Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

መቼም ደረጃውና ስፋቱ ይለያይ እንጂ ሐሜት በሁሉም ሥፍራ አለ። በፍፁም ሊታሰብ በማይችልባቸው በፀሎት ሥፍራዎች፣ በሕሙማን መንከባከቢያ ማዕከላት፣ በትምህርት ተቋማት፣ በዓብያተ መንግሥታትና በዓብያተ መጻሕፍት ጭምር ሐሜት ሥር ሰዶ ይታያል። ዱሮስ ቢሆን አዚማም ነገር አይደል? የማይገባበት ቀዳዳ፣ የማይገኝበት ሥፍራ፣ የማይወጣበት አቀበት፣ የማይወርድበት ቁልቁለት፣ የማይፈትነው ሰው የለም። የእንስሳቱን አላውቅም እንጂ። አሁን ሐሜት በቀብርና በሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ውስጥ ሰርጎ ይገባል ብላችሁ ትገምታላችሁ ጎበዝ? ግን እዚህም ዋናው መንሰራፊያው ሆኗል።

በቅርቡ ለስብሰባ ወደ አዳማ ከተማ ብቅ ብለን ነበር። እናም እኔና ጓደኞቼ ከስብሰባው በኋላ ማታ ማታ በየሆቴሎቹ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን ዘና እያልን ወሬ እንጠርቃለን። እንዲያው የሐሜትና የሐሜተኞች ነገር በሆነ አጋጣሚ በወጋችን መሀል ድንገት ተነሳና ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቀጠለ። የሦስት ቀናት የምሽት ጊዜያችንን በሙሉ ወሰደ። ሙክክ አድርገን አበሰልነው። አደቀቅነው። አላምነው። እኛም በትንሹ ሐሜተኞች ሆንን ልበል? ለማንኛውም በመጨረሻ በሚከተለው ነጥብ ላይ ተስማማንና ስምምነታችን በአቋም መግለጫ መልክ ተዘጋጅቶ ለአንባብያን እንዲደርስ እንደ ዘመኑ ስብሰባ አቅጣጫ አስቀመጥን እላችኋለሁ። እነሆላችሁ ወጉ። እኔና ጓደኞቼ በሙሉ ድምፅ ዓበይት የሐሜት ሥፍራዎች ብለን የመረጥናቸው የጀበና ቡና (ቡና ጠጡ)፣ ፀጉር ቤት (የውበት ሳሎን)፣ ጫት መቃሚያና ሺሻ ቤቶች፣ ለቅሶ ቤት፣ መጠጥ ቤቶችና ካፌዎች፣ ድድ ማስጫዎችና የመሳሰሉት ናቸው። እናንተም በታያችሁ መንገድ ልታሰፏቸው ትችላላችሁ። ክልክል የለውም።

በአገራችን የጀበና ቡና አቅርቦት እሰየው በሚያሰኝ ሁኔታ በየስርቻው፣ በየጉራንጉሩ፣ በየበረንዳው፣ በየግንቡና ግድግዳው ሥር መስፋፋቱ በተለይ ከሥራ ዕድል ፈጠራና ሰዎች አዕምሮአቸውን የሚያሳርፉበት፣ የዕረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ምቹ ሥፍራ ከመሆን አንፃር በጣም ያስደስታል። ነገር ግን በእነዚህ ሥፍራዎች አጅሬ ሐሜት ጉልበቱ ይበልጥ አላፈረጠመም፣ ልቡ ይበልጥ አላበጠም፣ የመስፋፋት ፍጥነቱ እጅግ አልጨመረም ትላላችሁ? ከፈለጋችሁ እንወራረድ። እግዚኦ! በጀበናና በስኒ በተከበበች አንዲት የጀበና ቡና ቤት (መጠለያም ሊሆን ይችላል) ኮረዳ ላይ ዙሪያውን ተቀምጠው ያፈጠጡ የበርካታ ወጣቶች ዓይኖች ሁልጊዜም ይገርማሉ። ልጅቱ ጠዋት ገና የዕለት ሥራዋን ለመቀጠል ከሰል ማቀጣጠል ስትጀምር ጀምሮ አንድ ሁለት እያሉ መጥተው የተኮለኮሉ ወጣቶች መዋያቸው እዚያው ነው። በአንዲት ልጅ ላይ ተፋጠው። መደበሪያቸው መሆኑ ነው።

