Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአላርፍ ያለች ጣት. . .

አላርፍ ያለች ጣት. . .

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግን) ከመሠረቱት ድርጅቶች መካከል ምንጊዜም ቢሆን፣ ፊት ለፊት የሚመጡት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ግንባር (ሕወሓት) እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ አባል ድርጅቶች፣ ማለትም የትናንቱ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ደግሞ በአንፃራዊነት ዘግይተው የተፈጠሩና ግንባሩን የተቀላቀሉ ኃይሎች ስለመሆናቸው ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

ከእነዚህ አባል ድርጅቶች ውስጥ በተለይ ኢሕዴን ከመነሻው ሁሉንም አቃፊ ተፈጥሮና ኅብረ ብሔራዊ አወቃቀር የነበረው ድርጅት ቢሆንም፣ ለአያሌ ዓመታት የማይደፈር አበ ነፍሱ ሆኖ በዘለቀው በሕወሓት መመርያ ሰጪነት በአገሪቱ ውስጥ አዲስ ለተቀነቀነው የብሔር ፖለቲካ ሥርዓትና አደረጃጀት የሚመጥን የተፀውኦ ስም ለውጥ እንዲያደርግ በመገደዱ፣ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ተብሏል፡፡ ከመሠረቱ ሕወሓት የመለመላቸውና ሥምሪት የሰጣቸው ቀደምት የኢሕዴን አባላት፣ ይህንን የመከላከል ፍላጎቱም ሆነ ሀሞቱ የነበራቸው አይመስልም፡፡

እነሆ ለለውጡ ምሥጋና ይግባውና ብአዴን ራሱ ከሁለት አሥርተ ዓመታት በኋላ ደግሞ አዲሱና የተሻሻለው መጠሪያዬ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሆኗል በማለት በይፋ ለማወጅ፣ እንደ ቀድሞው የሕወሓት የቅድሚያ ፈቃድ አላስፈለገውም፡፡ ኦሕዴድ ይሰኝ የነበረው ሌላው፣ ተጣማሪ ኃይል ትንሽ ቀደም ብሎ ከእንግዲህ በኋላ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እያላችሁ ጥሩኝ በማለት እንዳወጀው መሆኑ ነው፡፡

አገሪቱን ከተቆጣጠረ ድፍን 30 ዓመት ሊሞላው ሁለት ዓመታት ብቻ የቀሩትና በሕወሓት ፊታውራሪነት ሲዘወር የኖረው ኢሕአዴግ ለይስሙላ ያህል ለባለ ብዙ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት የታመነና ጥብቅና የቆመ ቢመስልም፣ በፀባዩም ሆነ በአሠራሩ ፍፁም አምባገነንና መፍቀሬ ሥልጣን ነው፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ የሽግግር ጊዜው ተጠናቆ በአገራችን ከአምስት ያላነሱ፣ ተከታታይ ብሔራዊና ክልላዊ ምርጫዎች በተካሄዱበት ትዕይንት እንደ ተመለከትነው፣ እርሱ አጥብቆ ከሚከተለው የአገዛዝ ፍልስፍና በተፃራሪ የተሠለፈን የትኛውንም ዓይነት ጠንካራ ተወዳዳሪ ኃይል ማየትና መጋፈጥ አይፈልግም፡፡

በአራቱ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች አማካይነት ጥምረቱ የሚወክለው የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎችን እንደሆነ ቢታወቅም በሒደት እንደታየው ግን እጁን አስረዝሞ ሌሎች ክልሎችን ሳይቀር ከርቀት የመቆጣጠርና ምንጊዜም ቢሆን፣ በመዳፉ ሥር መዋላቸውን የማረጋገጥ አሠራር አጎልብቶ ቆይቷል፡፡ እንዲያውም በእነዚህ አዳጊ ክልሎች ውስጥ ተደራጅተው በምርጫ መንግሥታዊ ሥልጣን የሚይዙትን የፖለቲካ ድርጅቶች አጋሮቼ ናቸው ሲል ነው የሚያቆላምጣቸውና በ’አዛኝ ቅቤ አንጓች’ ምላሱ አብዝቶ የሚሸነግላቸው፡፡

   ድንቄም እህትማማችነት

ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶቹን በእህትማማችነትና አማራጭ አሳጥቶ የሚገዛቸውን ማኅበረሰቦች ደግሞ በወንድማማችነት መጥራት ያስደስተዋል፡፡ ከእውነተኛ ፍቅር የመነጨና የምር የሆነ አጠራር፣  ሆኖም ሕወሓት እህቶቼ ናቸው እያለ በአደባባይ የሚያንቆለጳጵሳቸውን ተጣማሪ ድርጅቶች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይመለከታቸው የነበረው በአጫፋሪነት እንጂ በእኩል ባልንጀርነት እንዳልነበር አብረን ለምንሠራ ሰዎች ቀርቶ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ አንድን ብሔራዊ አጀንዳ ሕወሓት ያመነጫል፣ እርሱ በብቸኝነት ይወስናል፣ ሌሎች እህት ድርጅቶች ያንኑ በፀጋ ተቀብለው በተናጠልና በጋራ አደረጃጀቶቻቸው አማካይነት በተባበረ ድምፅ ያፀድቃሉ፡፡ በዚያ ሒደት የሕወሓት ሆኖ በይፋ የወጣውን አቋም በትንሹ ለመገዳደር የሚሞክሩ ወገኖች ቢያጋጥሙ በራሱ በሕወሓት ሳይሆን፣ ወደተወከሉባቸው አባል ድርጅቶች ሲመለሱ አውራውን ባልተገባ ድፍረት እንደተነኮሱ ተቆጥሮ በጠንካራ ግምገማ የመሪር ግለ ሂስና የከባድ ሥነ ሥርዓት ዕርምጃ ሰለባዎች ይሆናሉ፡፡

ይህ ጸሐፊ በመቀሌና በአዳማ የተካሄዱትን ስድስተኛውንና ስምንተኛውን የኢሕአዴግ ጉባዔዎች በታዛቢነት ተጋብዞ የመከታተል ዕድል አግኝቷል፡፡ ሁለቱም ጉባዔዎች የተመሩት በሟቹ የግንባሩ ሊቀመንበር በአቶ መለስ ዜናዊ ነበር፡፡ ሰውየው በመቀሌው መድረክ ኢሕአዴግ እስከዛሬም ድረስ በአወዛጋቢነቱ ወደር ያልተገኘለትን የ1997 ዓ.ም. ምርጫ አሸንፏል ያሉበትን የተራቀቀ ስትራቴጂ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ለጉባዔተኛው የተነተኑና ያስረዱ ሲሆን፣ በድርጅታዊ ሪፖርት ስም ዕቡይነት በተቀላቀለበት ከፍተኛ የራስ መተማመን መንፈስ ያሰሙትን ያንን የተራዘመ የድል አድራጊነት ዲስኩር ደፍሮ የተገዳደረ ወይም የሞገተ አንድም አባል አልነበረም፡፡ እውነትም ከሕወሓት ውጪ ባሉት የግንባሩ አባል ድርጅቶች ውስጥ ማን አህሎኝነታቸውን በአደባባይ የመገዳደር አቅም ያለው ባላንጣ እንደሌለ ይበልጥ የተገነዘብኩት ያኔ ነበር ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ በታዛቢነት የተጋበዝነው ጉባዔተኞች ድምፅ የመስጠት መብት ባይኖረንም የመጠየቅ ዕድል ስላለን፣ በዚያ ጉባዔ ለአቶ መለስ ሁለት አስተያየቶችና ከሲቪል ሰርቪሱ አያያዥና አስተዳደር ሥርዓት ጋር የተገናኘ አንድ ጥያቄ አቅርቤላቸው እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ አፈሩ ይቅለላቸውና ሰውየው በቂ ሊባል የሚችል ምላሽና ማብራሪያ እንደሰጡኝ ባውቅም፣ ከጉባዔው አዳራሽ ከወጣሁ በኋላ በርካታ ወገኖች ድፍረቴን እያደነቁ በአጀብ ከበው ሲያበረታቱኝ በገዛ አባሎቻቸው ሳይቀር ምን ያህል የተፈሩና የታፈሩ ቢሆኑ ነው ብዬ ተገርሜአለሁ፡፡ ይኸው አጋጣሚ ታዲያ አምባገነንነትን አንዳንዴ የምንፈጥረው እኛው ራሳችን ስለመሆናችን መጠነኛ ፍንጭ ሰጥቶኝ አልፏል ለማለት እደፍራለሁ፡፡

