Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያድኑትም!

ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያድኑትም!

ቀን:

በወንድምስሻ አየለ

በረቡዕ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የሪፖርተር ዕትም፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣበትን የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ እንዲታደጉ ተጠየቀ›› በሚል ርዕስ ከኬሚካልና ከኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሃላላ ጋር ያደረገውን የቃለ መጠይቅ ዘገባ ይዞ ወጥቷል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ የገለጿቸው ችግሮችም በአብዛኛው ሜቴክን በብቸኝነት ተጠያቂ ለማድረግ የሚሞክሩ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፕሮጀክቱ አማራጭ መፍትሔዎች እንዳሉት ተስፋ በማድረግ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጣልቃ ገብተው መፍትሔ እንዲሰጡ ይማፀናል፡፡

አቶ ሳሙኤል ስለፕሮጀክቱ ሊኖራቸው የሚችለውን መረጃ ቀጥታ ካልሆነ ምንጭ ለማጣራት ብሞክርም አልተሳካልኝም፡፡ ይሁን እንጂ እሳቸውም ኃላፊነት ወስደው ችግሮቹን ቆጥረው ስለነገሩንና መፍትሔ አለው ስላሉን፣ ከጀርባቸው ያለውን የሙያ አማካሪ ቡድን ማግኘት ባለመቻሌና ጉዳዩም አደባባይ የወጣ ስለሆነ እኔም በአደባባይ ልጽፍ መረጥኩ፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ጉዳይ ለመጻፍ የተነሳሁበት ምክንያት የፕሮጀክቱ ቁልፍ ተግባር ወቅት በሥራ አስኪያጅነት ስሠራ ስለነበረና በኃላፊነት በነበርኩበት ወቅት ጭምር፣ በፕሮጀክቱ ላይ ተስፋ ቆርጬ ለሚመለከተው አካል ሙያዊ ምክረ ሐሳብ አቅርቤ ስለወጣሁ አስተያየት ለመስጠት ተገቢ ሰው ነኝ ብዬ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ለፕሮጀክቱ ወሳኝ የሆኑና ዋና ዳይሬክተሩ ያልገለጿቸውን መነሻ ጉዳዮችን ጠቅሼ ለፍርድ እንዲመች (ጀስቲፋየብል) አድርጌ ምክረ ሐሳቤን ላቅርብ፡፡ ፈረንጆቹ ፖለቲከኞች እንዲህ ባለ ጉዳይ ላይ “science based, risk informed decision making” ያስፈልጋል እንዲሉ፡፡

ፕሮጀክቱ

የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ታሳቢ የምርት ዕቅዶች በተጠቀሰው ዕትም ላይ እንደተገለጸው ሆኖ፣ ለብያኔ አስፈላጊ መረጃዎችን ልጨምር፡፡ የፋብሪካው ቦታ በዋናነት 60 ሔክታር ላይ የሚያርፍና ከባህር ወለል በላይ በ1,600 ሜትር ላይ ከአገር አቋራጭ መንገድ አጠገብ (ከበደሌ-መቱ 40 ኪሎ ሜትር) የሚገኝ በደን በተሸፈነው የያዩ ወረዳ ውብ አካባቢ ነው፡፡ የአፈር ጠባዩም በዋናነት ቀይና ነጭ ቅልቅል ክሌይ ሲሆን፣ ለውጭ ገበያ ውሏል ከሚባለው የጅማ/ጎጀብ ክምችት የተሻለ የድንጋይ ከሰል ክምችት በያዩ ወረዳ መኖሩን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር መረጃዎች ይናገራሉ፡፡ በቅርብ ርቀት ጅማ ዙሪያ ሌላ የድንጋይ ከሰል ክምችት በኤክስፖርት ደረጃ እየተመረተ መሆኑ (በውጭ አገር ድርጅት)፣ የግብዓቱ ጥራትና በቂነት ላይ አቶ ሳሙኤል ያቀረቡት ሥጋት ምክንያት ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡ በአገር ደረጃ ደልቢ፣ ሞዬ እና ያዩ ያሉ ክምችቶች በጣም የተሻሉት ሲሆኑ፣ በተጨማሪም በጭልጋና በሙሽ ሸለቆዎች እንዲሁም በጎጀብ (ጅማ እየተመረተ ያለው)፣ ጭንዳ፣ ኪንዶ፣ ሃሉልና ዋቄ በተባሉ የአማራ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች በስፋት እንደሚገኝ በግልጽ ይታወቃል፡፡

እዚያው የያዩው ፋብሪካ አካባቢ 70 ሜትር ጥልቀት ላይ ከሚገኝ ክምችት ሜቴክ እያመረተው ለገበያ እየቀረበ እንደነበረ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም በ2010 ዓ.ም. የተወሰኑ ክምችቶችን ለተደራጁ ወጣቶች እንዳስተላለፈው ይታወቃል፡፡ ይህ ፋብሪካ ከናይትሮጂናዊ ማዳበሪያው በተጨማሪ በተረፈ ምርትነት (ዋና ዕቅድ ያልሆነ የጎንዮሽ ምርትነት) 90 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይልና ለጦር መሣሪያ ተተኳሾች (ፈንጂ፣ ቦምብ፣ ጥይት፣…) የሚሆኑ ግብዓቶችን ያስገኛል፡፡

ፕሮጀክቱ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በ1980ዎቹ ሲጠና ቢቆይም፣ ተግባራዊ የተደረገው በ2004 ዓ.ም. በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው፡፡ ይህም ሜቴክ የተመሠረተበት የመጀመሪያ ዓመት ሲሆን፣ ወዲያው በ2005 ዓ.ም. ኬሚካል ኮርፖሬሽን እንደ አዲስ ተቋቁሞ ሥራው ወደ ኮርፖሬሽኑ ተላልፏል፡፡ ይህ የተቋማት አደረጃጀት መለዋወጥ በራሱ በሁለት ዓመት ተኩል ሊጠናቀቅ ውል ተፈርሞለት የነበረው ፕሮጀክት ላይ ከፍተኛ መጓተት ፈጥሮ ነበረ፡፡ በ2007 ዓ.ም. ፕሮጀክቱን በሲቪል ሥራዎች መሪነት ስቀላቀል፣ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለ2008 ዓ.ም. ጥር ወር ማዳበሪያ ማምረት ይችላል ተብሎ የተነገራቸውን ዕቅድ ለፓርላማ ቃል የገቡበት በመሆኑ፣ የሚፋጀውን ትኩስ ድንች ነው የተረከብኩት፡፡ ከ11 ቢሊዮን ብር ውል ውስጥ ሲቪል ሥራው ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ቢወስድም፣ እኔ እስክገባ የተከናወነው ከሁለት ቢሊዮን ብር ያልበለጠ ነው፡፡ ለሕዝብ ሲነገር የነበረው ግን እጅግ የተጋነነ ነው፡፡ ከሲቪል ሥራው በተጨማሪ ብዙ ያልተሠራው የኤሌክትሮ ሜካኒካል በመሆኑ፣ ሜቴክ ከአንድ ቻይናዊ ድርጅት ጋር በመቀናጀት ዝግጅቱን እያደረገ የማሽን አካላት የሆኑ ብረታ ብረቶችንም ማቅረብ ጀምሮ ነበረ፡፡

በሥራው አደረጃጀትም ኬሚካል ኮርፖሬሽን የሥራው አማካሪ አድርጎ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሲጠቀም ሜቴክ የወሰደው ዲዛይኑንም ግንባታውንም ለማከናወን በመሆኑ (ዲዛይን ኤንድ ቢዩልድ)፣ የቆየ የቻይናን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ዲዛይኑን ያዘጋጁ ኮሪያውያን ፕሮሰስ ኢንጂነሮችን ቀጥሮ አሠርቷል፡፡ ሲቪል ሥራውንም ለአገር ውስጥ ተቋራጭ በመስጠቱ ነው እኔ የሲቪል ሥራው ላይ ተቀጥሬ የገባሁት፡፡ ሜቴክ እንደ ድርጅት አጠቃላይ ሥራዎቹን የሚያማክረው ዕውቅ አማካሪ የነበረው ሲሆን፣ ይህን ፕሮጀክት ብቻ የሚቆጣጠር ሌላ የአገር ውስጥ አማካሪ ቀጥሯል፡፡ ይህ አደረጃጀት ሥራውን ለማከናወን በቂ የነበረና የአቅም ማነስ ለፕሮጀክቱ ውድቀት ምክንያቱ የሜቴክ አቅም ማነስ ነው ተብሎ ለመጥቀስ የሚቸግር ነው፡፡ ከቴክኖሎጂ መረጣ ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችል የአዋጭነት መጠን ልዩነት ካልሆነ በቀር፣ ጋዜጣው ላይ የተጠቀሱትን ችግሮች በዚህ ፕሮጀክት ላይ ለማሰብ በቂ ምክንያት አለ ብዬ አላምንም፡፡