እናም ወሬያቸው ሁሉ ፌስቡክ እንዲህ አለ። የእንቶኔ ሬዲዮ እንዲህ ተናገረ። አገር ተቃጠለ። ሰው አለቀ። እገሌ የተባለው ተቃዋሚ በዚህ/በዚያ በኩል ጦርነት ጀመረ፣ ወዘተ. ከሚለው ጀምሮ ስለኑሮ ውድነት፣ በፊት ለፊታቸው በመንገድ ላይ ስለሚያልፉት ሰዎች ሲያሙ፣ ሲያኝኩ፣ ሲያመነዥኩ ቀኑ መሽቶላቸው ወደ ማምሻ ማደሪያቸው ይሄዳሉ። ትልቁን የሐሜት ዕዳ ያሸከሙት ደግሞ ለመንግሥት ነው። በውኃና በመብራት መቆራረጥ፣ በጤፍና በብረት ውድነት፣ በሥራ አጥነት ጉዳይ ሁሉ መንግሥትን ያማሉ። ሐሜት ሰውነትን የሚያቆስል ወይም ነፍስን የሚገድል ቢሆን ኖሮ መንግሥት የሚባለውን አካል በሕይወት አናገኘውም ነበር። ነገር ግን ሐሜት አዕምሮን እንጂ ሰውነትን የማቁሰል አንዳችም አቅም ስለሌለው ሐሜተኞቹም ሽንጣቸውን ገትረው፣ መላ አቅማቸውን ተጠቅመው፣ ጊዜያቸውን ሰውተው ያማሉ፣ ያማሉ፣ ያማሉ። መንግሥትም የዘወትር ተግባሩን ያለ ማመንታት ይቀጥላል።

እንዲያው ግን ለነገሩ ሐሜተኞቹ እዚህ ሥፍራ ተቀምጠው ወይም ተኮልኩለው ሐሜት ሲያዳውሩ ከዋሉ ምን ጊዜ ነው የሠሩትን በልተው የሚኖሩት? ነው ወይስ እንደ ሰማይ አዕዋፋት እግዜር በቸርነቱ ነው የሚመግባቸው? አንዳንዶቹ ከቦታቸው ላለመልቀቅ ቡና ደጋግመው ጠጥተው ተቃጥለው አለመሞታቸውም ይገርማል እኮ። አንዳንዴ ቡና አፍይዋም ቡናዋ ፈልቶ ተፍለቅልቆ ከሰሏን እስኪያጠፋባት ድረስ ሥራዋን ትታ አብራ የሐሜት ድር ታዳውራለች። ይህንን አንድ በሉልኝ። ሌላውን እቀጥላለሁ።

የወንዶችም የሴቶችም ፀጉር ቤቶች (የውበት ሳሎኖች) የዋዛ የሐሜት ሥፍራ አይደሉም። ‹‹እንዲያው አሁንስ የመብራቱ ጉዳይ ምን ይሻላል? ለማን ይነገራል? መንግሥት እንደሆነ ጉዳዬም አላለው፣ ያው ህዳሴው ግድብም ቶሎ ሊያልቅ አልቻለም፣ ዝናቡም በቀበሌ ሆነ፤›› ይቀጥላል ሐሜቱና ምሬቱ። እየተቀባበሉ ይታማል። ስለአሜሪካም፣ ስለአውሮፓም፣ ስለገጠርም፣ ስለከተማም፣ ስለኑሮ ውድነትም፣ ስለግለሰቦችም ይወራል። ሰው የሚያውቀውንም የማያውቀውንም እርግጠኛ እንደሆነ አድርጎ ፍጥጥ ብሎ ይናገራል። ልክ አይደላችሁም፣ ተሳስታችኋል፣ መንግሥት የአገሪቱን ፈርጀ ብዙ ችግሮች ለመፍታት አቅሙ ከሚፈቅደው በላይ ተለጥጦ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው። የግለሰቦችን ጥሬ ሥጋ መብላት ምን ፋይዳ ይሰጣችኋል? ብሎ የሚጠይቅ፣ የሚያርማቸው ብዙም የለም።

