ሰላም! ሰላም! የኑሮ ውድነቱ እንዴት አርድጓችሁ ሰነበተ ይሆን? ‹‹ዘንድሮ በ‘ሳይለንሰር’ ማለቃችን ነው፤›› ያለኝ አንድ አብሮ አደግ ወዳጄ ነው። ድምፁን አጥፍቶ የሚጠፋውና የሚያጠፋን በዝቷል ለማለት ፈልጎ እኮ ነው። ቅኔውም ሳይቀር እንግሊዝኛ ጣል ይደረግበት መጀመሩን ንገረን ባላላችሁኝ! ታዲያ እኛ ደግሞ ሰበብ አይጥፋ እንጂ ሰበብ ከተገኘ፣ ነገር ዓለሙን ለመተው የሚቀድመን የለም አይደል? የሚቀድመንን ተውት የሚደርስብን ሲኖር እኮ ነው! ወደን አይደለም በክፉም በደጉም አንደኛ የምንወጣው ለካ? ቢያንስ በትንሹ ለ48 ሰዓት ‘አይገርምህም? አይገርምሽም?’ ስንባባል ኑሮአችን ሲኦል ይሆናል። ድሮስ ከስንፍና የገዘፈ ምን ሲኦል አለ አትሉም? እውነቴን ነው። ከዋጋ ጭማሪው እኮ እየባሰ የመጣው በጭምርማሪ ወሬ የታገዘ ሥራ ፈትነት ነው። ‹‹ወይ አንሠራ ወይ አናሠራ በቃ ጠቅላላችን በመሸ በከንቱነት ልንጠቃለል ምን ቀረን?›› ስትል ማንጠግቦሽን የሚሰሟት ጎረቤት ያሉ ሴት፣ ‹‹እኛ ምን እናድርግ ምኑንስ አጠፋን፣ ተኙ ተኙ እያሉን ሳያንቀላፋን፤›› ይሏታል። ጉድ እኮ ነው ዘንድሮ እናንተ! ነጋ ጠባ ስለሥራ ክቡርነት ብዙ ይባላል ሰው ስለእንቅልፍ ያወራል። አልጨበጥ ያለ ነገር!
ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደግሞ ሰሞኑን የድለላው ሠፈር እንደ ውርጭ አዘሉ የአየር ንብረት ሥራችን ጭር ብሎ ቢመለከት ተገርሞ፣ ‹‹መንግሥት በጥርጣሬ እያደነ ከሚያስረው ይልቅ ራሱን በወሬ ያሰረው ብዛቱ፤›› ሲለኝ ሰነበተ። እኔም እንደ ነገርኳችሁ ምሬቱና ሁካታው አልጣጣም ብሎኝ ስለነበር ለባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ሰበብ ይገኝ እንጂ ደግሞ ለመቀመጥ!›› ብዬው እጥፍ አልኩ። ‹‹ይታያችሁ ‘ዳገቱ ላይ መቆምም ሆነ መቀመጥ አይፈቀድም’ በተባለበት በዚህ ዘመን ምንም ላይፈይድለት ሰው የወሬ ችግኝ መንከባከቡን አልተወው አለ፤›› ስል ቢሰማኝ ደግሞ አንዱ፣ ‹‹ከዘንድሮ ልማት የአዛውንቶች ልማድ አትራፊ ሆኗል አንበርብር። ዝም ብለህ ነው አንተ!›› አይለኝ መሰላችሁ? ኧረ እንዲያው በሞቴ እንዲህ ያለውን ጨዋታ ባወጋው ያለ እናንተ ማን ያምነኛል? ያውም እምነት ተረት በሆነበት ዘመን? ኧረ ተውኝ! ኋላ እንዲህ የሚሉኝን ዝም ብዬ ባስተውላቸው አንዱ ያላቅሙ ገብር ተብሎ የተማረረ፣ ሌላው የክፍለ ከተማ ጣጣ ያበገነው፣ በአጠቃላይ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ያንገበገበው ተሰብስቦ እንደሚወርድብኝ ተረዳሁ። ሰው ቅሬታ ሰሚው ሳይቀር ቅር እያሰኘው ቢቸገር ሲያገኛችሁ እናንተው ላይ ማራገፉን ሥራ አድርጎታል። ከመሥራት እጅን አጣጥፎ መቀመጥ እንዳማራጭ እየወሰደም መጥቷል። ‹‹በዚህ ከቀጠለ መጨረሻው ምን ይሆን?›› እያልኩ ወዳጆቼን ባዋያቸው፣ ‹‹ስንቱን እንተንብይ?›› ነበር መልሳቸው። ‘አንዳንዴ እያሰብኩት የዚያችን ልጅ ነገር፣ ካልመሸ አይታወቅ ካልነጋ አይነገር፤’ ያለው አዝማሪ ለካስ ወዶ አልነበረም?
