Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሜሪ ጆይ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ወገኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ነው

ሜሪ ጆይ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ወገኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ነው

ቀን:

ሜሪ ጆይ የልማት ማኅበር ባለፉት 25 ዓመታት 322 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ 1.6 ሚሊዮን ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የኢኮኖሚና የልዩ ልዩ ማኅበራዊ ፕሮግራሞች ተጠቃሚ አደረገ፡፡ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ደግሞ የፕሮግራሞቹን ተደራሽነት አሁን ካለበት ወደ 58  በመቶ የማሳደግ ዕቅድ ይዟል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን 349,486,463 ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የማኅበሩን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል አስመልክቶ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ የልማት ማኅበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይስማሸዋ ሥዩም ማኅበሩ እስካሁን የአቅም ግንባታና የኑሮ ማሻሻያ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት የማስፋፋት ፕሮግራሞች ላይ እንደሠራ ገልጸዋል፡፡

ፕሮግራሞቹም ተፈጻሚ የሚሆኑት በአዲስ አበባ ስድስት ክፍላተ ከተሞች፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ 112 ወረዳዎች ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትና ወላጆች፣ አቅመ ደካማ አረጋውያን፣ ሴቶችና ወጣቶች፣ የኤችአይቪ ሕሙማን መሆናቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

እነዚህን የኅብረተሰቡን ክፍሎች ለመርዳት ማኅበሩ በአዲስ አበባና በሐዋሳ ከተማ ሦስት የሕክምና ማዕከላት እንዲገነባ፣ እንዲሁም ሴቶች የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ሕክምናና እንክብካቤ እንዲያገኙ፣ ከዚህም ሌላ በአዲስ አበባና በደቡብ ክልል 15,456 ወጣቶች ሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርት ሥልጠናና አገልግሎት እንዳደራጁ፣ መሆናቸው፣ እንዲሁም በ450 የራስ አገዝ ቁጠባ ቡድኖች የተደራጁ 13,200 እናቶች 16.6 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንዲፈጥሩ ማገዙን፣ በሐዋሳ ለ100 አረጋውያን አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው አረጋውያን ማዕከል በ20 ሚሊዮን ብር መገንባትና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጨምረው አብራርተዋል፡፡

እንደ ሰብሳቢው ማብራሪያ በቀጣይ አምስት ዓመታት ማኅበሩ የሚንቀሳቀስባቸውን ክልሎች ወደ አምስት፣ አገልግሎቱን ደግሞ ወደ 58 በመቶ የማሳደግ ዕቅድ አለው፡፡ ለዕቅዱም  ተግባራዊነት ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ 52 በመቶ ከአገር ውስጥ የቀረውን 48 በመቶ ደግሞ ከውጭ ለጋሽ ድርጅቶች ለመሰብሰብ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡

የሜሪ ጆይ የልማት ማኅበር መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ፣ የልማት ማኅበሩ በ122 ወረዳዎች ውስጥ በሚያካሂደው እንቅስቃሴ ከ4000 በላይ በጎ ፈቃደኛ ዜጎችን እንደሚያስተባብር ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ላካሄዳቸው የልማት ፕሮግራሞች ወጪ ውስጥ 37 ከመቶ ያህሉን የሰበሰበው ከአገር ውስጥ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

ከነሐሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ ጥር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ‹‹25 የበጎ ሥራ ዓመታትና የነገ ብሩህ ተስፋ›› በሚል መሪ ቃል በሚከበረው በዚሁ የምሥረታ በዓሉ የእግር ጉዞ፣ የእግር ኳስ ውድድር፣ ልዩ ልዩ ኩነት፣ ዘጋቢ ፊልምና ገቢ ማስገኛ እንደሚዘጋጁ አስረድተዋል፡፡

ሜሪ ጆይ የልማት ማኅበር ከአሜሪካ ኤምባሲና ዩኤስኤ ትሪክል አፕ ከተሰኘ ድርጅት በተገኘ 41,625 ብር ድጋፍ በ1986 ዓ.ም. ተቋቁሞ ሥራ እንደጀመረ ከሲስተር ዘቢደር ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...