ፖለቲካ እየሰበኩ ስለፍቅርና አንድነት የሚያወሩ ደግሞ፣ ሌሎቹ አስገራሚዎቹ ናቸው፡፡ ፍቅርን በዘረኝነት ውስጥ ለማጨድ መጠበቅ ቂልነት ነው፡፡ የሶሺያል ዳርዊንሰቶች ፈሽስታዊ/ናዚያው/አፓርታይድ የዘረኝነት የጎሳ ፖለቲካ የሚሰብከው መለያየትን፣ የበታችና የበላይነትን፣ ልዩ ዘርን፣ ልዩ ቋንቋን ወዘተ. ነው፡፡ በሩዋንዳ ቤልጂየሞች ባመጡት የሶሺያል ዳርዊንሰቶች ፈሽስታዊ/ናዚያው/አፓርታይድ ሥርዓት ሕዝቡን ቱቲስና ሁቱ በማለት አንዱን ከፍ በማድረግ ሌላውን ዝቅ በማድረግ በመታወቂያ ሳይቀር በመለየት በዓለም ታሪክ ከሂትለር ቀጥሎ ዘግናኝ የሆነው ጭፍጨፋ ሊከሰት ችሏል፡፡

ፋሽስቶች በአገራችን ከ1928 እሰከ 1933 ዓ.ም. ልክ ቤልጂየሞች በሩዋንዳ ያደረጉትን ዓይነት ሕዝቡን በዘርና፣ በሃይማኖት በመክፈል አንዱን ከፍ አንዱን ዝቅ፣ አንዱን በደለኛ አንዱን ተበዳይ አድርገው ዘመናቸውን ለማራዘም የሞከሩት ሙከራ በሕዝቡ ጠንካራ ማኀበራዊ እሴት ምክንያት በወቅቱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በወቅቱ የዘሩት ዘር  ባያድግም፣ የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ እንደሚባለው ሁሉ፣ በእኛው በራሳችን ልጆች ማርኪስስት ነን በሚሉ በ1960ዎቹ የተዘራው ዘር ዛሬ አፍርቶ በማጨድ ላይ እንገኛለን፡፡ ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ (ወደ ገላትያ ሰዎች ምዕራፍ፣ አምስት፣ ቁጥር፣ 15) ተብሎ እንደተጻፈው እርስ በርስ የዘራነውን በማጨድ እየተበላላን እንገኛለን።

በአሁኑ ጊዜ ዘረኝነትን ዘርተን ያጨድናቸውን ወጣቶች የተለያየ የዘር ስያሜ በመለጠፍ  (ፋኖ፣ ቄሮ፣ ዘርማ፣ ኤጄቶ፣ ናቶ፣ ወዘተ.) የበለጠ የሶሺያል ዳርዊንሰቶች (ፈሽስታዊ/ናዚያው/አፓርታይድ) የዘረኝነት የጎሳ ፖለቲካ አራማጆችን እያዘጋጀን እንገኛለን፡፡ ይህንን ደግሞ እንደ ታላቅ ጀብዱ ፖለቲከኞች በየአደባባዩ በየሚዲያው ሲሰብኩ ይሰማል፡፡ ከዚያም አልፎ ዘርተን፣ አብቅለን፣ አሳድገን ያጨድነውን የእኔ ነው፣ የእኔ ነው፣ በመባባል ልክ በ1960ዎቹ መጨረሻ የወዛደር/የላብአደር ተወካይ ለመሆን በተደረገው ጥረት እንደተጠፋፋነው አሁንም የእነዚህ ወጣቶች ተወካይ ለመሆን በዘር ፖለቲከኞች መካከል የሚደረገው ፉክክር የሚያሳዝን ነው፡፡ ላለፉት ዓመታት የሰበክነውና አሁን ላይ ያጨድነው ሳያንስ ወጣቱ አድጎ ሌላ ክፉ ዘር እንዲዘራና እንዲያጭድ እያደረግን ነው፡፡