እናላችሁ በዚህ አካሄዳችን እንኳን ሌላ ሌላው ውጥንና የተጀመረው ለውጥ ሊሳካ አራት ቢሊዮን ችግኝ ተክለን መፅደቁን መጠራጠር መጀመር አለብን። እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ላይ ተስፋ መቁረጥ ተጨመረበት የሚለውን አስባችሁታል? ‘መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንሠለፋለን ብለው፣ ወንዝ እንገድባለን ብለው . . .’ እያለ አቤት ስንቱ ይሆን የሚሳለቅብን? ‹‹እንዴ! ምንድነው እንዲህ ማለቃቀስ? ከአገርህ ሌላ አገር እንደሌለህ እያወቅህ የሰውን አገር የራስ ማስመሰል ምን የሚሉት በሽታ ነው?›› እያሉ አዛውነቱ ባሻዬ አንድ አይቼው የማላውቅ እንግዳ ሰው ሲገስፁ ሰማሁ። ‹‹ለመሸነፍም እኮ ጥሩ ምክንያት ያስፈልጋል!›› ያሉዋት አባባል ግን ሆዴ ቀረች። ከሐዲዱ ያፈነገጠውን በማስተካከል እኮ ባሻዬን የሚደርስባቸው የለም። ድሮም የአዛውንት ክብሩ መካሪነቱና አስታራቂነቱም አይደል? በዚያው ልክ ወስላቹና ሂያጁ ‘ኧረ ማን ነው የሚታመነው ዘንድሮ?!’ እያሰኘን ግራ አጋባን እንጂ! ምን ልላችሁ ነው ይሄን ያመጣሁት መሰላችሁ? ለመቆምም ለመውደቅም ጥሩ ምክንያት ማለፊያ ነው። በሌላ በሌላው ይሁን ግድ የለም። አገር በብሔርተኞች ታመሰ፣ በሐሰተኛ ወሬ መተማመን ጠፋ፣ አሉባልታ የምሁራን መለያ ሆነ፣ ወዘተ. እያሉ መጉበጥ ግን ለማን ተብሎ? ኧረ ለማን?!
‹‹ሳይንቀሳቀሱ ረብጣው እንደ ቅጠል የሚረግፍላቸው የቅባት ልጆች ብቻ ናቸው፤›› ብሎ አንድ የመንደሬ ጎረምሳ የነገረኝ ትዝ ቢለኝ ተወዝፌ መቅረቴ ትውስ አለኝና መሯሯጥ ጀመርኩ። በከባዱ በሺዎች ለሚከራይ ቪላ ቤት የሚመጥነውን ስፈልግ ውዬ ተቀጣጠርኩና ጫማ ላስጠርግ አረፍ አልኩ። አጠገቤ ሁለት ወጣቶች እንደ እኔው ጫማ እያስቦረሹ ሙግት ገጥመዋል። መስማት ጀመርኩ። ‹‹ኮምፒዩተር ኢትዮጵያ ውስጥ ቢፈለሰፍ የላሊበላን ያህል አይደንቀኝም፤›› ይላል አንደኛው። ይህን የሚለው ኋላ ላይ እንደተረዳሁት ላሊበላን እኛ አልሠራነውም ለማለት ነው። ‹‹እንዴት እንደዚያ ትላለህ?›› ይለዋል ጓደኛው። ተማሮበታል። እኔም ‹‹ለምን?›› ብዬ ጣልቃ ገባሁ። ‹‹መረጃውና ዕውቀቱ በአግቦ፣ በሽሙጥና በሐሜት ላይ የተመሠረተ አገር እንዴት ብሎ ነው በምክንያታዊ አስተሳሰብ ላይ የተንጠለጠለ ያንን የመሰለ ረቂቅ የሥነ ሕንፃ ‘ቴክኒክ’ ሊያሳይ የሚችለው?›› ሲል መልሶ ጠየቀን። ማናችንም ልንመልስለት አልሞከርንም። የዛሬው እኛነታችን ዝብርቅርቅ ቢሆንበት ነው ያ ወጣት ይህን መሰል ሙግት ማንሳቱ፡፡ ለነገሩ ልክ መስሎ ታይቶኛል። የቀጠሩኝ ደንበኞቼ ደርሰናል ብለው ሲደውሉልኝ ተነስቼ ስሮጥ ኑሮ ቀልባችንን ነጥቆን መጠያየቅ ያለብንን ጥያቄዎች እንደረሳናቸው ታወቀኝ። የትናንቱን የመንፈስ ከፍታ ተረስቶ ዛሬ በቁሳቁስ የበላይነት፣ በስመ ማንነት በደል ትርክትና በከንቱ ነገሮች ላይ ተጥደን ውለን ማደራችንን የሚያጤነንን ግራ እንዳጋባን በስሱ ገባኝ። በስሜት መነዳቱ እስከ መቼ እንደሚያዛልቀን እንጃ!
