Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ከቡና ሲጠበቅ 768 ሚሊዮን  ዶላር ገቢ አስገኝቷል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

2011 በጀት ዓመት መጨረሻ ከቡና ወጪ ንግድ በጠቅላላው ይጠበቅ የነበረው ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ቢሆንም፣ 768.4 ሚሊዮን ዶላር ገደማ በማስገኘት ዓመቱን ለማጠናቀ ተገዷል፡፡ ከስምንት ዓመታት በፊት ከ840 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስገኘው ቡና፣ ከሁለት ዓመታት በፊት ከ880 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስመዝግቦ ነበር፡፡

እስካለፈው ግንቦት መጨረሻ ድረስ ከ669 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገቢ ያስገኘው የቡና የወጪ ንግድ አፈጻጸም፣ በሰኔ ወር መጨረሻ 94.4 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘቱ በጠቅላላው ከ768.4 ሚሊዮን ዶላር ፈቅ ያላለ ገቢ በማስገኘት የዓመቱን ጉዞውን አገባዷል፡፡

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ መሠረት፣ በሰኔ ወር መጨረሻ 36,750 ቶን ቡና እንደሚላክና ከዚህም 134.33 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚገኝበት ታቅዶ እንደነበር አስታውሷል፡፡ ይሁን እንጂ 29,294.46 ቶን ብቻ ቡና ለመላክ በመቻሉ ከዕቅዱ 79.71 በመቶ እንደተከናወነና 94.39 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 70.27 በመቶ ገቢ እንዳስገኘ ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡ የወሩ አፈጻጸምም ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጋር ሲነፃፀር በመጠን 2,212.20 ቶን ወይም የ8.17 በመቶ፣ በገቢ የ2.47 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ2.69 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ይህ ይባል እንጂ በዚህ ዓመት ለታየው የቡና አፈጻጸም መዳከም ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ቀርበዋል፡፡ ባለሥልጣኑ የዓለም የቡና ዋጋ 20 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን በግንቦት ወር ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ላይ በውጫዊ ምክንያትነት ያጣቀሰ ሲሆን፣ ቡና አምራች አገሮች በርካታ የቡና ምርት ማቅረባቸው፣ የኢትዮጵያን ቡና የሚገዙ ደንበኞች ግዥ ከመፈጸም መዘግየታቸውና አምና ከነበራቸው ክምችት አኳያ የግዥ ፍላጎታቸው መቀነሱ ከቀረቡት ምክንያቶች ውስጥ ተካተዋል፡፡

በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንደጠቀሱት፣ በአብዛኛው የቡና አፈጻጸም ያሽቆለቆለው በዓለም ገበያ ላይ በታየው የዋጋ መውረድ ምክንያት ከፍተኛ ቅናሽ ታይቷል፡፡

‹‹ዘንድሮ የቡና ዋጋ እጅግ ወርዷል፡፡ አንድ ፓውንድ ወይም 2.2 ኪሎ ግራም የሚመዝን ቡና 80 የአሜሪካ ሳንቲም እየተሸጠ ነው፡፡ ይሁንና አንዱን ኪሎ ቡና ለማምረት ቢያንስ ከአንድ ዶላር በላይ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን 2.2 ኪሎ ግራም ቡና እየተሸጠ ያለው ከአንድ ዶላር በታች በመሆኑ፣ ይህ ሁኔታ ባለበት ወደ ውጭ ወስዶ መሸጡ አስቸጋሪ ይሆናል፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ዋጋው እጅጉን ቢቀንስም ላኪዎች መላክ እንዳላቋረጡ አስታውቀው ነበር፡፡

የቡና ዋጋ ቢወርድም እስካሁን 200 ሺሕ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ መላኩን ጠቅሰው ይህም ሆኖ ከዋጋ አንፃር እንደ ዓምናው ዓይነት ገቢ ላይገኝ እንደሚችል ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹ምክንያቱም ዓምና እስከ ሦስት ዶላር ሲሸጥ የነበረው ቡና ዘንድሮ ወደ 80 ሳንቲም (በዶላር) ወርዷል፡፡ ይህ ትልቅ ልዩነት ነው፡፡ ይህንን ለማካካስ በመጠን ከፍ አድርጎ ለመሸጥ ተሞክሯል፤›› ብለዋል፡፡

በአንፃሩ ከውስጣዊ ችግሮች መካከል የአገር ውስጥ የቡና ዋጋ ከዓለም ዋጋ ጋር ባለው ልዩነት ሳቢያ ላኪዎች የውል ስምምነታቸውን ማክበር አለመቻላቸው አንዱ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል በየጊዜው መቆራረጡ ቡናውን በወቅቱ አዘጋጅቶ ለመላክ እንዳላስቻለና የኮንቴይነር ዕጥረት መታየት በምክንያትነት ቀርበዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ተደጋግሞ መታየት የጀመረው የኮንቴይነር ቡና ቅሸባ ወይም ዝርፊያ በባለሥልጣኑ ወርኃዊ ሪፖርቶች ውስጥ ተካቶ ባይገኝም፣ የላኪዎች ከፍተኛ የሥጋት ምንጭ እየሆነ፣ ከወጪ ንግድ ገበያ ሊያስወጣ የሚችል አደጋ የደገነ አዲስ ዓይነት የሥርቆት ዘይቤ እንደሆነ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ እስካሁንም ከ400 ኩንታል በላይ ከኮንቴይነር በረቀቀ ዘዴ መዘረፋቸውን የገለጹ ኩባንያዎች መንግሥት ችግሩን በሚገባ ካልፈታውና ዕርምጃ ካልወሰደ ላኪዎች ከጨዋታ ውጪ የሚሆኑበት፣ ኢትዮጵያም ከቡና ገበያ ልትወጣ የምትችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል ሲያስጠነቅቁ ተደምጠዋል፡፡

እስካለፈው ግንቦት ወር በነበረው የዚህ ዓመት የቡና ወጪ ንግድ አፈጻጸም ከመዳረሻ አገሮች አኳያ ሲታይ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ 40,432 ቶን ወይም 20 በመቶ ድርሻ ቀዳሚዋ የኢትዮጵያ ቡና ገዥ ተብላለች፡፡ በገቢም 107.76 ሚሊዮን ዶላር ወይም 16 በመቶ ድርሻ ነበራት፡፡ አሜሪካ 20,222 ቶን  ወይም አሥር በመቶ  ድርሻ፣ 106.32 ሚሊዮን ዶላር ወይም 16 በመቶ የገቢ ድርሻ ሁለተኛውን ደረጃ ይዛለች፡፡ ጀርመን  29,049.53  ቶን  ወይም 14 በመቶ  የመጠን ድርሻ ያለውን ቡና 83.89 ሚሊዮን ዶላር  በመግዛት ሦስተኛዋ የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ሆናለች፡፡ የተቀሩት አገሮች በገቢ ቅደም ተከተል ሲቀመጡ ጃፓን አራተኛ፣  ቤልጅየም አምስተኛ፣ ደቡብኮሪያ ስድስተኛ፣ ጣሊያን ሰባተኛ፣ ሱዳን ስምንተኛ አውስትራሊያ ዘጠነኛ፣ እንዲሁም እንግሊዝ የአሥረኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ 

በጠቅላላው አሥሩ አገሮች  84 በመቶ የቡና መጠን እንደሚገዙና 82 በመቶው የቡና የወጪ ንግድ ገቢም ከእነዚህ አገሮች እንደሚመነጭ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሪፖርት ያብራራል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች