Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለኢኮኖሚው የሕመም ምልክቶች የመንግሥት ዘገምተኛነት ችግሮችን እንዳባባሰ ምሁራን ገለጹ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ላይ ያጠነጠነው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ መጽሐፍ ለገበያ ቀረበ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ በማተኮር በየዓመቱ የሚሰናዳው ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ዘንድሮ ለ17ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር አዘጋጅነት ለሦስት ቀናት ተካሂዷል፡፡ በጉባዔውም በርካታ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ታደለ ፈረደ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት በአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ሲታዩ የቆዩ የሥጋት ምልክቶችን ቸል በማለቱ አሁን ላይ አጣብቂኝ ውስጥ የሚከቱ አሥጊ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ‹‹በሽታው ቀደም ብሎ ይታወቅ ነበር›› ያሉት ታደለ (ዶ/ር)፣ በተለይም በወጪ ንግዱ በኩል የታየው ማሽቆልቆል ዓመታት ማስቆጠሩን፣  የመንግሥት ምላሽ ግን ቸልተኝነትና ዳተኝነት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ ማክሮ ኢኮኖሚው ምላሽ ሊሰጥባቸው የሚገቡ የሥራ አጥ ቁጥርን የመቀነስ፣ ሚዛናዊ የሀብት ክፍፍል ሥርዓትን የመፍጠር፣ የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠር፣ የወጪ ንግድ ዘርፉን የማስፋፋት፣ የውጭ ብድር ዕዳ ጫናዎችን ዝቅተኛ የማድረግ፣ የመንግሥት ገቢና ወጪን የማጣጣምና መሰል ሥራዎች አንድ ጤነኛ ማክሮ ኢኮኖሚ ከሚለካባቸው መሥፈርቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹እነዚህ እንደ መኪና ዳሽ ቦርድ የሚያገለግሉ የማክሮ ኦኮኖሚው ጤናማነት ምልክቶች ናቸው፡፡ ዳሽ ቦርዱ ቀይ ሲያበራ መኪና ላይ ችግር አለ እንደምንለው ሁሉ፣ ኢኮኖሚው ውስጥም ችግሮች መኖራቸውን የሚያመላክቱን እነዚህ ናቸው፡፡››

ይሁንና እነዚህን ችግሮች ማስተካከሉ ላይ መንግሥት ዘገምተኛ ነው ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ የወጪ ንግዱን በአብነት በማንሳት በመንግሥት የአምስት ዓመታት ዕቅድ ዘመን ውስጥ ቁልቁል እየተጓዘም ለዘጠኝ ዓመታት መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚው አመላካች ችግር ውስጥ መግባቱን እያየ መፍትሔ አለመስጠቱ ‹‹ምን ሲሠራ ነበር?›› እንደሚያሰኘው የገለጹት ታደለ (ዶ/ር)፣ ‹‹አካሄዳችን ልክ አይደለም፡፡ የምንከተለው ፖሊሲ ልክ አይደለም፡፡ ቆም ብለን መመርመር አለብን፤›› ማለት ይገባ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የወጪ ንግዱን በባለቤትነት የሚመራው መንግሥታዊ አካል ማን እንደሆነ አለመታወቁ ዘርፉን ይበልጥ እንደጎዳው አንስተዋል፡፡

የሌሎች አገሮች ተሞክሮ የወጪ ንግድ ማስፋፊያና ልማት በሚል ስያሜ የሚንቀሳቀሱ ተቋማትን በመፍጠር ስኬታማ መሆን እንደቻሉ ያወሱት ባለሙያው፣ ተቋሙ ክህሎቱ ባላቸውና ከፖለቲካ ነፃ በሆኑ ባለሙያዎች ሊመራ እንደሚገባው በርካታ ጥናቶች እዚሁ መደረጋቸውን አውስተዋል፡፡ ከተቋማዊ ችግሮቹ በተጨማሪም ላኪዎችም የአቅምና የክህሎት ችግሮች እንዳሉባቸው ጠቅሰው፣ እንዲህ ያለው ተቋም በኢትዮጵያ እንዲመሠረት ለመንግሥት ምክረ ሐሳብ ከቀረበለት አምስት ዓመታት ማለፋቸውን አስታውሰዋል፡፡

ኢኮኖሚ የሚመራበትና የሚተገበርበት ግልጽ ፍኖተ ካርታ ያስፈልገዋል ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ እያንዳንዱ ዘርፍ መሥሪያ ቤት በየዓመቱ ለሚያቅደው ዕቅድም ተጠያቂ እንዲሆን፣ መልካም አፈጻጸም ሲያስመዘግብም ዕውቅና በመስጠት፣ መሸለም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ይህ ሥርዓት በሩዋንዳ ሲተገበር መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወቅታዊ የኢኮሚው ጉዳይ ያሳሰባቸው ባለሙያዎች፣ ‹‹ኢኮኖሚው ኮማ ውስጥ ገብቷል፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አንዳንዶቹም ኢኮኖሚውም እንደ ፖለቲካው ሽግግር ላይ ነው በማለት ከልማታዊ መንግሥት ሞዴል ወደ ሊበራል ኢኮኖሚነት እያመራ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ የትኛው የኢኮኖሚ ሞዴል ነው አሁን ላይ ያለውን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚገልጸው? ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ ምሁሩ እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹ልማታዊ መንግሥት የሚባለው ሥርዓት መሰል ቅርፅ ያለውና የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ተግብረው ስኬት ያገኙበት አካሄድ ነው፤›› ይሉታል፡፡ ‹‹ልማታዊ መንግሥት ማለት ገበያው በሚገባ ባላደገባቸው አገሮች ውስጥ የመንግሥት ሚና ከፍተኛ የሚሆንበት ነገር ግን ሁሉ ቦታ የማይገባበት ሥርዓት ነው፤›› በማለት፣ መንግሥት አስፈላጊውን መሠረተ ልማት በማሟላት የግሉን ዘርፍ የሚደግፍበት፣ ብቃት ያላቸው መንግሥታዊ ተቋማትና ከፍተኛ ክህሎት ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የሚገነቡበት ሥርዓት ነው፡፡

እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ባልተሟሉበት ወቅት በኢትዮጵያ የተሞከረው የልማታዊ መንግሥትነት እሳቤ ‹‹ያልተሟላ ቁመና›› ተላብሶ በመምጣቱ በደካማ የመንግሥት ተቋማት ትከሻ የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብን ለመተግበር መሞከሩ ውጤቱን ደካማ እንዳደረገው የገለጹት ታደለ (ዶ/ር) ‹‹ልማታዊ መንግሥት ሲባል አንዴ ከተበላሸ ሳይወልቅ አብሮን የሚያረጅ ሳይሆን፣ ኢኮኖሚውንና የግሉን ዘርፍ እያሻሻለ ቀስ በቀስ ወደ ገበያ መር ኢኮኖሚ የሚያሸጋግር ወደ ሊበራል ኢኮኖሚ የሚያደርስ ሥርዓት ነው፤›› በማለት ኢትዮጵያ ከልማታዊ መንግሥትነቱም ከሊበራል ወይም ከገበያ መር ኢኮኖሚውም ሳትሆን መንገድ ላይ የምትገኝና ብዙ የሚቀራት ተጓዥ አገር መሆኗን በመገልጽ ሐሳባቸውን አፍታተው ገልጸዋል፡፡

 እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ጨምሮ ኢኮኖሚው ምንም እንኳ ግብርና የተጫነው ቢሆንም፣ ከግብርና ይልቅ ከተማ አቀፍ በሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ኢንቨስት ማድረጉ ግብርና ከሚያስገኘው በላይ ጠቀሜታ እንደሚመጣ በጥናት ከሞገቱ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች መካከል የዓለም አቀፉ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት (ኢፍፕሪ) የልማት ስትራቴጂና ገቨርናንስ ዘርፍ ዳይሬክተር ፖል ዶሮሽ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በግብርና ላይ ጥገኛ ብትሆንም፣ በኢኮኖሚው ትልቁን ተጠቃሚነት የሚያስገኘው ግን ከግብርና ውጪ ባሉት መስኮች ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ይህም ይባል እንጂ ግብርና ላይ ኢንቨስት ማድረጉና ግብርናን ማሳደጉ መቀጠል እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ለአራት ዓመታት የቆየውና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ ከ1983 ዓ.ም. በፊት ጀምሮ የዳሰሰውን የዳጎሰ መጽሐፍ በአርትኦትም በጸሐፊነም ካሰናዱት በርካታ ምሁራን አንዱ የሆኑት አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) በጉባዔው ወቅት ተገኝተው መጽሐፉን አስተዋውቀዋል፡፡ የእንግሊዝ ኦክስፎድ ዩኒቨርሲቲ ያሳተመው ይህ መጽሐፍ ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት እንደ ማጣቀሻነት እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ ቢሆኑም፣ በኢኮኖሚ ምሁራኑ ጉባዔ ላይ የተገኙት ግን እንደ አንድ የጥናት ባለሙያና እንደ ማኅበሩ አባል እንደሆነ በመገለጽ በዚሁ ስለመጽሐፉ የተወሰኑ ነጥቦችን ለታዳሚው አጋርተዋል፡፡

በ1,000 ገጾችና በስድስት ክፍሎች የተቀነበበው ይህ መጽሐፍ ‹‹ኦክስፎርድ ሃንድቡክ ኦን ኢትዮጵያን ኢኮኖሚ›› የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን፣ የመሸጫ ዋጋው 100 ዶላር ነው፡፡ ይሁንና መጽሐፉ በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለተማሪዎችና ተመራማሪዎች ማጣቀሻነት ይውል ዘንድ ድጋፍ እንደሚሰጥ የገለጹት አርከበ (ዶ/ር)፣ መጽሐፉ የመንግሥትን ሐሳብና አቋም የማያንፀባርቅ ይልቁንም ብዝኃ ሐሳቦችን፣ ሞጋችና ተቺ ሐተታዎችን በማስረጃ አስደግፎ ያቀረበ 70 ምሑራን የተሳተፉበት ሥራ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

በህልውና ለመቆየት ሲንገታገት የሰነበተው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር፣ ዳግም አንሠራርቶ በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ጋር እያካደ፣ የጥናት ውጤቶችንም ይፋ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዘንድሮው ኮንፈረንስ ላይ በእንግድነት ከተገኙት መካከል የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፣ የአፍሪካ ዳይሬክተር አበበ አዕምሮ ሥላሴ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት ኑሯቸውን በውጭ ያደረጉት አበበ (ዶ/ር) በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ በርካታ ለውጦች ማስዝገቧን፣ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወሳኝ በሚባሉ ጫናዎች ሚዛኑን የሳተ ኢኮኖሚ እያንገዳደጋት እንደምትገኝ ባቀረቡት ጽሑፍ አመላክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች