በአንዳርጋቸው አሰግድ
የሕወሓትና የአዴፓ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች በሐምሌ 2 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም. በመግለጫዎች ተመላለሱ። መግለጫዎቹ ከሁለት ረዥም የፖለቲካ፣ የመንግሥትና የሕዝብ አመራር ታሪክ ካላቸው ድርጅቶች መሰጠት የማይገባቸው ነበሩ። በተለይም በዛሬይቱ እነሱ ራሳችው አመራሩን በያዙበት ውስብስብ የኢትዮጵያ ሁኔታ ውስጥ በይፋ ሊሰጡ ቀርቶ፣ ሊታሰቡም አይገባም ነበር። እናንት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋናዮች ከታሪካችንም ጭምር ተምራችሁና አደብ ገዝታችሁ፣ ሕዝብን በተለይም ወጣቱን አደብ እያስገዛችሁ እስካልተራመዳችሁ ድረስ፣ አገሪቱንና ሕዝቦቿን መውጪያው ወደ ማይታወቅ አዘቅት እየወሰዳችሁ እንደሆነ ልታስትውሉና ልትገነዘቡ ይገባችኋል።
የፖለቲካ ድርጅቶችና ተዋናዮች ወደ ግጭት የሚያመሩት በቅድሚያ በሆነ ባልሆነውና በእውነታና በሐሰት እየተወነጃጀሉና እየተካረሩ ሲቃ ከተያያዙ በኋላ ነው። ለዚህም ሩቅ መሄድ አያስፈልግም። የራሳችን የፖለቲካ ታሪክ ከመግለጫዎች መወራወር ወደ ግጭት ባመሩ ምሳሌዎች የተሞላ ነው።
አቤቶ ኢያሱ ‹‹ሰለሙ›› የተባለው እስከ ዛሬም ያከራክራል። አቤቶ ኢያሱ ‹‹ከቱርክ ተወዳጁ›› የተባለውም እንደዚሁ። ይሁንና የሰገሌ ጠርነት ተከተለ። ብዙ ሺሕ ሕዝብ አለቀ። ብዙ ሺሕ አካለ ጎደሎ ሆነ። አፄ ኃይለ ሥላሴ ‹‹ቢሊዮን ዶላር በውጭ አስቀምጠው›› የተባለውም እስከ ዛሬ መረጃ አልባ ነው። ይሁንና ከ44 እና ከ58 ዓመታት በኋላ መኳንንቶቻቸውና ባለሥልጣኖቻቸው የፍርድን ከፍታ ሳያዩ ካንዴም ሁለቴ በታሰሩበት በግፍ ተረሸኑ። ንጉሠ ነገሥቱም ታፍነው ተገደሉ። የአብዮቱ ዘመን ድርጅቶችና ተዋናዮች በሆነ ባልሆነውና በዕውነታና በሐሰት እየተወነጃጀሉና እየተካረሩ ሲቃ ከተያያዙ በኋላ የ‹‹ነጭ/ቀይ ሽብር›› ሰለባ ሆኑ። ሌሎቹም (ሻዕቢያ፣ ሕወሓት፣ ኢሕአፓ፣ ኦነግ) በየድርጅታቸው ውስጥ በሆነ ባልሆነውና በዕውነታና በሐሰት የገዛ አባሎቻቸውን እየወነጀሉ ረሸኑ።
የተመለከቱት ጉዳዮች የፖለቲካና ማኅበራዊ መዘዝ እስከዛሪም አልደረቀ። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ዳግም በሲቃ ተያይዞ ሌላ የግጭት ዙርን መጋበዝ ከፖለቲካ ታሪካችን አለመማር ብቻ አይደለም። ንፁህ የፖለቲካ ዕብደት ነው። ወይም ኢትዮጵያን ሌላዋ የመንና ሊቢያ ለማድረግ ወስኖ የመነሳት ያህል ነው።
የፖለቲካ ግጭትን ሜዳ ጠርጎና አምቻችቶ የሚደለድለው የፖልቲካ ቋንቋ ንስሐን ወደ ክስ፣ ትንተናን ወደ ፕሮፓጋንዳ፣ እውነታን ወደ ሐሰት እየተለወጠ መነዛት ሲጀምር እንደሆነ የፖለቲካ ተመራማሪዎች ያስተምራሉ። ሌሎችም እንደሚሉት፣ ፖለቲከኞች የሸቀጥ አስተዋዋቂን (Salesman) ዘይቤ ከመጠቀም አባዜ ውስጥ ሲገቡ ነው የፖለቲካው ሜዳ ለግጭት ፖለቲካ እየተጠረገ የሚመቻቸው ።
የሕወሓትንና የአዴፓን፣ እንዲሁም የሌሎቹን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋናዮች ‹‹የፖለቲካ›› ቋንቋ ምንነት መመረመር፣ ማስታወቅና ማስተማር የቋንቋ ሊቃውንቱ ፈንታ ነው። ኢትዮጵያን መውጪያው ወደማይታወቅ አዘቅት እየወሰዳት ካለው የይዋጣልን ፖለቲካ ማዳንና ማትረፍ ግን፣ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግዴታ ብቻ አይደለም። ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የህልውናው ጥያቄ ነው።
እናንት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋናዮች ተመርጣችሁም ይሁን ሳትመረጡ የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል እየወሰናችሁ ናችሁ። ኢትዮጵያን መውጪያው ወደማይታወቅ አዘቅት እንድትወስዱ የተሰጣችሁ ሥልጣን ግን የለም። የዛሬው ወጣቶችም አባቶቹ ሕይወታቸውን ከፍለው ያቆዩለትን አገሩን አተራምሶና ከፋፍሎ ለልጆቹ የማውረስ መበት የለውም።
ከእነ አባባሉ ‹‹መፍትሔ የሌለው ችግር፣ ችግር አይደለም›› ይባላል። እውነተኛ ችግር ይክበድም/ይቅለልም፣ ይዋልም/ይደርም መፍትሔ አለው ለማለት ነው። የእናንተ የነገ ‹‹ተሳስተን ነበር›› ከተደገሠው ሰቆቃ አያድንም። ለማንኛውም የፖለቲካ ጥያቄ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የፖለቲካ መፍትሔ አለ። ለፖለቲካ ጥያቄዎች ተወያይታችሁና ተደራድራችሁ የፖለቲካ መፍትሔዎችን የመሻት ኃላፊነትና ግዴታ አለባችሁ።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