Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክዘፈቀዳዊ የበይነመረብ አዘጋግ ሕጋዊ አንድምታ

ዘፈቀዳዊ የበይነመረብ አዘጋግ ሕጋዊ አንድምታ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

በሰበብ አስባቡ የበይነመረብን (ኢንተርኔትን) አገልግሎትን ጥርቅም አድርጎ መዝጋት በአገራችን የተለመደና እንደ ተራ ነገር እየተቆጠረ የሄደ ይመስላል፡፡ ለቀናት ጥርቅም አድርጎ ከመዝጋት በመለስም በብሮድባንድ (የመስመር እና ዋይፋይ) ብቻ የበይነመረብ አገልግሎት በማቅረብ፣ በተንቀሳቃሽ ስልክ ብቻ መዝጋትም ሌላው የአዘጋግ ምርጫ ነው፡፡

 ከበይነመረብ አገልግሎት ባለፈም በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚተላለፉ አጫጭር መልዕክቶችም የዚሁ የመዘጋት ዕጣ ፋንታ አልፎ አልፎ እየገጠማቸው ነው፡፡ አንዳንዴም፣ የተወሰኑ አካባቢዎችን ብቻ በመምረጥ የበይነመረብ አገልግሎት ሲቋረጥ እንደነበር አስተውለናል፡፡ በማቋረጥ ፋንታ የአውታር (ኔትወርክ) መጨናነቅ እንዲፈጠር በማድረግ የበይነመረብ አገልግሎቱ ሲበዛ እንደ ካፊያ ዝናብ በመሆን፣ አለበለዚያም ሳይዘንብ በጉርምርምታ ብቻ እንደሚያልፍ ደመና የበይነመረብ አገልግሎት የሚሰጥ እየመሰለ አጓጉቶ የሚያልፍ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡

 የበይነመረብ አገልግሎት የሚሰጠው አንድ ለእናቱ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጭው በኢትዮ ቴሌኮም አማካይነት ስለሆነ ሙሉ በሙሉ ጥርቅም አድርጎ የሚዘጋውም (Complete Internet Shutdown or Block out) ወይም ደግሞ በከፊልም የሚዘጋው በእሱው አማካይነት ነው፡፡ አውታርን በማጨናነቅ ወይም አገልግሎቱ እንዲቆራረጥ፣ የሚተላለፈውም የውሂብ (Data) ፍሰት ዝቅ እንዲል የሚያደርገውም (Throttling) ያው ኢትዮ ቴሌኮም ነው፡፡ በእርግጥ የአውታር መስመሮች ላይ በሚደርስ ጉዳትም የበይነመረብ አገልግሎት እክል ሊገጥመው እንደሚችል ይታወቃል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ትኩረት በመንግሥት ትዕዛዝ (ውሳኔ) አማካይነት ኢትዮ ቴሌኮም እያወቀ የሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የሚያደርገውን በይነመረብ መዝጋት አልያም የበይነመረብ አገልግሎት ማስተጓጎልን ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሚፈጸመው ተግባር በአንድ በኩል መንግሥት ለሕዝብና ለአገር የተሻለ ጥቅም ሲባል እንደሚያደርግ ምክንያቶችን ሲያቀርብ በሌላ በኩል ደግሞ ዜጎችና የአገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎችም ድርጅትና ተቋማት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ብቻ ሳይገታ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን እያሳጣቸው እንደሆነ ሲያማርሩ መስማት ተዘውትሯል፡፡ ይህ ጽሑፍ እነዚህን ተፃራሪ ትርክቶች ከሕግ አንፃር መፈተሸ ነው ዓላማው፡፡ የችግሩን ግዝፈት ለመገንዘብ ይረዳ ዘንድ የበይነመረብ በሙሉም ሆነ በከፊል ሲዘጋ የሚጥሳቸውንም የሚያጣብባቸውንም መብቶች በመግለጽ የአዘጋጉን (ኢ)ሕጋዊ ገጽታ ገለጥለጥ በማድረግ ቅጥ ያጣው የበይነመረብ አዘጋግ ሒደት ሥርዓት እንዲይዝ ማድረግ የሚኖረውን ፋይዳ መጠቋቆምን ሳይዘነጋ ነው፡፡