ሌላው የመዝራትና የማጨድ ሥርዓት የሚያስገነዝበን ከዘራነው በላይ ብዙ እጥፍ ማጨድ ነው፡፡ በመሆኑም የሶሺያል ዳርዊንስቶች ፈሽስታዊ/ናዚያው/አፓርታይድ የዘረኝነት የጎሳ ፖለቲካ መዝራት በተጀመረበት በ1960ዎቹ ወቅት በጣም ጥቂት ዘር ነበር፡፡ ይህ ጥቂት ዘር ዛሬ ላይ በብዙ እጥፍ ተባዝቶ በብዙ ሚሊዮኖች ደርሷል፡፡ ብዙዎች በማያውቁት፣ ከየት እንዳመጡት ሳይረዱት ራሳቸውን በዘረኝነት ከረጢት ውስጥ የሚያገኙበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡

በጣም የሚያሳዝነው እናቶች ከሚታወቁበት የእናትነት ፍቅር ወጥተው ለዘረኝነት ሲሠለፉ ማየት እጅግ የሚዘገንን ነው፡፡ እናት ለልጇ ያላትን ልዩ ፍቅር እናት ያልሆነ ሊረዳው አይችልም፡፡ የሶሺያል ዳርዊንሰቶች ፈሽስታዊ/ናዚያው/አፓርታይድ፣ ለዘረኝነት በሚፈጥሩት የጎሳ ፖለቲካ የመጀመርያውና ዋንኛ ተጠቂ እናቶችና ሕፃናት እንደሆኑ በተግባር የታየ ጉዳይ ነው፡፡ እናቶች ዘረኝነትን ለማወደስ እንዲሠለፉ ማድረግ ምናልባት ከዓለም በጊነስ መዝገብ ሊያስመዘግበን ይችላል፡፡ እናት የምትወልደው ልጅ እንጂ ቋንቋ ወይም ዘውግ አይደለም፡፡ በአብዛኛው ከአባቶች ይልቅ የልጆችን አስተሳሰብ ቀርፃ በማሳደግ የበለጠ ተፅዕኖ የምታሳድረው እናት ናት፡፡ እናት በሶሺያል ዳርዊንሰቶች ፈሽስታዊ/ናዚያው/አፓርታይድ፣ የዘር ፖለቲካ ከተጠመደች ምን ዓይነት ትውልድ እንደምናጭድ ለመረዳት ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡

በአገራችን ያሉ ሚዲያዎችም የሚዘሩት የሶሺያል ዳርዊንሰቶች ፈሽስታዊ/ናዚያው/አፓርታይድ፣ የዘር ፖለቲካ ሌላው ችግር ነው፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላል እንደፈሊጥ የተያያዙት በምድሪቱ ላይ ክፉ ዘር ሲዘሩና እየዘሩ ያሉትን የሶሺያል ዳርዊንሰቶች ፈሽስታዊ/ናዚያው/አፓርታይድ፣ የዘር ፖለቲከኞችን እያቀረቡ ማነጋገር ላይ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለሠሩት ክፋት ንሰኃ መግባት ሲገባቸው ልክ መልካም ዘር እንደዘሩ የዘረኝነት ገድላቸውን እንዲሰብኩ ይደረጋል፡፡ አብዛኛውም ሚዲያ የሶሺያል ዳርዊንሰቶች ፈሽስታዊ/ናዚያው/አፓርታይድ፣ የዘር ፖለቲከኞች የተያዘ በመሆኑ ከዕባብ፣ ዕንቁላል ዕርግብን እንደመጠበቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል፡፡ ዛሬ በዘረኝነት ስሜት የሚዲያ ተመልካች መብዛቱና የማስታወቂያ ገቢ መበርከቱን ብቻ በማተኮር የሚሠራ ሥራ ወደፊት ‹‹እዩኝ እዩኝ ያለ ደብቁኝ ደብቁኝ ይላል›› እንደሚባለው አገር ከሌለች ማስታወቂያም፣ ገቢም፣ መኖርም አይቻልም፡፡ ሚዲያ ትኩረት ማድረግ የነበረበት በሰዎች ልጆች እኩልነት በሚያምኑ ከዘረኝነት ነፃ የሆነ ትውልድ በመቅረፅ ላይ ነበር፡፡

