Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኢትዮጵያን ያላጠገቡ ከብቶች

ኢትዮጵያን ያላጠገቡ ከብቶች

ቀን:

ጥሩ መኖሪያ ቤት፣ ዘናጭ መኪና፣ በቂ ገቢ ያለው ሀብታም ባይሆንም ደህና ኑሮ ከሚኖሩት መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ በከተሜዎች ዓይን እነዚህ ቁሶች የኑሮ ደረጃ ማሳያ፣ የገቢ መለኪያ የሀብትና ድህነት መሥፈሪያ ቁና ናቸው፡፡ አቶ ዳሉ ቦሩ ግን መኪናም፣ ዘናጭ ቤትም የሚያስተዳድረው ድርጅት አሊያም በወር የሚከፍለው ቀጣሪም የለውም፡፡ ግን በሚኖርበት አካባቢ ባለ ፀጋ ከሚባሉት ውስጥ ነው፡፡ የሚኖረው የሳር ክፈፍ ባላት እንደ ነገሩ ተደርጋ በተሠራች ጎጆ ውስጥ ነው፡፡ የሚቀመጥበት የረባ ወንበር እንኳ የለውም፡፡

ነገር ግን 100 ከብቶች፣ 20 ግመሎች፣ 80 በጎችና ፍየሎች ያለው ቱጃር ነው፡፡ ወላጆቹም ባለፀጋ ናቸው፡፡ አባቱ በሚኖሩበት ቦረና አካባቢ አባ ኦላ እየተባሉ የሚጠሩ የተከበሩ ሰው ናቸው፡፡ አባ ኦላ የሚሏቸው የአካባቢው ቆርቋሪ መሆናቸውን በማስታወስ ነው፡፡ ከባለ ፀጋ ቤተሰብ የተገኘው አቶ ዳሉ በጉርምስና ዕድሜው ትዳር ለመያዝ ቅድሚያ ጥሩ ደመወዝ፣ ቪላ፣ መኪና ይኑረኝ አላለም፡፡ በረቱን የሞሉት ከብቶች ጥሎሽ፣ ጎጆ መውጫና መተዳደሪያ ሆነውታል፡፡

በትዳራቸው ልጆች አፍርተዋል፡፡ ከማጀት እርጎ፣ ቅቤና ወተት በገፍ ነው፡፡ ባንክ ያስቀመጡት ረብጣ ብር ባይኖራቸውም እያንዳንዱ ከብት በሺዎች የሚቆጠር ገንዘባቸው ነው፡፡ አንዱን ኮርማ ገበያ ነድቶ ሸጦ በሚያገኘው የጎደለውን ይገዛል፣ ለልጆች ትምህርት ቤት የሚያስፈልገውን ያደርጋል፡፡ ከብቶቹን ደህና አድርጎ የቀለባቸው እንደሆነ፣ ዋጋቸው በዕጥፍ ይጨምራል፡፡ በአጠቃላይ ከብቶቹ የኑሮው መሠረት፣ ዋስትናው፣ መከበሪያውና መኩራሪያው ጭምር ናቸው፡፡

ለነገሩ ደረቃማውንና ሞቃታማውን የአየር ንብረት ተቋቁመው ጥሩ ምርት የሚሰጡት የቦረና ከብቶች ለአቶ ዳሉ ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካም የማይተኩ ሀብት ናቸው፡፡ የቦረና ከብቶች የአፍሪካ ሀብት ናቸው የሚባለው ከቁጥር ባለፈ በሌሎች ከብቶች ላይ የማይስተዋሉ ባህሪ ያላቸው ልዩ ዝርያ ስለሆኑ ነው፡፡

‹‹ቦረና ብዙ መኖ በሌለበት፣ ብዙ ውኃ በሌለበትና ብዙ አረንጓዴ ተክል በሌለበት ቦታ መኖር፣ ማምረት የሚችል ዝርያ ነው፡፡ ጥሩ የሥጋ ምርት ይሰጣል፡፡ ቦረና አካባቢ ያሉ አብዛኛዎቹ አርብቶ አደሮች ሕይወታቸው ከዚህ ዝርያ ጋርተቆራኘ ነው፤›› የሚሉት በዓለም አቀፍ የእንስሳት ጥናት ተቋም የአኒማል ጀኒቲክስ ብሪዲንግ ባለሙያ ታደለ ደሴ (/) ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር በመተባበርThe Story of Cattle in Africa” የሚል መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ 200 በላይ ገጾች ባሉት ትልቅ ጥራዝ የቦረና ከብትን ጨምሮ ሌሎች በአፍሪካ የሚገኙ ልዩ ልዩ የከብት ዝርያዎች፣ ታሪክ፣ የተጋረጡባቸው ፈተናዎችና ዝርያዎቹን እንዴት ከመጥፋት መታደግ እንደሚቻል ከዝርያዎቹ ልዩ ልዩ ባህሪያት ጋር አቀናጅተው በጽሑፉ አሥፍረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ልዩ ዝርያዎች መካከል የማይመች የአየር ፀባይን ተቋቁሞ ጥሩ ምርት የሚሰጠውን የቦረና ከብት ጠንካራ ጎኑን እንዴት መጠበቅና በምርምር ማጎልበት እንደሚቻልም በጽሑፉ አሳይተዋል፡፡ ‹‹እያንዳንዱ ዝርያ የራሱ የሆነ ጠንካራና ደካማ ጎን አለው፤›› የሚሉት / ታደለ፣ በእያንዳንዱ ዝርያ ውስጥ ያሉ ጠንካራ ባህሪያትን ማጎልበት፣ ደካማ የሚመስሉትን ደግሞ በምርምር በማሻሻል ከእንስሳት ዕርባታው ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም አሁን ካለበት የላቀ ማድረግ እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ ይንንም ለማድረግ በአገሪቱ የሚገኙ 27 ዓይነት የከብት ዝርያዎች እንዳይጠፉ ጠብቆ ማቆየት ግድ ይላል፡፡

የኢትዮጵያ ሀብት ከሚባሉት 27 የከብት ዝርያዎች መካከል ሚዛን ቴፒ አካባቢ የሚገኝኘው ‹‹ሸኮ›› የሚባለው አንዱ ነው፡፡ ሸኮ ለበርካታ እንስሳት ዕልቂት ምክንያት የሆነውን በቆላ ዝንብ የሚመጣውን የገንዲ በሽታን የመቋቋም ልዩ ባህሪ ያለው ዝርያ ነው፡፡ ይህ የከብት ዝርያ ግዙፍና የሚሰጠው ምርትም ከፍተኛ የሚባል ቢሆንም፣ የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው ዝርያዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

በአካባቢው ያሉ ገበሬዎች ደግሞ የሸኮ ልዩ ዝርያ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ የሚኖሩት በግብርና ነውና የእርሻ በሬ ይፈልጋሉ፡፡ ሸኮን እንደ ማንኛውም ከብት ጠምዶ ማረስ ግን አይቻልም፣ አደገኛ ነው፡፡ ስለዚህም ወደ ወልቂጤ፣ ወለጋና ጎጃም አካባቢ ሄደው የእርሻ በሬ ይገዛሉ፡፡ እነዚህ ከሌላ አካባቢዎች የሚገዙ ከብቶች ከሸኮ ሲዳቀሉ ዝርያው እየተበረዘ ሊጠፋ ሥጋት ማሳደሩን ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡

የሙርሲ ከብትም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ልዩ ባህሪ ካላቸው የከብት ዝርያዎች አንዱ ነው፡፡ የሙርሲ ከብት ወበቃማና እርጥበት አዘል በሆነ ዝንብና ሌሎች ጥገኞች በሚበዙበት አካባቢ ሁሉንም ተቋቁሞ ምርት መስጠት የሚችል ዝርያ ነው፡፡