እኔም እንደ ጉድለት መጥቀስ ካለብኝ የሚታየው ጉድለት ዲዛይኑንና የግንባታ ቁጥጥሩን በቅጥር ሠራተኛ ከማሠራት ይልቅ፣ ኃላፊነት መውሰድ ለሚችልና በዘርፉ በቂ ልምድ ላለው ድርጅት ቢሰጥ ይሻል ነበረ፡፡ ይህን ስል ስንሠራ የነበረውን ሥራ በዝርዝር ሳየው የሲቪል ሥራው ግንባታ በአገር ውስጥ ተቋራጮች በትክክል መፈጸም እንደሚችል በተግባር እያሳየን ስለነበረ፣ እንዲሁም ዲዛይኑ ተሟልቶ ከቀረበና ኤሌክትሮ ሜካኒካሉን ቻይናዎችም ገብተውበት ስለነበረ ችግሩን ሜቴክ ጋ የሚወስደው ምክንያት ኢምንት ስለሆነ ነው፡፡

ሲቪል ሥራው

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የገቡትን ቀጠሮ ለማክበር ዕቅድ ከልሰን ከ50 በላይ መሐንዲሶች፣ ከሦስት ሺሕ በላይ ልዩ ልዩ ሠራተኞች፣ ከ200 በላይ ማሽነሪዎችና የሥራ ተሸከርካሪዎች ቀጥረን ስንሠራ በወር ለደመወዝና ለሥራ ማስኬጃ ብቻ ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት በቀን 15 ሰዓት ድረስ እንሠራ ነበር፡፡ ይህን እያደረግን የፕሮጀክቱን ወሳኝ ጉዳዮች በዝርዝር እያቀድን የምንመራ 11 ከፍተኛ መሐንዲሶች በ20 ቀናት ውስጥ ባሳየነው ከፍተኛ ለውጥ ሜቴክ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ (ማርሽ ቀይራችኋል ብሎ)፣ በወቅቱ ውል ያልተገባባቸውን ቀሪ ሥራዎች እኔ ባለሁበት ድርጅት እንዲከናወን በመወሰን፣ ከአካባቢው ወረዳ አስተዳደር ጋር ያልተቋጩ የካሳ ክፍያ ችግሮችና ለፕሮጀክቱ አስፈላጊ የነበሩ ተጨማሪ ቦታዎችን በፍጥነት ማመቻቸት ተችሎ ነበረ፡፡

በዚህ መሠረት ለፋብሪካው የተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ከ88 በላይ ሕንፃዎች፣ ሰባት ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ፣ ስምንት ኪሎ ሜትር የአፈር ደጋፊ ግድግዳዎች (ሪቴይኒንግ ዎል)፣ የጋዝና የፈሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮችና ደጋፊዎች፣ የፋብሪካ ሠራተኞች ካምፕ፣ ወዘተ ሁሉንም በዕቅዱ መሠረት ማከናወን ተሞክሯል፡፡ በጋዜጣው የተጠቀሰው የስድስት ቢሊዮን ብር ክንውን እነዚህን ይጨምራል፡፡ ይህ ሥራ በአገር ደረጃ አዲስና ግዙፍ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሥራውን የምንመራ መሐንዲሶች በጥሩ መናበብና ‹‹ኢትዮጵያውያን መሥራት እንችላለን!›› የሚለውን መርሕ በተግባር ለማሳየት ጥረት ያደረግንበት ነው፣ ተሳክቶልናል ብዬም አምናለሁ፡፡ በዋናነት በኮርፖሬሽኑ ከዚያም በሜቴክ አደረጃጀት በኩል ግን የጠቀስኩትን ሀብትና የሥራ ማስኬጃ መድቦ ለሚንቀሳቀስ ፕሮጀክት የሚመጥን የሥራ አመራር አልነበራቸውም፡፡

