Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የትምህርት ጥራት ከሙአለ ሕፃናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ለማቅናት የሰነቀው ተቋም

ዋና ሊቃ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ምርምር ተቋም አባል ናቸው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በወላይታ ሶዶ ከተማ፣ የዘጠነኛና አሥረኛ ክፍል ትምህርታቸውን ደግሞ በይርጋዓለም አጠናቀዋል፡፡ ደብረብርሃን መምህራን ማሠልጠኛ ገብተው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመት ያህል ቴክኒካል ቲቸርስ ኢዱኬሽን ትምህርት ከተከታተሉ በኋላ ወደ አሜሪካ አቅንተው ኤሊኖስ ዩኒቨርሲቲ በኦኩፔሽናል ኢዱኬሽን (ቴክኒክና ሙያ) ለሁለት ዓመት ተምረው፣ በቴክኒክና ሙያ በመጀመርያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በትምህርትና ሥልጠና የማስተርስና የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በሥራ ዓለምም እዛው አሜሪካ ካሊፎርኒያ በሚገኙ የተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ለአንድ ዓመት የምርምር ሥራ አከናውነዋል፡፡ በአገር ውስጥም በሶዶ ከተማና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት በዋና ሥራ አስኪያጅነት አገልግለዋል፡፡ ዋና ሊቃን (ዶ/ር) በቅድመ መደበኛ ትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና፣ በትምህርት ፍኖተ ካርታና ሌሎች ትምህርት ነክ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ቢገልጹልን?

ዶ/ር ዋና፡- ተቋሙ ከሙአለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ባሉ የትምህርት ጉዳዮች ያተኮሩ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ይዘት ያላቸው ተግባራት ያከናውናል፡፡ ከአገር አቀፍ ጉዳዮች መካከል የሥርዓተ ትምህርት፣ የማስተማር ዘዴዎች፣ የተማሪዎች ብቃትና አጠቃላይ የትምህርቱን አካሄድ በተመለከተ ምርምሮችን ያካሂዳል፡፡ ከትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተናዎችን ያዘጋጃል፣ ያስተባብራል፡፡ እንደየአመቺነቱ በየዓመቱ የትምህርት ኮንፈረንስ ያካሂዳል፡፡ የሕክምና ብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት የሚያስችል ፈተና እያዘጋጀ ይፈትናል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአድሚኒስትሬሽንና በአካውንቲንግ ሙያ ለሚቀጥራቸው ሰዎች የሚያዘጋጀውን የመግቢያ ፈተና በማማከር፣ በመፈተንና በማስተዳደር፣ አልፎ አልፎ ራሱ እያዘጋጀ በመፈተን ይንቀሳቀሳል፡፡ ዓለም አቀፍ ፈተናዎችንም በማስተዳደር ይሠራል፡፡ ከእነዚህም ፈተናዎች መካከል አንዱ ‹‹ስኮላርስቲክ አፕቲትዩድ ቴስት (ሳት) ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ቶፍል›› (ቲቺንግ ኢንግሊሽ ፎር ፎረን ላንጉጅ) ነው፡፡ ሳት እና ቶፍል ኢትዮጵያ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው አሜሪካ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ትምህርታቸውን ለመከታተል ለሚፈልጉ ወጣቶች የሚሰጥ ፈተና ነው፡፡ ከዚህም በስተቀር ዓለም አቀፍ ዕውቅና የሚቸረው ቻርተርድ አካውንታንት ለመሆን የሚያስችለውንም ፈተና የማስተዳደሩ ሥራ እንደተጠበቀ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተጠቀሱትን ፈተናዎች እንዴት ነው የሚያስተዳድረው?

ዶ/ር ዋና፡- የአስተዳደሩ ሥራ የሚካሄደው በልዩ ልዩ ዓይነት መንገድ ነው፡፡ መጀመርያ ፈተናው ታሽጎ ይቀርባል፣ ተፈታኞች ይመዘገባሉ፣ የፈተና  አዳራሽ ይዘጋጃል፡፡ ተፈታኞች ክፍያ እንዲፈጽሙና መታወቂያም እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡ በፈተናው ሒደት ላይ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ ፈተናውም ካበቃ በኋላ የጥያቄ ወረቀቱና መልሱ ተሰብስቦና ታሽጎ ወደ መጣበት ተቋም ይላካል፡፡

ሪፖርተር፡- ፈተናዎቹ ምን ያህል ጥብቅ ናቸው?

