Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጭነት ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው መመርያ እያወዛገበ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከባድ የጭነት ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በሰዓት የሚገድበው መመርያ እያወዛገበ ነው፡፡ መመርያው ወደ ውጭ የሚላኩና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በጊዜ ከወደብ ለማንሳትና ለማድረስ እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው፣ ሐሙስ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በኔክሰስ ሆቴል በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙ አንድ የጉምሩክ ኮሚሽን ባለሙያ ገልጸዋል፡፡ ተሽከርካሪዎቹ ምርቶችን በፍጥነት ማንሳት ካልቻሉ ወደብ ላይ የሚከፈለው ገንዘብ እንደሚጨምር፣ ይህም መመርያው ከሚያድነው የበለጠ ወጪ የሚያስወጣ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

መመርያው ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በሥራቸው ላይ ከባድ መስተጓጎል ካጋጠማቸው ተቋማት መካከል የቡናና ሻይ ባለሥልጣን አንዱ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ባለፈው በጀት ዓመት 2.4 ሚሊዮን ኩንታል ቡና ወደ ውጭ ልኮ 800 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቶ እንደነበር ያስታወሱት የንግድ መረጃና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ኑሩ፣ ከባድ የውጭ ምንዛሪ ችግር ላለባት አገር ይህንን ያህል ገቢ የሚያስገኝን ዘርፍ በመደገፍ ፋንታ፣ እንቅስቃሴውን ወደ ኋላ የሚስብ አሠራር መዘርጋት በመሆኑ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

 ቡና የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ከተማው ለመግባት ፈረቃችሁን ጠብቁ ተብሎ መግቢያ ላይ እንዲቆሙ የሚደረግበት አግባብ መኖሩ፣ በቡና ወጪ ንግድ ላይ መስተጓጎል እየፈጠረ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ መመርያው ተግባራዊ በተደረገ በአንድ ሳምንት ውስጥ የቡና የወጪ ንግድ በግማሽ መቀነሱን ተናግረዋል፡፡

በአርሶ አደሩ እጅ የሚገኘውን የቡና ምርት በአግባቡ ተቀብሎ ለገበያ ማቅረብ ላይ ካሳደረው ተፅዕኖ ባሻገር መግቢያ ላይ ያለውን መጉላላት ሽሽት አሽከርካሪዎች ቡና አንጭንም ማለት እንደጀመሩ፣ የቡና ላኪዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ገልጸዋል፡፡ አሠራሩ በዚህ የሚቀጥል ከሆነም ምርት ጊዜውን ጠብቆ ለመላክ እንደሚቸገሩ፣ የቡና ምርት ስድስት ወራት ካለፈው ጥራቱ እንደሚቀንስና ተፈላጊነቱም በዚያው መጠን እንደሚወርድ በመግለጽ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ከ200 የሚበልጡ የመስክ ተሽከርካሪዎችን አሰማርቶ ለተለያዩ አፋጣኝ ምላሽ ለሚያስፈልጋቸው የጥገናና የፍሳሽ መምጠጥ አገልግሎት የሚሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣንም፣ የከባድ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ በፈረቃ ባደረገው መመርያ ምክንያት እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት መቸገሩን አሳውቋል፡፡ ባለሥልጣኑ የከተማው ነዋሪ በሚፈልገው መጠን አገልግሎቱን ለማቅረብ የተደራሽነት ችግር እያለበት፣ የተሽከርካሪዎቹን እንቅስቃሴ በሰዓት የሚገድበው መመርያው ሌላ ፈተና እንደሆነበት ተወካዩ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በፊት በቀን 800 ባለጉዳዮችን ያስተናግድ እንደነበር፣ መመርያው ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ግን በቀን ከ100 በላይ ባለጉዳዮች ማስተናገድ እንደማይችል አክለው ገልጸዋል፡፡

