የአክሲዮን ገበያ፣ የ‹‹ካፒታል ገበያ››፣ ‹‹የሀብት ድርሻ ገበያ›› ወይም ‹‹ስቶክ ማርኬት›› መሥራች ከሆኑ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነበረች፡፡ የአክሲዮን ገበያ በኢትዮጵያ መተግበር የጀመረው ከ60 ዓመታት በፊት እንደነበር ይታመናል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ ከሌላቸው ጥቂት አገሮች አንዷ ነች፡፡
በአሁኑ ወቅት የአክሲዮን ገበያ ስለሚጀመርበት ሁኔታ ሐሳቦች ከግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ባሻገር በመንግሥት ባለሥልጣናትም ሲሰነዘሩ እየተደመጡ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ የስቶክ ማርኬትን ለማስጀመር ያግዛል የተባለው ፎረም ሐሙስ፣ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በኔክሰስ ሆቴል ተካሂዷል፡፡ በፎረሙ ጥናታዊ ጽሑፎችና ቀርበው፣ ውይይትም ተካሂዶባቸዋል፡፡
የፎረሙ አዘጋጅ አቡሽ አያሌው (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ የስኬትና የቢዝነስ መጻሕፍትን በማዘጋጀት ይታወቃሉ፡፡ አቡሽ (ዶ/ር) ስቶክ ማርኬትን፣ ‹‹ሰዎች የቦንድ ሰርተፍኬቶችንና የአክሲዮን ሰርተፍኬቶችን እርስ በርስ በብዛት የሚያሻሽጡበት ገበያ›› በማለት ይገልጹታል፡፡ ስቶክ ማርኬት ከኢኮኖሚ አንፃር ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ጥቅም ሲገልጹም፣ ‹‹የሰዎች ሀብት ባደገ ቁጥር የአገር ሀብት ያድጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቶች ገንዘብ በሚፈልጉበት ጊዜ በቦንድ መልክ ወይም በአክሲዮን ሽያጭ መልክ ከተለያዩ ማኅበረሰቦች ገንዘብ መሰብሰብ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡
ሕጋዊ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ድርጅቶች አክሲዮን ሸጠው የከሰሩና የጠፉ መኖራቸውንም አክለዋል፡፡ ‹‹የስቶክ ማርኬትና ኢንቨስትመንት›› በሚል ርዕስ ያሳተሙትን መጽሐፍ በዕለቱ ያስመረቁ ሲሆን፣ የመጽሐፉ ይዘት ማኅበረሰቡ በስቶክ ገበያ ውስጥ እንዴት ኢንቨስት እንደሚያደርግና የተሻለ ሀብት ማፍራት እንደሚችል የሚያብራራ ነው፡፡ የስቶክ ማርኬት የረቀቀ ዕውቀትን ስለሚጠይቅ፣ ለማኀበረሰቡ ከፍተኛ ዕገዛ እንደሚኖረውም ያስባሉ፡፡ መጽሐፉ የፋይናንስ አማራጭ ዕድል እንደሚኖረውም ያምናሉ፡፡
በዚሁ ዕለትም ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ካቀረቡት መካከል አቶ ሚሊዮን ክብረት አንዱ ሲሆኑ፣ ስለስቶክ ማርኬት ጠቀሜታዎችና አተገባበር ገልጸዋል፡፡ ስቶክ ማርኬት ከማለታችን በፊት ማርኬትን መግለጽ ተገቢ ነው በማለት ማርኬት በዓይን የሚታይ የሚዳሰስ የሚጨበጥ ሲሆን፣ ስቶክ ማርኬት ግን ከዚህ በተቃራኒ የማይታይ የማይጨበጥ ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ላይ አሁን ስላለው የውጭ ምንዛሪ እጥረትም ሲገልጹ፣ ይህ ገበያ ሲገባ ቀላል፣ ሲወጣም ቀላል በመሆኑ ነው እንጂ ኢኮኖሚያችን የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት እንዳላቃተው ገልጸዋል፡፡ ሌላኛው ጥናታዊ ጽሑቸውን ያቀረቡት የኮርነር ስቶክ አማካሪ ኩባንያ ባለቤት የሆኑት አቶ ተስፋዬ ኃይለ ሚካኤል ሲሆኑ፣ ስቶክ ማርኬት ላይ ቅድሚያ የሚያስፈልገው ግልጸኝነት ነው ይላሉ፡፡ ስቶክ ሲሸጥ ቁርጠኝነትና እውነተኝነት በጣም አስፈላጊ መሆናቸውንም አመላክተዋል፡፡
አንድ ሰው አክሲዮኑ ከመግዛቱ በፊት እዚያ አክሲዮን ላይ በዘርፉ ባለሙያዎች አሉ ወይ ብሎ መጠየቁና ኢንቨስት ስለሚያደርግበት ዘርፍ ማወቁ ጠቃሚ እንደሚሆን አክለዋል፡፡ በዓመት ከ19 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በካፒታል ገበያዎች አማካይነት እንደሚንቀሳቀስ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም 200 አገሮች የካፒታል ገበያን በመመሥረት ከፍተኛ ገንዘብ በማንሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ሲታወቅ፣ በተለይ የኒውዮርክና የለንደን አክሲዮን ገበያዎች በዓለም የስቶክ ገበያ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ሆነው ይገኛሉ፡፡