አንድ ሕፃን በፅንስም እያለ ሆነ ከተወለደ በኋላ የጤንነቱ ጉዳይ ከማንም በላይ የሚያስጨንቀው ቤተሰቦቹን ነው፡፡ ከሕመም ጋር የተወለዱ ወይም ከተወለዱ በኋላ ሕመም ያጋጠማቸው ሕፃናት ቤተሰቦች ሁሌም አቅላቸውን እንደሳቱ ነው፡፡
ልጃቸውን ለማዳን ላይ ታች ማለቱ፣ መባከኑ ከሁሉም በላይ ደግሞ እንቅልፍ የሚነሳውን ጭንቀት ተቋቁሞ መኖሩ ከባዱ የወላጆች ፈተና ነው፡፡ የወለዱትን ሕፃን በሞት መነጠቅ ወይም ያረገዙትን ፅንስ በሕመም ምክንያት ማጣትም ልጅ ወልዶ ለመሳም የጓጉ ቤተሰቦችን ልብ የሚሰብር ነው፡፡
ከተፈጥሮ ጋር ተያይዞ ልንከላከላቸው በማንችላቸው በሽታዎች ሕፃናትን ማጣት አሊያም ሕመምተኛ ሆነው ሕይወታቸውን ሲዘልቁ ማየት የተመደ ቢሆንም፣ መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች ሕፃናትን በሞት መነጠቅ ግን ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፡፡
ዛሬ ላይ እናቶች አሥር ብወልድ የሚያድግልኝ እኩሌታው ነው የሚሉበት ዘመንም እያለፈ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን በገጠርም ይሁን በከተማ ሕፃናት ተወልደው የመሞት ዕድላቸው በእጅጉ ቀንሷል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕይወት አድን ክትባት ያለው ፋይዳ ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡
ለጤናማ ሕይወት ስንቅ የሆኑና መቆጣጠር የሚቻሉ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰቱ ዋና መሣሪያ የሆኑት የክትባት ዓይነቶች፣ እንደተቀረው ዓለም ሁሉ በኢትዮጵያ እየተሰጡና የሕፃናትን ሞት በእጅጉ እየታደጉ ቢሆንም ክፍተቶች መታየታቸው እልቀረም፡፡
የዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ሰሞኑን በጋራ ባወጡት መግለጫም፣ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2018፣ ከ870 ሺሕ በላይ ሕፃናት፣ የኩፍኝ (ሚዝልስ)፣ የትክትክ/ቋቋት (ፐርቶሲሲ)፣ የመንጋጋ ቆልፍ (ቲታነስ) እና የዘጊያናዳ (ዲፍቴሪያ) ክትባት አለማግኘታቸውን አሳውቀዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ 20 ሚሊዮን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ 872,828 ሕፃናት እነዚህን ክትባቶች ባለማግኘታቸውም፣ ለከፋ የጤና እክል የመጋለጣቸው ዕድል የሰፋ ነው፡፡
ክትባቶች ወረርሽኞችን ለመከላከል ዋና መሣሪያዎች መሆናቸውን የሚገልጹት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) በርካቶች ክትባት ቢያገኙም ብዙዎች ደግሞ አልተከተቡም፣ በችግር ውስጥ ያሉ፣ ድሆች፣ የተገለሉና በግጭት ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ከክትባቱ ተቋዳሽ አልሆኑም ብለዋል፡፡
ከክትባት ተጠቃሚ የማይሆኑ ሕፃናት በአብዛኛው የሚገኙት በደሃና በግጭት በሚታመሱ አገሮች ነው፡፡ በዓለም አልተከተቡም ከተባሉ 20 ሚሊዮን ያህል ሕፃናትም፣ ግማሽ ያህሉ ኢትዮጵያን፣ ቻድን፣ ኢራቅን፣ ማሊን፣ ኒድርንና ሶማሊያን ጨምሮ በ16 ደሃ አገሮች የሚገኙ ናቸው፡፡