ዶ/ር ዋና፡- በኢንስቲትዩቱ ያሉት ሠራተኞች አብዛኞቹ ፒኤችዲ ያላቸው፣ በተለያዩ ቦታዎች የሠሩና ብዙ ልምድና ዕውቀት ያካበቱ ናቸው፡፡ በመሆኑም ፈተናዎች የመጥፋትና የመሰረቅ፣ የማጭበርበርና መዝረክረክ የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች ጭርሱኑ አይታዩም፡፡ ለተፈታኞችም ከፈተናው በፊት ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም በአሠራራችን ሙሉ ለሙሉ ይተማመናሉ፡፡ ምንም ዓይነት ችግርም አላጋጠመንም፡፡ ኢንስቲትዩቱም ከካምብሬጅና ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከደቡብ ኮርያ፣ ከጃፓንና ከጀርመን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ የአገር ውስጥ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች የመመረቂያ ጽሑፎቻቸውን የሚያዘጋጁትና የሚያቀርቡት የቀደሙት ተመራቂዎች የጻፉትን እየወሰዱና አንዳንድ ሐሳቦችን እየቀየሩ የራሳቸው በማስመሰል እንደሆነ ይወራል፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ዋና፡- አንድ ተማሪ የመመረቂያ ጽሑፍ ለማቅረብ በቅድሚያ ሦስት ቶፒኮችን አዘጋጅቶ ለሚመለከተው አካል ያቀርባል፡፡ ከዛም ከሦስቱ መካከል በአንዱ ላይ ለመሥራት ያለውን ፍላጎት ያሳያል፡፡ የሚያቀርበው ጽሑፍ ከዚህ በፊት ያልተጻፈ መሆኑን ለማረጋገጥ የተለያዩ ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡ በእርግጥ መቐለ ወይም ሌላ ቦታ ላይ የተሠራውን ገልብጦ እንደራሱ አድርጎ ቢያመጣ ለማወቅና ለማጣራት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ወደፊት ግን ይህ ዓይነቱን አቀራረብ የሚመረምርና የሚያጣራ ፕሮግራም ዕውን ለማድረግ እየታሰበ ነው፡፡ የተጠቀሰው ችግር በአንዳንድ ቦታ ላይ እንዳለ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን የጥናት አሠራር ስናስተምር የምርምር ሥነ ምግባር የሚባል አለ፡፡ በዚህ የምርምር ሥነ ምግባር የሰውን ጽሑፍ እንዳለ መውሰድ ወይም የሰውን ሐሳብ ወስዶ እንደራስ አድርጎ ማቅረብ የተወገዘ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ በአካዳሚክ አካባቢ ከባድ የሥነ ምግባር ነውጥ ይፈጥራል፡፡ በዚህም የተነሳ ጽሑፉ ብቁ ባለመሆኑ ወዲያውኑ ተቀባይነት ያጣል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በቅድመ መደበኛ ትምህርት (መዋዕለ ሕፃናት) ዙሪያ ያተኮረውና ‹‹እርሊ ቻይልድ ሁድ ኬር ኤንድ ኢዱሽን›› የሚል የሚሠራው ምርምር በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ዶ/ር ዋና፡- ጥናቱ ለሁለት ዓመት የሚቆይና በሁለት ዙር የሚካሄድ ነው፡፡ በመጀመርያው ዙር መምህራን ስለራሳቸው እንዲሁም ከትምህርት ሥራ ውጪ ያሉ ጓደኞቻቸውና ኅብረተሰቡ ስለመምህራን ምን ያስባሉ በሚሉት ነጥቦች ዙሪያ ያተኮረ ጥናት ተሠርቶ ጥናቱ እየተተነተነ ነው፡፡ ይህ እንዳበቃም ቀጣዩ ጥናት ይከናወናል፡፡ ቀደም ሲል መንግሥት በቅድመ መደበኛ ትምህርት ዙሪያ ብዙም ትኩረት አልሰጠም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የቅድመ መደበኛ ትምህርት በግሉ ዘርፍ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ እንቅስቃሴውም በከተማ እንጂ በገጠር ላይ ያተኮረ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ መልኩ የሚንቀሳቀሰው የቅድመ መደበኛ ትምህርት በሚያስፈልገው ትምህርት ላይ ከማተኮር ይልቅ በገንዘብ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ወላጆችም ሕፃኑ ወደ ትምህርት ቤት መሄዱን እንጂ ምን እንደሚማር ያለመከታተል ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡ የመምህራኑ ችሎታ ማነስ፣ ሙያቸውን ያለማክበር፣ ከክፍያቸውና ከኑሯቸው ሁኔታ ጋር ተዳምሮ በትምህርቱ ዙሪያ ያሉትን ችግሮች አወሳስቦታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር ግን በመዋዕለ ሕፃናት መምህራን ብቻ ሳይሆን እስከ ዩኒቨርሲቲ ባሉት መምህራንም ላይ ይስተዋላል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ግን እነዚህን ችግሮች ከምርምር ሥራዎች ጋር አጥንቶ ከማቅረብና በኮንፈረንስ ከማሳወቅ በስተቀር የማስፈጸም አቅም የለውም፡፡ ሆኖም የቅድመ መደበኛ ትምህርት፣ ለመጀመርያ፣ ለከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ለዩኒቨርሲቲ ተከታታይ ትምህርቶች መሠረት ሆኖ በመገኘቱ የተነሳ መንግሥት አሁን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶታል፡፡

