Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአካባቢ ተቆርቋሪዎችና በኢንዱስትሪ አቀንቃኞች መካከል አለመግባባት በመፈጠሩ የሶዳ አሽ ፋብሪካ ሥራ አቆመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአብያታና በሻላ ሐይቆች በሚካሄድ ልማት በአካባቢ ተቆርቋሪዎችና በኢንዱስትሪ አቀንቃኞች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሥራ በመስተጓጎሉ፣  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መመርያ እንዲሰጡ ተጠየቀ፡፡ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች በአካባቢው ማኅበረሰብ ተቀባይነት በማግኘታቸው፣ የሚድሮክ ደጓሚ ኩባንያ ናሽናል ማይኒንግ ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድረው ሶዳ አሽ ፋብሪካ ሥራ አቁሟል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን በስምጥ ሸለቆ ክልል ውስጥ አጠገብ ለአጠገብ የሚገኙት አብያታና ሻላ ሐይቆች፣ ለበርካታ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆኑትን ሶዳ አሽና ኮስቲክ ሶዳ የተሰኙ ኬሚካሎችን ማምረት ያስችላሉ፡፡

ሁለቱ ሐይቆች በአንድ በኩል የአብያታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ አካል ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል በደርግ ዘመን የተገነባው የአብያታ ሶዳ አሽ ፋብሪካ መሠረትም ናቸው፡፡

ሁለቱ ጨዋማ ሐይቆች የፓርኩ ወገን በክረምት ወራት ከአውሮፓ የሚሰደዱትን ፔሊካንና ፍላሚንጎን ጨምሮ በርካታ ድንቅዬና የቱሪስት ቀልብ የሚስቡ አዕዋፋት መኖርያ ሲሆኑ፣ የፋብሪካው ወገን ደግሞ ሶዳ አሽ ለማምረት በተዘጋጁ 16 ሰው ሠራሽ ሐይቆች በተለይ የአብያታ ውኃ ተስቦ በፀሐይ እየተሰጣ ትሮና የተሰኘ ንጥረ ነገር ይመረትበታል፡፡

ሁሉም ፋብሪካዎች የሚጠቀሙትን ሶዳ አሽና ኮስቲክ ሶዳ የሚያመርተውን ፋብሪካ  የሚድሮክ ደጓሚ ኩባንያ የሆነው ናሽናል ማይኒንግ ኮርፖሬሽን ከፕራይቬታይዜሽንና ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በመግዛት ሲያመርት ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአብያታ ሐይቅ እጅግ በጣም እየቀነሰ በመምጣቱም፣ በአካባቢ ተቆርቋሪዎችና በኢንዱስትሪ አቀንቃኞች መካከል የተለያዩ አመለካከቶች እየቀረቡ በመሆኑ ቀጣዩን ሻላ ሐይቅ መጠቀም አለመቻሉ ተገልጿል፡፡

የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ለአብያታ ሐይቅ መቀነስ ወይም ለመጥፋት መቃረብ የሚያቀርቡት ምክንያት፣ ፋብሪካው ትሮና ለማምረት ውኃውን እየሳበ 16 ሰው ሠራሽ ሐይቆች ላይ በፀሐይ በማስጣት እያተነነ የሚጠቀም በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡

የኢንዱስትሪ አቀንቃኞች ደግሞ ፋብሪካው ውኃውን ስቦ በማትነኑ ሳይሆን፣  የአካባቢው ደን በመመናመኑና ለሐይቁ የሚገብረው የቡልቡላ ወንዝ በከፍተኛ ደረጃ ለመስኖ በመዋሉ ወደ ሐይቁ የሚገባው ውኃ በመቀነሱ ነው ይላሉ፡፡

ክርክሩ በዋናነት የሚመራውም በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ እንዲሁም በማዕከል ደረጃ በሚገኙ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ነው፡፡ በኢንዱስትሪ አቀንቃኞች በኩል ደግሞ በዋናነት በኢትዮጵያ ኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንስቲትዩትና በብሔራዊ ማይኒንግ ኮርፖሬሽን አማካይነት ነው፡፡

በዚህ አለመግባባት የሚድሮክ ደጓሚ ድርጅት ከሻላ ሐይቅ ውኃ ስቦ በማምጣት ትሮና ለማምረት የያዘው ዕቅድ የተስተጓጎለ ሲሆን፣ በሁለቱ ተከራካሪ ተዋናዮች መካከል አስታራቂ ሐሳብ ባለመገኘቱ አገሪቱ በርካታ ወጪ እያወጣች ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንስቲትዩት ሰሞኑን ባወጣው ጥናት፣ ኢትዮጵያ ኬሚካሎችን ለመግዛት በየዓመቱ 209 ሚሊዮን ዶላር ታወጣለች፡፡

የኢንስቲትዩቱ ኬሚካል ክፍል ኃላፊ አቶ መቂ ከበደ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሻላ ሐይቅ  ጥቅም ላይ ቢውል አብያታ ላይ ያጋጠመው ክስተት አይገጥመውም፡፡ ምክንያቱም አብያታ ጥልቀት የሌለውና ለፀሐይ የተጋለጠ በመሆኑ ትነት ያጠቃዋል፡፡ ሻላ ሐይቅ ግን ጥልቅና ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ጥላ አለው ይላሉ፡፡ በአግባቡ ጥቅም ላይ ቢውል መልካም በመሆኑ አገሪቱንም ከአላስፈላጊ ወጪ ያድናታል ብለዋል፡፡

በዚህ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዮቹን አጢነው የመፍትሔ ሐሳብ እንዲሰጡ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚያስችላቸውን ምክረ ሐሳብ፣ በኢንስቲትዩቱ ተዘጋጅቶ እንደቀረበላቸው ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች