Wednesday, July 24, 2024

ደንታ ቢስነት አገሪቱንና ሕዝቡን የበለጠ ዋጋ እንዳያስከፍል!

ኢትዮጵያ አሁንም ወደ ሌላ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እየገባች ነው፡፡ የአሁኑን ቀውስ ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው በቀጠሮ ተይዞ ዓይን እያየ ስለተገባበት ነው፡፡ ሕጋዊ መንገዶችን ለመጠቀም የታየው ዳተኝነት፣ በደቡብ ክልልም ሆነ በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ጣት ያስቀስራል፡፡ የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሠረት  ተፈጻሚ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት ጥያቄው ከቀረበለት በኋላ በምክር ቤቱ አፀድቆ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ያቀረበበት ጊዜ እየታወቀ፣ ከወራት በፊት ጉዳዩ ቀን ተቆርጦለት የመልስ አምጡ ጥያቄ ሲዥጎደጎድ የት ነበር? ከሲዳማ ዞን ጀምሮ እስከ ክልሉ ድረስ ያሉ የምክር ቤት አባላትና አስፈጻሚዎች ከሕዝቡ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ጥያቄ ሊነሳበት ይገባል፡፡ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም.  የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ዕውቅና አግኝቶ፣ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ቀን ይቆረጣል ተብሎ ዝግጅት ሲደረግ የት ነበሩ? ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን አምስት ወራት እንደሚቀሩና ዝግጅቶች መጀመራቸውን መግለጫ ከሰጠ በኋላ፣ በተለይ ወጣቶች ሰከን እንዲሉ የአገም ጠቀም ዓይነት ማሳሰቢያ መስጠት ለምን አስፈለጋቸው? ከመግለጫው በኋላ በሲዳማ ዞን የተለያዩ አካባቢዎችና በሐዋሳ ከተማ ብጥብጦች ከመከሰታቸው በፊት ለማረጋጋት ለምን ጥረት አላደረጉም? በሌላ በኩል የፌዴራል መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት የጥያቄውን ተቀባይነት አምኖ፣ ጥያቄው ሕጋዊ መንገድ ካልተከተለ ችግር እንደሚፈጠር ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባለፈ፣ ከክልሉ አመራር ጋር በመሆን ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ የዝግጅት ሒደትን ማስረዳት ለምን ከበደው? አሁንም መፍትሔ የሚፈለግ ከሆነ ችግሩን በዚህ መንገድ መዝኖ፣ ወደ መፍትሔ መግባት የግድ ይሆናል፡፡

በደቡብ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚነሱ ማናቸውም ጥያቄዎች፣ ከሕግ አግባብ ውጪ በኃይል መፈጸም አይችሉም፡፡ ጥያቄ አለን የሚሉ ማናቸውም ወገኖች ተደማጭነት የሚኖራቸው፣ ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ ሲሰጡ ብቻ ነው፡፡ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ምላሾች ቢዘገዩ  እንኳን ትዕግሥት ሊኖር ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ የአገርንና የሕዝብን ሰላም የሚያናጉና ወደ በለጠ ቀውስ የሚወስዱ ዕርምጃዎች፣ ከውጤታቸው ይልቅ ጥፋታቸው የገዘፈ ይሆናል፡፡ በዚህ በኩል የመንግሥት አስፈጻሚዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ይመለከተናል የሚሉ የማኅበረሰቦች ተወካዮች ኃላፊነት ከበድ ማለት አለበት፡፡ እርግጥ ነው ከተለያዩ ድርጊቶች ማስተዋል እንደተቻለው፣ ከኋላ ሆነው በሥውር የሚገፉ ኃይሎች ሚና ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህን ኃይሎች አንጥሮ ማውጣት የሚገባው ደግሞ ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝብ ሰላሙ እየተናጋ የአገሩ ህልውና ችግር ሲገጥመው፣ እጁን አጣጥፎ ማየት የለበትም፡፡ ይልቁንም ሕግ ተከብሮ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲፈቱ መጠንከር ይኖርበታል፡፡ አንዱ መፍትሔ ይኼ ነው፡፡

በሐዋሳና በአካባቢው ከተሞች የፀጥታ ችግር ተፈጥሮ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ የሚያመላክተው፣ በሕግ አግባብ መፈታት ያለበትን ችግር  ችላ ማለት  ወይም ደንታ ቢስነት ነው፡፡ ክልል የመሆንን ጥያቄ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መንገድ መፍታት ከተቻለ፣ ‹‹ሱሪ በአንገት. . .›› ብሎ አገር መበጥበጥ ምን ማለት ነው?  ለቀረበው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ አይሆንም የሚል አይደለም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ በዝርዝር ተመላክቶ ሒደቱ በቅደም ተከተል ይከናወን ከተባለ፣ ሰከን ብሎ አፈጻጸሙን ከመከታተል ባለፈ ማገዝ ነው የሚገባው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን በርካታ ውስብስብ ችግሮች ባሉባት አገር ውስጥ የአመፃ መንገድ እየበረታ ነው፡፡ ለአገሩ ክብርና ፍቅር ያለው ማንም ሰው እንዲህ ዓይነቱን የቀውስ ጎዳና አይመኝም፡፡ አገር የእያንዳንዱን ዜጋ አስተዋጽኦ ለዕድገቷ ስትፈልግና አለሁልሽ ስትባል፣ ጉዞዋ ወደ ዴሞክራሲና ብልፅግና ይሆናል፡፡ ለአገር ዕድገት አንዲት ጠጠር ለማቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሲበዙ ደግሞ፣ ጉዞዋ ወደ እንጦሮጦስ እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ከአገር በላይ ራሳቸውን ያስቀደሙ ራስ ወዳዶች እየበዙ ነው፡፡ ችግር ከማስወገድ ይልቅ ችግር መፈልፈል ይወዳሉ፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ችግሮች በተባበረ መፍትሔ ይፈቱ ነበር፡፡ ፈቃደኝነት ካለ የማይፈታ ችግር የለም፡፡