የአዳማው ጉባዔ ደግሞ ትልቁ ሰውዬ በኢሕአዴግ ውስጥ እንዲሠራበት የተነደፈውን የመተካካት ፖሊሲ በማብራራት ሳይወሰኑ፣ የአውራ ፓርቲ ሥርዓትን አስፈላጊነትና ለወደፊቱም ቢሆን በብቸኝነት እየተተገበረ ቢቀጥል ለአገሪቱና ለሕዝቧ የሚኖረውን ፋይዳ ዘለግ ባለ ዲስኩር በሰፊው የተነተኑበት የመጨረሻው መድረካቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ያ ታሪካዊ ጉባዔ ከሁሉም በላይ ግንባሩን ለረዥም ጊዜ በምክትል ሊቀመንበርነት ሲያገለግሉ የኖሩት አቶ አዲሱ ለገሰ በክብር እንዲሰናበቱና በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዲተኩ የተደረገበት በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም በቀላሉ ሊረሳኝ የማይችለው፡፡

አቶ መለስ ጉባዔዎችን በሊቀመንበርነት ሲመሩ፣ እርሳቸው ሲናገሩም ሆነ ለተናጋሪዎች ዕድል ሲሰጡ በአካል ተገኝቶ ትዕይንቱን በንቃት መከታተል ለተመራማሪነት ይጋብዛል፡፡ ፈቅደውም ሆነ ሳይፈቅዱ በጉባዔው አዳራሽ ውስጥ አለቅጥ የሚያነግሡት የፍርኃትና የጭንቀት ድባብ ገራሚና አስደማሚ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ታዲያ ሰውዬው በተናገሩ ቁጥር ታዳሚው ፍርኃቱን እንደምንም ተቋቁሞ ዲስኩራቸውን እያቋረጠ ሳይመጣ በሳቅ ማጀብና በውሸትም ቢሆን፣ የሊቀመንበሩ ማዕከላዊ መልዕክት የገባው መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡

እንዳጋጣሚ ሆኖ በዚያ ጉባዔ ድምፅ የመስጠት መብት ካላቸው አባላት ጋር ተዘንቄ ነበር የተቀመጥኩት፡፡ ሰውዬው ፖለቲከኛ እንጂ ኮሜዲያን እንዳልሆኑ እየታወቀ መላ ጉባዔተኞች ለምን ያን ያህል ደጋግመው እንደሚስቁና እንደሚቦርቁላቸው እምብዛም አልገባኝም፡፡ ይልቁንም ከእነርሱ ጋር ተጃምዬ ስስቅ አለመታየቴ ያሳሰባቸው የጎንዮሽ ወንበር ተጋሪዎቼ ‘ሰማኸው? ሰማኸው?’ በማለት አብሬያቸው እንዳደንቅ ይነቀንቁኝና አልፎ ልፎም ያንቀላፋሁ እየመሰላቸው በለስላሳው ይጎሳስሙኝ ነበር፡፡ ሆኖም በእኔ በኩል አንዳች የሚያስቅ ነገር እንዳላጋጠመኝ ስገልጽላቸው፣ የሆዳቸውን ባላውቅም ሙከራው እንዳላዋጣቸው የተረዱ መሰለኝ በጉትጎታው አልገፉበትም፡፡