ሰው የዘራውን ያንኑ እንደሚያጭድ የተረጋገጠ እውነታ ነው፡፡ መለያየትን ዘርተን አንድነትን ለማጨድ የሚደረግ ጥረት ከንቱ ነው፡፡ አንድነትን፣ ፍቅርን ለማጨድ ከፈለግን ማስተካከል ያለብን የምንዘራውን ዘር ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት የአንድነትና የፍቅርን ዘር የሚዘራ ሠራተኛ ነው፡፡ ይህንንም ዘር ሊያበቅል የሚችል ለም አዕምሮ መቅረፅ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ትኩረት ተሰጥቶ በትምህርት ቤቶች፣ በኮሌጆች እንዲሁም በየአካባቢውና፣ በእምነት ተቋማት በኩል ሊሠራበት ይገባል፡፡

የኢትዮጵያን ችግር ማን ሊፈታ ይችላል

የኢትዮጵያን ችግር ሊፈቱ ይችላሉ ብሎ ሁሉም ሰው ተስፋ የሚያደርገው ፖለቲከኞች ላይ ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በመጀመርያ ስለፖለቲከኞቹ መረዳትና ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የሚከተሉት ሰባት መሠረታዊ ባህሪያት አላቸው፣

  1. በኢትዮጵያ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ፍልስፍና ላይ የተመሠረቱ አይደሉም፣
  2. በአብዛኛው ማለት ይቻላል ሶሺያል ዳርዊኒስት/ማርክሲሰት ፖለቲካ ፍልስፍና መሠረት ያደረጉ ናቸው፣
  3. ሁሉም ካለፉት 45 ዓመት ወዲህ የተመሠረቱ ናቸው፣
  4. በአብዛኛው ከሰማይ በታች የእኔ ፍልስፍና ብቻ መፍትሔ ነው ባይ ናቸው፣
  5. በአብዛኛው አገርን ማዕከል ያደረጉ ሳይሆኑ ቡድንን/ዘውግን መሠረት ያደረጉ ናቸው፣
  6. ሕዝብ ሳይወክላቸው ራሳቸውን የሕዝብ ወኪል ያደረጉና በሕዝብ ስም የሚምሉ ናቸው፣
  7. አብዛኛው የግል ወይም የቡድን ጥቅምና ዝና ደምረውና አባዝተው የተመሠረቱ ናቸው፡፡

ሁሉም የተፈጠሩት ባለፉት 45 ዓመታት ውስጥ ሲሆን፣ በዚህ ዘመን ደግሞ ማርክሲዝምና ዳርዊኒዝምን መሠረት ያደረገው ሶሽያል ዳርዊኒሰት የፖለቲካ ፍልስፍና ወደ አገሪቱ ዘልቆ የገባበት ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ባህሪያት በቀጥታ የሚያስረዱን ሁሉም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ፖለቲካዊ ፍልስፍና ባይተዋር የሆኑ፣ በዘመነ ማርክሲዝምና ዳርዊኒዝም የተመሠረቱ ውስጣቸው ሶሽያል ዳርዊኒሰት የፖለቲካ ፍልስፍናን የፀነሱ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡

 በመጀመርያ እግዚአብሔርን/ፈጣሪን የካደ ወይም በክህደት መንፈስ በተቀነባበረ የፖለቲካ አስተሳሰብ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም፡፡ መፍትሔ የሚቻል ቢሆን ኖሮ ያለፉት 45 ዓመታት ረጅም ጊዜ ነበር፡፡ ሁሉም ፖለቲከኛ መሠረታዊውን ችግር ሳይሆን ለመፍታት የሚያስበው በሌላው ላይ ጣት መጠቆም ነው፡፡ ዕድሉን ሲያገኝ ደግሞ እርሱ ራሱ የባሰ ሆኖ ይገኛል፣ ምክንያቱም መሠረቱ ሰይጣናዊ ፍልስፍና ስለሆነ ነው፡፡ በሰይጣናዊ ፍልስፍና መፍትሔ ለማምጣት አይቻልም፡፡ ቢቻል ኖሮ እኛ ነበርን የመፍትሔ ምሳሌ የምንሆነው፡፡ የ1966 ዓ.ም. አብዮት በተፈለገው አቅጣጫ ባለመሄዱ ምክንያት በዓለም ውስጥ ለረጅም ዓመታት የማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ያልተለያት ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ አብዮቱ ባስከተለው ችግር ምክንያት ለ45 ዓመታት የማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ያለች ነገር ግን መፍትሔ ያጣች ሆናለች፡፡