በ2018 በዓለም 350,000 የኩፍኝ ሕመሞች በመረጃ የቀረቡ ሲሆን፣ በኩፍኝ ወረርሽኝ በዓመቱ ከተጠቁ አገሮች አንዷም ኢትዮጵያ ናት፡፡ የኩፍኝ ወረርሽኝ መታየቱም የክትባት መስተጓጎል ወይም አለመድረስ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከወር በፊት በሰጠው መግለጫ፣ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ከታኅሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስካለፈው አንድ ወር ድረስ 3611 ሰዎች በኩፍኝ ተይዘዋል፡፡ በሶማሌ ክልል ደግሞ 1470 ሰዎች በኩፍኝ ሲታመሙ፣ በችጉንጉኒያ ትኩሳት በሽታ በአፋር ክልል አዳር ወረዳ ብቻ 118 ሰዎች ታመዋል፡፡ ይህም የክትባት መስተጓጎልን አመላካች ነው፡፡
እንደ ድርጅቶቹ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ሕፃናት ካልተከተቡባቸው ከቀዳሚዎቹ አገሮች በአምስተኛ ደረጃ ትገኛለች፡፡ ይህ ደግሞ በጤናው ዘርፍ ለውጥ በተለይም የሕፃናትና እናቶች ሞትን በመቀነስ ዕውቅና ለተቸራት ኢትዮጵያ መልካም ዜና አይደለም፡፡
በ2018፣ 872,828 ሕፃናት ሦስተኛውን የፔንታቫለንት ክትባት አልወሰዱም፡፡ 1,215,724 ሕፃናት ደግሞ የመጀመርያውን የኩፍኝ ክትባት አልወሰዱም፡፡ ምንም እንኳን የፔንታቫለንት (ዲቲፒ) የመጀመርያውና ሦስተኛው ክትባት በ2010 ከነበረበት 77 በመቶ በ2018 ወደ 85 በመቶ ከፍ ቢልም፣ የኩፍኝ ክትባት ሽፋን ግን ቀንሷል፡፡ በ2010፣ 64 በመቶ የነበረው የኩፍኝ ክትባት ሽፋን በ2018 ወደ 61 በመቶ ወርዷል፡፡
ኩፍኝን በተመለከተ የዚህን ዓመት ለየት ያደረገውም 467,586 ሕፃናት ጭራሹኑ የኩፍኝ ክትባት አለማግኘታቸው ነው፡፡ ለዚህም ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በአንዳንድ ቦታዎች የተከሰተው የኩፍኝ ወረርሽኝ ማሳያ ይሆናል፡፡
በ2016 ተሠርቶ በ2017 ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና ጤና ጥናት እንዳመለከተው፣ የአማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ሕዝቦች ክልሎች በኢትዮጵያ ካልተከተቡ ሕፃናት 85.5 በመቶውን ይይዛሉ፡፡
በኢትዮጵያ ለሕፃናት ከውልደት እስከ አንድ ዓመት ድረስ ከሚሰጡ 11 ዓይነት ክትባቶች በመቶኛ ሲሰላ በአፋር 80 በመቶ፣ በሶማሌ 64 በመቶ እንዲሁም በኦሮሚያ 60 በመቶ ያልተከተቡ ናቸው፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ከ12 እስከ 23 ወራት ዕድሜ ውስጥ ካሉ አሥር ሕፃናት አራቱ የቲቢ፣ የኩፍኝ፣ የፖሊዮና ሄፒታይተስ ቢን ጨምሮ መሠረታዊ የሚባሉትን ክትባቶች ሳያቋርጡ ወስደዋል፡፡ በከተማ የሚገኙ ሕፃናት ገጠር ከሚገኙት በላቀ በወቅቱ ይሰጡ የነበሩትን ስምንቱን መሠረታዊ ክትባቶች ማለትም በከተማ 65 በመቶ፣ በገጠር 35 በመቶ ወስደዋል፡፡
በአፋር 15 በመቶ ሕፃናት ብቻ መሠረታዊ ክትባት በማግኘት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፣ አዲስ አበባ ደግሞ 89 በመቶ መሠረታዊ ክትባት በመስጠት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ተገኝታለች፡፡