ይህንን ጸሐፊ ጨምሮ ብዙዎች እንደታዘቡት ሕወሓት በሊቀመንበሩ አማካይነት የመሾምና የመሻር ሥልጣኑን ተጠቅሞ፣ በእዚያ ጉባዔ ላይ ሲያሳድር የተስተዋለው ጉልህ ተፅዕኖ ጨርሶ የሚዘነጋ ነገር አይደለም፡፡ ከሁሉም ይልቅ አቶ መለስ የቀድሞውን የበረሃ ትግል አጋራቸውንና የዚያን ጊዜውን የብአዴን ሊቀመንበር ለድርጅቱ ስለሰጡት የረዥም ጊዜ አገልግሎትና በተጋድሎው ውስጥ ስለነበራቸው ድርሻ ካመሠጋገኑ በኋላ፣ ‹‹በል እንግዲህ ጓድ አዲሱ ተነስና ጉባዔውን በክብር ተሰናበት፤›› በማለት ያሰሙት ድምፀት ከጋባዥነት ይልቅ የትዕዛዝ ሰጪነት መንፈስ የተጫነው ሆኖ ተስተጋብቷል፡፡

ከሥሩ የተበላሸው የግንኙነት ሥሪት

ከቴክኒካዊ ገጽታው ባሻገር የተመለከትን እንደሆነ በሕወሓትና በሌሎች የግንባሩ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል ሰፍኖ የቆየው ግንኙነት የጌታና የሎሌ ዓይነት እንደነበር፣ ከእነርሱም ጋር ቢሆን ከቶ የምንካካድ አይመስለኝም፡፡ እነ ብአዴን ከሕወሓት ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሕወሓት ራሱ ከሻዕቢያ ጋር የነበረውን ዓይነት ግንኙነት ነው የሚመስለው፡፡ የኋላ ኋላ ለራሱ የጥርስ ደም እንደሚሆንበት ሳያስበው ሻዕቢያ ደርግን ለመገዳደር ሲል ሕወሓትን ቀድሞ እንደፈጠረ ወይም ቢያንስ መፈጠሩን እንደረዳ፣ እንዳሠለጠነና እንዳደራጀ በሰፊው ይነገራል፡፡ ሕወሓት በበኩሉ ወደ መሀል አገር ለመግባት ያመቸው ዘንድ የብሔርና የብሔረሰብ ስሞችን እየሰጠ በርካታ ድርጅቶችን መቀፍቀፍ ነበረበት፡፡

ታዲያ ከነዚሁ ድርጅቶች ውስጥ ‘ቡዳ በወዳጁ’ ሆኖበት ነው እንጂ፣ እንደ ዓይን ብሌን ሊሳሳለት ይገባው የነበረ የበኩር ልጁ ብአዴን ነበር ቢባል ፈፅሞ ማጋነን ሊሆን አይችልም፡፡ በእርግጥም ቅድመ አዴፓ ብአዴን ይመራውና ያስተዳድረው ከነበረው የአማራ ሕዝብ ሥነ ልቡና ባፈነገጠ መንገድ (ምናልባትም ከቀሪዎቹ የግንባሩ አባል ድርጅቶች በባሰ ሁኔታ) ከሁለት አሥርተ ዓመታት ለበለጠ ጊዜ የሕወሓት ለማዳ እንስሳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ታዲያ ይህ የኮሰመነ ቁመናው እመራዋለሁ ከሚለው ሕዝብ ጋር ክፉኛ አቆራርጦት እንደኖረ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