ታዲያ እውነት የማትጥመን እዚህ እዚህ ላይ ነው። ከኅብረተሰባዊነት ግለኝነት፣ ከጋራ ጥቅም የግል ፍላጎት ስለተቆጣጠሩን ችግሮቻችን አልተቀየሩም። ‹‹ፎርማታቸው›› ቢቀየር አሁንም የለቅሷችን ዜማዎች አልተቀየሩም። ለቅሶ ብል ይልቅ በቀደም ለታ ባሻዬ ከአልጋቸው ሳይወርዱ መርዶ ሰምተው፣ ‹‹ታሞ እያለ ምናለበት ሄጄ ብጠይቀው ኖሮ!›› በማለት በራሳቸው በጣም አዘኑ። ታዲያ ልጃቸው ልብ ብሏቸው ኖሮ፣ ‹‹አሁን ይህን ያህል ራስህን መውቀሱ ፋይዳ የለውም። ባሻዬ አውቀው ያጠፋሉ የሚል ማን አለ? ደግሞም ራስን እየወቀሱ ሆድን በቂም ከመወጠር ይቅርታ የማድረግን ባህል ብናዳብር ኖሮ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ንስኃ ለመግባት የሚቀድመው ባልነበር፤›› አይላቸው መሰላችሁ? ደፋር እኮ ነው! ባሻዬ ምሁሩ ልጃቸው ያላቸውን ሲነግሩኝ፣ ‹‹ይቅርታ ማለት ውርደት አከናናቢነቱ ጎልቶ ይሆን እንዴ ሙሰኛን መፈለግ የዱር እንስሳ ከማደን በላይ ከባድ የሆነው?’ ስል ራሴን ጠየቅኩ። ወይስ ውስጡ ለቄስ ነው? ለእናንተው ብተው ይሻላል።
የነገርኳችሁ ቪላ ቤት ደለብ ባለ ረብጣ ቢከራይልኝ ‘ኮሚሽኔን’ ተቀብዬ ወደ ሌላው የድለላ ሥራዬ ሮጥኩ። ታክሲ ተሳፍሬ በጉዞ ላይ ሳለሁ ታዲያ የሰማኋትን ቀልድ ጣል ላድርግላችሁ። ሁለት እጅግ የሚበሻሸቁ ጓደኛሞች ናቸው። አንደኛው አባቱ በቅርብ ከማረፋቸው፣ የሚበሻሸቀው አብሮ አደግ ጓደኛው ደግሞ በጠና ታመመበት። ሊጠይቀው ቤቱ ሲሄድ ሳቅ የራቀውን ታማሚ ወዳጁን ፈገግ ሊያሰኝ ያዘጋጀውን ደብዳቤ እየሰጠው፣ ‹‹በል እንግዲህ ለአባቴ የምታደርሰው ነው፤›› ቢለው፣ ‹‹ወዳጄ! እኔ እኮ ወደ ገሃነም አይደለሁም!›› አለው በማለት አንዱ የሴት ጓደኛውን ሲያስቅ እኔንም ፈገግ አሰኘኝ። በውጥረት ቀኑን አሳልፌ ስለነበር ከልቤ ሳቅኩ። ከሳቄ ጀርባ አንድ ተሳፋሪ፣ ‹‹አይ የሰው ልጅ! ገሃነም መውረድ ፈርቶ፣ ከሥልጣን በሰላም መውረድ ፈርቶ፣ ስንቱን ፈርቶ ይሆንለታል?›› ሲል ይሰማ ነበር። ለአምባገነኖች ከሥልጣናቸው መውረድ በቁም ከመሞት በላይ ሲዖል እንደ መውረድ እንደሚቆጥሩት ታሪክ አላነበበም መሰል? ከንባብ የተጣላ ትውልድ!