የጫት መቃሚያና ሺሻ መሸጫ ቤቶች ሐሜት ደግሞ ከላይኞቹ ትንሽ ለየት ይላል። ሐሜቱ ጥንን ያለ፣ የሰከነ፣ የሠለጠነ የሚመስል፣ ፍልስፍናም ብጤ የተቀላቀለበት ነው። ፀጉር ይፍተለተላል። ሞባይል ፌስቡክ ይጎረጎራል። ሐሜቱ ምርቃና መራሽ ስለሆነ፣ በሌሎች ሥፍራዎች ከሚካሄዱት ሐሜቶች ትንሽ ቀልብን የሚስብ፣ ይበልጥ የሚያሳስትም ዓይነት ነው። ከሐሜተኞቹ ሠራዊት መካከል በዕድሜ ተለቅ፣ በትምህርትም ገፋ ያደረጉ፣ በገቢም የተሻሉ፣ ምናልባትም ትንሽ ያነበቡ ሰዎችም ይታዩበታል። እዚህ ሥፍራ ላይ አብዛኛውን የሐሜት ሰዓት የሚወስደው ፖለቲካ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የባለሥልጣናት፣ የክልሎች፣ ወዘተ. ስም ይነሳል። ባህር ውስጥ ይጠለቃል። ጠፈር ላይ ይወጣል። መብረርም መንሳፈፍም ያለበት ነው የእነዚህኞቹ ሐሜት። የኑሮ ውድነት፣ የተቃራኒ ፆታ፣ የስደት፣ የዘር ጉዳዮችም እንደማጣፈጫ አልፎ አልፎ መሀል ይገባሉ። ሲጋራ እየተወጋጉ፣ አንዳንዶቹም መጽሔት ብጤ ይዘው እያነበቡ በየመካከሉ የሚቀባበሉት ሐሜት ነው።

ሌላው የሚገርመው የለቅሶ ቤት ሐሜት ነው። ‹‹ተናዞ ነው የሞተው? ልጆቹ ገንዘብ አላቸው? ለምን አማሪካ ወስደው አያሳክሙትም ነበር? አይ የዛሬ ልጆች! አሁን ገና አርባው ሳይወጣ በውርሱ ይጣላሉ። ሟቹ በጣም ጨፋሪ ነበር አሉ። ያለ ምክንያት እንዲህ አልከሳም። ኮብራው ነድፎት ይሆናል። ሚስቱ ፈረደባት፣ አሁን ይህች አማረብኝ ብላ ማልቀሷ ነው? ወይ ጉድ! እራትም ምሳም በምስር ጨጓራችንን ከሚጠብሱት ምናለ አንድ በሬ እንኳን እርድ አድርገው ጥሩ ነገር ቢያበሉን? ለካንስ ባለው ይብሳል፤›› ሌላም ሌላም የሐሜት አጀንዳ ይነሳል። የየሰው ሥጋ እኝክ ተደርጎ ይላመጣል። በደረቁ ይዋጣል። እዚህ ሥፍራ ዕድሜ ጠገብ ሐሜተኞች በዛ ይላሉ።

ድድ ማስጫዎች ብዙ ጊዜ ሻይ/ቡና እየተባለ ጋዜጦችና መጽሔቶች ገዝተው/ተከራይተው የሚያነቡባቸው ሥፍራዎች ናቸው። ከዚሁ ጎን ለጎን የጡረተኞች፣ ከቅጥር ሥራ የለቀቁ፣ የመሳሰሉ ዜጎች የመረጃ መለዋወጫም ናቸው። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ሥፍራዎቹ ለረጅም ጊዜ በግልጽ ይታወቃሉ። እዚህ ሥፍራ የሚታደሙት ትንሽም  ከሌላው ሰው በሰል ያሉ ሰዎች፣ አንባብያን ብቻ ሳይሆኑ ጸሐፍት፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማርያን፣ ወዘተ. ጭምር ሊሆኑ ይችላሉ። ታዲያ የግለሰብ ተራ ሐሜት፣ የተቃራኒ ፆታ ጉዳይ፣ ምናምን የሚባሉ ነገሮች እዚህ እምብዛም አይታወቁም። አብዛኛው ሐሜት በመንግሥት፣ በመሪዎች፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ያነጣጠረ ነው። ስለመጪው ምርጫ፣ ስለተራዘመው የሕዝብ ቆጠራ፣ ስለመሳሰሉት ጉዳዮች በስፋት ይነሳል እዚህ ሥፍራ። አራት ኪሎ፣ ፒያሳ፣ መገናኛ፣ ብሔራዊ፣ ስታዲየም አካባቢ ያሉ የበረንዳ ላይ ካፌዎች በብዛት ለዚህ ክስተት የተጋለጡ ናቸው።

