Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአዲሱ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ሕገወጦችን ያለ ምሕረት ታግለው እንደሚያስተካክሉ ቃል ገቡ

አዲሱ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ሕገወጦችን ያለ ምሕረት ታግለው እንደሚያስተካክሉ ቃል ገቡ

ቀን:

የአመራሮቹ ግድያ ‹‹መፈንቅለ መንግሥት›› የሚመስል ነገር የለውም ተባለ

የአማራ ክልልን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች በተገደሉ በ30ኛው ቀን ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ አላስፈላጊ ንግሥና የተሰጣቸውን ሕገወጦች ከሕዝቡ ጋር በመሆን ያለ ምሕረት ታግለው እንደሚያስተካክሏቸው ቃል ገቡ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በበዓለ ሲመታቸው የእራት ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹የክልሉ መንግሥት በክልሉ የተፈጠሩ የሰላም ሥጋቶችን በአፋጣኝ ለማረም ዝግጁ ነው፡፡ የተፈጠሩ የሰላም ሥጋቶችን ለማረምና ለማስተካከል ሕዝቡ ተባባሪ ከሆነ፣ አላስፈላጊ ንግሥና የተሰጣቸው ሕገወጦች ሕጋዊ መስመር ይይዛሉ ወይም ታግለን እናስተካክላለን፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሕዝቡ እንደ ጀግና የሚያያቸውና እያሳሳቁ የሚወስዱት ሰዎችን በሚመለከት አንድ አገራዊ አባባል እንዳለና ለታዳሚዎች ቢያካፍሉ እንደሚወዱ የተናገሩት አቶ ተመስገን፣ ‹‹ዛፎች ብዙ ጊዜ ሲቆረጡ ምሳርን (መጥረቢያን) ያማሉ፡፡ ከዛፎች አንዱ፣ ምሳርስ ምን ይበል የብረቶች ልጅ፣ ያ የእኛ ወልጋዳ አስጨረሰን እንጂ፤›› የሚለውን ብሂል ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ በየአካባቢው ያሉትን ወልጋዳዎች ማስተካከል ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ የክልሉን ሰላም በአስቸኳይ በመመለስ አንገብጋቢ ወደ ሆነው የልማት ጉዞ መግባት ግድ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ትግል ተሸጋጋሪ መሆኑንና በየጊዜው አዳዲስ ነገር እንደሚመጣና እንደሚሄድ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በክልሉ ላይ የተደቀነው አደጋ ቀላል ባይሆንም፣ ‹‹ግን እንሻገረዋለን›› ብለዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ በልማቱ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው፣ ዳቦ የሆነ መሬት ይዞና የጣናና የዓባይ መነሻ ሆኖ ራሱም መራብ ሌሎችንም ማስራብ እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ አቃፊ መሆኑን የገለጹት አቶ ተመስገን በየትኛውም ቦታና አካባቢ ኢትዮጵያን እንደሚወድ፣ ሕዝቧን እንደሚወድና እንደሚያከብር፣ እንዲሁም ለአንድነቷ የሚሞት መሆኑን ጠቁመው፣ የሌላውም አካባቢ ሕዝብ እንዲሁ ተመሳሳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹እኛ መሪዎች ከተዋደድን ሕዝቡም ይዋደዳል፡፡ እኛ ከተገፋፋን ሕዝቡም ይገፋፋል፡፡ እኛ ስንፋቀርና ስንዋደድ የትኛውም ቦታ ችግር ቢፈጠር መፍታት እንችላለን፤›› ያሉት አቶ ተመስገን፣ ‹‹እኛ ስለተዋደድን ብቻ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ ታች ቀበሌ ድረስ ወርደን እያንዳንዱን አመራር፣ በተለይም ችግር የሚፈጥርና የአክራሪ ብሔርተኝነት ሸለፈት ውስጥ ገብቶ ሕዝባችንን ለከፋ ሥቃይና ለአደጋ የሚዳርገውን ስንመነጥር ነው፣ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያን መገንባት የምንችለው፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የአማራ ክልል ምክር ቤት አምስተኛ ዙር አራተኛ ዓመት 13ኛ መደበኛ ጉባዔውን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ያደረገ ሲሆን፣ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ በተደረገው ግድያ ‹‹መፈንቅለ መንግሥት›› የሚመስል ነገር እንደሌለ የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል፡፡

ሰዎች ተለይተው መገደላቸውንና ግድያውን ማድበስበስ ስለማያዋጣና ቢተውም ስለማይተው፣ ሴራውን የፈጸመውን ለማውገዝና ከድርጊቱ ለመማር በግልጽ መነጋገር እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡ ‹‹በሽታውን ያልተናገረ መድኃኒት አይገኝለትም›› የሚለውን ብሂል በመጥቀስ፣ የሰኔ 15 ግድያን ሴራ ለይቶ አውጥቶ መታገል እንደሚያስፈልግ አባላቱ አክለዋል፡፡

አመራሮቹ የድርጊቱን አፈጻጸም መግለጽ እንደቻሉት ሁሉ የችግሩን ሴራ ለይቶ ለሕዝቡ ፍላጎቶች ምላሽ መስጠት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸውም፣ የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ እንደ አገር እያሰበ እንደ ክልል መሞት እንደሌለበትና በሕዝቡ ላይ ያነጣጠረ ሴራ ካለ የክልሉ መንግሥት አስቸኳይ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል፡፡ ሕግ ባለመከበሩ የክልሉ ሕዝብ አንድነት እንዲላላ በር መክፈቱንም ጠቁመዋል፡፡ ሕዝቡ ሕግ ለማስከበር ከመንግሥት ጎን እንዲቆም እየገለጸ፣ መንግሥት ግን ቸልተኛ በመሆኑ የፀጥታ መደፍረስ እንዲባባስ ማድረጉንም አባላቱ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ በተለያዩ ክልሎች እየተገፉ በመሆናቸው፣ የክልሉ መንግሥት ያለውን ሴራ በጥንቃቄ ዓይቶና ለይቶ መፍትሔ መስጠት እንዳለበትም የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል፡፡

የምክር ቤቶች ውሳኔዎችም ተሿሚዎች ማስፈጸም ባለመቻላቸው ወይም ባለመፈለጋቸው፣ ወይም በአቅም ችግር ምክንያት ችግሮች እየተፈጠሩ መሆኑን አክለዋል፡፡ መንግሥት ለሕዝቡ ሰላም ፀር የሆነውን ሴራ ከመበጠስ ይልቅ፣ በየጊዜው ‹‹እየሠራን ነው›› በማለት ብቻ በማለፉ፣ የዜጎች ሞት እንዲቀጥልና የመብት ጥሰቶች እንዲበራቱ ማድረጉንም አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት አሁን ለተደረሰበት ቀውስ ያበቃው በመርህና በሕግ ከመመራት ይልቅ፣ በማኅበራዊ ድረ ገጾች እየተመራ በመሆኑ አዴፓም ፈተና ውስጥ እንደሆነ አባላቱ ጠቁመዋል፡፡ የሰኔ 15 ቀን የአመራሮች ግድያን የማጣራት ተግባር የክልሉ መንግሥት በአግባቡ ትኩረት ሰጥቶ መምራት እንዳለበትም የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...