[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ስብሰባ ላይ ከአንድ ወጣት ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር የእውነት ለውጥ አለ፡፡
- እ. . .
- እኔ በእርግጠኝነት መመስከር እችላለሁ፡፡
- ስለምኑ?
- ስለለውጡ ነዋ፡፡
- እንዴት?
- የዓመታት ጥያቄያችን ሊመለስ እኮ ነው፡፡
- የምን ጥያቄ?
- የማንነታችን ጥያቄ ነዋ፡፡
- የማንነት ጥያቄማ ከተመለሰ ዓመታት ተቆጠሩ እኮ፡፡
- እኔ የምልዎት የእኛ የማንነት ጥያቄ ነው፡፡
- ማለት?
- ይኸው ክልል ልንሆን እኮ ነው፡፡
- እ. . .
- ለዓመታት ታፍነን ስንኖር ነበር፡፡
- ምን አልከኝ?
- ለውጡ እውነተኛ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እናንተ ክልል መሆናችሁ ነው የለውጡ መለኪያ?
- ምን ጥያቄ አለው?
- እ. . .
- እውነተኛ ዴሞክራሲ መኖሩ ተረጋግጧል፡፡
- የምን ዴሞክራሲ?
- በቃ መንግሥት የሕዝቡን ድምፅ መስማት ጀምሯላ፡፡
- እንዳትሳሳት፡፡
- ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
- ለነገሩ አንተ ምኑን ታውቀዋለህ?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- አሁን አገሪቱ ባለችበት ሁኔታ የክልልነት ጥያቄ ተገቢ ነው?
- ምን ችግር አለው?
- ስማ እንኳን ተነጣጥለን ተባብረንም አልቻልነውም እኮ፡፡
- ምኑን?
- ችግሩን ነዋ፡፡
- አንደኛው ችግር እኮ አለመነጣጠላችን ነው፡፡
- ምን?
- ይኸው እኛ ክልል ስንሆን የራሳችን በጀት ይኖረናል፡፡
- ዶሮ ብታልም ጥሬዋን አሉ?
- ምን ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- በቃ ሁሉም የሚያስበው ከነገሩ እኔ ምን አተርፋለሁ የሚለውን ነው አይደል?
- እንደዚያ ማሰብ ምን ችግር አለው?
- ሁሌ እኔ እያሉ ማሰብ እኛን ያስረሳላ፡፡
- እ. . .
- አየህ ሁሉ ከራሱ ጥቅም አንፃር ብቻ ነገሮችን መመልከት ካላቆመ በጋራ መጓዝ አንችልም፡፡
- ምን ማድረግ ይቻላል?
- በጋራ ለመጓዝ በጋራ ማሰብ መቻል አለብን፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- አሁን ጊዜው አይደለም እያልኩህ ነው፡፡
- የምን ጊዜ?
- የምንነጣጠልበት ጊዜ ነዋ፡፡
- ምን?
- አሁን ክልል መሆን አይቻልም፡፡
- ምን ችግር አለ?
- እንዴት?
- መንግሥት ባይፈቅድ እኛ ተሰብስበን እናፀድቀዋለን፡፡
- በምን?
- በጭብጨባ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የክልል ባለሥልጣን ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- ምን እየሆናችሁ ነው?
- ምን ሆንን ክቡር ሚኒስትር?
- ሁሉም ሰው ማሰብ አቆመ ልበል?
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው ትንሽ ሰከን ብትሉ?
- ምን አደረግን?
- አሁን አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ አጥታችሁት ነው?
- አገሪቱ ምን ሆነች?
- ምን እያልክ ነው?
- ለውጥ ላይ መሆናችንን ነው የማውቀው፡፡
- ወይ ይኼ ለውጥ ጉድ አፈላ እኮ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- በስመ ለውጥ አገሪቱ ታመሰች እኮ፡፡
- እኛ እኮ የዓመታት ጥያቄያችን በመመለሱ ነው ለውጥ አለ የምንለው፡፡
- ኧረ እስኪ ትንሽ ተረጋጉ፡፡
- የምን መረጋጋት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እስኪ ትንሽ ከራሳችን ባሻገር ስለሌሎችም እናስብ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ተረቱም እኮ ከራስ በላይ ንፋስ አይደል እንዴ የሚለው?
- ይኼ አካሄድ ማናችንንም አያዋጣንም፡፡
- ለምን?
- የጋራ እሴቶቻችን ላይ ብናተኩር ነው ለአንድነታችን የሚያዋጣው፡፡
- ልዩነታችንም እኮ ጌጥ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ እሱን መቼ ካድኩ?
- ታዲያ ምን እያሉ ነው?
- አሁን ጊዜው አይደለም፡፡
- እንዲያውም ጊዜው አሁን ነው፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- ለውጥ ላይ ነና፡፡
- እ. . .
- ለውጡ ሳይቀለበስ እኛም ጥያቄያችንን ማስከበር አለብን፡፡
- ወይ ጣጣ?
- እርስዎ ግን የእኛ ክልል መሆን ለምን አሳሰበዎት?
- እናንተ ከጀመራችሁት የሌሎቹም ጥያቄ አያባራማ፡፡
- ምን ችግር አለው?
- የእናንተን ከተቀበልን በአገሪቱ ላይ ሌሎች አሥራ አንድ ክልሎች መጨመራችን የማይቀር ነው፡፡
- ኢኮኖሚያችን ብቻ አይደለም በ11 በመቶ ማደግ ያለበት፣ የክልሎቻችን ቁጥር በ11 መጨመር አለበት፡፡
- እንግዲህ ሲነገርህ ስማ፡፡
- ምኑን ነው የነገሩኝ?
- አሁን ጊዜው አይደለም፡፡
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- አሁን ክልል መሆን አትችሉም፡፡
- እሱንማ መቀልበስ አይቻልም፡፡
- ምን?
- ሕዝቡን ማቆም አይቻልም፡፡
- ሕዝቡ እኮ እናንተን ነው የሚከተለው፡፡
- ጥያቄውን እኛም እናምንበታለን እኮ፡፡
- ሕዝቡን ከኋላ የምትቀሰቅሰው አንተ እንደሆንክ እናውቃለን፡፡
- ምን ችግር አለው?
- አርፈህ ተቀመጥ፡፡
- ባላርፍስ?
- አንተንም ከልለን እናስቀምጣሃለን፡፡
- የት?
- ቂሊንጦ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ቢሯቸው እያወሩ ነው]
- ምን ተሻለ ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑ?
- የአገሪቱ ጉዳይ ነዋ፡፡
- እንዴት?
- በቃ በየጊዜው በችግር ላይ ችግር ነው የሚደረበው፡፡
- ምን ታደርገዋለህ?
- ቆም ብሎ የሚያስብ ሰው ጠፋ ማለት ነው?
- የሚያሳዝንህ እሱ ነው፡፡
- ፖለቲከኞቻችን እኮ የለየለት ቁማርተኞች ሆነዋል፡፡
- እንዴት ማለት?
- ይኸው በሕዝቡ ሕይወት እየቆመሩ ነዋ፡፡
- እ. . .
- ቁማሩ ጠንከር ሲል የባለሥልጣናትንም ሕይወት እየቀጠፈ ነው፡፡
- ተወኝ እስኪ፡፡
- በተለይ ሰሞኑን ሁለቱ ወዳጅ ፓርቲዎች ያወጡት መግለጫ ያሳዝናል፡፡
- እ. . .
- ለነገሩ ከወዳጅነት ወደ ባላንጣነት መቀየራቸውን በአደባባይ አሳይተዋል፡፡
- ሁላችንም ነን ያዘነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በአሁኑ ጊዜ ግን ከእነሱ ይኼ ይጠበቃል?
- በፍፁም፡፡
- ቀጥሎ አብረው እንዴት ይሠራሉ?
- እሱ የሁላችንም የራስ ምታት ነው፡፡
- እንኳን አጋር ፓርቲ ተቃዋሚዎችም እርስ በርሳቸው እንደዚህ ዓይነት መግለጫ ያወጣሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡
- ምንም አልተሳሳትክም፡፡
- ታዲያ አበቃለት ማለት ነው?