ትግራይ 67 በመቶ፣ አማራ 46 በመቶ፣ ኦሮሚያ 25 በመቶ፣ ሶማሌ 22 በመቶ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ 57 በመቶ፣ ደቡብ 47 በመቶ፣ ጋምቤላ 41 በመቶ ሐረሪ 42 በመቶ፣ ድሬዳዋ 76 በመቶ ሕፃናት መደበኛውን የበሽታ መከላከያ ክትባት ያገኙ ሲያገኙ፣ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ሲታይ ሽፋኑ 39 በመቶ ነበር፡፡
አንድ ሕፃን ተወልዶ አንድ ዓመት እስኪሆነው ድረስ የሚወስዳቸው የተለያዩ ሕይወት አድን ክትባቶች ሲኖሩ፣ በኢትዮጵያም እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ በተለያዩ ጊዜያት 11 ዓይነት በሽታዎችን የሚከላከሉ ክትባቶች በነፃ ይሰጣሉ፡፡
አንድ ሕፃን እንደተወለደ፣ ከተወለደ በስድስተኛ ሳምንት፣ በ10ኛ ሳምንት በ14ኛ ሳምንትና በ9 ወር የሚከተበው ክትባት አለ፡፡ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት በሁለተኛ ዙር አንድ ዓመት ከሦስት ወር ሲሞላቸው የሚከተብ ቢሆንም ይህ አንድ ሕፃን አንድ ዓመት እስኪሞላው እንደሚወስዳቸው ክትባቶች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አልሆነም፡፡
በኢትዮጵያ አንድ ሕፃን ሙሉ ክትባት ወስዷል የሚባለው አንድ ሕፃን አንድ ዓመት እስኪሞላው የሚሰጡትን ክትባቶች በሙሉ ከወሰደ ነው፡፡ ሆኖም በአገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል የተከተበ፣ ጭራሹንም ያልተከተበ መኖሩ በየጊዜው ለሚከሰቱት ወረርሽኞች መገለጫ ናቸው፡፡
ዓለም አቀፍ ጤና ድርጅትና ዩኒሴፍ ያወጡት መረጃ የኩፍኝ፣ (ሚዝልስ) የዘጊያናዳ (ዲፍቴርያ) የመንጋጋ ቆልፍ (ቲታነስ) እንዲሁም የትክትክ/ቋቋት (ፐርቶሲስ) ያልተከተቡ ሕፃናት ሪፖርቱ ባወጣው መጠን ሊኖሩ እንደሚችሉ አጠቃላይ አገሪቱ የምትሰጠውን 11ዱንም ዓይነት ክትባቶች ያልተከተቡ ግን በዚህ መጠን እንደማይሆኑ፣ በጤና ሚኒስቴር የክትባት መርሐ ግብር ባለሙያ አቶ ጌትነት ባይህ ይናገራሉ፡፡
ክትባት ያለመከተብ ተፅዕኖው ሕፃናት በክትባት መከላከል የሚችሉ በሽታዎች እንዳይከላከሉ በማድረግ ለሞት መዳረጉ ነው፡፡ ስለሆነም የመከላከል አቅማቸው ዳብሮ በሽታውን የመከላከል አቅማቸው መንግሥት ክትባቱን ከፍተኛ ወጪ መድቦ በመግዛት ሕፃናት በነፃ የሚከተቡበት መርሐ ግብር ዘርግቶ መሥራት ከጀመረ አሠርታት ተቆጥረዋል፡፡
ሆኖም 2010 እስከ 2011 ዓ.ም. የነበረው የአገሪቱ ሁኔታ ችግር የበዛበት ስለነበር እንደማንኛውም ዘርፍ የጤና ዘርፍም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ የሕዝብ መፈናቀል ብቻ ሳይሆን የጤና ባለሙያዎችም የፈለሱበት፣ ጤና ተቋማት የተዘጉበት በተለይ በምሥራቅ አቅጣጫ ክፍተት የተጠረበት ዓመት መሆኑን አቶ ጌትነት ያስረዳሉ፡፡ ይህ ሕፃናት ክትባቱን ሙሉ ለሙሉ እንዲያገኙ ወይም እንዳያቋርጡ አንዱ ምክንያት ነው፡፡
በክትባት መከላከል ይቻል የነበሩ የተለያዩ ወረርሽኞች አጋጥመዋል፡፡ ይህም ልጆች አለመከተባቸውን አመላካች ነው፡፡
የሕይወት አድን ክትባት እንደ ሌሎች መድኃኒቶች በቀላሉ የሚጓጓዝ አይደለም፡፡ የራሱ የማጓጓዣ ሰንሰለት አለው፡፡ ሆኖም በነበረው ችግር ምክንያት ይህንን መተግበር ስላልተቻለ ክትባት በአውሮፕላን እስከማጓጓዝ ድረስ ሚኒስትሩ ሠርቷል፡፡
አገራዊ ችግሮቹ እንደ ሌላው ዘርፍ በጤናውም ላይ ችግሮች ያሳደረ ሲሆን፣ በማኅበረሰቡም ዘንድ በተለይ ሕፃን ልጅ ሲከተብ መጀመርያ የሚያጋጥመውን ትኩሳት በመፍራት ማቋረጥ ወይም ጭራሹኑ ያለማስከተብ ይስተዋላል፡፡