ሌላው የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ባህሪይ፣ በሰው ልጅ ሕልውናና መብት ላይ የተመሠረቱ ሳይሆን የግል ዝና፣ የግል ጥቅምና የቡድን ጥቅምን መሠረት ያደረጉ መሆናቸው ነው፡፡ የእነሱ ጥቅም እስካልተነካ ድረስ ሌላው ቢሞት ቢሰደድ ምንም አይመስላቸውም፡፡ ፖለቲካ እንደማንኛውም ሸቀጥ ይነገድበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ አትራፊ ንግድ የፖለቲካ ንግድ ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ በዙሪያው ያሠለፈ ብዙ አትራፊ የሆነ ድርጅት ነው፡፡ ሌላው ፖለቲከኛ የመሆን ጥቅሙ በውጭ አገሮች እየዞሩ ቪዛና የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት ያስችላል፡፡ ንግዱም ኢንተርናሽናል ይሆናል፡፡

ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትህትና ይቁጠር፣ (ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች ምዕራፍ፣ ሁለት፣ ቁጥር፣ ሦስት) ሰው ቢሳሳት እንኳን ፈሪኃ እግዚአብሔር ካለበት በንሰኃ ይመለሳል፡፡ ፈሪኃ እግዚአብሔር የሌለው ስህተትን በሌላ ስህተት ለመመለስ ይሞክራል እንጂ፣ ከስህተቱ አይመለስም፡፡ በአገራችንም በአውሮፓም እንደሆነው ዳርዊኒዝምና/ማርክሲዝምን መሠረት ያደረጉ ፖለቲከኞች እሰከ መጨረሻው እስከ ሚሞቱ ድረስ ስህተትን በስህተት ለመመለስ ጥረት አድርገው ነው ያለፉት፡፡ ምክንያቱም ፍልስፍናው ራሱ ከበስተጀርባው የዲያብሎስ እጅ ስላለበት ወደ መልካም መንገድ እንዲመለሱ ሳይሆን ጨካኝና እልኸኛ ስለሚያደርጋቸው፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የተማረ ይግደለኝ ብሎ በየዋህነት ያመናቸውን ሕዝብ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እነሱ የፈለሰፉትን ተረትና ትርክት ሕዝብ እንዲያምናቸው ማድረግ ነው፡፡ አምኖም የእነሱ ጥቅም እሰከ ተጠበቀ ድረስ እንዲሞትላቸው፣ እንዲታሰር እንዲሰደድ ማድረግ ለእነሱ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ሌላው ችግር ሕዝብን ወከልን ብለው ራሳቸውን የአንድ ወገን ወኪል በማስመሰል ሌላው ወደዚያ ሕዝብ እንዳይደርስ ገደብ ያስቀምጣሉ፡፡ እነሱም የሕዝቡን ትክክለኛ ሥነ ልቦናና ማኅበራዊ ፍልስፍና ስለማያውቁትና በእራሳቸው በፈጠሩት ተረት የሚኖሩና ይህም ተረት የጥቅምና የሥልጣን መሠረት ይሆናል ብለው ስለሚያስቡ ሌላውን እንደ ሥጋት ይቆጥሩታል፡፡ ተረቱ ከተጋለጠ የጥቅምና የሥልጣን ምንጭ ስለሚደርቅ ነው፡፡

የሶሽያል ዳርዊኒስት የፖለቲካ ፍልስፍና ዋና መሠረቱ ዘውግ ወይም ቡድን ነው፡፡ ስለዚህ በአብዛኛው የዘውግን የበላይነት ወይም ጥቅም አስጠባቂ መስሎ መቅረብ በቀላሉ የቡድንን ስሜት በመኮርኮር ለሥልጣን፣ ለዝናና ጥቅም ያደርሳል፡፡ ከአገራዊ ወይም አኅጉራዊ አስተሳሰብ ይልቅ በቀላሉ ምኞትን ማሳካት የሚቻልበት አቋራጭ ስለሆነ፡፡ አገር አቀፍ የፖለቲካ ሥራ ግን፣ ሁሉን በእኩልነት ማየትን፡ የሁሉንም ሕዝብ ታሪከ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ፍልስፍናን መረዳት ለሁሉም የሚስማማ አገር አቀፍ የሆነ የኢኮኖሚ ለውጥ የሚያመጣ አስተሳሰብና ፖሊሲ መተለምን ይጠይቃል፡፡ ይህ ዓይነቱ ብቃትን፣ አስተዋይነትን፣ ፍቅርን ትዕግሥትንና ሁሉን እንደ ሰው በእኩልነት መመልከትን በሁሉም ሕዝብ ተዓማኒነትንና ተቀባይነትን ማግኘትን ይጠይቃል፡፡ የእራስን ጥቅምና ፍላጎትን ሳይሆን የሕዝብን ፍላጎትና ጥቅም ያለምንም የቡድን/ዘውግ ልዩነት ማስቀደም ይጠይቃል፡፡ የአገርን ጥቅምና ፍላጎት በእኩልነት ለማስጠበቅ አቋራጭ መንገድ ከባድ ነው፡፡ ስለሆነም ቀላሉ መንገድ ቡድን/ዘውግ ውስጥ መደበቁ አቋራጭ ኢንቨስትመንት ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው በአገራችን ከ100 በላይ የፖለቲካ ፓርቲ እንደአሸን የፈላው፡፡