ስልሳ በሚጠጉ ከባድ ተሽከርካሪዎች 1,000 የቁም እንስሳትን በየቀኑ እየበለተ ለልኳንዳዎች፣ ለሱፐር ማርኬቶችና ለሆቴሎች የሚያከፋፍለው የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅትም በቀን በሦስት ፈረቃ (ሌሊትን ጨምሮ) እየሠራም የሥጋ ምርት በሚፈለገው መጠን ማቅረብ እንዳልቻለ፣ በዚህ ላይ መመርያው ሲታከልበት ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ከመሥራት እንዳገደው አስታውቋል፡፡ አጋጣሚው ሕገወጥ ዕርድ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ እንዲስፋፋ ማድረጉን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

መመርያው የከተማዋን የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ ሒደትም እያደናቀፈ እንደሚገኝ የደረቅ ቆሻሻ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሃይማኖት ዘለቀ ተናግረዋል፡፡ በከተማዋ በየቀኑ 3,200 ቶን ቀሻሻ እንደሚመነጭ፣ ቆሻሻውን ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት በተለያዩ ፈተናዎች የታጠረ እንደሆነ፣ የተሽከርካሪዎቹን እንቅስቃሴ በፈረቃ ያደረገው መመርያው ሲታከልበት ደግሞ ተግባሩን ለማከናወን ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ እንደተቸገረ አስረድተዋል፡፡

የቆሻሻ ጉዳይ ከጤና ጋር በቀጥታ ይያያዛል በማለት ወ/ሮ ሃይማኖት መመርያው መውጣቱ ጠቃሚ ቢሆንም፣ በቆሻሻ አሰባሰብ ሒደቱ ላይ የሚያሳድረው ጫና ያልታሰበ የጤና ችግር እንዳይፈጥር እንደሚሠጉ ገልጸዋል፡፡ ከሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ወዲህ ተግባራዊ የተደረገው መመርያው በወተት አቀናባሪ ተቋማትና በሌሎችም ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን መደቀኑ ተነግሯል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ በከተማው የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓታት ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅና አደጋ ለመቀነስ፣ ተሽከርካሪዎች በተቀላጠፈና የሎጂስቲክ ወጪን በሚቀንስ መንገድ መሥራት ያስችላቸዋል የተባለውን መመርያ፣ ከሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ሲያደርግ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቂ ምክክር አለመደረጉንም ተሳታፊዎች ኮንነዋል፡፡

በምክትል ከንቲባው ማዕረግ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከባለድርሻ አካላት የተነሱ ጉዳዮች የየተቋማቱን ቁርጠኝነት የሚጠይቁ እንጂ የመመርያው ክፍተት እንዳልሆኑ አስረድተዋል፡፡ መመርያው በሚያዘው መሠረት ሥራቸውን ለማቀላጠፍ ተቋማት ሌሊትም ጭምር መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

በሌሊት የሚደረገው እንቅስቃሴ የትራፊክ ፍሰቱን ከማሳለጥ ባለፈ ከተማዋ ነፍስ እንድትዘራና ለወጣቱ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር በመግለጽ፣ በፈረቃ የተደረገው የከባድ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ጊዜን በአግባቡ በመቀጠም የሚፈታ እንጂ መመርያውን በማንሳት የሚታረም አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በልዩ ጉዳይ የሚታዩ አፋጣኝ ምላሽ የሚያሻቸው ጉዳዮችን በተመለከተ ግን፣ መመርያው በሚፈቅደው መጠን በመነጋገር መፍትሔ እንደሚያገኙ አብራርተዋል፡፡

መመርያው ቀላል የጭነት ተሽከርካሪዎች ከጠዋቱ 12፡30 እስከ 4፡00 ሰዓት፣ እንዲሁም ከቀትር በኋላ ከቀኑ 10፡00 እስከ ምሽት 2፡00 ሰዓት፣ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከማለዳው 12፡30 እስከ ምሽቱ 2፡00 ሰዓት ወደ ከተማ እንዳይገቡ፣ እንዳይንቀሳቀሱ ያዛል፡፡ የኮንስትራክሽን ተሽከርካሪዎችም ከተማ መግባት፣ ጭነት ማራገፍና መጫን የሚችሉት ከምሽት 2፡00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12፡30 ሰዓት እንደሚሆን መመርያው ያስገድዳል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የተመዘገቡ 130 ሺሕ ገደማ 25 ኩንታልና ከዚያ በላይ የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች