Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኑሮ የገፋቸውን ለመታደግ

ኑሮ የገፋቸውን ለመታደግ

ቀን:

በተመስገን ተጋፋው

ባረጀው ሶፋ ላይ ጋደም ብለዋል፡፡ እንደ አብዛኛዎቹ የቤታቸው ዕቃዎች እሳቸውም እርጅና ተጭኗቸዋል፣ ዓይናቸውም ደክሟል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የተለያዩ በሽታዎች ይፈራረቁባቸዋል፡፡ በአንድ ወቅት ላይ ታች ብለው ቤተሰብ ያስተዳድሩ የነበሩት ወ/ሮ ብዙነሽ መኮንን፣ ዓይናቸው ብቻ ሳይሆን እግራቸውም ደክሟልና እንደ ልብ አይንቀሳቀሱም፡፡ የተጨማደደ ገጻቸው፣ ደስታ የተለየው ፊታቸው፣ በኑሮ መፈተናቸውን ያሳብቃል፡፡

በ90ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የሚመስሉት ወ/ሮ ብዙነሽ፣ በኮልፌ አጠና ተራ ወረዳ 12 ሲኖሩ፣ ከባለቤታቸው ከአቶ ወንድሙ ወልደ ማርያም አራት ልጆችን አፍርተዋል፡፡

ወ/ሮ ብዙነሽ መንግሥት በሰጣቸው ደሳሳ የቀበሌ ቤት ውስጥ ለዘመናት ኖረዋል፡፡ እርጅና ከቤት ያዋላቸው አዛውንቷ በጉብዝናቸው ወቅት የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ቤተሰባቸውን ያስተዳድሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ጥጥ ፈትለው፣ ነጠላ ቋጭተውና እንጀራ ጋግረው የሚያገኙት በቂ ባይሆንም በልቶ ለማደር ግን አያንሳቸውም ነበር፡፡

ከ20 ዓመታት በፊት ሁለት ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን በሞት ማጣታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ልጆቻቸውን መነጠቃቸው ከባድ ሐዘን ውስጥ ሲከታቸው፣ የባለቤታቸው መሞት ደግሞ መላው ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነቱን በሐዘነተኛዋ ወ/ሮ ብዙነሽ ጫንቃ ላይ ብቻ እንዲያርፍ አደረገ፡፡

ችግራቸውን ከማንም የበለጠ የምትረዳላቸው የወ/ሮ ብዙነሽ የመጀመርያ ልጅ  የኔነሽ ወንድሙ ኤችአይቪ ሕመምተኛ ነች፡፡ እናቷን ለመጦርና የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ግን ከበሽታው ታግላ በየሠፈሩ እየዞረች ልብስ በማጠብ፣ አሻሮ በመቁላት፣ ሊጥ በማቡካትና እንጀራ በመጋገር ስትደክም ትውላለች፡፡ አንዳንዴ የሚያሠራት ከጠፋም የዕለት ጉርስ ለመግዛት የሚሆናትን ገንዘብ ሳታገኝ ትውላለች፡፡

ታናሽ ወንድሟም ከባድ የእግር ሕመም እንዳለበት የምትናገረው የኔነሽ፣ ወ/ሮ ብዙነሽ በዕድሜ ምክንያት ቤት ሲውሉ ቤተሰቡን ማስተዳደር የማትወጣው ፈተና እንደሆነባት ተናግራለች፡፡ ለልመና አደባባይ ባይወጡም የሚላስ የሚቀመስ እስኪያጡ የሚራቡበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡

ያለወገን ዕርዳታ ሕይወታቸውን ማስቀጠል የማይታሰብ ሆኗል፡፡ የባዩሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት ድርጅትም የዕለት ጉርስ የሚሆናቸው የተለያዩ የቤት አስቤዛዎችን እንደሚረዳቸው፣ ይህም በተወሰነ መጠን እያገዛቸው መሆኑን ለሪፖርተር ተናግራለች፡፡ 