መንግሥት ግን ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጡን ሳይጨምርና የኩፍኝ ሁለትና የማሕፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባትን ሳይጨምር ለክትባትና መርፌ ብቻ በዓመት ከ12 ሚሊዮን እስከ 13 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ያወጣል፡፡ ይህ ወጪ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያወጡትንም ሆነ ለጤና ባለሙያ የሚከፈል፣ የሎጅስቲክስና ሌሎችንም ወጪዎች አይጨምርም፡፡
ለክትባት ከፍተኛ ወጪ በመመደብ የሕፃናትን ሞት ለመቀነስ በተሠራው ሥራ ውጤት ተገኝቷል፡፡ አቶ ጌትነት እንደሚሉትም፣ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ሞት ከዚህ ቀደም ከአንድ ሺሕ 88 የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ከአንድ ሺሕ 60 ውስጥ ሆኗል፡፡ ለዚህ ትልቁን ድርሻ ያበረከተው ደግሞ ክትባት ነው፡፡ በፖሊዮ፣ በኩፍኝ፣ በትክትክና በመንጋጋ ቆልፍ የሚሞቱ ሕፃናት ቁጥር በከፍተኛ ለመቀነሱም ክትባት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡
በዩኒሴፍና በዓለም ጤና ድርጅት ከጥር 2010 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 2011 ዓ.ም. የተሠራውን የክትባት መረጃ አስመልክቶ ያነጋገርናቸው በዩኒሴፍ የክትባት መርሐ ግብር ስፔሻሊስት አቶ አምሳሉ ሽፈራው፣ አንድ አገር የክትባት ሽፋኗ ጥሩ ነው የሚባለው 90 በመቶ የሚሆኑ ሕፃናት ዲቲፒ ለሦስት ጊዜ ማግኘት ሲችሉ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
በዚህ ከ195 አገሮች 112 አገሮች ከ90 በመቶ በላይ ሽፋን ሲኖራቸው 83 አገሮች ደግሞ ከ90 በታች ሽፋን አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከ83 አገሮች አንዷ ስትሆን፣ ሽፋኗም 72 በመቶ ነው፡፡ የዓለም አማካይ የክትባት ሽፋን 86 በመቶ ሲሆን አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት 72 በመቶ ከ18 ዓመት በፊት የዓለም አማካይ የነበረ ሽፋን ነው፡፡
እንደ አቶ አምሳሉ፣ ይህ የቀነሰው በተደራሽነት ችግር፣ ሕፃናቱ የት ነው ያሉት ተብሎ በጥናት ሲታይ አርብቶ አደር፣ ገጠር አካባቢ ከጤና ተቋማት ርቀው ያሉ፣ በሀብትና በትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ቤተሰቦች የተለዱ፣ ከተማ ውስጥ ሆነውም ለክትባት ቅድሚያ የማይሰጡ በመኖራቸው ነው፡፡
ክትባትን ተከታትሎ ከማስጨረስ አኳያ የግንዛቤ ችግር ያለ ሲሆን፣ ከግጭት ጋር ተያይዞ ያሉ መፈናቅሎች፣ የአገልግሎት መቋረጦች በተለይ በ2018 በኢትዮጵያ ለነበረው የክትባት ሽፋን መቀነስ ምክንያቶች ናቸው፡፡
በትጋት አለመሥራት በተለይ ከታች አገልግሎት በሚሰጠው ክፍል መረጃ በመስጠት እጥረት መታየቱና አገልግሎት በሚሰጥባቸው ጤና ተቋማት ላይም አልፎ አልፎ የክትባት እጥረት መታየታቸውን አቶ አምሳሉ ተናግረዋል፡፡
ዩኒሴፍና የዓለም ጤና ድርጅት በ195 አገሮች የክትባት ሁኔታን በመከታተል መረጃ በየዓመቱ የሚያወጡ መሆኑ ይታወቃል፡፡