በዓባይ ዙሪያ የሚገኘው የፎገራ ከብትም ልዩ ዝርያ ተብለው ከተመዘገቡት 27 የኢትዮጵያ ሀብቶች መካከል ነው፡፡ የፎገራ ከብቶች ውኃ በሚያቁር ጨፌ ቦታ ላይ ይኖራሉ፡፡ ‹‹ቀኑን ሙሉ ውኃ ውስጥ ቆመው እየጋጡ የፎገራ ከብቶች ሸሆናቸው አይበሰብስም፡፡ ሌሎች ከብቶች ግን ወዲያው ቁስል በቁስል ይሆናሉ፤›› የሚሉት ዶክተሩ የፎገራ ከብት እርጥበትን የሚቋቋም ልዩ ጂን እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ ወለጋ ውስጥ ሆሮ ጉድሩ አካባቢ የሚገኘው የሆሮ ከብትም ዝርያው ልዩ ነው፡፡ አካባቢው በእርሻ የሚታወቅ ሲሆን፣ የሆሮ ከብት ደግሞ ለእርሻ የተመቸ ነው፡፡ የሆሮ ከብቶች በግዙፍ ተክለ ቁመናቸው፣ በጉልበታቸው ለእርሻ በጣም ተመራጭ ናቸው፡፡

‹‹የሕዝብ ቁጥራችን እየጨመረ ነው፡፡ ብዙ ወተት፣ ብዙ ሥጋ እንፈልጋለን እነዚህን ከብቶች ካጠፋናቸው ወይም በሌላ ዝርያ ከተካናቸው ዝርያዎቹ ያላቸውን ልዩ ባህሪ እናጣለን፡፡ ያላቸውን ልዩ ባህሪ እየጠበቅን ማሻሻል አለብን፤›› የሚሉት ዶክተሩ ዝርያዎቹን ጠብቆ ለማሻሻል ደግሞ የዘረመል ዱካቸው መመዝገብ፣ የገንዲ በሽታ መቋቋም የሚያስችሉትንሸኮን ጂኖችን መለየትና ብዙ ወተት የሚሰጡ ዝርያዎች ላይ መክተት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በዚህም ገንዲ በሽታን የሚቋቋሙና ምርታማ የሆኑ ከብቶች ተገኙ ማለት ነው፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ገንዲን ካላጠፋን በስተቀር የሸኮ መጥፋት በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ እነዚህ ከብቶች ያላቸው ጥሩ ጎን ምንድነው የሚለውን ለይቶ፣ ዝርያዎቹ የማይጠፉበትን መንገድ በጥናትና ምርምር በፖሊሲ እንዲታገዝ መደረግ አለበት፤›› ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ የከብት ሀብትና ሌሎች የዘርፉ ፈተናዎች

2010 .ም. በኢትዮጵያ 60,392.019 ከብቶች፣ 31 ሚሊዮን በላይ በጎች፣ 32 ሚሊዮን በላይ ፍየሎች፣ 1.4 ሚሊዮን በላይ ግመሎች እንደሚገኙ የእንስሳት ጥናት ተቋሙ ሪፖርት ያሳያል፡፡ 60 ሚሊዮን የሚበልጥ ቁጥር ያላቸውን ከብቶች (በሬና ላም) ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም ማግኘት ግን አልተቻለም፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የወተት ላሞች፣ የሥጋ በሬዎች ያሏት ኢትዮጵያ ማግኘት ያለባትን ያህል ምርት እያገኘች እንዳልሆነ ከሆላንድ የሚላኩ ልዩ ልዩ የወተት ምርቶች ምስክር ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በከብት ቁጥር በአፍሪካ አንደኛ ብትሆንም፣ ምርቱ ግን እዚህ ግባ የማይባል ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ይዘረዘራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ የከብት በሽታዎች ዘርፉን ይፈታተናሉ፡፡ የመጀመርያው በቆላ ዝንብ የሚመጣው ገንዲ ነው፡፡ የከብቶችን እግርና አፋቸው አካባቢ የሚያቆስል በሽታም እንዲሁ ፈተና ነው፡፡ እነዚህን በሽታዎች በሕክምና መከላከል ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን የከብት ሀብት ያህል ተጠቃሚ እንዳትሆን የሚያደርጋት የከብቶች በሽታ ግን አይደለም፡፡ አገሪቱ ከዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነት ያመነመነው በዋናነት ያሉት የከብት ዝርያዎች በርካታ ጠንካራ ጎኖች ቢኖሯቸውም ምርታማ አለመሆናቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ላሞች በቀን በአማካይ ከሁለት ሊትር ወተት በላይ አይሰጡም፡፡ የውጭ ዝርያዎች ግን በቀን 30 ሊትር ድረስ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡

ከዚህ በሻገርም 30 በመቶ የሚሆነውን የከብት ሀብት የሚይዘው ደገኛው ነው፡፡ የደገኛው ቀዳሚ መተዳደሪያ ደግሞ እርሻ ነው፡፡ ከብት የሚረባውም የእርሻ በሬ ስለሚፈለግ እንጂ ለወተትና ሥጋ ምርት አይደለም፡፡ 70 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የከብት ሀብት የሚይዙት ቆለኞቹ አርብቶ አደሮች ደግሞ ከብት የሚያረቡት ቁጥር ማብዛት ላይ ትኩረት በማድረግ ነው፡፡ ጥቂት ከብት ይዞ ብዙ ምርት ማግኘት ላይ አይሠሩም፡፡

በቆላማው የአገሪቱ ክፍሎች የአርብቶ አደሩን ብቸኛ ሀብት በአንድ ጀንበር ድምጥማጡን የሚያጠፋ የተፈጥሮ አደጋ ጎርፍ ሊከሰት ይችላል፡፡ ድርቅም ሌላው ከብቶቻቸውን የሚጨርስባቸው ክስተት ነው፡፡ ቁጥሩ የበዛ ከብት ያለው ሰው የተወሰኑት ሊተርፉለት ይችላሉ፡፡ ግማሹ ቢጠፋ ግማሹ ስለሚቀር በአንዴ ባዶ እጃቸውን የሚቀሩበትን ዕድል ጠባብ ይሆናል፡፡

‹‹አንድ አርብቶ አደር ብዙ ከብቶች ባሉት መጠን ነው ከሥጋት ነፃ እንደሆነ የሚሰማው፡፡ ለዚህም ነው የከብቶቹን ቁጥር የሚያበዛው፤›› በማለት ዶክተር ታደለ ሁለተኛውን ምክንያት ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ቁጥሩ የበዛ ከብት ያለው የሀብት መደቡ ይለያል፡፡ ብዙ የከብት ቁጥር ያለው ሰው የሚሰጠው ክብርም ከሌላው የተለየ ነው፡፡ ‹‹ሚስቱ ውኃ ልትቀዳ ብትሄድ ቅድሚያ የሚሰጣት ለእርሷ ነው፤›› በማለት ዶክተር ታደለ በአንዳንድ ማኅረበሰብ ውስጥ ብዙ የከብት ቁጥር ላለው ሰው የሚሰጠው ቦታ ልዩ በመሆኑ ቁጥር ማብዛት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ያስረዳሉ፡፡

በቆለኛው ደገኛው ከብት አርቢ የማኅበረሰቡ ክፍል ያለው ዓላማ ነው አገሪቱ ካለባት የከብት ሀብት መጠን ተጠቃሚ እንዳትሆን ያደረጋት ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ በሁለቱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያለውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለደገኞቹ ዘመናዊ የማረሻ ዘዴ ማስተዋወቅ፣ ለቆለኛው ደግሞ የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎችን የተመለከተ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክት የማተላለፍበት ሥርዓት መዘርጋት፣ ሀብት በቁጥር ብቻ ሳይሆን በምርታማነት መሆኑንም ማስተማር እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...