በአማራ ክልል አመራሮች ላይ ከሳምንታት በፊት በተፈጸመው ግድያ ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ከተገደሉ በኋላ፣ በክልሉ የፖለቲካ ቀውስ ሥጋት ማንዣበቡ ይታወቃል፡፡ በክልሉ አስተዳደርና ክልሉን በሚያስተዳደረው ገዥው የፖለቲካ ድርጅት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (አዴፓ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥም የአመራር ክፍተት መፍጠሩም ይታወቃል፡፡
ይህንን ክፍተት ለመሙላትና በክልሉ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት የመከረ ሲሆን፣ በሥራ አስፈጻሚው የተለዩ የውይይት ሐሳቦችን መሠረት በማድረግ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአራት ቀናት የፈጀ ዝርዝር ውይይትና ግምገማ በማካሄድ ሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. አጠናቋል፡፡
ከተደረገው ጥልቅ ግምገማና ውይይት በተጨማሪ በተፈጸመባቸው አሰቃቂ ጥቃት በሞቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች የክልሉ መንግሥት አመራሮች፣ እንዲሁም በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የምትክ ዕጩ ርዕሰ መስተዳድር ምርጫና ምክትል የፓርቲ ሊቀመንበርና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ አድርጓል፡፡
የማዕከላዊ ኮሚቴውን አጠቃላይ ውይይትና ግምገማ በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የአዴፓ የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ፣ የማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ በመሠረታዊነት በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት በመስጠት ጥልቅ ግምገማ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ብሎም በአገሪቱ ያለው ነባራዊ ሁኔታና አዴፓ ከገጠመው ቀውስ ለመውጣት ሊከተላቸው የሚገቡ ጉዳዮች በዝርዝር ግምገማ እንደተደረገባቸው፣ ሪፖርተር ያገኘው መረጃም ያመለክታል፡፡
በክልሉ ሕዝብ ውስጥ ያሉ ሁኔታዎችን የገመገመው አዴፓ፣ ለሚስተዋሉ እንከኖች በዋናነት ራሱን በተጠያቂነት መገምገሙን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የክልሉ ሕዝብ በለውጡ ደስተኛ መሆኑንና በዚህ ምክንያት ያገኘው ድል እንዳያመልጠው በተለያየ መንገድ በራሱ ተነሳሽነት እየታገለ እንደሚገኝ፣ አጥቶት የቆየውን ድል በቁጥጥር ሥር ለማዋልና ያገኘውን ለማጣጣም ማንኛውንም ዓይነት ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጀ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የተጠቀሰው ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ የክልሉ ሕዝብ ከፍተኛ ቅሬታ እንዳለው፣ የቅሬታ ምንጮች የሆኑ ጉዳዮችም በርካታ መሆናቸውን፣ ከእነዚህም ውስጥ የክልሉ መንግሥትና የፖለቲካ አመራሩ ሥርዓት አልበኝነትን መቆጣጠር አለመቻሉ፣ ማኅበረሰቡ ሰላምና መረጋጋትና የውስጥ ደኅንነት እንዳይሰማው ያደረገው ስለመሆኑ ማዕከላዊ ኮሚቴው መወያየቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚህም ምክንያት የክልሉ ሕዝብ በመሪ ድርጅቱ አዴፓና በክልሉ መንግሥት ላይ እምነቱ እየተሸረሸረ መምጣቱን የገመገመው ማዕከላዊ ኮሚቴው፣ አዴፓ የክልሉን ሰላም በሚገባ ማረጋገጥ አለመቻሉን እንደ መሠረታዊ የድርጅቱ ጉድለት ገምግሞታል፡፡
በሌላ በኩል ማኅበረሰቡ አዴፓ ያለበት ቁመና ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥርጣሬ የሚታይበት መሆኑን፣ የዚህም ምክንያት ከአሁን በፊት በነበረው ልምድ ይህ ድርጅት ለአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥቅም ቆሞ አያውቅም ከሚል የሚነሳ መሆኑን፣ ሌላው ደግሞ አሁን አንዳንድ በሚያያቸው ተግባራትና አስተሳሰብ ምክንያት ይህ ድርጅት አሁንም አልተለወጠም፣ ለመለወጥም ዝግጁ አይደለም፣ ተላላኪ ነው የሚል አስተሳሰብ እንዳለው ተመልክቷል፡፡ ይህ ሁኔታም ለአዴፓ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ተግባራት ከባድ ትርጉም ያለው ችግር እንደሆነ መገምገሙን መረጃ ያመለክታል፡፡