ፋብሪካው የድንጋይ ከሰልን በማቃጠል የሚገኘውን ጋዝ ተቀብሎ እየጨመቀ (ኮምፕሬስ) እያጓጓዘ፣ እንዲሁም የጋዞቹን ውህድ በመለየትና በማዋሀድ (ኤየር ሴፓሬሽንና ሪአክሽን) መጨረሻ ላይ ደረቅ የሆነ የማዳበሪያ ፍሬ (ሶሊድ) ዩሪያ ማዳበሪያ የሚያስገኝ የምርት ሒደት ነው፡፡ ይህ የምርት ሒደት ለሰውም ሆነ ለአካባቢ ተፈጥሮ አደገኛ የሆኑ ኬሚካሎችን (ካርቦን ዳይኦክሳይድ፣ ሰልፈር፣ አሞንያ፣ ፒዩር ኃይድሮጅንና ፒዩር ናይትሮጅን) በጋዝነት እያሉ የሚያጓጉዙና የሚያመርቱ አሃዶች (ዩኒትስ) አሉት፡፡ በእነዚህ አሃዶች የእርስ በርስ ትስስር ምክንያት ለደኅንነት ሲባል ግንባታው የጥራት ችግር አይፈልግም፡፡ ማለትም ግንባታ ላይ በሚፈጠር የጥራት ጉድለት ምክንያት የጋዞቹ ምርት ሒደት ላይ የሚፈጠር የአንድ የሕንጻ አካል ውድቀት (ፌይለር) ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል፡፡ በፋብሪካው መደበኛ የምርት ሒደት ጭምር አደጋ ቢያጋጥም ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያደርስ፣ በየአሃዱ ግዙፍ የአደጋ መከላከያ ሥርዓትን (ፋየር ፋይቲንግ ሲስተምስ) ያካተተ ፕሮጀክት ነው፡፡

የንድፈ ሐሳብ ችግር

የፋብሪካውን ቁልፍ ችግር ሳንለይ ስለመፍትሔ መነጋገር ትርጉም አልባ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የሚወስዱት ኃላፊነት ካለ ግልጽ ያለ፣ የሚታወቅ ኪሣራ/አደጋ ካለም አካቶና የመጨረሻውን ግብ የሚያሳካ መሆን አለበት፡፡ ከላይ ከገለጽኩት የፕሮጀክቱ ፀባይ አንፃር ችግሩን ስጠቅስ ሙያዊ ድርሻዬን ለመወጣትና ወደኋላ መመለስ የማንችለውን ኪሳራ እያመመንም ቢሆን በመቀበል ወደፊት ለመራመድ ጊዜያችንን መጠቀም እንድንችል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ንድፈ ሐሳባዊውን አመክንዮ (ሎጂክ) ላስቀድምና በተግባር የታየውን ችግር ላስከትል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና ችግር የሚነሳው ከፋብሪካው ፀባይና ከአካባቢው የቦታ አቀማመጥ አንፃር ሲሆን፣ መጀመሪያ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ወይም ኬሚካል ኮርፖሬሽን ፋብሪካው በሁለት ዓመት ተኩል እንዲጠናቀቅ ማቀዱ ስለፋብሪካውና ቦታው የተዛባ መረጃ የተሰጠው ይመስለኛል፡፡ ቦታው ከፍተኛ የመሬት ቆረጣና የአፈር ሙሌት ሊኖረው እንዲችል አስቀድሞ መገንዘብ የሚቻል ሆኖ እያለ፣ ፋብሪካውም ከሚፈልገው የደኅንነት ደረጃ አንፃር ገና የአዋጭነት ጥናቱ ላይ መሐንዲሶች መገንዘብ የሚችሉት ስለሆነ ነው ንድፈ ሐሳባዊ ችግር ያልኩት፡፡

የአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ላይ ከአንድ ሜትር በላይ አፈር ሙሌት የሚያጋጥመው ሕንፃ ቢኖር፣ የአፈር ሙሌት ሥራውን ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ካከናወኑ በኋላ ወለሉን አርማታ ሳይሞሉ እንዲያልፉና ሙሌቱ በግንባታው ምክንያት የሚፈጠርበትን ጫና ተጠቅሞ፣ ውስጡ ሊኖር የሚችለውን አየር እንዲያስወግድ (አርቲፊሻል ኮንሶሊዴሽን እንዲከናወን) ጊዜ ይሰጠዋል፡፡ በአዲስ አበባ የኮንዶሚኒየም ግንባታ ያልታቀደ መዘግየት ምክንያት በዝቅተኛ ግምት ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ ያገኛል፡፡ ይኸውም አፈር ውስጥ ያለው አየር በማንኛውም የግንባታ አሠራር ዘዴ ወደ ተፈጥሯዊው ምጣኔ (ናቹራል ስታብሊቲ) ሊያደርሰው ስለማይችል፣ ሙሌቱ በራሱ ይህን እንዲያከናውን ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠዋል፡፡ ይህም ሰው ሠራሽ ዘዴን መከተል ከተቻለ አንድ ዓመት የሚበቃው ሲሆን፣ ተፈጥሯዊ ሒደቱን እንዲከተል መተው ካለበት ከአራት እስከ አምስት ዓመት ያስፈልገዋል፡፡

ለዚህ ማዳበሪያ ፋብሪካ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድ የአፈር ሙሌት አሠራር ነው፡፡ የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ላይ የተተገበረውና ከ20 ሜትር በላይ የአፈር ሙሌት ያከናወኑበትን ቦታ ለአንድ ክረምትና ለአንድ በጋ (አንድ ዓመት) የግንባታ ግብዓት የሆኑ ኮረትና ምርጥ አፈር (ፊል ማቴርያልስ)፣ በበቂ መጠን ጭኖበት ሰው ሠራሽ መፍትሔ ሰጥቷል፡፡ ይህ ሒደት ውጤታማ ለመሆኑ በቅድሚያ በተደረገ የላብራቶሪ ፍተሻ መተንበይ ስለሚችል፣ ከአንድ ዓመት በኋላ በሚወሰድ ልኬት ተፈጥሯዊ የመጠቅጠቅ ሒደቱን (ኮንሶሊዴሽን) መጨረሱን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

የዚህ ፋብሪካ ማረፊያ ቦታ ከግቢው መግቢያ ጀምሮ የመጨረሻው የፍሳሽ ቆሻሻ መውጫ ዝቅተኛ ቦታ በ600 ሜትር ርቀት ውስጥ ከ50 ሜትር በላይ የከፍታ ቅናሽ (ኢሊቬሽን ዲፈረንስ) አለው፡፡ በዚህም ምክንያት ቆረጣ ከሚፈልጉት ውጪ በአብዛኛው ቦታ እስከ ሰባት ሜትር የአፈር ሙሌት ይፈልግ የነበረና የተወሰኑ ቦታዎችም እስከ 20 ሜትር ድረስ ሙሌት የተከናወነበት ፕሮጀክት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ግን ቦታው ሜዳ እንደሆነ ተደርጎ የተሠራ የሚመስለው የተጣበበ የቦታ አጠቃቀም የፋብሪካ ዲዛይኑን የሚያግዝ የመሬት ቆረጣና አፈር ሙሌት፣ ከዚህም ጋር የአፈር ደጋፊ ግድግዳና የጋዝና ፈሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮች ቅብብሎሽ ከመሬት በላይና በጥልቅ ወለል ላይ ይከናወናል፡፡ ይህ ሁሉ ሲደመር ቦታውን ለመደልደልና ለዋናው የፋብሪካ ሕንፃዎች ግንባታ ዝግጁ መሆኑን ለማረጋገጥ ብቻ በትንሹ ከሁለት ዓመት በላይ ያስፈልግ ነበረ፡፡ ለመሬት ቆረጣ፣ ለአፈር ሙሌትና ለአፈር መደገፊያ ግድግዳ ግንባታ ቢያንስ አንድ ዓመት፣ ከሙሌቱ አፈር ውስጥ በሰው ሠራሽ ዘዴ አየር ማስወገድ (አርቲፊሻል ኮንሶሊዴሽን) ሌላ አንድ ዓመት፡፡

ይህን ንድፈ ሐሳብ በተመለከተ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ያሉት አማካሪዎች ለኮርፖሬሽኑ ማሳሰቢያና መመርያ ሊሰጡ ይገባ ነበረ፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ከሁለት ዓመት በኋላ እኔ ስቀላቀል ላገኝ ይገባ የነበረው የሥራ ሒደት አልተከናወነም፡፡ ይህንም ርዕስ አድርጌ ከለሆሳስ ምክክር ጀምሮ በመድረክ እስከማንሳት ድረስ ስሞክር ግልጽ መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ በዚህም ምክንያት የሜቴክ መሐንዲሶችና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ሁሉ ባሉበት ዕቅድ ለማዘግየት የማይታሰብ ተደርጎ በመወሰኑ፣ ይልቁንም የመንግሥት መሪዎችን ፖለቲካዊ መመርያና የሜቴክ የጦር መኮንኖችን መጋፈጥ የማይታሰብ በመሆኑ፣ በዚህ ፕሮጀክት ላይ መቀጠል እንደሌለብኝ ወስኜ ራሴን አግልያለሁ፡፡ ቁም ነገሩ የእኔ ጉዳይ ስላልሆነ ወደ ጉዳዩ እንቀጥላለን፡፡