የፖለቲካ ድርጅቶቹ ከእራሳቸው ሐሳብ ውጪ ሌላው የሚያቀርበው ሐሳብ ሁል ጊዜ ስህተት ነው፡፡ እያንዳንዱ የራሱ ሐሳብ ብቻ ፍቱን መድኃኒት እንደሆነ ያስባል፣ የሌላውን ለማዳመጥም ሆነ ለመማር ዝግጁ አይደለም፡፡ ሐሳቡን አቅርቦ በሕዝብ መዳኘትን ሳይሆን የሚፈልገው ሌላው ሐሳቡን እንዳይገልጽ በማድረግ እሱ ብቻ የሕዝብ ተወካይ ሆኖ መቅረብን ነው የሚፈልገው፡፡ ከዚህ የተነሳ የአገርን ጉዳይ ከቡድን ጥቅም በስተጀርባ ስለሚመለከቱ ለአገር የሚጠቅምና የጋራ የሆነ አስተሳሰብ መፍጠር ወይም መስማማት አይችሉም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ስለእንግሊዝ ሊቅ አባባል እንዳቀረቡት፣ ‹‹መንገዱን ጠንቅቆ ለማያውቅ መንገደኛ የሚያዋጣውና የሚጠቅመው የተሳሳተውን አቅጣጫ ይዞ መገስገሱ ሳይሆን ቆም ብሎ ትክክለኛውን መንገድ መፈለጉ ነው፤››

በመሆኑም ከላይ በተጠቀሱት ዋና ዋና ምክንያቶች የተነሳ ፖለቲከኞች የኢትዮጵያን ችግር ይፈታሉ ብለን አናምንም፡፡ የኢትዮጵያን ችግር ሊፈቱ የሚችሉት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችን ሕዝብ ይሰማቸዋል፣ እነሱም ሕዝቡን ያዳምጣሉ፡፡ ሕዝብ ያከብራቸዋል እነሱም ሕዝቡን ያከብራሉ፡፡ ከሕዝቡ የሚጠብቁት ልዩ ጥቅም ወይም ሥልጣን የላቸውም፡፡ ሰጪነትን እንጂ ተቀባይነትን አያስተምሩም፡፡ ሕዝብን ማስታረቅ እንጂ ፀብን አይዘሩም፡፡ የተለየ ዘውግን/ቡድንን አይወክሉም፡፡ ሃይማኖት ዘውግ የለውም፣ ቀለም የለውም፣ ወሰን የለውም ሁሉንም ሕዝብ ያዋህዳል፡፡ የአገር ሽማግሌዎች እንደ ቃሉ የሚወክሉት አገርን ነው ጎሳን ወይም ቡድንን አይደለም፡፡

በአስተዳደሩም ሆነ በማኅበራዊው የሕዝቡን ስነ ልቦና በደንብ ይረዳሉ፣ ለሕዝብ የሚጠቅመውን ለይተው ያወቃሉ፡፡ ሕዝብን አቻችሎ አብሮ የሚኖረበትን መንገድ ከማንም በላይ ይረዳሉ፡፡ ሕዝብን የማስተዳደሪያ ዘይቤዎችን ከማንኛውም ፖለቲከኛና ሊሂቅ የበለጠ ይረዳሉ፡፡ በሕዝብ ሥነ ልቦና ላይ የተመሠረተ የአስተዳደር ዘይቤ መቀየስ ይችላሉ፡፡ በሚቀጥለው ሠንጠረዥ ላይ ሁለቱን ማወዳደር ይቻላል፡፡