የበይነመረብ መዘጋት ምንነት

በይነመረብ መዝጋት ሲባል የመጀመሪያው ነጥብ ሆን ተብሎ መደረጉ ላይ ነው፡፡ የበይነመረብ አገልግሎት ሰጭዎች ወይም በየትኛውም እርከን የሚገኝ የመንግሥት መዋቅር ሆን ብሎ አገልግሎቱ በሙሉም ይሁን በከፊል ሲዘጋ ነው፡፡ መዝጋቱ ወይም ማቆራረጡ በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት የሚከናወኑ ማናቸውንም ግንኙነቶች (የበይነመረብንም ጨምሮ) ያካትታል፡፡ በመዘጋቱ ወይም በመቆራረጡ ምክንያት አገልግሎቱ ተደራሽ እንዳይሆን ማድረግ ወይም ውጤታማ የሆነ ጠቀሜታ እንዳይሰጥ ማድረግን ይጨምራል፡፡ ሁኔታው በተወሰነ አካባቢ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ብቻ በመነጠል ወይም በአንድ አገር በሞላ ሊፈጸም ይችላል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ሲከሠቱ ነው በይነመረብ ተዘጋ የሚባለው ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎችን ሰፋ ባለ መልኩ ይስማማሉ፡፡ 

የተለያዩ አገር መንግሥታት የበይነመረብን አገልግሎትን ሲዘጉ ወይም ሲያቆራርጡ ምክንያት ሳይሰጡ በዝምታ ከማለፍ ጀምሮ እውነተኛ ምክንያቱንም ካልሆነም ማሳበቢያ አያጡም፡፡ ያም ሆኖ ግን፣ መንግሥታት በደስታ የሚፈጽሙት ሳይሆን በሆነ መንገድ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ ነው፡፡ አጣብቂኙ ፖለቲካዊ ሥልጣንን የሚነካ ሲሆን፣ በምክንያትነት ሰበብ ሊደረደር ይቻላል፡፡ ሲሆንም እየታየ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛ፣ ትክክለኛና አሳማኝ  ምክንያቶች በማጋጠማቸውም ይዘጋሉ፡፡

የበይነመረብ መዘጋት ሁኔታ በኢትዮጵያ

የተወሰኑ መካነድሮችን (Websites) መርጦ መዝጋት የኢትዮጵያ መንግሥት የሚታወቅበት አንዱ አካሄድ ነበር፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ይፋ እንዳደረጉት፣ በመንግሥት የመዘጋት በትር አርፎባቸው የነበሩ ወደ 200 የሚሆኑ መካነድሮች እንዲከፈቱ አድርገዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ በነበረባቸው ወቅቶች በግልጽ የበይነመረብ አገልግሎትም ሊቋረጥ እንደሚችል ተገልጾ ነበር፡፡ በዚሁ ምክንያት አልፎ አልፎ ሲዘጋና ሲከፈትም ነበር፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ሾልኮ በመውጣቱ ምክንያት ከዚያ በኋላ እነዚህ ፈተናዎች ሲካሄዱ በተለይ በተንቀሳቃሽ ስልክ የበይነመረብ አገልግሎት እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

በዚህም ዓመት ተደግሟል፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ እንኳን፣ የቡራዩውን ክስተት ተከትሎ ለተወሰኑ ቀናት ተቋርጦ ነበር፡፡ ወታደሮች ወደ ቤተ መንግሥት መግባታቸውን ተክትሎ፣ የሰኔ 15ቱን ባህርዳርና አዲስ አበባ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ ተቋርጧል፡፡

ባለፈው ዓመት ክረምት ጅግጅጋ ላይ የተፈጸመውን አሳዛኝና የክልሉን ፕሬዚዳንት ለእሥር የዳረገውን  ክስተት ተከትሎም በእዚያ አካባቢ ብቻ በይነመረብ ተቋርጧል፡፡ በተለይ በዚህ ዓመት ሰኔ ላይ የደረሰውን መዝጋት ተከትሎ ዋና ትኩረቱ የበይነመረብ ሳንሱርንና መዘጋትን፣ የአውታር መረበሽና መቆጣጠርን ለመቀነስ፣ለማስቀረትና ለማጋለጥ የሆነው ኔትብሎክስ (NetBlocks) የተባለው ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አልፕ ቶከር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ተዘግተው የነበሩ 200 መካነድሮች መከፈታቸውን ባበሰሩ ልክ በዓመቱ በይነመረብን ጥርቅም አድርገው ዘጉት በማለት ለአልጀዚራ እ.ኤ.አ. ሰኔ 25 ቀን 2019 ተናግሯል፡፡

ይኼው ድርጅት ኢትዮጵያ በይነመረብን በመዝጋቷ በቀጥታ ሊገኝ ከሚችል ገቢ ብቻ በቀን በአማካይ 4.5 ሚሊዮን ዶላር (130 ሚሊዮን ብር ገደማ) እንደምታጣ ገልጿል፡፡ አገልግሎቱ በመቋረጡ ምክንያት ሊገኝ ይችል የነበረ ነገር ግን የሚታጣ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያለውን አይጨምርም፡፡

ስለሆነም፣ የበይነመረብ መዘጋት አንዱ ጉዳት አገሪቱ ልታገኝ ከምትችለው ገቢ በማጣት ኢኮኖሚያዊ ነው ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ወደ 16.5 ሚሊዮን ገደማ የበይነመረብ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋው ደግሞ የማኅበራዊ ሚዲያ ይጠቀማል፡፡

በይነመረብ ልክ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል መሠረታዊ ቴክኖሎጂ ሆኖ መቆጠር ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በመንግሥታዊ አገልግሎቶች እንኳን ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና እንዲሁም አስተዳደራዊ ተግባራት በይነመረብ ላይ የሙጥኝ እያሉ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ‹‹ወረዳኔት››፣ ‹‹ስኩልኔት›› የሚል ሥያሜ የተሰጣቸውና ከፍተኛ ገንዘብ የወጣባቸው አገልግሎቶች የተዘረጉት መነሻው ይኼው ነው፡፡

በግሉ ዘርፍም ሥራን ሌላ ቦታ ሆኖ መሥራት፣ ግብርን ባሉበት ቦታ ሆኖ መክፈል፣ ንግድ ማከናወን፣ ክፍያ መፈጸም ወዘተ እንዲሁ የበይነመረብ ትሩፋቶች ናቸው፡፡ በይነመረብ ሌሎች ሥራዎችን የማፋጠንና የማሳለጥ ሚናው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ የገቢ ምንጫቸውም በዚሁ አገልግሎት መኖር ላይ ጥገኛ የሆኑት እየበዙ ነው፡፡

በመሆኑም የበይነመረብ መዘጋት ኢኮኖሚያዊ ዳፋው እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ የመሄድ ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት፣ ማለትም በ2018 በተለያዩ አገሮች የተፈጸመውን የበይነመረብ መዘጋት መረጃዎችን ያጠናቀረውን የኔትብሎክስ ዘገባ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ በዚሁ ዓመት በ25 አገሮች 196 ጊዜ በይነመረብ ተዘግቷል፡፡ በ2017 የተዘጋው 107 ጊዜ ሲሆን፣ በ2016 ደግሞ 75 ነበር፡፡ እነዚህ የተመዘገቡና የተረጋገጡት ብቻ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ የመዝጋት አዝማሚያው አስደንጋጭ በሆነ መልኩ  እየጨመረ መሄዱ ግልጽ ነው፡፡