ይቅርታ አድርጉልኝና እኔ ግን ከሁሉም የሚዘገንነኝ በእምነት ሥፍራዎች የምሰማው ሐሜት ነው። ተራ ሐሜት። በተቀደሰ ሥፍራ ላይ ሥርዓተ ቅዳሴ እየተካሄደ፣ ታቦት ወጥቶ ዓውደ ምሕረቱ ላይ ቆሞ፣ ዳዊት እየደገሙና ኪዳን እያደረሱ ወይም የተለያዩ ቅዱሳት መጻሕፍትን እያነበቡ አፀድ ተደግፈው በየመካከሉ ቀና እያሉ ወደ ጎን ከጓደኛ ጋር ‹‹አየሻት፣ አሁን አማረብኝ ብላ ነው ሱሪ ለብሳ ቤተ ክርስቲያን የምትመጣው? አየኸው፣ አሁን እሱም እግዜር ይሰማኛል ብሎ ነው እዚህ የመጣው. . .›› እያሉ የሚያወርዱት የሐሜት ናዳ ‹‹የማይሆን ፀሎት ለቅስፈት›› የሚለውን ምሳሌ ያስታውሰኛል። ‹‹ቂም ይዞ ፀሎት ሳል ይዞ ሥርቆት›› የተባለውም ያለ ምክንያት አይደለም። እናም ከሕፃን እስከ አዋቂ፣ አዛውንቱም፣ የሃይማኖት አባቶችና እናቶችም፣ ምሁራኑም ወንዱም ሴቱም ሐሜተኞች ከሆንን ምን ይበጀናል። በራሱ በሐሜተኛው ላይም እኮ ‹‹የሚሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ›› የሚለው አባባል እንደሚፈጸምበት አያውቅም? እዚህ የሚያማ እዚያ ይታማል። በየመኖሪያ ቤቱም አቦሉ፣ ቶናውና በረካው ተጠጥቶ ቡናው እስኪከትም ድረስ ከጎረቤትና ከጓደኛ ጋር የሚቀልጠው ሐሜት ቀላል አይደለም።

እንግዲህ ውድ ወገኖቼ እንኳን ቁጭ ብለው ወሬ እየሰለቁ፣ እንኳንስ በሥራ ሰዓት ሥራ ፈትቶ ከቢሮ ቢሮ እየተዘዋወሩ፣ በስልክ ሒሳብ ብዛት የሚሠሩበትን ተቋም እያከሰሩ በወሬ ዘመቻ ተጠምዶ ቀርቶ ላብን ጠብ አድርጎ ደም ተፍቶም ተሠርቶ አልሞላ ያለ ኑሮ እንዴት ይዘለቃል! በዚህ ዓይነት እንዴት ሊያልፍልን፣ መቼስ ከድህነት ልንላቀቅ እንችላለን? ሐሜት የዕለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስ ወይም መጠለያ አይሆን። ሐሜት በውስጡ ጥላቻና ቂምም ስላለው ግንኙነቶቻችንንም ያበላሻል። የሰው መልካም ስም ያጠለሻል። የመንግሥትን ድካም ዋጋ አልባ ያደርጋል። ልምድ ይሆንና እንደ ኮሶ ይጣባል። እንደ ካንሰር ይጠነክርና መዳኛ የለውም። ሐሜት ጉዳት እንጂ አንዳችም ፋይዳ የለውም። እዚህ ላይ ሐሜትንና አሉባልታን ወይም የተዛባ መረጃን ከጤነኛ የመረጃ ልውውጥ በጣም መለየት አለብን። የምናወግዘው አንዳንድ ሰዎች ሥራዬ ብለው ወይም ባለማወቅ በዘፈቀደ የሚያሠራጩትን የበሬ ወለደ ትርክት እንጂ፣ እውነተኛ የሆነ የመረጃ ልውውጥ የትም ቦታ ቢደረግ ሊደገፍ እንጂ ሊነቀፍ አይገባውም። ስለዚህ የሐሜት ዛር የሰፈረብን፣ ሐሜት የሚርበን፣ የሚጠማንና የሚያርዘን አንዳንድ ሰዎች ይህንን ቆሻሻ አመል ተወት አድርገነው ወደ ሥራ ብንሠማራ። የሐሜት ሥፍራዎችም ወደ ታቀደላቸው ተግባር ቢውሉ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን እኔና ጓደኞቼ።

(በተስፋዬ ጎይቴ፣ ከአዲስ አበባ)   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...