Thursday, February 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢዜማ በሲዳማ ዞን የተፈጸመውን ጥቃት አሳፋሪና አሳዛኝ በማለት አወገዘ

ኢዜማ በሲዳማ ዞን የተፈጸመውን ጥቃት አሳፋሪና አሳዛኝ በማለት አወገዘ

ቀን:

ከቀናት በፊት በደቡብ ክልል ከሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች በሚኖሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ እጅግ አሳዛኝ ጉዳት መድረሱ፣ የዜጎች ሕይወት መጥፋቱ፣ በርካታ ንብረት መውደሙ፣ የቤተ እምነቶች መቃጠል፣ እንዲሁም ከጥያቄው ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው ሰላማዊ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የደረሰው ጉዳት አሳዛኝና አሳፋሪ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ገለጸ፡፡

ኢዜማ ይህን አቋሙን ያስታወቀው ማክሰኞ ሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. በቀድሞው የኢትጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ጽሕፈት ቤት፣ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

ከቀናት በፊት ከሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ክስተት አሳዛኝና አሳፋሪ ብሎ ከመግለጽ በተጨማሪ፣ ‹‹እንደ አገር የደረስንበትን አስከፊ ደረጃ የሚጠቁም ነው፤›› ሲል ፓርቲው አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ይህ ጉዳት ከመድረሱ በፊት አደጋ እንዳለ በቂ ምልክቶች የታዩ ቢሆንም፣ ኢመደበኛ በሆኑ ቡድኖች በዜጎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ግፊት ያደረጉ የፖለቲካ ኃይሎች ለደረሰው መጠነ ሰፊ ጉዳት ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል፤›› ብሎ እንደሚያምን ኢዜማ አቋሙን አስታውቋል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ እየታዩ ላሉ የፖለቲካ ውጥንቅጦች ሁሉ መነሻ በተወሰነ ደረጃ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት መሆኑን፣ የአገሪቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በዘላቂነት የሚፈቱት በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ አሉ የሚባሉ ችግሮች ሲሻሻሉ እንደሆነ እምነቱን እንደሆነ ገልጾ፣ ‹‹ነገር ግን አሁን አገሪቱ ውስጥ ባለው ያለመረጋጋት ሁኔታና በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሕዝብ ወኪሎች በሌሉበት፣ በሕገ መንግሥቱ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን በሰከነና በሠለጠነ መንገድ ችግሮችን መፍታት ይቻላል ብለን አናምንም፤›› በማለት፣ ከሁሉም በፊት ሰላምና መረጋጋት ይሰፍን ዘንድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

በመሆኑም መንግሥት አሁን በሲዳማ ዞንም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለተፈጠሩ ችግሮች አፋጣኝ ፖለቲካዊና ሕጋዊ ዕርምጃ በመውሰድ፣ በዚህ ጥፋት እጃቸው ያለበትን አካላት ሁሉ የሕግ አግባቡን በመከተል በተገቢው አካላት በማጣራት ለፍርድ እንዲያቀርብና ውጤቱንም ለሕዝብ እንዲያሳውቅ ሲል ጥያቄውን አቅርቧል፡፡

‹‹በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ መንግሥት የፀጥታ መዋቅሩን በማጠናከር ዜጎችን ከጥቃት የመከላከል ኃላፊነቱን ይወጣ፤›› በማለት ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ የማንነትና የክልልነት ጥያቄዎችን የሚያቀርቡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄ የማቅረብ መብት እንዳላቸው የሚያምን መሆኑን የጠቆሙት ኢዜማ፣ ‹‹ይሁን እንጂ በክልል ከሚቀርቡ ጥያቄዎች ጋር ተዛማጅነት በሌለው ሁኔታ የሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዳይጣሱ፣ ሕዝቡ የማናቸውንም ቡድኖች ሕገወጥ ድርጊቶች እንዲከላከልና አጥፊዎችን ለሕግ አሳልፎ በመስጠት የዜግነት ድርሻውን ይወጣ፤›› ሲልም ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ፖለቲካዊ ክስተቶችና ግጭቶች ጋር ተያይዞ በወንጀል ተጠርጥረው የሚታሰሩ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ፓርቲው መታዘቡን በመግለጽ፣ ‹‹አልፎ አልፎ የኢዜማ አባላትም የእስሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ሕግን ለማስከበር በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ሕግ ፊት መቅረባቸው ተገቢ መሆኑን ብናምንም፣ ተጠርጣሪዎች ከመታሰራቸው በፊት ለእስር የሚያበቃ በቂ ምክንያት መኖሩ መረጋገጥ አለበት፤›› በማለት አሳስቧል፡፡

ኢዜማ ከሁለት ወር ከግማሽ በፊት የተመሠረተ ፓርቲ ነው፡፡ ራሳቸውን በማክሰም ፓርቲውን የመሠረቱት ደግሞ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ)፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት (አግ 7)፣ ሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ)፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ)፣ የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ፣ አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ (አንድነት) ፓርቲ ሲሆኑ፣ ከሳምንት በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ተቀላቅሎታል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...