በአኅጉር ደረጃ እስያ በመዝጋት ቀዳሚ ስትሆን፣ አፍሪካ በሁለተኛነት ትከተላለች፡፡ በ2018 በመዝጋት አንደኛ ደረጃ ላይ ፊጥ ያለችው ህንድ ናት 134 ጊዜ በመዝጋት፡፡ በእርግጥ ይኼ ቁጥር በህንድ ውስጥ በየትኛውም ቦታ ሳይሆን ቦታ እየተመረጠ ነው የተዘጋው፡፡ በሁለተኛነት ህንድን የተከተለችው ጎረቤቷ ፓኪስታን ስትሆን እሷም በበኩሏ 12 ጊዜ ጠርቅማዋለች፡፡ ሦስተኛ የሆኑት የመንና ኢራቅ ሲሆኑ፣ ሰባት ጊዜ ዘግተዋል፡፡ አራተኝነትን የያዘችው ኢትዮጵያ ስትሆን ስድስት ጊዜ ዘግታለች፡፡

ለመዝጋት በምክንያትነት የሚቀርቡት

ከሚዘጉባቸው ምክንያቶች (ሰበቦች) መካከል የሕዝብና የአገር ደኅንነት፣ የሐሰትና የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር፣ በፈተና ወቅት መኮራረጅን ለማስቀረት የሚሉት በስፋት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ በመንግሥታት በኩል የሚቀርቡ የተለመዱ ሰበቦች ሲሆኑ ጥናቶች የሚያሳዩት ግን ፓለቲካዊ አለመረጋጋት፣ ተቃውሞ፣ ምርጫ፣ ማኅበረሰባዊ ግጭት፣ መረጃን መቆጣጠርና መኮራረጅን መቆጣጠር የሚሉት ናቸው፡፡

 ይህ ማለት ግን መንግሥታት የሚዘጉት በሐሳዊ ሰበብ ብቻ ነው ለማለት አይደለም፡፡ የመዝጋት ምክንያቶቹ ምንም ይሁኑ ምን፣ በይነመረብ ሲዘጋ ከኢኮኖሚያዊ ጉዳት ባለፈም መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጸም መሆኑ ነው፡፡ ይህንን የመብት ጥሰት የጉዳት መጠን ለመቀነስና መዝጋት የመጨረሻ አማራጭ ከሆነም መንግሥታት ከመዝጋታቸው በፊት ሊያሟሏቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን ጠንቅቆ በማወቅ ብሎም ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራርን ማስፈን ነው፡፡

የመዝጋት ሥልጣን ሕጋዊ መሠረቱ

በይነመረብ መሠረታዊ ቴክኖሎጂ ነው ብለናል፡፡ የበይነመረብ አገልግሎት የሚሠራጨው በመሠረቱ የቴሌ አማካይነት ነው፡፡ ይህ ማለት፣ አገልግሎቱን የሚሰጡት የቴሌኮሙዩኒኬሽን ውጤቶችን የሚያቀርቡ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ይህን አገልግሎት በብቸኝነት የሚያቀርበው ኢትዮ ቴሌኮም ሲሆን፣ እሱን የሚቆጣጠር የተለያየ አቋምና ተጠሪነትን ያፈራረቁ ተቋማት አሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም አቀፉ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኅብረት (International Telecommunications Union/ITU) አባል ስለሆነ (መሆን ግዴታ ነው) ኅብረቱ የተመሠረተበትን ሕግ እንዲሁም እሱ የሚወጣቸውን ድንጋጌዎች አክብሮ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም በዚሁ መሠረት ሥራውን ያከናውናል፡፡ አባል አገሮች የቴሌኮም አገልግሎቶችን ሊያቋርጡ እንደሚችሉ በኅብረቱ መመሥረቻ ሰነድ  አንቀጽ 34 (2) እና 35 ሥልጣን ይሰጣቸዋል፡፡

ይህንን ለማድረግ በብሔራዊ ሕጋቸው በመወሰን የአገርና የመንግሥት ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ሥጋት ሲፈጠር፣ በሕግ የተከለከሉ ነገሮች ሲፈጸሙ እንዲሁም ለመልካም ባሕርይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮች ሲፈጸሙ ገደብ የማድረግን ሥልጣን አይነፍግም፡፡ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ የቴሌኮሙዩኬሽን አገልግሎትን በጊዜያዊነት ለመገደብ የሚያስችል ሕጋዊ መነሻ አላቸው፡፡