ሠንጠረዥ፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች

የመፍትሔ አቅጣጫዎች ለዘላቂ አስተሳሰብ ለውጥ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን

የመፍትሔ አቅጣጫዎች ለዘላቂ አስተሳሰብ ለውጥ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን

የመፍትሔ አቅጣጫዎች ለዘላቂ አስተሳሰብ ለውጥ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን

የሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች ከኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በተለይ ለሕዝብ የቀረቡና ለሕዝብ የሚሠሩ ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች ከሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችና፣ ከፖለቲካ ገለልተኛ ከሆኑ ምሁራን አቀናጅተን ብንጠቀም ለአገር ዘላቂ ሰላምና የአስተዳደር ሥርዓት መፍጠር ይቻላል፡፡ የሃይማኖት መሪዎችና ሽማግሌዎችን ከሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ ከፖለቲካ ገለልተኛ ከሆኑ ምሁራን ጋር  በማቀናጀት የሃይማኖት መሪዎችና ሽማግሌዎች ሕዝቡን በማስማማትና በማቀራረብ የአስተዳደርና ዘላቂ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲዘረጉ ቢደረግ በሁሉ ሕዝብ ተቀባይነት ስለሚኖረው ዘላቂ የሰላምና የአንድነት መሠረትን ለመጣል ያስችላል፡፡ የሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች ዘላቂ የሆነ የአስተዳደር ሥርዓት እሰከ ሚዘረጉ ድረስ  ፖለቲከኞች አገር ከመበጥበጥ ሙሉ በሙሉ አርፈው እንዲቀመጡ ቢደረግ መልካም ይሆናል፡፡

ከዚህ ከሚዘረጋው ሥርዓት ጎን ለጎን መንግሥት የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር  የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፍና ለኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚያገለግሉ አስፈላጊ ተቋማትን ማቋቋምና መሠረቱን መጣል ይጠበቅበታል፡፡

የኢትዮጵያን የጋራ የሆኑ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ግብረ ገባዊ/ሥነ ምግባራዊና ሕጋዊ እሴቶች በመለየት በቅንነት ለእነዚህ እሴቶች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያዊ የሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት መሠረት መጣል ይቻላል፡፡ በዚህ መሠረት ላይ ሁሉም/አብዛኛው የሚስማማበትን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትን አሻሽሎ መቅረፅ፡፡ ይህ ሁኔታ ለዘላቂ ሰላማዊ ልማትና፣ ለልዩነትና ለአንድነት ትኩረት በመስጠት ለአገራዊ ግንባታ ለሚደረገው ጥረት መንገድ ይጠርጋል፡፡ በዚህ በተዘረጋው ሥርዓት ላይ የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ዕድገት ፖሊሲ እያቀረቡ ተወዳድረው ወደ ሥልጣን እንዲመጡና አገር እንዲያስተዳድሩ ቢደረግ ጠንካራና ብቃት ያላቸው አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መፍጠር ያስችላል እንዲሁም ዘላቂ የአገር ዕድገትና ልማትን ማምጣት ይቻላል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን የትምህርት ፖሊሲን ለአንደኛና ሁለተኛ ደረጃና ለከፍተኛ ትምህርትም ጭምር የአገሪቱን እሴት በጠበቀ መልኩ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚሆን ካሪኩለም መቅረፅና የትምህርት ሥርዓትን መዘርጋት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ በተጨማሪም በተዘረጋው ሥርዓት በሁሉም የትምህርት ደረጃ ትውልድን አስተካክሎ መቅረፅ ግድ ይላል፡፡ እጓለ ገብረ ዮሐንስ እንዳሉት ‹‹ስለትምህርት ያለን አስተያየት ትክክለኛ ከሆነ  ማናቸውም የሕይወት ችግር ሊፈታ ይችላል፡፡ ሰው ከሙሉ የሰውነት ደረጃ የሚደርሰው በትምህርት ነው፤››

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል  [email protected] እና [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡ተፈጸመ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...