በሉ እንሰነባበት። የቀረኝን ሥራ አጠናቅቄ ወደ ቤቴ ስመለስ አመል ነውና ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ብቅ አልኩ። በጂን፣ በቢራና በድራፍት ቸበርቻቻ ያለው የግሮሰሪዋ ታዳሚ ወሬው ሁሉ ስለነፃነት ታጋይ ሟቹ ማንዴላ ነበር። የባሻዬ ልጅም በወሬው ዋና ተሳታፊ ስለነበር በቅጡ ሰላም አላለኝም። እየቆየሁ የሚያወሩትን ሳዳምጥ ውይይት ሳይሆን ክርክር ይዘው ነበር። ምን መሰላችሁ? ‘ማንዴላ የኖቤል ሽልማት ሲሸለሙ ጋንዲ ሁለት ጊዜ ለኖቤል ሽልማት ታጭተው ሳይሸለሙ የቀሩበት ምክንያት ምንድነው?’፣ ‘ማንዴላ በአሜሪካ ከአሸባሪዎች ስም ዝርዝር መሀል ስማቸው በቅርብ ተሰርዞ ወዲያው ሲሞቱ ምዕራባውያን መሬት ሊነጠፉ መድረሳቸው አያዝተዛዝብም ወይ?!’ ወዘተ. በሚሉ ሐሳቦች ሌላ ዓለም ተፈጥሯል። የባሻዬ ልጅ ደግሞ፣ ‹‹ምንም አልን ምን ማንዴላ ታላቅ ሰው ናቸው። የጥቁሮች ፈርጥ ሆነው ሲታወሱ መኖራቸው ክብራችን ነው፤›› እያለ በስሜት ተናገረ። ነገር ማለዘቡን መቼም እንደ ባሻዬ ልጅ የሚያውቅበት የለም፡፡ ያን ሁሉ ሲንጫጩ የነበሩትን ጠጪዎች ዝም አሰኝቶ፣ ‹‹በአፓርታይድ የሰቆቃ አገዛዝ ፍዳዋን ያየች አገር ነፃ ለማውጣትና እንደ እንስሳ ይቆጠር የነበረን ሕዝብ ሰብዓዊ ክብሩን ለማስመለስ የተደረገ ትግል የመራ ጀግና ሊወደስና ሊከበር ግድ ይላል፡፡ ምንም እንኳ ሞት የማይቀር ክስተት ቢሆንም ማንዴላ ሞቱ አይባልም፡፡ ጥላቻን በፍቅር፣ ጭቆናን በእኩልነት፣ ጭፍጨፋን በሰላማዊ ድርድር የቀየረ ጀግና ሞተ አይባልም፤›› እያለ ሲናገር የሁላችንም ልብ አብሮት ነበር፡፡ ጀግና ይፎከርለታል እንጂ አይፎክርም፡፡ ዓለም ስለማንዴለ ጀግንነት ብዙ ተናገረ እንጂ ከእሳቸው አፍ የወጣው ሰላም፣ እኩልነትና የጋራ ዕድገት ነበር፡፡ ለዚህም ነው ጀግና ይፎከርለታል እንጂ አይፎክርም የሚባለው፡፡ እናማ ወገኖቼ! እስቲ እኛም ታሪክ ሠርተን ሌሎቹ ያውሩልን፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ፍለጠው፣ ቁረጠው፣ በለው፣ ዘራፍ. . . ስንል ከፉከራችን በስተጀርባ ፍርኃት ያለ ይመስለኛል፡፡ አይመስላችሁም? መልካም ሰንበት!