ሌላው ችግር ከክልሉ ውጭ ያለው የአማራ መብት አለመረጋገጡ፣ መፈናቀሉ አሁንም በስፋት የቀጠለ መሆኑ፣ የአዴፓ አመራርም ይህንን ችግር መቀነስና ማስቆም አለመቻሉ ተጨማሪ ቅሬታን በማኅበረሰቡ ውስጥ መፍጠሩን ገምግሟል፡፡ በክልሉ ማኅበረሰብ ላይ እስካሁን ተከማችቶ የቆየው ችግር ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝቡ ፍላጎትና ድርጅቱ ፍላጎቶቹን የመመለስ አቅሙ አለመመጣጠን መሠረታዊ ችግር መሆኑን፣ ይህንን ችግር በፍጥነት መቅረፍ ካልተቻለም ድርጅቱን ከባድ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ሥጋት መሆኑን ሳይሸፋፍን መገምገሙ ተጠቁሟል፡፡
ነባራዊ የክልሉ ሁኔታዎችን በመጠቀም የክልሉ ሕዝብ አንገቱን እንዲደፋና እንዲጠቃ፣ ብሎም ያልተረጋጋ ክልል እንዲሆን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን፣ ይህም ክልሉንና የአማራ ሕዝብን ለአደጋ ተጋላጭ እንደሚያደርገው የሚያጠያይቅ አለመሆኑን መገምገሙ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ በመነሳት የአስቸኳይ ጊዜ ተግባራት ሊሆኑ ይገባቸዋል ከተባሉት ውስጥ በዋነኛነት የተቀመጠው፣ የክልሉን ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህንን ለመመከትና አጠቃላይ የፖለቲካ ቅርቃሩን ለመስበርም በውል የተደራጀ፣ የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ምን ያህል መሆኑን የመረዳት አቅም ያለው አመራር መመደብ እንደሚገባ በግልጽ ተወያይቶ ከመግባባት መድረሱን መረጃው ያመለክታል፡፡
የአመራር ምርጫው
ማዕከላዊ ኮሚቴው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በነበሩት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ምትክ ከማዕከላዊ ኮሚቴው አባላት ከሦስት በላይ ዕጩዎች ቀርበውለት እንደነበር፣ ለስብሰባው ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዕጩነት የተጠቆሙ ግለሰቦች ባነሷቸው የተለያዩ የግልና ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሳ ወደ ውድድር አለመግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመሆኑም የዕጩነት ጥቆማውን የተቀበሉት የማዕከላዊ ኮሚቴው አባል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማዕከላዊ ኮሚቴው ተቀባይነትን አግኝተው የክልሉ ዕጩ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተመረጡ ሲሆን፣ ሹመታቸውም በቀጣይ በክልሉ ምክር ቤት እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡
አቶ ተመስገን በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ በውትድርና ያገለገሉና እስከ ሻለቃ ማዕረግ የደረሱ ሲሆን፣ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ከተቋቋመ በኋላ ተመድበው ለረጅም ጊዜ በዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡ ከዚህ ተቋም ከተገለሉ በኋላ በአማራ ክልል በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የክልሉ ፕሬዚዳንት የደኅንነት አማካሪና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ማገልገላቸው ይጠቀሳል፡፡
ከመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. በኋላ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አድርገው የሾሟቸው ቢሆንም፣ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከዚህ ኃላፊነት ተነስተው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሆነው እስካሁን ድረስ ሲያገላግሉ ቆይተዋል፡፡ አቶ ተመስገን ከውትድርና አገልግሎታቸው አንስቶ፣ በኋላም በመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) እንዲሁም በብሔራዊ ደኅንነት አማካሪነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጋር ለረጅም ጊዜ የሠሩና ጥብቅ ወዳጅነትም እንዳላቸው ይነገራል፡፡
