Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየኢራንና እንግሊዝ ውዝግብ

የኢራንና እንግሊዝ ውዝግብ

ቀን:

ኢራን ከአሜሪካ ጋር የገባችውን ውዝግብ ሳትፈታ፣ በኢራንና በአሜሪካ መካከል ያለውን ፍጥጫ ለመፍታት ከሚሠሩ አገሮች አንዷ ከሆነችው እንግሊዝ ጋር ተወዛግባለች፡፡

ኢራንና እንግሊዝን ለውዝግብ ያበቃቸው እንግሊዝ ከሁለት ሳምንት በፊት የኢራንን ነዳጅ ጫኝ መርከብ ማሰሯና ለዚሁ የአፀፋ ምት በሚመስል መልኩ ኢራን የእንግሊዝ ባንዲራን የሚያውለበልብ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ከአራት ቀን በፊት ማገቷ ነው፡፡

እንግሊዝ ከሁለት ሳምንት በፊት የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከብን ከጅብራታል ደሴት አቅራቢያ ያሰረችው፣ የኢራንን ነዳጅ የጫነ መርከብ የአውሮፓ ኅብረት በሶሪያ ላይ የጣለውን ገደብ በመተላለፍ ለሶሪያ ነዳጅ ዘይት ጭኖ እየሄደ ነው በሚል ጥርጣሬ ሲሆን፣ ኢራን ደግሞ የእንግሊዝን ነዳጅ ጫኝ መርከብ ያገትኩት መርከቧ ዓለም አቀፍ የባህር ሕግን በሚጥስ መልኩ ስትንቀሳቀስ ነው ማለቷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ኢራን የእንግሊዝን መርከብ ያገተችው በኦማን አካባቢ እንደሆነ፣ መርከቡም በግዳጅ በኢራን ባንዳር አባስ ወደብ እንዲጓዝ መደረጉን እንግሊዝ ስትገልጽ፣ ኢራን በበኩሏ፣ የኢራንን ነዳጅ የጫነው መርከብ ወደ ሶሪያ እያመራ እንዳልነበረና ድርጊቱ የእንግሊዝን የባህር ላይ ዝርፊያ የሚያሳይ መሆኑን አሳውቃለች፡፡

እንግሊዝና ኢራን በሁለቱ መርከቦች ምክንያት ያልተጠበቀ ውዝግብ ውስጥ ከገቡ በኋላ በኢራን አብዮታዊ ዘብ የታገተችውን ሴንታ ኢምፒሮ የምትባለውና የእንግሊዝ ባንዲራ የምታውለበልብ መርከብ ከነ 23 ሠራተኞቿ የኢራን መንግሥት ሚዲያ በምስል አስደግፎ ለቋል፡፡

አሜሪካና ኢራን በኑክሌር ውዝግብ በጦዙበት ወቅት የእንግሊዝ ከኢራን መቃረን እንግሊዝና አሜሪካ ተጣምረው በኢራን ላይ ሊዘምቱ ነው የሚል መላምት እንዲሰነዘር ምክንያት ቢሆንም፣ እንግሊዝ በኢራን ላይ ምንም ዓይነት፣ ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ዓላማ እንደሌላት፣ ይልቁንም ውጥረቱን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት እንደምትፈልግ አሳውቃለች፡፡

​​የኢራንና እንግሊዝ ውዝግብ

 

ኢራንና አሜሪካ የገቡበትን ፍጥጫ ለማርገብ እንደምትሠራ እንግሊዝ አሳውቃ፣ የአውሮፓ ኅብረት በኢራን የተያዘውንና የእንግሊዝን ባንዲራ የሚያውለበልበውን ነዳጅ ጫኝ መርከብ ኢራን እንድትለቅ እንዲተባበራቸው ጥሪ አቅርባለች፡፡

የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ሃንት የኢራንን ዕርምጃ በእንግሊዝ ላይ የተቃጣ የመርከብ ላይ ዘረፋ ነው ብለው፣ እንግሊዝ ከሌሎች የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ጋር በመተባበር የመርከቦች ደኅንነትን የሚጠብቅ የባህር ጥበቃ ቡድን እንደሚያቋቁሙ ተናግረዋል፡፡

ጀርመንና ፈረንሳይ የባህር ጥበቃ ቡድንን ለማቋቋም እንግሊዝ ያነሳችውን ሐሳብ የሚደግፉ መሆኑን ሲገልጹ፣ ሃንት በበኩላቸው ኢራን በዚሁ ፀባይዋ የምትቀጥል ከሆነ ከፍተኛ አቅም ያለው የምዕራባውያን መከላከያ ሠራዊት በመርከብ መጓጓዣ የባህር ክፍሉ ላይ ጥበቃ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

የመርከቧ ባለቤትም ሆነ በውስጡ የነበሩት ሠራተኞች እንግሊዛውያን ባይሆኑም፣ የእንግሊዝን ባንዲራ የምታውለበልበውን መርከብ ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት እንግሊዝ እንዳለባት የማሪታይም ፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

ኢራን የአውሮፓ ኅብረት በሶሪያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ በመተላለፍ ነዳጅ የጫነ መርከብ ወደሥፍራው እየላከች ነበር በሚል እንግሊዝ የኢራንን ነዳጅ ጫኝ መርከብ ከያዘች ወዲህ፣ በኢራን እንዲሁም እንግሊዝና አሜሪካ መካከል ውጥረት ሰፍኗል ተብሏል፡፡

‹‹የባህር ላይ ትራንስፖርት ነፃነት የሁሉም ሕዝቦች ፍላጎት ነው›› ያሉት ሚስተር ሃንት፣ በአውሮፓ ኅብረት የሚመራ የባህር ጠባቂ ዘብ የሚያስፈልግ መሆኑን አስረግጠዋል፡፡

የእንግሊዝ ጥበቃ ሚሽን አሜሪካን እንደማያካትት፣ ለዚህም ምክንያቱ ብሪታኒያ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚከተሉት ‹‹ከፍተኛ ጫና›› የመፍጠር ፖሊሲ እንደማትከተል አሳውቀዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም እንግሊዝ በኢራንና አሜሪካ መካከል እ.ኤ.አ. በ2015 የተደረሰው የኑክሌር ስምምነት እንዳይፈርስ የምትሠራ መሆኑን መናገራቸውን ኒውዮርክ ታይምስ አስፍሯል፡፡

እንግሊዝ ምንም እንኳን ባንዲራዋ የሚውለበለብበትን መርከብ ለማስለቀቅ እየሠራች ቢሆንም፣ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ወግና አተካራ የማትገባ መሆኑን፣ የማሪታይም ጥበቃውን በገልፍ ለማጠናከር የምትሠራ ቢሆንም የአሜሪካ ፖሊሲ አካል አለመሆኑን፣ ሚስተር ሃንት በተያዘው መርከብ ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ አሳውቀዋል፡፡

አሜሪካ ከዚህ ቀደም ከተለያዩ  አገሮች የተውጣጡ የማሪታይም ደኅንነት አካላት በገልፍ እንደምታሰፍር ያሳወቀች ቢሆንም፣ እንግሊዝ ከምዕራባውያን ጋር ለማዋቀር የፈለገችውን የማሪታይም ደኅንነት ሚሽን እንዴት ከአሜካ ምክረ ሐሳብ ጋር አጣጥማ እንደምትቀጥል ከአሜሪካ ጋር እንደምትወያይ ሚስተር ሃንት ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...