አስተዋዮቹ ኢትዮጵያውያን የዘመኑ ዓይነት ሸፍጥ ሲያስቸግራቸው፣ ‹‹ተሸፋፍነው ቢተኙ ገላልጦ የሚያይ አምላክ አለ፤›› ይሉ ነበር፡፡ ዛሬም በሴረኞችና በሸፍጠኞች ደባ በቀላሉ የሚፈቱ ችግሮች እየተወሳሰቡ ነው፡፡ ይህንን በትኩረት መከታተል ያስፈልጋል፡፡ ከአንዱ ቀውስ ለመውጣት ጥረት ሲደረግ በአቋራጭ ሌላ ቀውስ ይከተላል፡፡ አንዱ ችግር ታለፈ ሲባል ሌላው ይደቀናል፡፡ ከሸፍጠኞች ጋር የሚያብሩ ምሁራን ተብዬዎች፣ አሳሳች ባለሽበቶችና ቤተ እምነቶች ውስጥ የመሸጉ የቀበሮ ባህታውያን ችግሮችን ያባብሳሉ፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ የተዛቡ መረጃዎችን እያሠራጩ ወጣቶችን በደም ፍላት ያነሳሳሉ፡፡ ከዚህ ማን ያተርፋል ሲባል መልሱ የግጭት ነጋዴዎች ናቸው ይሆናል፡፡ የአገር ጉዳይ ወደ ጎን እየተባለ የግለሰቦችና የቡድኖች ፍላጎት ሲቀድም፣ አይሆንም የሚል ተቆጪ ሲጠፋና ሕገወጥነት የበላይነቱን ሲይዝ ሥርዓተ አልበኝነት ይነግሣል፡፡ ሕጋዊ መንገዶችን አሟጦ ለመጠቀም ሲቻል የነውጥ መንገድ መምረጥ ሌላ ዓላማ እንዳለው ያሳብቃል፡፡ ከቀረበው ጥያቄ ጎን ለጎን በሰዎች ላይ ጥቃት በመፈጸምና ንብረት በማውደም ሥጋት መፍጠር አንዱ ነው፡፡ ይህ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ መፍትሔ በዚህ መንገድም አይገኝም፡፡ መፍትሔ የሚገኘው በሰከነ መንገድ በመነጋገር ብቻ ነው፡፡

አሁንም ጊዜ አለ፡፡ ጥያቄ አለን የሚሉ በሰከነ መንገድ ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ፣ ምላጭ ሰጪዎችም በተቻለ ፍጥነት እየተንቀሳቀሱ በትኩረት እንዲሠሩ መግባባት ላይ መድረስ የግድ ይሆናል፡፡ በዚህ መንገድ መተባበር ከተቻለ ለሴረኞች ክፍተት መስጠት አይቻልም፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ግን ለአገር የሚበጅ አይደለም፡፡ የሰው ሕይወትና የአገር አንጡራ ሀብት ለአደጋ ተጋልጦ የሚፈለገው ውጤት አይገኝም፡፡ ውጤት ለሌለው ነገር መተራመስ የሚፈይደው ለሴረኞች ብቻ ነው፡፡ ሴረኞችን ከጨዋታው መሀል በጥበብ በማውጣት ዓላማን ማሳከት ሰላማዊ መፍትሔ ለማግኘት ይረዳል፡፡ ነውጥ የመፍትሔ አካል ሊሆን አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ችግር መደራረብ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው፡፡ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ለአገር እናስባለን የምትሉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች የኢትዮጵያን መከራ ለመቀነስ ተረባረቡ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ አስመራሪ የሆነ የድህነት ሕይወት እየገፋ፣ ይህ አልበቃ ብሎ ለሌላ መከራ መዳረግ ይብቃ፡፡ ጥያቄዎች በሥርዓት ቀርበው በሥርዓት እንዲፈቱ የአገር ጉዳይ ያገባናል የምትሉ በሙሉ ሐሳብ አዋጡ፡፡ ይህንን ማድረግ ሳይቻል አገርን ቀውስ ውስጥ መክተት በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ግን ከቀውስ ውስጥ ለመውጣት መፍትሔው ቅርብ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ አሁን እየታየ ያለው ደንታ ቢስነት አገሪቱንና ሕዝቡን የበለጠ ዋጋ ያስከፍላል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...

የአገሪቱን የፖለቲካ ዕብደት ለማርገብ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሚና ምን ይሁን?

በያሲን ባህሩ   የኦሮሚያ ብልፅግና      በአገር ደረጃ የብሔር ፖለቲካ በሥራ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእንቆቅልሽ ጨዋታ ውስጥ ውጡ!

በወርኃ ሚያዝያ ተካሂዶ የነበረው ውይይት ቀጣይ ነው የተባለው መድረክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደገና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አገናኝቶ ነበር፡፡ መንግሥትን የሚመራው...

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...