ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአንድ ዓመት በፊት ሥልጣን መያዛቸውን ተከትሎ ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አንፃር ተጀምሮ የነበረው ተስፋ ሰጪ ዕርምጃ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲሸረሸር ቆይቶ ሁኔታው አሁን ላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) አስታወቀ፡፡
ጉባዔው ይህን ሥጋቱን የገለጸው ሐሙስ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በዋና ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሆን፣ በመግለጫውም ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታ ከሰብዓዊ መብቶች አንፃር መገምገሙን አስታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳርና በአዲስ አበባ በአማራ ክልልና ከፍተኛ አመራሮችና በወታደራዊ ሹማምንት ላይ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ፣ በመንግሥት እየተወሰዱ ባሉት ዕርምጃዎች ቅሬታውን ገልጿል፡፡
‹‹ከለውጡ በፊት የነበረውን የጭቆናና የአፈና ሥርዓት በሚያስታውስ መልኩ መንግሥት በተለይ ድርጊቱ በተፈጸሙባቸው ከተሞች እየተወሰደ ያለው መጠነ ሰፊ እስራት፣ እየታየ ያለውን ተስፋ የሚያደበዝዝ ተግባር ነው፤›› ሲል ክስተቱን ተከትሎ ያሉ መጠነ ሰፊ እስራቶችን ኮንኗል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የእስራት ዘመቻው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትን፣ እንዲሁም በመንግሥት ላይ ጠንካራ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ግለሰቦችን ማካተቱ የለውጥ ሒደቱን ወደኋላ እንዳያጓትተው የሚል ሥጋት እንዳለው ኢሰማጉ አስታውቋል፡፡
‹‹በተለይም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት በመባል የሚታወቀው ስብስብ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው በተባሉ ግለሰቦች ላይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጸሙ እስራቶች፣ ከፖለቲካ ተሳትፏቸውና ከሚያራምዱት አስተሳሰብ ጋር ተጣምሮ ሲታዩ እያስከተሉ ያለው ተፅዕኖ በፖለቲካ ፓርቲዎቹና በአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤቱ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ አገራችን በጀመረችው አጠቃላይ የለውጥ ሒደት ላይ መሆኑ በእጅጉ አሳሳቢ ያደርገዋል፤›› በማለት ሥጋቱን አብራርቷል፡፡
የሲዳማ የክልልነት ጥያቄን በተመለከተ ደግሞ፣ ‹‹መንግሥት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም ጥያቄውን የሚያስተባብሩ አካላትና ምሁራን በፍጥነት የጋራ መፍትሔ በመፈለግ የደኅንነት ሥጋቱን እንዲያቃልሉ ወይም ዳግመኛ እንዲህ ዓይነቱ የደኅንነት ሥጋት እንዳይፈጠር፣ እንዲሁም ጥያቄው በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲፈታ፤›› ሲል ጥያቄውን አቅርቧል፡፡
በቅርቡ ከወጡት የገዥው ፓርቲ አባል ፓርቲዎች መግለጫ ጋር በተያያዘም፣ ‹‹ሕወሓትና አዴፓ በቅርቡ በየበኩላቸው የሰጧቸው መግለጫዎች በፓርቲዎቹ መካከል ያሉትን ልዩነቶች ወደ ቃላት ጦርነት ከፍ ማለቱን የሚያሳዩ ከመሆኑም በላይ፣ በክልሎቹ መስተዳድሮች መካከል ባለፈው አንድ ዓመት የታየውን የመገዳደር ሥርዓት ወደ ግጭት እንዳያመራ ያሠጋል፤›› በማለት ሁኔታውን ገልጾታል፡፡
‹‹ሁለቱ ድርጅቶች በሰላማዊና በሠለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ፣ በከረሩ መግለጫዎቻቸው የሁለቱን እህትማማች ሕዝቦች ወደ ግጭት እንዳይገፉ፣ መንግሥት ፓርቲዎቹ ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን መንገድ እንዲያመቻችና የክልሎቹንም ሆነ የመላው የአገሪቱን ነዋሪዎች ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራውን ይወጣ፤›› በማለት ጥሪ አቅርቧል፡፡