በይነመረብና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት

በይነመረብ፣ አመለካከትና ሐሳብን በነፃ ለመግልጽ ጥቅም ላይ የሚውል የማሰራጫ ዘዴ ነው፡፡ በይነመረብን በመጠቀም በማኅበራዊ ሚዲያም ይሁን በሌላ አኳኋን ሰዎች ሐሳባቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይቀበላሉ፡፡ ያጋራሉ፡፡ ሰው የመሰለውን አመለካከት የመያዝና ሐሳቡን የመግልጽ መብት ደግሞ በተለያዩ ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ጥበቃ የተደረገለት መብት ነው፡፡

አብዛኛዎቹን ሰነዶች ኢትዮጵያም ተቀብላ አጽድቃቸዋለች፡፡ በሕገ መንግሥቱም ቢሆን ዕውቅናና ጥበቃ ተሰጥቶታል፡፡ አንቀጽ 29 (2) ላይ ‹‹ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ መብት አለው፡፡ ይህ ነፃነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል፡፡›› ይኼ በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ የሚለው በይነመረብን ሊጨምር እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡

ስለሆነም፣ መንግሥት በይነመረብን ሲዘጋ ወይም የአውታር መቆራረጥና መረበሽ እንዲከሰት ሲያደርግ ይህንን የሰብዓዊ መብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥት የሰብዓዊ መብትን በሚመለከት ረገድ የማክበር፣የማስከበርና የማሟላት የታወቁ ግዴታዎች አሉበት፡፡

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትንም በሚመለከትና ከርዕሰ ጉዳያችን ጋር በተያያዘ፣ የበይነመረብን ተደራሽነትን የማስፋፋት (የማሟላት)፣ አገልግሎቱን የሚያገኙትን ደግሞ አለማቋረጥና አለመዝጋት (የማክበር) እንዲሁም ሌሎች ይህን መብት እንዳይጥሱ ወይም እንዳያጣብቡ የማሠራት (የማስከበር) ግዴታዎች አሉበት ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ መብቶች ደግሞ በማናቸውም ሁኔታ ሁልጊዜም ፀንተው የሚቆዩ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ለአጠቃቀማቸው ወሰን መኖሩ አይቀርም፡፡

የበይነመረብ አገልግሎት የማግኘትም የመገልገልም መብት እንደብዙዎቹ መብቶች ፍጹማዊ መብት አይደለም፡፡ ገደብ ሊደረግበት ይችላል፡፡ ዋናው ነገር የበይነመረብ አገልግሎትን ከማቋረጥ አስቀድሞ ከግምት ሊገቡ የሚገቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ መሥፈርቶች ስላሉ እነሱን ሥራ ላይ በማዋል መንግሥታዊ ግዴታን መወጣት በብዙ አገሮች የተለመደ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመዱት መለኪያዎች ከማየታችን በፊት ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ ያሉትን ገደቦች አስቀድመን እንመለከታለን፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(6) ላይ በማያሻማና በግልጽ ቋንቋ እንደተገለጸው ሐሳብን በፕሬስና በማናቸውም መገናኛ ብዙኃን ማንኛውም ሰው ሲገልጽ የሐሳቡ ይዘት ምንም ይሁን ምን፣ ሐሳቡ በመገለጹ የሚያስከትለው ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ መከልከል አይቻልም፡፡ ይኼ በየትኛውም የማሰራጫ ዘዴ ማስተላለፍንም መቀበልንም ይጨምራል፡፡ በሕግ የሚገደብባቸው ‘የወጣቶችን ደኅንነት የሚያናጉ፣ የግለሰብን መብት የሚጥሱና ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫ ማድረግ፣ የጦርነት ቅስቀሳ ማድረግ’ ናቸው፡፡ በይነመረብን ለመዝጋትም መለኪያዎቹ እነዚህ ናቸው፡፡ እነዚህ መለኪያዎችም በዝርዝር አሠራራቸው የሚታወቅ ሥርዓት እንዲኖር እንዲሁም ዘፈቀዳዊ እንዳይሆን ታስቦ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር መንግሥት በተደጋጋሚ በይነመረብ ሲዘጋ በአንድ በኩል የትኛውን ሕግ መሠረት አድርጎ፣ በሌላ በኩል እነዚህ ሁኔታዎች መሟላታቸውን የሚያረጋግጠውና የመዝጋት ውሳኔ የሚያሳልፈው ማነው? ወደሚለው ይወስደናል፡፡

በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ላይ የተቀመጠው መለኪያ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይነት አለው፡፡ የብዙዎቹ መለኪያዎች በሕግ መደንገግና ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ አስፈላጊ መሆኑ ሲሆን፣ የሁለተኛውን መሥፈርት አስፈላጊነቱን የመወሰን በአብዛኛው የተተወው ለሚመለከታቸው አገሮች ነው፡፡ እነዚህን መስፈርቶች ወደ አራት ምድብ በመከፋፈል መብቶች የሚገደቡበትን ሁኔታ መወሰን የተለመደ ነው፡፡ እነዚህም፣ ሕጋዊነት፣ ቅቡልነት፣ አስፈላጊነትና ተመጣጣኝነት በመባል ይታወቃሉ፡፡

የሕጋዊነት (Legality) መርሕ የሚያመለክተው መብቶች ከመገደባቸው አስቀድሞ በሕግ የታወቀ እንዴት ሊገደቡ እንደሚችሉ ሥርዓት የመኖር አስፈላጊነትን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሕገ መንግሥቱ በጥቅል ማዕቀፉን ያስቀመጠ ሲሆን፣ በተለያዩ ሕግጋት (የወንጀል፣ የፀረ ሽብር፣ የኮምፒዩተር ወንጀል፣ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ወዘተ) አማካይነት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ወሰን ምን ድረስ እንደሆነ እናገኛለን፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ወቅትም የተፈጸመው የበይነመረብ የመዝጋት ድርጊት እንዲሁ ሕጋዊ መነሻ እንዳለው እንገነዘባለን፡፡

የቅቡልነት (Legitimacy) መርሕን ስናይ የሚይዘው የሕጉን ተቀባይነት ነው፡፡ በስመ ሕግ በዘፈቀደና ተቀባይነት የሌለው ግብን ለማሳካት የሚወጣ መሆን እንደሌለበት ለማጠየቅ ነው፡፡ ገደብ ጣይ ሕግጋት የሕዝብን የጋራ ጥቅም የሚያስቀድሙ፣ እንዲሁም የሌሎችን መብት ከግምት ያስገቡ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር በተለያዩ አዋጆች ውስጥ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ከዚህ መርሕ አንፃር ሊታዩና ሊፈተሹ እንደሚገባ መገንዘብ ይቻላል፡፡

አስፈላጊነት (Necessity) መርሕ በበኩሉ ቅቡልነት ያለው ሕግም ቢኖር ገደብ ለማድረግ ወይም ይህንን መብት ከመጠቀም ለመቆጠብ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች መኖር አለባቸው፡፡ ሁኔታዎቹም በሌላ መንገድ ሊቀረፉ የማይችሉና አሳሳቢ መሆን እንዳለባቸው ነው ይኼ መርሕ የሚጠይቀው፡፡

አራተኛው መርሕ ተመጣጣኝነት (Proportionality) ነው፡፡ ገደብ ሲደረግ የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ተመጣጣኝ የሆነ፣ ችግሩን ለመቅረፍ መፍትሔ በሚሆን መልኩ ነው፡፡ ጅግጅጋ ላይ ችግር ሲፈጠር፣ መቐለ ወይም ባህር ዳር ላይ የሚሰጥን አገልግሎት መዝጋት አይደለም፡፡ ተማሪዎች ፈተና እንዳይኮራረጁ ከሆነ ከስልክ በስተቀር በሌላ መንገድ አገልግሎት ማገኘትን አለመዝጋት እንደማለት ነው፡፡

