Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዋጋ የሚያንሩ ይመንጠሩ!

ገበያ ወጥቶ አቅም በፈቀደ መጠን መገበያየት ፈተናም ዘበትም እየሆነ ነው፡፡ ደጋግመን እንደምንለው የግብይት ሥርዓታችን ቅጥ ያጣና ጨዋነት የጎደለው መሆኑ  ችግሩን አብሶታል፡፡

ለዋጋ ጭማሪው ወይም ለዋጋ ግሽበቱ መንስዔ ናቸው ብለን የምጠቅሳቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ በዋናነት ልናስቀምጠው የምንችለው አጋጣሚዎችን እየጠበቁ በመጠቀም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪዎች ምንኛ ልጓም አልባ እየሆኑ እንደመጡ ነው፡፡ ሆን ብሎ እጥረት በመፍጠርና ገበያውን በመቆጣጠር ትርፍ ለማጋበስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ለዋጋ ግሽበት ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አለው፡፡

የራስ ጥቅምን እንጂ አገር የሚጎዳ ጣጣ እያመጡ ስለመሆናቸው ማሰብ የሚሳናቸው ግለሰቦችና መረባቸው የሚፈጥሩት ያልተገባ ተግባር ሊቆም ባለመቻሉ ይኸው ዘወትር እየወቀስናቸው ነው፡፡ እየተማረርንባቸው ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ዘወትር የሚፈጸም ቢሆንም ተገቢው ዕርምጃ ባለመወሰዱ፣ ችግሩ ዘልቆ ለሸማቾች ምሬት መባባስና አለሁ ባይ ማጣት ምክንያት ሆኗል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከልብ ምላሽ የሚሰጥ አካሄድ ካልተዘረጋና የግብይት ሥርዓቱን መስመር ሊያሲዝ የሚችል ዕርምጃ  ካልተወሰዱ በቀር ችግሩ ተባብሶ ይቀጥላል፡፡ ጤናማ የሚባለውን ገበያ እየበከለ  ይቀጥላል፡፡ ገበያውን በማጋጋል ያልተገባ ዋጋ የሚተክሉ አካላት በግልጽ ስለሚታዩ መፍትሔ ማበጀቱ ጊዜ የሚጠይቅ እንዳልሆነ በመረዳት ጠበቅ ያለ ዕርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባቀረቡት ሪፖርት፣ ለኑሮ ውድነቱ አንዱ መንስኤ ይኸው ያልተገባ የግብይት ሥርዓት ስለመሆኑ መንግሥታቸው መረዳቱንና ዕርምጃ መወሰድ እንደጀመረ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ በተግባር ምን ውጤት እንደመጣም ማሳወቅ ተገቢ ነው፡፡

ችግሩ አሳሳቢ እንደመሆኑ መጠን ለዋጋ ግሽበት ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች ለይቶ ዕርምጃ እንዲወስድ ኃላፊነት የተሰጠው ግብር ኃይልም ኃላፊነቱን ተወጥቷል የሚባለው የችግሩ ፈጣሪዎች ላይ ዕርምጃ ሲወሰድና የተሰቀለውን ዋጋ ለማውረድ ተገቢው የምርት አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ የተረጋጋ ገበያ ስለመፈጠሩ በተግባር ማሳየት ሲችል ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ ምን ተሠራ? ምን ውጤት መጣ ለሚለው ጥያቄ ግብረ ኃይሉ ምላሹን ሊያሳውቀን ይገባል፡፡

ከሁሉ በላይ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የገቢ ንግዱን መቆጣጠሩ ላይ ነው፡፡ ለዋጋ ግሽበት መጋጋል ምክንያት የሆነው ሌላው ጉዳይ በአሁኑ ወቅት እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች ውስጥ የሚታየው የቤት ኪራይ ዋጋ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሰሞኑ የፓርላማ ማብራሪያቸው ገልጸውታል፡፡ የቤት ኪራይ ዋጋ ለኑሮ ውድነት መንስኤ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህም ችግር ለዓመታት የዘለቀና የመፍትሔ ያለ ሲባልበት የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ የቤት ኪራይ ዋጋን የሚቆጣጠር ሕግ ይወጣል ተብሎ ረቂቁ እንደተዘጋጀ ከተነገረ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ የውኃ ሽታ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ለኑሮ ውድነት መባባስና ለተከራዮች ሰቀቀን በመሆን የዘለቀውን ይህንን ችግር ፈር ለማስያዝ ይረዳል የተባለው ሕግ ምንልባትም ፀድቆ ሊወጣ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ መስማታቸን መልካም ነው፡፡ ሁሉም እንዳሻው እየተነሳ መንግሥት ባንበሸበሸበው ቤት ወራት እየጠበቀ ለደሳሳ ጎጆ ራስ የሚያዞር የኪራይ ዋጋ እየቆለለ የተከራይ ኑሮን ማናጋቱ አደብ የሚገዛበት ሕግ ከወጣ ኢኮኖሚውንም ተራውን ዜጋም ከጉስቁልና መታደግ ይቻላል፡፡