ሌላኛዋ ችግረኛ ወ/ሮ ጉቺ ደበሌ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ጉቺ ዕድሜያቸው ወደ 80ዎቹ የሚጠጋ ሲሆን፣ ያለባቸው የዓይን ሕመም ወደ ፈለጉበት ቦታ እንዳይንቀሳቀሱና የአልጋ ቁራኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

ወ/ሮ ጉቺ የሁለት ልጆች እናት ናቸው፡፡ አንዷ ልጃቸው የካንሰር ሕመምተኛ፣ ሌላዋ ደግሞ የተለያዩ የመሳሰሉ በሽታዎች የሚፈራረቁባት እንደሆነ ሰምተናል፡፡   

ወ/ሮ ጉቺ ከዚህ በፊት እንጨት ለቅሞ በመሸጥ ይተዳደሩ ነበር፡፡ ከልጆቻቸው አባት ጋር ከተለያዩ ቆይተዋል፡፡

መንግሥት በሰጣቸው በትንሿ የቀበሌ ቤት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት መሯሯጥ ቀርቶ ከአልጋቸው ተነስተው ሰገራ መውጣት እንደሚከብዳቸው ይናገራሉ፡፡ የአጥንት መሳሳት በሽታ ያለባት ልጃቸውም የአልጋ ቁራኛ መሆኗን  የሚናገሩት ወ/ሮ ጉቺ፣ ኑሮ የማይወጡት ፈተና እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡

የወ/ሮ ጉቺ የመጀመርያ ልጅ አየለች ጥላሁን፣ በአሁን ሰዓት የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ደፋ ቀና ብሎ መሥራት ከብዷታል፡፡ በበሽታዋ ምክንያት ብዙ ሥራዎችን መሥራት እንደማትችልና እናቷን ለመጦር ስትል ግን ጠዋት ጠዋት አካባቢን የማፅዳት ሥራ (የሴፍቲኔት ፕሮግራም) እንደምትሠራ፣ በዚህም የምታገኘው ገቢ ከእጅ ወደ አፍ እንደሆነና የዕለት ጉርሳቸውን እንማይሸፍንላቸው ተናገራለች፡፡ የባዩሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት ድርጅትም ባያግዛቸው መኖር እንደሚከብዳቸው ትገልጻለች፡፡

ለመሰል የአካባቢው ነዋሪዎች ቤዛ የሆነው የባዩሽ በአሥር ሰዎች የተጀመረ በጎ አድራጎት ድርጅት ነው፡፡ 20 የሚሆኑ ተማሪዎችንና አንድ አዛውንትን በመርዳት የተጀመረ የዕርዳታ ድርጅት ነው፡፡

የባዩሽ ኮልፌ የበጎ አድራጎት ድርጅት በአሁን ሰዓት በቋሚነት 300 ለሚሆኑ ችግረኛ ተማሪዎችና 30 ለሚሆኑ አረጋውያን በየቤቱ በመሄድ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እንደሚሠራ የድርጅቱ ፕሬዚዳንት አቶ ውብሸት ተካ ተናግረዋል፡፡

የባዩሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት ድርጅት ከ200 በላይ የሚሆኑ አባላት ያሉት ሲሆን፣ በየሳምንቱ በቡድን በመከፋፈልና በየተረጂዎቹ ቤት በመሄድ ለአረጋውያንና ለተማሪዎች ድጋፍ ይሰጣል፡፡

የባዩሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት ድርጅት በተለያዩ በዓላትም ሃይማኖት ሳይለዩ በየቤቱ በመሄድ ከተረጂዎቹ ጋር አብረው እንደሚያሳልፍ አቶ ውብሸት ገልጸዋል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቱም አረጋውያንም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ሕክምና በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ወደ ሕክምና በመውሰድ፣ ቤት የፈረሰባቸው ካሉ ቤት በማደስ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሠሩ አቶ ውብሸት አስታውሰዋል፡፡ 

የባዩሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት ድርጅምት በየዓመቱ ሊስትሮ በመሥራት፣ ሶፍት በመሸጥና እንዲሁም ሌሎች ገንዘብ የሚያስገኙ ሥራዎችን በመሥራት ለአረጋውያንና ለሕፃናት የሚሆን የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...