- ማን?
- ኢሕአዴግ ነዋ፡፡
- ኧረ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት እንደዚህ ዓይነት ክፉ ሐሳብ ታስባለህ?
- ሕዝቡማ ጥሩ ሐሳብ ነው እያለ ነው፡፡
- ለምን?
- አገሪቱን ለዚህ ያበቃት ኢሕአዴግ ነው ብሎ ነዋ የሚያስበው፡፡
- ተው እንጂ፡፡
- እውነቴን እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ኢሕአዴግ ከፈረሰ አገሪቱም እንደምትፈርስ አታውቅም?
- ክቡር ሚኒስትር ኢትዮጵያ እኮ ከኢሕአዴግ በፊት ነበረች፡፡
- እ. . .
- ስለዚህ እያሰቡ እንዲያውም ጥሩ ዕድል ሊሆን ይችላለ፡፡
- የምን ዕድል?
- ለእውነተኛው የአገሪቱ ለውጥ ነዋ፡፡
- ተው ስልህ፡፡
- እኔ እንዲያውም ማሠራት ልጀምር ነው፡፡
- ምንድነው የምታሠራው?
- የአበባ ጉንጉን ነዋ፡፡
- የምን የአበባ ጉንጉን?
- መቃብር ላይ የሚቀመጥ፡፡
- የማን መቃብር ላይ?
- የኢሕአዴግ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]
- አሁንስ መላ ቅጡ ጠፋችሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን?
- ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር አሉ፡፡
- ምን ለማለት ነው?
- እንዲያው ሥልጣኑን እኛ ላይ ስታዩት ቀላል መስሏችሁ ነው አይደል?
- ምን የተለየ ነገር ሠራችሁና?
- ይኸው እናንተ እኮ ቅጥ አምባሩ ጠፍቶባችኋል፡፡
- እንዴት?
- ሕወሓትና አዴፓ የቃላት ጦርነት ጀምረዋል፡፡
- እሱ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው፡፡
- እየተዋወቅን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማለት?
- ይኸው ትግራይ ክልል አኩርፎ ከማዕከላዊ መንግሥት ከተነጣጠለ ሰነባበተ፡፡
- ኩርፊያው ሲለቃቸው ይመለሳሉ፡፡
- አማራ ክልል ያለውን ትርምስ መቼም ለእርስዎ አልነግርዎትም?
- እንደዚህ ዓይነት ፈተና ያጠነክረናል፡፡
- ይኸው ደቡብ ክልል ተበታትኖ በመንደር መደራጀት ተጀምሯል፡፡
- እሱም ቢሆን የዓመታት ጥያቄ ነው፡፡
- ኦሮሚያም ቢሆን ከኦነግ የገጠመው ፈተና ያልተጠናቀቀ ነው፡፡
- ስለእሱ አታስብ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ሌሎቹም የአገሪቱ ክልሎችም ቢሆኑ የግጭቶች መናኸሪያ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡
- የእናተው ሥራ ነዋ፡፡
- ይልቁንስ ጣት መጠቆሙን ትታችሁ ሥራችሁን በአግባቡ ሥሩ፡፡
- የምን ሥራ?
- የፌዴራል መንግሥቱ እኮ ክፉኛ ተዳክሟል፡፡
- ማን ነው ያለው?
- እየነገርኩዎት አሁን እኮ የፌዴራል መንግሥቱ በአግባቡ እያስተዳደረው ያለው አዲስ አበባን ብቻ ነው፡፡
- ምን?
- እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን እንደተባሉ አልሰሙም?
- ምን ተባሉ?
- አዲስ አበባን በምክትል ከንቲባነት የሚያስተዷድሯት አውቀው ነው፡፡
- ማለት?
- እሳቸው የከተማዋ ምን እንደሚባሉ ያውቃሉ?
- ምን ይባላሉ?
- ቀዳማይ ከንቲባ!