ሪፖርተር፡- ለቅድመ መደበኛ ትምህርት መንግሥት ትኩረት ከሰጠው በየወረዳውና በየገጠሩ ለምንድነው የመስፋፋት ሁኔታ የማይታይበት?

ዶ/ር ዋና፡- በእርግጥ ተዘዋውሬ አላየሁም፡፡ ነገር ግን በየወረዳውና በየገጠሩ የማስፋፋት ሙከራዎች አሉ፡፡ ግን ደረጃውን የጠበቀ ላይሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት (መዋዕለ ሕፃናት) ምን ዓይነት ደረጃ አለው?

ዶ/ር ዋና፡- ደረጃው እንደየአገሩ ሁኔታ ይለያያል፡፡ የውጪውን ትተን በአዲስ አበባና በገጠር ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መካከል በጣም ሰፊ የሆነ ልዩነት አለ፡፡ የሕፃናቱ የመጫወቻ ቦታዎች፣ የመምህራን አያያዝ፣ ለየት ያለ የማስተማር ሥልጠና የወሰዱ መምህራን መኖር ደረጃው ካካተታቸው የመመዘኛ ነጥቦች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሥልጠናው ለየት የሚያደርገውም የሕፃናትን ሳይኮሎጂ ማወቅ፣ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ ከሚያድርባቸው ፍርሃት እንዴት እንደሚወጡና የመሳሰሉትን በማካተቱ ነው፡፡ በሠለጠነው ዓለም መዋዕለ ሕፃናት የሚያስተምሩት መምህራን ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸውና ርህራሄ ያደረባቸው ናቸው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የማስተማሩን ሥራ የሚጀምሩት ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸውና ካለፉ በኋላ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት መዋዕለ ሕፃናት ለሁሉም ዕውቀት መሠረት ስለሆነ ነው፡፡ መሠረቱ ከተበላሸ አጠቃላይ ትምህርቱ ይበላሻል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመፍታትና ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እንዲኖር በማድረግ ረገድ ያለው ፋይዳ ምን ይመስልዎታል? ለተግባራዊነቱ የሚያጋጥም ተግዳሮት ይኖር ይሆን?

