አንጋፋው የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ የገጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በምርታማነቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳሳደረበት አስታወቀ፡፡
የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አካሉ ገብረ ሕይወት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ፋብሪካው በገጠመው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ዓመታዊ ጥገና ማካሄድ ተቸግሯል፡፡ ይህም በምርታማነቱ ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረበት ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ አካሉ ገለጻ ፋብሪካው ለዓመታዊ ጥገና የመለዋወጫ ግዥ እስከ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚያደርግ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ከንግድ ባንክ ሊፈቀድለት የቻለው አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም. የተፈቀደለት ምንዛሪ መጠን 500,000 ዶላር፣ በ2011 ዓ.ም. ደግሞ 400,000 ዶላር ብቻ እንደሆነ አቶ አካሉ አስረድተዋል፡፡
የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃነት የሚጠቀሙባቸው ግብዓቶች 90 በመቶ የአገር ውስጥ ምርት ሲሆኑ፣ የሚያስፈልጓቸው መለዋወጫዎች ግን ሙሉ በሙሉ ከውጭ የሚገቡ ናቸው፡፡ በዓመታዊ ጥገና ወቅት በርካታ መለዋወጫዎች እንደሚሸመቱ የተናገሩት አቶ አካሉ፣ የኖራ ድንጋይ የሚቃጠልበት ተሽከርካሪ ክሊን ማሸን ውስጥ የሚገኙት ሸክላዎች ወሳኝ ከሚባሉት መለዋወጫዎች ውስጥ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሸክላ ከሌለ ክሊንከር ማምረት አይቻልም፡፡ ክሊንከር ካልተመረተ ሲሚንቶ የለም ማለት ነው፤›› ያሉት አቶ አካሉ፣ ሙገር ሲሚንቶ በ2010 ዓ.ም. በተመደበለት 500,000 ዶላር የሸክላዎች ግዥ ብቻ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሌላውን መለዋወጫ ትተን ለሸክላ ግዥ ብቻ አውለናል፡፡ በዚህ ዓመት ከተፈቀደልን 400,000 ዶላር ውስጥ 300,000 ዶላር ለሸክላ ግዥ፣ 100,000 ዶላር ለሌሎች መለዋወጫዎች ግዥ አውለናል፤›› ብለዋል፡፡
በሸክላ ምርት የኦስትሪያና የጀርመን ኩባንያዎች የታወቁ እንደሆኑ የገለጹት አቶ አካሉ፣ ሙገር ሲሚንቶ ለሸክላ ግዥ ብቻ በዓመት 1.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው እስካሁን በመጋዘን የነበሩትን መለዋወጫዎችና በአንዳንዶቹ ላይ መጠነኛ ለውጥ በማድረግ ፋብሪካው እንዳይቆም ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸው፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በፋብሪካው ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳሳደረ አስረድተዋል፡፡
ፋብሪካው በዓመት 1.7 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ቢኖረውም፣ በአሁኑ ወቅት 1.2 ሚሊዮን ቶን ብቻ ለማምረት እንደተገደደ ተናግረዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን በተመለከተ የሙገር ማኔጅመንት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊዎች ጋር በየጊዜው ውይይት እንደሚያካሂድ ገልጸው፣ ጉዳዩ አገራዊ ችግር በመሆኑ መፍትሔ ለማግኘት በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
በቀድሞ ወታደራዊ መንግሥት በምዕራብ ሸዋ አዳበርጋ ወረዳ በ1976 ዓ.ም. ለአሥረኛው የአብዮት በዓል ዋዜማ የተመረቀው የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በምሥራቅ ጀርመን ባለሙያዎች የተተከለ ሲሆን፣ በ1982 እና በ1998 ዓ.ም. ሁለት ግዙፍ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች አካሂዷል፡፡ በኮንስትራከሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ የሚገልጹት ኃላፊዎቹ፣ በማኅበረሰብና በአካባቢ ልማት ፕሮጀክቶች እንደሚታወቅ ተናግረዋል፡፡