እንቆቅልሽ የሆነው ነገር ከገዛ ሕዝቡ መነጠልን ጨምሮ የቱንም ያህል ዋጋ ቢከፍልለት ሕወሓት ለዚህ ብርቱ ውለታው ብአዴንን በታሪክ አንድም ቀን ሲያመሠግነው ተሰምቶ የማያውቅ መሆኑ ነው፡፡ በተቃራኒው አጋጣሚዎችን እየተጠቀመ ለእርሱ ያለውን ንቀትና ጥላቻ በህቡዕም ሆነ በይፋ ሲገልጽ ነው የምናስታውሰው፡፡ ብአዴን 35ኛውን የልደት በዓሉን ያከበረበት ደማቅ ሥነ ሥርዓት ሕወሓትን ክፉኛ ሲያወራጨው እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ደርግን ለመጣል በተካሄደው መራራ ተጋድሎ ብአዴን በዚያ በዓል ሰሞን ያሳየው ዓይነት የጀግንነት ሚና ነበረው ብሎ ሕወሓት አያምንም፡፡

ሲፈጥረው የለየለት ራስ ወዳድ በመሆኑ ከራሱ በስተቀር የሌሎች አጋሮቹን የጦር ሜዳ ውሎ ዘወትር ማንኳሰስ ይቀናዋል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ አፈ ቀላጤዎቹ የብአዴንን የትግል ተሳትፎ ትግሉን በሚያበረታቱ የኪነ ጥበብ ውጤቶች፣ ማለትም በዜማና በግጥም ደራሲነት ለመወሰን ሲዳዳቸው አስተውለናል፡፡ ይህ በራሱ ሌላው የአዕምሮ ጀግንነት መገለጫ ቢሆንም፣ ሕወሓት በጊዜው ያላግባብ የተጠቀመበት ግን የእህት ድርጅቱን ሚና ለማጣጣል እንደነበር አያጠያይቅም፡፡

አነቃቂው የአዴፓ ምላሽ

ይህ ሁሉ ሲሆን የብአዴን የእስካሁኑ ምላሽ አብዛኛውን ጊዜ በጣም ቀዝቃዛ፣ አለቅጥ የተለሳለሰና አይናፋርነት የተጠናወተው ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለዚህ ይመስላል ሰሞነኛው የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ ከጓዳ እስከ አደባባይ ብዙዎችን ሲያነጋግርና ጎራ ለይቶ ሲያከራክር የሰነበተው፡፡ የቀድሞውን ብአዴን በቅርቡ ለተካው ለዚህ የአዴፓ ድርጅታዊ መግለጫ ሪባኑን የቆረጠው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ባስቸኳይ ጥሪ ካካሄደው ከስብሰባ ማግሥት ያወጣው የትንኮሳ መግለጫ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በእርግጥም አዴፓ ከፍተኛ መሪዎቹን ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በድንገተኛና አስደንጋጭ የነፍስ ግድያ ተነጥቆ በከባድ ሐዘን ላይ መሆኑን እያወቀ የአገሩ ወግና ባህል በሚያዘው መሠረት ለቅሶ መድረሱና የተጎዱትን ወገኖች ማፅናናቱ ቢቀር እንኳ ያንን ዓይነቱን አናዳጅና ግራ አጋቢ የአቋም መግለጫ ለምን ማውጣትና ለሕዝብ ማሠራጨት እንዳስፈለገው የሚያውቀው ራሱ ሕወሓት ብቻ ነው፡፡

የሕወሓት ድርጅታዊ መግለጫ ሰባት የተነባበሩ ነጥቦችን የያዘ ነው ቢባልም፣ ብዙዎቹ ለቁጥር ማሟያነት ብቻ የተካተቱ ናቸው ለማለት እደፍራለሁ፡፡ ግንባር ቀደሙ ነጥብ ‹‹አዴፓ በራሱ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ለተፈጸመው የግፍ ግድያና በአገሪቱ ደኅንነት ላይ ለተቃጣው አደጋ ተጠያቂ ነውና ጉዳዩን አጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እስካላደረገና ይቅርታ እስካልጠየቀኝ ድረስ ወደ ፊት አብሬው ለመሥራት እቸገራለሁ፤›› በሚል እየታበየ የሰነዘረውም ፀጥታዊ አነጋገር ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ዓይነቱ ያልታረመና ማናህሎኝነት የተጫነው ትንኮሳ አርፎ የተቀመጠውንና ከደረሰበት ሐዘን ቀስ በቀስ ለማገገም በመጣጣር ላይ ያለውን ሰለባ ካላናደደና ካላስቆጣ፣ ከቶ ሌላ ምን የሚያበሳጭ ነገር ሊኖር ይችላል ተብሎ ይጠበቃል? በታጋሽነቱ የማይታማው የአገራችን ሰው ይህንኑ ትዕግሥቱንና አርቆ አስተዋይነቱን ካልተገነዘቡ          ወገኖች  በኩል መገፋት ሲበዛበትና ከልቡ ሲከፋው እንዲህ ያንጎራጉራል፣ ‹‹ኧረ ምን ጅሉ ነው ኧረ ምን ጅሉ ነው፣ ሲሰድቡት ዝም ያለ ቢመቱትም ያው ነው፡፡››

እንግዲህ አዴፓ ለዘመናት ከዘለቀውና ነባሩ ብአዴን ካወረሰው እስረኝነት ተላቆ በግንባሩ ታሪክ እስከ ዛሬ ድረስ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ አቀራረብና ድምፀት አብዝቶ ከመስመር ያልወጣ፣ ሚዛኑን የጠበቀና የሕወሓትን ቅስም እስከ ወዲያኛው የሰበረ አስደማሚ ምላሽ የሰጠው ከፍ ብሎ በተጠቀሰው አገርኛ ብሂል ላይ ተደግፎ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡

  ማጠቃለያ

ሕወሓት በእህት ድርጅቱ መሪር ሐዘን ሳቢያ እላፊ የፖለቲካ ትርፍ ያገኘ መስሎት ያላግባብ በተሳለቀበት ማግሥት፣ አዴፓ ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ለሕዝብ ያሠራጨው ምላሽ እንደከዚህ በፊቱ ያልተገባ አባባይነት፣ አድርባይነትና አቆላማጭነት አይታይበትም፣ አይደመጥበትምም፡፡ ሕወሓትም ቢሆን በህልሙም ሆነ በዕውኑ ይገጥመኛል ብሎ ከማይጠብቀው ከዚኛው የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተናዳፊ የመልስ ምት ብዙ መማርና መገንዘብ የሚችልና የሚገባውም ይመስለኛል፡፡

‹‹አላርፍ ያለች ጣት ያሻትን ሁሉ ለመዳሰስ በተቅበዘበዘች ቁጥር ምናምን ቢጤ ነካክታት መለሳለች፤›› እንዲሉ ነውና ‘ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል’ የተባለበትን መዘዘኛ መግለጫ ኤዲት ሳያደርግ፣ እንደ ወረደ ለሕዝብ ከማሠራጨቱ በፊት ሁለት ጊዜ ማሰብ ነበረበት ያሰኛል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ጨርሶ የማይፈወስ መስሎ ለሚታየው የዕብሪት፣ የማናህሎኝነትና የሴረኝነት በሽታ ይኸው ቡድን ትክክለኛ ምሱን እንዳገኘ በአደባባይ ሲመሰክሩ ታዝቤአለሁ፡፡