የበይነመረብ አገልግሎት ከላይ በቀረቡት መለኪያዎች እየተመዘነ ሊገደብ እንደሚችል የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ላይ ተገልጿል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች መሟላታቸውን አረጋግጦ አገልግሎቱን እንዲቋረጥ የመወሰን ሥልጣን የመንግሥት (አስፈጻሚው)  ነው፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ በሕግ ይህን ሁኔታ መወሰንና ከእዚያ አልፎና ተሻግሮ ሲገኝ ቁጥጥር የሚደረግበት የፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ መኖር አለበት፡፡

የበይነመረብ አግልገሎት በተደጋጋሚ የሚዘጉ አገሮች እንዴትና በማን ውሳኔ እንደሚዘጋ ሕግ ያላቸው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ግን ግልጽ ፖሊሲም፣ የመዝጋጋት ውሳኔ የሚሰጡ አካላት እነማን እንደሆኑም የሚገልጽ ሕግ የላትም፡፡

ከላይ ለማየት እንደሞከርነው፣ የበይነመረብ አገልግሎት ጥብቅ የሆኑ መሥፈርቶችን አልፎ ሊዘጋ መቻሉን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን የመዝጋት ውሳኔ እየተደጋገመ መምጣቱ ቢጨምርም፣ እንዴት እንደሚዘጋ የሚያሳይ ግልጽ ሕግ የለም፡፡ እንደሚዘጋም ቀድሞ ማሳወቅም (ለምሳሌ በፈተና ወቅት)፣ ከተዘጋ በኋላም እስከመቼ ድረስ እንደሚዘጋም ለምን እንደተዘጋም የሚገለጽበት ሥርዓት የለም፡፡

 በዓለም አቀፉ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኅብረት መመሥረቻ ጽሑፍ ከሚጠይቀው ግዴታ ውስጥ አንዱ ግልጽነት ያለበት አሠራር ማስፈንን ነው፡፡ አገሮች የቴሌ አገልግሎቶችን በሚያቋርጡበት ወይም በሚገድቡበት ጊዜም በተቻለ ፍጥነት ለኅብረቱ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ ኢትዮጵያ ከዲጂታል የኢኮኖሚ ሥርዓቱ ተጠቃሚነቷን ወይም ድርሻዋን (Digital Dividend) ለማሳደግ የበይነመረብ ተደራሽነትን ጥራትን ማሳደግ ያለባት ሲሆን፣ የተደራሽነትም የጥራትም ሁኔታው በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ዝቅተኛ በሆነበት ሁኔታ የዲጂታል ኢኮኖሚው ድርሻዋ በአንፃራዊነት ልዩነቱ አሁንም እንዲሰፋ (Digital Divide) ማድረግ የለባትም፡፡

ስለሆነም፣ ኢትዮጵያ የበይነመረብ አስተዳደር ፖሊሲ አላት ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር የሚቻል ስላልሆነ፣ ፍተሻ በማድረግ በዘፈቀደ የሚፈጸመውን የበይነመረብ መዝጋትና መክፈት ሥርዓት እንዲይዝ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ከማከበር አንፃር፣ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው አኳያ እንዲሁም የውጭ ባለሀብቶችንም ለመሳብ ሲባል የታወቀና ግልጽ አሠራር ማስፈን ለነገ የሚባል የቤት ሥራ አይደለም፡፡ 

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...

የአገሪቱን የፖለቲካ ዕብደት ለማርገብ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሚና ምን ይሁን?

በያሲን ባህሩ   የኦሮሚያ ብልፅግና      በአገር ደረጃ የብሔር ፖለቲካ በሥራ...

ለቀድሞ የሕግ ታራሚዎች የቆመው ሰው ለሰው

የደርግ መንግሥት ደጋፊዎችና የሥልጣን ተጋሪዎች፣ ከከፍተኛ የቀድሞ መንግሥት ባለሥልጣናት...

ባይደን ከምርጫ ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ የዴሞክራቱን መድረክ የተቆጣጠሩት ካማላ ሃሪስ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ኮቪድ መያዛቸው በተነገረ ሳምንት ነበር...