አቶ ተመስገን በፀጥታና ደኅንነት ዘርፍ ለረጅም ዓመታት በማገልገል ልምድ ያካበቱ መሆናቸውና አዴፓ ሰሞኑን ባደረገው ግምገማው፣ በክልሉ ሰላምና ደኅንነትን ለማስፈን ቅድሚያ ከመስጠቱ ጋር ተያይዞ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደርነት በመታጨታቸው ተገቢነት ላይ የሚስማሙ አሉ፡፡
ይሁን እንጂ በርካቶች ስለአቶ ተመስገን እምብዛም የሚያውቁት ስለሌላቸው አስተያየት ለመስጠት ተቸግረዋል፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአዴፓና የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ቹቹ አለባቸው ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህን በአካል እንጂ ስለአመራር ብቃታቸው እንደማያውቁና የአዴፓ ውሳኔ ግን ስህተት ይሆናል ለማለት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡
አቶ ተመስገን ለክልሉ አመራርነት የታጩት በፀጥታና ደኅንነት ዘርፍ ባላቸው ልምድ ሊሆን ይችላል የሚለውን ለመቀበል እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ደግሞ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባካሄደው የአመራሮች ምርጫ በመጀመሪያ የተጠቆሙት ግለሰቦች በፀጥታ ዘርፍ ልምድ ያልነበራቸው መሆኑ፣ ድርጅቱ የክልሉን ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ይህንን ጉዳይ መመዘኛ እንዳላደረገው የሚያመለክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚሁ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገሯቸው የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አቶ ውብሸት ሙላትም፣ በተመሳሳይ ስለአቶ ጥሩነህ ብቃት ለመመዘን እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡ አቶ ተመስገን በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ቢሆንም፣ በበርካታዎቹ ኃላፊነቶች የነበራቸው የአገልግሎት ቆይታ አጭር በመሆኑ ለመገምገም አዳጋች መሆኑን በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡
በደኅንነት ዘርፍ ያካበቱት ልምድ በክልሉ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ያስችል እንደሆነ ተጠይቀው፣ በክልሉ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ እንዲሳካላቸው የተመኙት አቶ ውብሸት በዘርፉ ልምድ ያካበቱ መሆኑ ብቻውን ይህንን ያስችላል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል፡፡ ይህ መለኪያ የሚሠራ ቢሆን ኖሮ ተመሳሳይ ልምድ ያላቸው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በአገሪቱ የሚታየውን የደኅንነት ቀውስ ለመፍታት ይችሉ እንደነበር ንፅፅራዊ አመክንዮዋቸውን አቅርበዋል፡፡
የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን ባካሄደው የአመራሮች ምርጫ፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለውን የአዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ሾሟል፡፡
ይህንን በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ቹቹ የአቶ ዮሐንስ የአዴፓ ምክትል ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥ ትክክለኛ እንደሆነ፣ አዴፓ ይህንን በማድረጉ ከሌሎቹ የኢሕአዴግ ፓርቲዎች በተለየ መንገድ የፓርቲና የመንግሥት ሥራ እንዳይጣረስ ማድረጉን በአድናቆት ያወሳሉ፡፡ በዋናነት ግን ውሳኔው አዴፓን ለማጠናከር ትልቅ ትኩረት መስጠቱን በግልጽ የሚያስገነዝብ ነው ብለዋል፡፡