ያጋጠመው ችግር

ከላይ የጠቀስኩት ንድፈ ሐሳባዊው እውነታ ታሳቢ ባለመደረጉ ፕሮጀክቱ ችግሮች እንዳጋጠሙት በየጊዜው ሲዘገብ አይ ነበረ፡፡ እነዚህ ችግሮች ሪፖርተር ጋዜጣን ጨምሮ በየሚዲያው ሲነገሩ የቆዩ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ላይ የነበሩ ወዳጆቼ ግን የምሕንድስና ፕሮፌሰሮችን ጭምር ቦታው ድረስ በማድከም ጥገናዊ መፍትሔ ሲሞክሩ እንደነበረ ነግረውኛል፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ሞሮኳዊ ባለሀብት ፕሮጀክቱን ተረክቦ ሊሠራ ነው ተብሎ ተዘግቦ ነበረ፡፡ በዚህም ምክንያት በመንግሥታዊ ሥርዓታችን ችግርን ለመፍታት አገራዊ ጥቅምን ማስቀደም ስላለመደብንና ጥፋተኛ ፈልጎ መወንጀል ስለሚያረካን ነገሩን በዝምታ ስከታተል ነበረ፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ችግሩን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስተላለፋቸውን ሳይ ግን ከሚከተለው አደጋ ጭምር መጠቆም ተገቢ ስለሆነ ዝምታዬን ሰብሬያለሁ፡፡ የሲቪል ሥራዎች ተቋራጩ ፕሮፌሰሮቹን ጭምር በአካል ከመውሰዱ በፊት እያንዳንዷን አጋጣሚዎቻችንን ለዋና ቢሮ እያቀረብን፣ ዋና ቢሯችንም ለመፍትሔው ራሱን ሲያደክም ቆይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም መጠቀም የሚችሉት እነዚሁኑ ፕሮፌሰሮች በመሆኑ አዲስ የችግርና የመፍትሔ ግምገማ አልጠብቅም፡፡

በዋናነት የሸሹትና የተሰነጠቁት የአፈር ደጋፊ ግድግዳዎች መልሶ ማከም የማይቻልና ከላይ ለገለጽኩት የፋብሪካው ጠባይ ፍፁም የማይመቹ ናቸው፡፡ ከለውጡ ወዲህ በኢቲቪ በተላለፈ ሜቴክን በሚመለከት አንድ ዶክመንተሪ ፊልም ላይ (‹‹ምናባዊ›› የሚለው አይደለም) እንደተገለጸው የፋብሪካው ማሽኖች አለመገዛታቸው በራሱ ከተጨማሪ ኪሳራ አድኖናል፡፡ ስለዚህም የፋብሪካው ጠባይ የሚፈልገውን ደኅንነቱ የተሟላ ግንባታ ለማከናወን በቂ ዕቅድና የሥራ ሒደት ያልነበረ በመሆኑ፣ ዛሬ ላይ ከቆመበት መቀጠልና ለዚህ ፋብሪካ ማዋል አንችልም፡፡ የፕሮጀክቱ የፋብሪካ ቦታ ረግቶ ፋብሪካውን መሸከም ስለማይችልና ደኅንነቱ የተጠበቀ የኬሚካል ምርት ማከናወን የሚቻልበት ባለመሆኑ፣ ቦታው ላይ አዲስ ዕቅድ ወጥቶ እንደ አገር ያለንን ውስን ሀብት ለሌላ ዓላማ ማዋል ይሻላል፡፡

ይልቁንም ወንጀለኛ ፍለጋውን ትተን የፕሮጀክቱ ይዞታዎች ላይ ያሉትንና መነቃቀል የሚችሉ ብረት ነክ ምርቶችን፣ እንዲሁም ሥጋት የሌለባቸውንና በመቶዎች ሚሊዮን ብር የሚገመቱትን ብዙ ሕንፃዎች ጫካ ውስጥ ትተን ለሌላ ወጪ ሳይዳርጉን በፊት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚሻል እመክራለሁ፡፡ ይህ እንደ አገር ያጋጠመን የጋራ ስህተት አድርገን ብንወስደው ምልባትም ለመማርያና ለምርምር ሥራ በሚያመች መልክ አደራጅተን፣ ለመጪው የምሕንድስናና የፖለቲከኞች ትውልድ ብናደርስ የበለጠ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህን በወቅቱ አለማድረግ በራሱ ቦታውን ኃላፊ የሌለው ሆኖ የአካባቢ ተፈጥሮና ማኅበረሰብ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር ለሚችል ሌላ ችግር ምክንያት ልናደርገው እንችላለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...