ዶ/ር ዋና፡- ነባሩ የትምህርት ፖሊሲ የወጣው በ1986 ዓ.ም. ነው፡፡ አንድ ፖሊሲ አንድ ጊዜ ከወጣ ዝንተ ዓለም ይኖራል ማለት አይደለም፡፡ ከጊዜው ጋር አብሮ የሚሄድና የሚያድግ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ፖሊሲ እንደወጣ የትምህርቱ ዘርፍ እምብዛም አልተስፋፋም ነበር፡፡ አሁን ግን ላቅ ያለ ዕድገት ታይቷል፡፡ ለምሳሌ ያህል የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ወደ 50 ከፍ ብሏል፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ብዛት ከ11 ሚሊዮን በላይ ሆኗል፡፡ ከዚህ አኳያ ከዕድገቱ ጋር የተጣጣመ ፖሊሲ ሊኖር ግድ ይላል፡፡ በዚህም የተነሳ የቀድሞውን ፖሊሲ የሚተካ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተረቋል፡፡ በረቂቁ ሥራ ላይ በኃላፊነት የሚሠሩና ችሎታ ያላቸው፣ በየሙያውና በየዘርፉ ለብዙ ዓመታት ያገለገሉ፣ የኢትዮጵያን የውስጥ ሁኔታ በደንብ የሚያውቁ፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያላቸው፣ የተመራመሩና ብዙ የጻፉ ምሁራን ተሳትፈዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱን ወክለው ከተሳተፉት ምሁራን መካከልም አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ተሳትፎ በመነሳት መቶ በመቶ እንኳን ለማለት ባይቻልም የትምህርቱን ጥራትና ደረጃውን የሚያስጠብቅ ፍኖተ ካርታ ይወጣዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ረቂቁ አልቆና በደንብ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ አንዳንድ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ የሚልም ሥጋት አለኝ፡፡ ከችግሮቹም መካከል አንዱና ዋነኛው የፋይናንስ ጉዳይ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የመምህራን እጥረት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና የተጠቀሰውን ያህል ውጤታማ አልሆነም  እየተባለ ነው፡፡ በዚህ ላይ ያለዎትን አስተያየት ቢገልጹልን፡-

ዶ/ር ዋና፡- የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በጣም ውድ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ሠልጣኞቹ የሚማሩባቸው ወይም የሚሠለጥኑባቸው ማሽኖች በፋብሪካዎች ካሉት ማሽኖች ጋር አነሰም በዛም ተመሳሳይ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በሥልጠና ተቋማት ያሉት ማሽኖች አሮጌና ኋላቀር፣ በአንጻሩ ደግሞ የፋብሪካዎች ማሽኖች እጅግ ዘመናዊ ከሆኑ ለአፓራንትስ የሚወጡት ሠልጣኞች ግራ ሊገባቸውና ሊደነጋገሩ ይችላል፡፡ በዚህም ሳቢያ የፋብሪካዎች ማሽኖች ለብልሽት ይዳረጋሉ፡፡ ኢንሹራንስ አልባ በመሆናቸውም የተነሳ ችግሩ ይባባሳል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና 70/30 የሚል አፕልኬሽን አለው፡፡ ይህም ማለት ለሠልጣኞች ከሚሰጣቸው ሥልጠናዎች መካከል 30 በመቶ ንድፈ ሐሳብ (ቲዎሪ) ሲሆን፣ የቀረው 70 በመቶ ደግሞ በፋብሪካዎች የሚቀስሙት ሥልጠናና ትምህርት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ አሠለጣጠን ትኩረት ቢሰጠውም እንደተፈለገውና እንደታሰበው ሆኖ አልተገኘም፡፡ ኅብረተሰቡ በቴክኒክና ሙያ ላይ ያለው የተሳሳተ አመለካከት ወይም ዝቅ አድርጎ ማየት ለዘርፉ ዕድገት መጓተት መንስዔ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡- የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና እንዲያድግና በኅብረተሰቡም ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ዶ/ር ዋና፡- ከታች ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ልጆች የእጅ ሥራ እየለመዱ እንዲያድጉ የሚያደርግ ሥራ ቢከናወን፤ ልጆቹ በውስጣቸው ፍላጎታቸው እየሠረጸ ለአገሪቷም  ዕድገት መሠረት መሆኑ እየታወቀ ይመጣል፡፡ አሁን እየታየ ያለው ችግር ግን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ እንዲለማመዱ ሳይደረግ ካደጉና ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና እንዲገቡ መደረጉ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...