በእርግጥ ዘግይቶም ቢሆን አዴፓ ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው በዚህ መግለጫው ላይ በሰፊው እንዳተተው፣ ሕወሓት ገና ከፅንሰቱ አንስቶ ጀብደኛና ሃኬተኛ ቡድን ስለመሆኑ ያን ያህል እንግዶች አይደለንም፡፡ የውቅያኖስ ዓሳ ሲልሰው እንደኖረ ድንጋይ በአደገኛ አሙለጭላጭነቱ ስለሚታወቀው ስለዚህ ቡድን የማይጨበጥ ሰብዕናና የተንሸዋረረ ዕይታ፣ የመጀመርያው ነጋሪያችን አዴፓ ሊሆን ምምከቶ አይችልም፡፡ እንዲያም ሆኖ አዴፓና ሕወሓት በአንድ የጋራ ግንባር የታቀፉ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አልፎ ከሌሎች ሁለት አቻ ድርጅቶች ማለትም ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ጋር ከ1980 ዓ.ም. አንስቶ በአንድ ዓይነት የፖለቲካ ፕሮግራም ሥር በመጣመር መንግሥታዊ ሥልጣኑን በምርጫ ተረክበው ለወጉ ያህልም ቢሆን፣ ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ አገር የሚያስተዳድሩ መሆናቸውን ስንረዳ ሥርዓት ያለው ደንበኛ ፍቺ ከመፈጸማቸው በፊት እዚህና እዚያ እርስ በርስ በሚወራወሩት የቃላት ፍላፃ አጃኢብ ማለታችን አይቀርም፡፡ ‹‹የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል›› እንደሚባለው ቀድሞ ነገር የምንዋደድ እህትማማቾች ነን እያሉ በአደባባይ ሲቀፍሉን እንዳልኖሩ ሁሉ፣ የፖለቲካ እንካ ስላንቲያውን በዚህ ደረጃ በይዋጣልን መንፈስ ሲያጦዙት መመልከት ዘይገርም ያሰኛል፡፡

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ሁለቱም ብሔራዊ ድርጅቶች እነርሱ ያለመታከት በሚለፍፉት ልክ እህትማማቾች ይሁኑ አይሁኑ የብዙኃኑ ሕዝባችን አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ አያውቅም፡፡ ሊሆንም ከቶ አይችልም፡፡ ግና ደግሞ አሁን የሚያሳዩን ዓይነቱ የብሽሽቅ ፖለቲካ መቼውንም ቢሆን፣ የሀቀኛ ደጋፊዎቻቸውንም ሆነ የምልዓተ ሕዝቡን አክብሮት ያተርፍላቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ቀደምት አዋቂዎች እንደሚነግሩን በሁለት ዝሆኖች መካከል ያለማቋረጥ የሚካሄደው የይዋጣልን ልፊያ ምንጊዜም ቢሆን፣ አብዝቶ የሚያጎሳቁለውና የሚጎዳው ሳሩን ነው፡፡ “when the two elephants fight, it is the grass which suffers the most” እንዲሉ፡፡

ማንም እንደሚያውቀው ሁለቱም ተፋላሚ ድርጅቶች ሕዝብ መርጦናል በማለት በክልልና በፌዴራል ደረጃ መንግሥታዊ ሥልጣን የያዙ፣ አገሩን በተናጠልና በጣምራ እንዲያስተዳድሩ ከባድ ኃላፊነት የወደቀባቸው ኃይሎች ናቸው፡፡ ስለሆነም አሸናፊው በውል ሊለይ በማይችልበት እንካ ስላንትያ ተጠምደው ጊዜያዊ ባለ አደራነታቸውን ጨርሶ እስከ መዘንጋት መድረስ የለባቸውም፡፡ እነሆ ሕወሓት ውጤቱን አስቀድሞ ሳይተነብይ ያልተመከረበት የሚመስለውን አደገኛ ትንኮሳ በአዴፓ ላይ ፈጽሟል፡፡ አዴፓ በበኩሉ ለዚህ ትንኮሳ ውሎ ሳያድር አፀፋውን መልሷል፡፡ ከዚህ በኋላ ሁለቱም ባላንጣዎች አደብ መግዛት ይኖርባቸዋል፡፡ ምን እየሠሩ እንደሆነ እንኳ ለአንዳፍታ ቆም ብለው በጥሞና ሊያስቡበት ይገባል፡፡

መንግሥቱን እንዲመሩ ተወከሉ ወይም ራሳቸውን ወከሉ እንጂ፣ አገሪቱ የእነርሱ አንጡራ ሀብት እንዳልሆነች መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይታወስ እንደሆን አዴፓ ለሕወሐት ትንኮሳ ይመጥናል ያለውን ምላሽ የሰጠው የከፍተኛ አመራሮቹን ግድያን ጨምሮ በወቅታዊ አጀንዳዎች ላይ ሸንጎ ተቀምጦ ሲመክር የነበረውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ አቋርጦ ነው፡፡ ከወትሮው አስፋፍቶ በሰጠው በዚህ ምላሽ ቅሬታ ያደረባቸው አንዳንድ ወገኖች እንዳሉ አስተውያለሁ፡፡ እነዚህ ወገኖች ‘አበጀህ፣ ደግ አደረግህ’ ባይሉት እንኳ፣ በዚህ ጸሐፊ አስተያየት መረን የወጣውን ትንኮሳ አስቀድሞ ከሰነዘረበት ባላጋራው ጋር እኩል በማሠለፍ ሊከሱትና በአደባባይ ሊኮንኑት ከቶ አይገባቸውም፡፡ ያ በእርግጥ ዓይን ያወጣ ፍርደ ገምድልነት ይሆናል፡፡

በመሠረቱ የትግራይና የአማራ ሕዝብ ግንኙነት በውስጡ ከበቀሉት ከእነዚህ ተወናጫፊ የፖለቲካ ድርጅቶች ግንኙነት በብዙ እጥፍ የላቀ መሆኑ እዚህ ላይ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ስለሆነም ድርጅቶቹ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማጥቃትም ሆነ በመልሶ ማጥቃት ሒሳብ አፋፍመው የቀጠሉበትን ልብ አቁሳይ የቃላት ተኩስ በአስቸኳይ ማቆም ይኖርባቸዋል፡፡ አንዱ የሌላውን ዱካ እየተከተለ ስሜት አነሳሽ መግለጫዎችን ማዥጎድጎዱ ቋሚና መደበኛ ተግባራቸው እንዳልሆነ ሁለቱም ወገኖች በውል ሊረዱት ይገባል፡፡ ይነስም ይብዛ የእነርሱ የሥልጣን መቆያ ዕድሜ በምርጫ ዘመን የተገደበ ሲሆን፣ አገርና ሕዝብ ግን ዘለዓለማዊ መሆናቸውን አለመዘንጋት ብልህነት ይሆናል፡፡

በመጨረሻም አንድ ነገር ልበልና መጣጥፌን ልቋጨው፡፡ በገዥነትና በወዳጅነት መካከል ግልጽ ልዩነት አለ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ቋሚ ወዳጁ የአማራ ሕዝብ እንጂ፣ ሕወሓት አይደለም፡፡ የአማራ ሕዝብም ቢሆን አዴፓን ከወንድሙ የትግራይ ሕዝብ ጋር ሊያወዳድረው ከቶ አይችልም፡፡ የፖለቲካ ቡድኖች ከቻልን በራሳችን ምርጫና ውሳኔ በጊዜያዊነት ሥልጣን ላይ የምንሰቅላቸው፣ አለበለዚያም በራሳቸው ኃይል ተጭነው የሚያስተዳድሩን ገዥዎቻችን እንጂ፣ ቋሚና ዘላቂ ወዳጆቻችን እንዳልሆኑ ማወቅ አለብን፡፡ የቱንም ያህል በስማችን ሲምሉና ሲገዘቱ ውለው ቢያድሩ እነዚህ ቡድኖች ተግተው የሚሠሩት፣ በአመዛኙ የራሳቸውን የተለካ ፍላጎት ለማሳካት እንጂ በአደባባይ እንወክልሃለን ለሚሉት ለብዙኃኑ ጥቅም መከበር ስላልሆነ፣ ተመሳሳይ መግለጫዎችን ባወጡና ባስደመጡን ቁጥር በንቃት እየመረጥን ልንሰማቸውና ለመፃኢው ዕድላችን መቃናት የሚበጀውን ለእነርሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ሳንንበረከክ በራሳችን ልንወስን ይገባል፡፡

     ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋከልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...