አከራይና ተከራይን የሚዳኝ የቤት ኪራይ ዋጋም ገበያውን ያገናዘበ እንዲሆን፣ የአከራይና ተከራይ መብትና ግዴታዎችን ቁልጭ አድርጎ የሚያስቀምጥ ስለመሆኑ የተነገረለት ረቂቅ ሕግ ሲተገበር የሚኖረው አወንታዊ አስተዋጽኦ ጉልህ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲህ ያለውን ሕግ ሥራ ላይ ለማዋል እንደሚደረገው ጥረት ሁሉ፣ ለዋጋ ንረቱ መንስኤ የተባሉ ክስተቶችን፣ ለገበያ መበረዝ እጃቸውን ያስረዘሙት ሁሉ በገበያ ሕግ እንዲዳኙ የሚያደርግ አሠራር መዘርጋት ይገባል፡፡

የአገሪቱን ገበያ የሞሉት ሸቀጣ ሸቀጦች በምን ዋጋ ከውጭ መጥተው በምን ያህል ዋጋ እየተሸጡ ነው? የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ከልብ አልተሠራበትም፡፡ ግልጽ አሠራር እንዲኖር በመረጃ የተደገፈ ግብይትና የገበያ ክትትል መፍጠር ያሻል፡፡ ይህ ባለመኖሩ ኢትዮጵያ ወጥ የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ እስከ አንድ ሺሕ በመቶ ትርፍ ታክሎበት ይሸጣል፡፡ ዕርምጃ ሲወሰድ ግን አይታይም፡፡ ዕቃው ከሚገባው በላይ ዋጋ የሚጫንበት ዕውን ትርፍ ለማጋበስ ብቻ ነው ወይ? ለዚህ ጥያቄ አንዱ መልስ በተለይም የሸቀጥ አስመጪነት ሥራ፣ ሲከፋም የአከፋፋይት ሥራ በአብዛኛው በሞኖፖል መያዙ ነው፡፡ ጥቂቶች እንዳሻቸው የሚሆኑበት ዘርፍ በመሆኑ ነው፡፡

ገበያን በሞኖፖል የያዙ ጥቂቶች እንዳሻቸው ሲፈነጩ ዝም መባላቸው የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ እንዲህ ያለው ክፍተትና የተጋነነ ዋጋ የሚተክሉ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ተወዳዳሪዎችን ማብዛት የግድ ይላል፡፡ ተመጣጣኝ ትርፍ በመያዝ ሊሠሩ የሚችሉትን ማብዛት ብቻ ሳይሆን፣ ማበርታትም አንዱ መፍትሔ ነው፡፡ በሞኖፖል የተያዘውን ገበያ መስበር ያስፈልጋል፡፡

ከዋናው የምርት ምንጭ የሚገዛበትን ዋጋ ማሳወቅ አንዱ ነው፡፡ ይህም በአግባቡ የሚሠራበትንና የማይሠራውን ለመለየት ይችላል፡፡ ይህንን የጠቀስኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ዛሬ አብዛኛውን ከውጭ የምናስገባቸው ዕቃዎች ምርቱ ከሚመጣበት አገር የሚገዛበትና እዚህ የሚሸጥበት ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት ካላጋነንኩ ዘግናኝ መሆኑን ማረጋገጥ የሚችል በመሆኑ ነው፡፡

ከሰሞኑ ዕቃዎች እጅግ በተጋነነ ዋጋ የወጣላቸውን አንዳንድ ምርቶች ከምርቱ መነሻ ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ያለውን ልዩነት ለተመለከተ ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ ዋጋ ግሽበት በመጠቃት ተወዳዳሪ የሌላት መሆኑን መመስከር ይቻላል፡፡

ስለዚህ መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር አስመጪዎቻችንን ለብቻ መመልከት ይገባዋል፡፡ ዜጎች በዓለም ላይ በማይታይ የትርፍ ኅዳግ በማይዙ እየተበዘበዙ ነውና ለምን ይህንን ያህል ትርፍ ያዝክ ብሎ መመርመር ይገባዋል፡፡ እንዲያውም ትልቁ ችግር የትርፍ ኅዳግ በዘፈቀደ መንገድ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት አንዱ ዕርምጃ ያላግባብ የተጋነነ ዋጋ በመስጠት አገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ጫና እያሳደረ ባለው ገቢ ንግድ ውስጥ ተዋንያኖችን በማብዛት በዚያ በሚፈጠር ውድድር ሸማቹንም መታገድ አለበት፡፡

አንዳንድ ቢዝነሶች በሞኖፖል መያዛቸውንም በማጤን ይህንን በመስበር በነፃ ገበያ ሥርዓት እንዲመራ ማደረግም የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስ ይረዳልና ትኩረቱን በተለያየ አቅጣጫ መዘርጋት ይኖርበታል፡፡

ጥቂቶች የሚያሽከረክሩት ገበያ ሁሌም በገበያ ዋጋ እንዳንገበያይ የሚደረግ ከመሆኑ አንፃር መንግሥት ዓይኑን ሰፋ በማድረግ ተጨማሪ ምርመራዎችን በማድረግ ሸማቹንም ኢኮኖሚውንም መታደግ አለበት፡፡ የሸቀጥ አስመጪዎች ብሎ በሰንሰለት የሚተሳሰሩትን አከፋፋዮች ሁሉ ይፈተሹ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት